ከዓመታት በፊት በእርሻ መሬት ማነስ ምክንያት ወደ 400 የሚሆኑ የዓድዋ ተወላጆች (ልዩ ስሙ ‘ወርዒለኸ’ ከሚባል ቦታ) በመንግስት አካላት ከቀያቸው ተነስተው በቃፍታ ሑመራ ወረዳ (ጣብያ ማይወይኒ፣ ቁሸት መንሼን) እንዲሰፍሩ ተደረገ። ቤት ሰሩ፤ ኑሯቸው እዛው መሰረቱ።
አሁን ግን አዲስ ነገር ተከሰተ። የሰፈሩበት፣ ኑሯቸው የመሰረቱበት መንደር ለከብቶች እርባታ ‘ተስማሚ ሁኖ ስለተገኘ’ በኢንቨስትመንት ስም ከብቶች ለሚያረባ ድርጅት እንዲሰጥ ተወሰነ። አርሶአደሮቹ ያለ ምንም ካሳ ቀያቸው ለቀው እንዲነሱ ታዘዙ። ካሳ ጠየቁ፤ እንደማይሰጣቸው ተነገራቸው። ለመኖርያ የሚሆን ቅያሪ ቦታ ጠየቁ። መልስ አልተሰጣቸውም። ቀያቸው ባጭር ግዜ ዉስጥ ለቀው እንዲወጡ ሲነገራቸው አርሶአደሮቹ ጠንከር ያለ ተቃውሞ አሰሙ።
ከነዚህ 400 የሚሆኑ የተፈናቀሉ አርሶአደሮች ‘የተቃውሞው አስተባባሪዎች ናቸው’ ተብለው የተጠረጠሩ 40 አባወራዎች ታሰሩ። ክስ መመስረት እንኳን አይችሉም። ምክንያቱም መሬት የመንግስት ነው።
መሬት የሌለው ዜጋ ሀገር የለውም። መሬት የመንግስት ከሆነ የመንግስት አካላት (የገዢው ፓርቲ አባላት) በፈለጉበት ግዜ ዜጎችን ማፈናቀል ይችላሉ።
ለትግራይ ተወላጆች በሙሉ …….
Abraha Desta
——————————
‘ዜጎች ነንና ፍትሓዊ ልማት ያስፈልገናል’ ሲንል አሰሩን። ‘ደማችን ገብረናልና ሰለማዊ ሰልፍ የመውጣት መብታችን ይከበርልን’ ስንል ደበደቡን። ‘ብዙ መስዋእት ከፍለናልና ነፃነታችንን አትንፈጉን’ ስንል ትጥቃችንን አስፈቱን። መብታችንን ለማስከበር ስንሞክር ገደሉን።
ግን ይህን ሁሉ ወላጆቻችን፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የከፈሉት መስዋእት ዓላማው ምን ነበር? ደርግን ደምስሶ ሌላ ደርግ መመስረት? ይሄማ ሊሆን አይችልም። ደርግ’ኮ ደርግ ያሰኘው ተግባሩ ነው።
ደርግን የምንጠላው ደርግ ስለሆነ አይደለም። መጥፎ ምግባር ስለነበረው ነው። ጨቋኝ ስለነበረ ነው። ገዳይ ስለነበረ ነው። ገዳዮቹ ቢቀያየሩ እንኳን ተግባራቸው ያው ግድያ መሆኑ አይቀርም። ገዳይ ማን ይሁን ምን ያው ገዳይ ነው። ደርግ እንዲጠላ ያደረገው ገዳይነቱ ነው። ለኛ የገደለ ሁሉ ደርግ ነው። መግደል፣ በሰው ልጅ ላይ ግፍ መፈፀም፣ መጨፍጨፍ ምን ያህል መጥፎ መሆኑ ከልምድ እናውቀዋለን። ስቃዩ ምን ያህል መራራ እንደሆነ ከራሳችን በላይ ማንም ሊያስረዳን አይችልም።
የኢህአዴግ ወታደሮች (ይቅርታ የመንግስት ወታደር ስለሌለ ነው) ኮፈሌ አከባቢ በህዝቡ ላይ ችግር መፍጠራቸው እየሰማን ነው። ወታደሮቹ ለሚወስዱት እርምጃ ምክንያት ያቀርቡ ይሆናል። የፈለገ ምክንያት ቢኖር እንኳን በሰለማዊ ዜጎች ላይ ግፍ መፈፀም ሊደገፍ አይችልም። መፍትሔም ሊሆን አይችልም። የኃይል እርምጃ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደማይሆን ለመገንዘብ የደርግ ስርዓት ትግራይን ሲደበድብ የተከሰተውን ማስታወስ በቂ ይመስለኛል።
የኢህአዴግ ወታደሮቹ በኮፈሌ ሰለማዊ ህዝብ ላይ ችግር ሲፈጥሩ በተጎጂዎች ስነልቦና የሚፈጠር ስሜት ልክ የደርግ ወታደሮች እኛ ላይ ግፍ ሲፈፅሙ በኛ አእምሮ ዉስጥ የተከሰተው ሓዘንና የእልህ መንፈስ ነው። ደርግ የፈፀመው ግፍ በኛ ከባድ ጠባሳ ጥሎ አልፈዋል። በኮፈሌዎችም ተመሳሳይ ነው። ለኮፈሌዎች (በኛ ስሜት) ኢህአዴግ ደርግ ሁነዋል። ደርግ እኛን ገደለ፤ ኢህአዴግ እነሱን ገደለ። ያው የሁለቱም ግድያ ነው። ሁለቱም ስርዓቶች በየ አቅጣጫቸው ተመሳሳይ ናቸው። ገዳዮች ናቸው።
በሰዎች ላይ ግፍ ሲፈፀም መቃወም ይኖርብናል። ደርግ ሲገድለን ግድያው ለደገፉ፣ የደርግ ተግባር ደጋፊዎች ለነበሩ፣ ወይ ተቃውሟቸውን በግልፅ ላላሰሙ ወገኖች የሚኖረንን ስሜት በራሳችን እንገምግመው። ቤተሰቦቻችን ላይ በደል ወይ ግድያ ሲፈፀም ከጎናችን ለቆሙ ወገኖች ትልቅ ውለታ እንደዋሉልን የሚሰማንን ያህል በሌሎችም ተመሳሳይ ግብረመልስ ይኖራል። ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች ጎን መሰለፍ የብሄር ወይ የሃይማኖት ጉዳይ አይደለም፤ የሰብአዊነት ጥያቄ እንጂ።
ስለዚህ ይህን የኢህአዴግ ዜጎች የመበደል ተግባር መቃወም ይኖርብናል። ፖለቲከኞች ስልጣናቸው ለማደላደል ሰለማዊ ሰዎች ላይ ግፍ ይፈፅማሉ። ሰለማዊ ሰው ሲበደል ሌላ የሚጠቀም ሰለማዊ ሰው ሊኖር አይችልም (ከፖለቲከኞች በቀር)። በስልጣን ላይ ያለው አካል ሰው የሚበድለው በስልጣኑ ለመቆየት ሲል ነው፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ሰው መንግስት ሲበደል ድጋፍ የሚያገኙበት ዕድል ይኖሯቸዋል። ስለዚህ ከህዝብ በደል ሊጠቀሙ የሚችሉ ፖለቲከኞች ብቻ ናቸው። ለሰለማዊ ሰው ግን (የሰለማዊ ሰዎች በደል) ጉዳት ብቻ ነው ያለው። ስለዚህ መቃወማችን ግድ ይላል።
ህወሓት ኢህአዴግ ከኛ ወጣ። እኛን ተመልሶ በደለ። ይባስ ብሎ ደግሞ በኛ ስም ሌሎችን ይበድላል። ይህ ህዝቦችን የመበደል ተግባሩ ሁላችን እንቃወመው።
ይህ የሰብአዊነት ድምፅ ነው።
It is so!!!