* እያንዳንዱ ዜጋ የህወሓትን እኩይ ሴራ ተገንዝቦ ራሱን፣ ቤተሰቡንና አካባቢውን ከጥቃት እንዲጠብቅ
* ዘረኛውና ፋሽስቱ የህወሓት አገዛዝ፣ በሕዝባዊ ኃይሎች ላይ ሊወስድ ያሰበው እርምጃ ተቀባይነት እንዲያገኝለት የሽብር ተግባር ፈጽሞ በአርበኞች ግንቦት 7 ላይ ለማላከክ ወስኗል
* በህወሓት የተደገሰልንን የሽብር ጥቃት ማምከን ይኖርብናል
ዘረኛውና ፋሽስቱ የህወሓት አገዛዝ፣ በሕዝባዊ ኃይሎች ላይ ሊወስድ ያሰበው እርምጃ ተቀባይነት እንዲያገኝለት የሽብር ተግባር ፈጽሞ በአርበኞች ግንቦት 7 ላይ ለማላከክ ወስኗል። እንዲህ ዓይነቱ እኩይ ተግባር ህወሓት ስልጣን ከመያዙ በፊትም በኋላም ሲያደርገው የነበረ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ህወሓት እንዲህ ዓይነቱ ኢሰብዓዊና ዘግናኝ ተግባር ለመፈፀም የሚያስችሉ እኩይ ስለልቦና እና ልምድ አለው።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በቅርቡ የጀመረው የነፃነት ትግል የፈጠረበት መደናገጥ ለመሸፈንና ንቅናቄውን በኢትዮጵያ ሕዝብና በዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብ ለማስወገዝ ያግዘኛል ብሎ ያመነበት ይህን ዘግናኝ ሴራ ከሳምንት በፊት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁቱን አጠናቆ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ የነፃ ሚዲያ አባላት ደርሰውበት ለሕዝብ ይፋ በማድረጋቸው እንዲዘገይ ተደርጎ ነበር። አሁን በደረሰን መረጃ ደግሞ ሴራው ከበፊቱ በባሰ እና ይበልጥ አውዳሚ በሆነ መጠን ተግባራዊ ለማድረግ የህወሓት “ስውር” መንግሥት ወስኗል። በዚህም ምክንያት ይህ የማስጠንቀቂያ መግለጫ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በማያሻማ ሁኔታ እንዲገነዘብ የምንፈልገው ሀቅ የሚከተለው ነው። አርበኞች ግንቦት 7 በደረሰው መረጃ መሠረት ህወሓት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ወስኗል። የእቅዱ ዓላማ ዘግናኝ እርምጃ በንፁሃን ዜጎችና ሕፃናት ላይ በማድረስ “የሽብር ጥቃቶች ሰለባ” ነኝ በማለት የኢትዮጵያ እና የዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ አዘኔታ ማግኘት ነው። የዩ. ኤስ. አሜሪካ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን የሚጎበኙ መሆኑ ደግሞ ይህንን እቅድ ተግባራዊ የማድረግ ጉጉቱ እንዲጨምር አድርጓል። ስለሆነም ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ በህወሓት የሽብር አደጋ ውስጥ ነች። የቦሌ ዓለም ዓቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ እና ወደዚያ የሚያደርሰው መንገድ፣ የአፍሪቃ ኅብረት ጽ/ቤት እና የአሜሪካ ኤምባሲ ህወሓት በሽብር ጥቃት ዒላማነት ከመዘገባቸው ውስጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው።
አርበኞች ግንቦት 7 በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚቃጡ የሽብር ጥቃቶችን መቃወም ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብሮ ያመክናል። ይህ በህወሓት የተደገሰልንን የሽብር ጥቃት ማምከን ይኖርብናል። እኩይ እቅድን አስቀድሞ አውቆ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አንድ ዓይነተኛ የሽብር መከላከያ ዘዴ ነው። በዚህ ረገድ በአገዛዙ ውስጥ ያላችሁ የሕዝብ ወገኖች ባለውለታዎች ናችሁ።
የእያንዳንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሕይወት መለኪያ በሌለው መጠን ውድና ክቡር ነው። በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ዜጋ የህወሓትን እኩይ ሴራ ተገንዝቦ ራሱን፣ ቤተሰቡንና አካባቢውን ከጥቃት እንዲጠብቅ አርበኞች ግንቦት 7 በጥብቅ ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!