Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የችግሮች መንስኤ እኛ እራሳችን ነን –በይበልጣል ጋሹ

$
0
0

በይበልጣል ጋሹ

commnetዛሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግር እየጨመረ መምጣቱ ዓለምን ስጋትና ጭንቀት ውስጥ ከቷታል። ለአንዱ ችግር መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የቀረበው ሃሳብ በሌላ በኩል ሊፈታ የማይችል ችግር ፈጣሪ ሲሆን መመልከት የተለመደ ነገር ነው። ምንም እንኳ /ከተለዩ ሰዎች በስተቀር/ ሰው በራሱ ችግር ለመፍጠር ተነሳሽ ባይሆንም ለመፍትሔም የዘገኘና ቆራጥነት የማይታይበት በመሆኑ ለችግሩ መበባስ መንስኤም ምክንያትም ነው። በዚህች አጭር ጽሁፍም የእኛ የችግር መንስኤነትን በአጭሩ ለማሳየት እሞክራለሁ። ሙህራን በዚህ ዙርያ ሰፊ ጥናት በማድረግ እንዲያቀርቡልን ግብዣየ በደስታ ነው።

 

  • እንደሚታወቀው እንደ አህጉራችን አፍሪካና አገራችን ኢትዮጵያ ሁላችንንም የሚያሳስበንና ጎልቶ የሚታየው የአስተዳደር/ፖለቲካዊ ችግር ነው። እንደሚታወቀው ሁሉም የፖለቲካ ድርጅት/ገዢው ፓርቲ/ ለነጻነት፣ ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለሰባዊ መብትና ለዲሞክራሲ እቆማለሁ ብሎ መነሳቱንና የህዝብ ድጋፍ ማግኘቱን ረስቶ የበፊቱንና የአለፈውን የአስተዳደር ዘመን በእጅጉ የሚያስመሰግን ሁኖ እናገኘዋለን። ዘረኝነትንና አድሎአዊነትን ለመዋጋት የተነሳ ድርጅት ከበፊቱ በበለጠ ችግር ፈጣሪ ሲሆን ጎልቶ ይታያል። ሙስናን ለመዋጋት የተነሳ ድርጅት ለሙስና መስፋፋት ዋነኛ ተዋናይ መሆኑ በእጅጉ ያሳስባል። ድህነትን ለማጥፋት የተነሳ ድርጅት ራሱን ከማበልጸግ ባለፈ የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ከቲዮሪ/theory/ ባለፈ መቀየር አልቻለም። ዲሞክራሲን አሰፍናለሁ ብሎ የተነሳ ድርጅት ሚድያ ላይ ከመናገር ባሻገር ህብረተሰቡን የዲሞክራሲ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ግን አልቻለም። ምን አልባት ኢትዮጵያ በዲሞክራሲዊ አስተዳድር ስርዓት ትመራለች፣ ድህነት ቀንሷል ልንል እንችል ይሆናል፤ እውነት ነው የእኛም ትልቁ ችግራችን ይህ ነው። በመካከላችን 100% ልዩነት መኖሩ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል በምቾት፣ በሰላም፣ በደስታ፣ በነጻነትና ዲሞክራሲ ሲኖር አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ በእጅጉ በሚያሳዝን ሁኔታ በርሀብ፣ በችግር፣ በስቃይ፣ በአድሎአዊነትና በነጻነት እጦት ውስጥ መኖሩ ችግሩ ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል።

ለችግር መንስኤዎች እኛው ነን ያልኩበት ምክንያትም የፓርቲውን/የድርጅቱን ዓላም በሚገባ ሳንረዳና ሳንገነዘብ ከመጀመሪያው ጀምረን ይሁን ብለን ድጋፍ እና እንክብካቤ በማድረጋችን ነው። ግማሾቻችን ደግሞ ሳይመቸን እንደ ተመቸን፣ ሳንጠግብ እንደ ጠገብን፣ ነጻነትና ዲሞክራሲ ሳይኖር በነጻነት እንደምንኖር ሁሉ እንደ ሄሮዶሳውያን ሺ ዓመት ንገስ፣ ከአለአንተ አገር ትገለበጣለች፣ ለህዝቡ ተቆርቋሪ የለም እያልን ችግሩን እንዲያስተካክል በግልጽ ከመናገር ይልቅ የማይገባውን የምስጋና ቅኔ ስለምናቀርብ፤ ከፊሎች ደግሞ በጊዜያዊ ጥቅም ተይዘው ችግሩን እንዳንመለከት ከለላ ስለሆነብንና መሰል ችግሮች ስላሉብን ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ተጠያቂዎችም መንስኤዎችም እኛው እራሳችን ነን።

  • ለተለያዩ ችግሮች የመፍትሔ ሃሳብ ከምንጠብቅባቸው የእምነት ተቋማት ሳይቀር በመሪዎቻችን መካከል ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እናገኛለን። ጥቂት የእምነት መሪዎች/አባቶች ነን ባዮች ከአለም ባለስልጣናት ባልተለየ መልኩ አስተዳደራዊ በደል በእምነት ተቋማቸው ላይ ሲያደርሱ መመልከት የተለመደ ነገር ሁኗል። ዘረኝነትንና ሙስናን ይዋጉልናል ያልናቸው ሰዎች ለችግሩ መፋጠን ዋነኛ አካል ሁነዋል። ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር በተሰጠችው መመርያ ተጠቅማ ለአለም ሰላም የማደል ፀጋ ቢኖራትም ዳሩ ግን እነዚያ ጥቅመኞች ፀጋዋን ለዓለም እንዳታድል አዚም ሁነውባታል።

ለዚህም ችግር መንስኤ  እኛው የእምነቱ ተከታዮች ነን። ለምን ቢባል በተለያየ ዘርፍ ላይ ለሚገኙ የእምነት ተቋም አስተዳዳሪዎች ፊት በሙስና፣ በስርቆትና በብልሹ አስተዳደር ስለበለጸጉ ሰዎች እናወራለን፣ እንተርክላቸዋለን። በእነዚህ ነውረኛ  ሰዎች ላይም ምንም አይነት የእምነት ሃላፊነታችንንና ግዴታችንን መወጣት ባለመቻላችን ሌሎች እንደማበረታቻ ቆጥረውታል። በእነዚህ እና መሰል ምክንያቶች ችግሮች እንዲበባሱ የእኛ አስተዋጾ ቀላል እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል።

  • ወደ ባዕድ ሀገር በስደት የሚጎርፈው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ሀገር ቤት ሰው የማይኖር እስኪመስል ድረስ ፍላጎቱና ፍልሰቱ ከፍተኛ ሁኗል። ለዚህ ችግር በዋናነት የመንግሥት አስተዳደራዊ ድክመት ቢሆንም እኛም የበኩላችንን ድርሻ ባለመወጣታችን የመጣ ትልቅ ችግር ነው። በስደት የሚኖሩ ወገኖች የስደትን አስከፊነት እያወቁ ነገር ግን በሀገር ቤት ለሚኖሩ ወገኖቻቸው ችግሩን በሚገባ አለማስረዳት፣ ወደ ሀገር ቤት በሚሄዱበት ጊዜም የተለየ ለብሰውና መስለው መታየታቸው እና የሚሰሩትን የሥራ አይነት እንኳ በትክክል አድካሚነቱንና አሰልችነቱን አለመናገር ለሌሎች ከሀገር መውጣት ምክንያት ሁኗቸዋል። ስለዚህ የሆነውንና የሚሆነውን በትክክል መረጃ መስጠት ብንችል ወገኖቻችን በይሆናልና በማይሆን ተስፋ ከሀገር ወጥተው የስደትን አስከፊ ህይወት ተጠቂ ባልሆኑ ነበር።

ስደት ምንልባት በኢኮኖሚ የተሻለ ነገር ሊኖረን ይችል ይሆናል እንጂ የሰላም ኑሮ  ግን መኖር የሚቻለው ተወልደው በአደጉበት ሀገር ነው። በስደት ህይወት የባህል፣ የእምነት፣ የአለማዊነትና የቋንቋ ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ የተረጋጋና ሰላማዊ ህይወት መምራት በጣም አስቸጋሪና ከባድ ነው። በዚህም የተነሳ በጭንቀትና በውጥረት የሚኖሩ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ስለዚህ ሰውን ወደ ስደት ህይወት መጋበዝ በጭንቀትና በሃሳብ እንዲኖር መፍረድ የሚል ድምዳሜ ቢሰጥ ያንሳል እንጂ ማጋነን አይሆንም።

በአጠቃላይ እኛ ሁላችንም ብንችል የችግር መፍትሔዎች እንድንሆን ባንችል ደግሞ የችግር መንስኤዎች እንዳንሆን የራሳችንን በጎ አስትዋጾ ማድረግ ይኖርብናል። ለችግር መፍትሔ ይሆናሉ ያልካቸውን 2 ላንሳና ሌላውን እናንተ ቀጥሉበት።

  1.  ችግሮችን በትክክል መረዳት፦ ችግሩን ከስር መሰረቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ በአጠቃላይ ሀገራዊ ጉዳቱን መረዳትና ችግሩ እንዳይበባስ የራሳችንን አስተዋጾ ለማድረግ ችግሩን በትክክል መረዳት ይጠበቅብናል። ሙህራን “ችግሩን ማዎቅ የመፍትሔ 50% ነው” እንዲሉ  ችግሩን በትክክልና በጥልቀት መረዳት ካልቻልን መፍትሔ በቀላሉ ለማግኘት አስቸጋሪ ስለሚሆን የችግሩን የት፣ መቼ፣ እንዴትና ወዴት የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ችግሩን ከመሰረቱ ማዎቅ ከሁላችን የሚጠበቅ ተግባር ነው።
  2. ችግሩን ለማሶገድ በቆራጥነት መነሳት፦ ችግሩን በትክክል ከተረዳን መፍትሔ ለማምጣት ደግሞ  በቆራጠነት መነሳት ይኖርብናል። ፍራትን፣ ቸልተኝነትን፣ አይሆንም ባይነትን፣ አድርባይነትን፣ ጥቅመኝነትንና ዘረኝነትን ከውስጣችን አሶጥተን ለሀገርና ለተተኪ ትውልድ በሁሉም በኩል የበለጸገች ሀገር ለማስረከብ ቆራጥነትና ሰማትዕነት ያስፈልጋል። የማንም ርዳታ ሳያሻን በራሳችን ተነሳሽነት ሀገራዊ ሃላፊነታችንን ለመወጣት እና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሁላችንም ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል።…………………….+++

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>