የማንችስተር ሲቲን እጅግ ውጤታማ ጊዜ የሚዘክር ታሪክ በሚፃፍበት ወቅት ጋሪ ኩክ ጎላ ያለ ስፍራ ይኖራቸዋል፡፡ ሮቤርቶ ማንቺኒ፣ ሰርጂዮ አጉዌሮ፣ ያያ ቱሬ እና ማኑኤል ፔሌግሪኒን የመሳሰሉ ስሞችም የትርክቱ ዋነኛ ገፀ ባህሪያት መሆናቸው አይቀርም፡፡ ደግሞም ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሲቲ በቅርቡ ያሳካቸው ድሎች እውን የሆኑት እንዲሁም ወደ ፊት ሊያሳካቸው እየተንደረደረ ያለው ነገሮች የሚሳኩት ኩክ ክለቡን ከኪሳራ አፋፍ መልሶ ወደ ስኬት ጉዞ እንዲጀምር እና ከእግር ኳስ ሃያላን ጎራ እንዲቀላቀል ያስቻለውን ህልም ለሼህ ማንሱር በመሸጣቸው ነው፡፡
‹‹የማንችስተር ሲቲ አዳኝ እንደሆንኩ ተደርጎ እንዲወራ አልፈልግም›› ሲሉ በኤቲሃድ ባሳለፉት በውጣ ውረድ ተሞሉ ሶስት ዓመታት ለራሳቸውም ሆነ ለክለባቸው ዝቅ ያለ አመለካከት ባለመያዛቸው የሚታወቁት ግለሰብ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን ኩክ መታወስ ያለባቸው በዚያ መልኩ ነው፡፡
በ2008 የቀድሞው የናይኪ የማርኬቲንግ ሰራተኛ ለማንችስተር ሲቲ ደጋፊዎች ቡድናቸው ከመራራ ባላንጣቸው ማንቸስተር ዩናይትድ ብቻ ሳይሆን በተቀረው ዓለም ከሚገኙ ቡድኖች ሁሉ የበላይ ይሆናል ብለው ሲናገሩ ብዙዎች አላመኗቸውም ነበር፡፡
በ2011 በስህተት የላኩት የኢሜይል መልዕክት በካንሰር ህመም እየተሰቃየች ባለችው የኔዱም ኦኑሃ እናት ላይ የሚያፌዝ ሆኖ በመገኘቱ ሲቲ የኤፍኤ ካፑን ዋንጫ ካነሳ ከአራት ወራት በኋላ ራሳቸውን ከኃላፊነት አነሱ፡፡
ከትዳራቸው ያስቀደሙትን ስራ ሲያጡም ‹‹ልባቸው ደምቶ እና ቅስማቸው ተሰብሮ›› ክለቡን እንደለቀቁም ተናግረዋል፡፡ አሁንም ድረስ ግን በኤቲሃዱ ክለብ ባለስልጣናት ዘንድ ከፍተኛ ክብር አላቸው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በሚቀጥለው ሳምንት በቻምፒዮንስ ሊግ ሲቲ ከባርሴሎና ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በምቹው የዳይሬክተሮች መቀመጫ ክፍል ተገኝተው እንዲከታተሉ መጋበዛቸው ነው፡፡ በዚያ ተቀምጠውም በሜይ 2008 ታክሲን ሺናዋትራ በናይኪ የነበራቸውን ኃላፊነት በመተው የሲቲ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ እንዲሆኑ ያቀረቡላቸውን ጥያቄ የተቀበሉበትን ወቅት ወደኋላ መለስ ብለው ማስታወሳቸው አይቀርም፡፡
በትውልድ ሀገራቸው በሰብአዊ መብት ጥሰት እና ማጭበርበር የሚከሰሱት የቀድሞው የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው እና በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጉት ኢንቨስትመንት እያሳሰባቸው መሆኑን ለመረዳት ኩክ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ ‹‹ለሺናዋትራ ለክለቡ ገዢ ከማፈላለግ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ለማሳወቅ ወደ 10 ቀናት ወስዶብኛል፡፡ ምክሬን ባይቀበሉ ኖሮ ሲቲን የሚጠብቀው ወደ መቀመቅ መውረድ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር እጅግ በከፋ መጥፎ እና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነበርን፡፡ የቆምነው በገደል አፋፍ ላይ ነበር፡፡
‹‹ችግሩን ለመቅረፍ የተጓዝንበት መንገድ ዘላቂነት አልነበረውም፡፡ ለምሳሌ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም የሚረዳንን ገንዘብ ለማግኘት የቴሌቪዥን ስርጭት ሽያጭ ክፍያን ከጊዜው አስቀድመን እንሰበስብ ነበር፡፡ ይህ በራሱ ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበርን ያሳያል፡፡ ከዚህም አለፈ እና ደግሞ የተጫዋቾችን ደመወዝ ለመክፈል ክለቡን ለሺናዋትራ አሳልፈው ከሸጡት የቀድሞው ሊቀመንበር ጆን ዋርድልን ገንዘብ መበደር ጀመርን፡፡
‹‹ሲቲ እንደ ክለብ ፀንቶ እንዲቆም ወሳኙን ሚና የተጫወቱት ጆን ነበሩ፡፡ በእርሳቸው ደግነት እና ልገሳ እየተደገፈም እንኳን ሲቲ ወደ አዘቅት ሊያመራ ከጫፍ ደርሶ ነበር፡፡ በመጨረሻም ተሳካልኝ እና ናኪን ለመልቀቅ ስወስን ለክለቡ የነበረኝን ህልም ለሼክ ማንሱር እና በእርሱ ስር ለሚሰሩ ሰዎች ለመሸጥ ቻልኩ፡፡
‹‹ትክክለኛ ማዕበል ነበር፡፡ ሲቲ እጅግ በከፋ ሁኔታ ውስጥ ነበር፡፡ አቡ ዳቢ ደግሞ በዓለም ያላትን ስም ለማሳደግ በፕሪሚየር ሊጉ ኢንቨስት ማድረግ ትፈልግ ነበር፡፡ ጥሩ ግጥምጥሞሽ ሆነ›› ሲሉ ሁኔታውን መለስ ብለው ያስታውሱታል፡፡
ከዚያን ጊዜ ወዲህም የአቡ ዳቢ ከበርቴዎች ከ1 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ለማፍሰስ ወደ ውድቀት እያመራ የነበረውን ክለብ ወደ ሃያልነት እየቀየሩ ነው፡፡ ሆኖም ኩክ ለዘመናት ሲቲን ሲፈታተነው በከረመው ችግር ላይ ገንዘብ ማፍሰስ ብቻውን መፍትሄ እንደማይሆን ተረድተዋል፡፡ ከክለቡ ጋር ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ ቁርኝት ያላቸውን ሰዎች ልብ እና አዕምሮ መማረክ ወሳኝ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
‹‹ለአቡ ዳቢ ዩናይትድ ግሩፕ ያቀረብኩት ገለፃ አሁንም ድረስ በእጄ ይገኛል፡፡ አቡ ዳቢ ዩናትድ ግሩፕ እንደ አማራጭ የያዛቸው ሌሎች ሶስት ክለቦች ነበሩ፡፡ እኛ ግን ከሁሉም ተሽለን ተገኘን፡፡ ያቀረብነው ማንቸስተር የሚለውን ስም ይዘን ነው፡፡ ያለ ሀፍረት በግልፅ የምናደርገው ሀሳባችንን ከግብ ለማድረስ የባላንጣችን ማንቸስተር ዩናይትድን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንደ መሳሪያ መጠቀማችንን ነው፡፡ ሲቲ የሚለውን ወደ ፊት በታም ሃያል የሚሆን ብራንድ እና የማስፋፊያ ስራ በሚያመች 800 ሺ ካሬ ሜትር ዙሪያውን የተከበበ ስታዲየም ባለቤት እንደሆነ ተናገርኩ፡፡
‹‹መልዕክቱን ያስተላለፍኩት ማንቸስተር ሲቲ ምን ያህል እምቅ አቅም እንዳለው መረዳት ለቻሉ ብልህ እና አስተዋይ ሰዎች ነበር፡፡ ህልሜ እውን ሊሆን እንደሚችል አውቀውት ነበር፡፡
‹‹የሚገርመው ለማሳመን የተቸገርኩት በክለቡ ሲያገለግሉ የከረሙ ሰዎችን እና ብዙሃኑን የሲቲ ታማኝ ደጋፊዎች ነበር፡፡ ወደ ማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች ክለብ ሄጄ ማንቸስተርን ማሸነፍ እንደምንችል እና አንድ ቀን የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ እንደምናነሳ ነገርኳቸው፡፡ አያይዤም በቋሚነት በቻምፒዮንስ ሊጉ ተወዳዳሪ እንደምንሆን አሳወቅኳቸው፡፡ ሁሉም ግን የተመለከቱኝ እንደ እብድ ነበር፡፡
‹‹በክለቡ የሚሰሩ ደጋፊዎች በፕሪሚየር ሊጉ ሊያቆየን የሚችለውን 40 ነጥቦች መሰብሰባችንን ሲያውቁ በደስታ ይፍነከነኩ ነበር፡፡ የ35 ዓመታት ውድቀትን እልባት ልናበጅለት ተገደን ነበር፡፡ የቡድኑን ባህል እና አብዛኞቹን በቡድኑ ያሉ መሰረተ ልማት እንደ አዲስ መገንባት ነበረብን፡፡
‹‹መፍትሄውን ዝግመተ ለውጥ ሳይሆን አብዮት ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎችን በተናገርኳቸው ነገሮች እንዳስከፋኋቸው አውቃለሁ፡፡ መሰረታችንን ላለመልቀቅ ታግለናል፡፡ ምንም እንኳን አንዳንዱ የክለቡ ታሪክ ውድቀት ቢሆንም የክለቡን ታሪክ ጠብቀን ለማቆየት ታግለናል፡፡ መጥፎዎቹን አሮጌ ዘመናት ወደ ኋላ በመተው ከዜሮ መጀመር ነበረብን፡፡
‹‹የመጣሁት ከአሜሪካዊ ባህል ነው፡፡ ናይኪን ከመሰለ ታላቅ ካምፓኒ የተገኘሁ ነኝ፡፡ በዚያ በነበርኩበት ወቅት አንዲትም ቀን አዲዳስ ስለሚሰራው ነገር ተጨንቀን አናውቅም ነበርር፡ በመሆኑም ወደ ማንቸስተር ሲቲ ስመጣ እና የምንፎካከረው ማንቸስተር ዩናይትድን እንደሆነ ሲነግረኝ ለሰከንድ እንኳን በኦልድትራፎርድ ምን እንደሚሰራ ለማሰብ አልሞከርኩም፡፡ በቀጥታ ትኩረቴን ያደረግኩት በባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ላይ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ከማንቸስተር ዩናይትድ የበለጠ ቡድን እንሆን ይሆን እንዴ ብለው ሲነጋገሩ እኔ ግን የምፈልገው ከባርሴሎና እንድንበልጥ ነበር›› በማለት ለክለቡ የተመኙትን ከፍታ አሳውቀዋል፡፡
ኩክ በአሁኑ ወቅት የአልቲሜት ፋይቲንግ ቻምፒዮንሺፕ ምክትል ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ የተቋሙ አላማ ቅይጥ ማርሻል አርትን በአውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ማስተዋወቅ ነው፡፡ በለንደን እና ላስ ቬጋስ ቤት እና ንብረት አላቸው፡፡ በሲቲ የነበራቸው ቆይታ የማይሽር ጠባሳ ጥሎባቸው ያለፈ ቢሆንም ቤቴ ብለው የሚተሩት ማንቸስተርን ነው፡፡
‹‹በሲቲ በሰራሁት ስራ እኮራለሁ፡፡ ስሜቴ የተጎዳ ቢሆንም እንደ ፕሮፌሽናል ሁኔታውን ከገመገምነው እኔ ዕድለኛ ነኝ፡፡ 24 ሰዓቱን በሙሉ የምኖረው ለስራዬ ነበርር፡ ስበላም፣ ስተኛም የማስበው ስለ ስራዬ ነበር፡፡
‹‹ከዚህ በፊት ስህተቶችን እፈፅም ነበር፡፡ የፈፀምኩት አንድ ትልቅ ጥፋት ግን ስራዬን እንዳጣ አስገደደኝ፡፡ መልቀቂያ ያስገባሁት ክለቡን ለማዋረድ ባለመፈለጌ ነው፡፡ ነገር ግን ልቤ ደምቶ እና ቅስሜ ተሰብሮ እንደነበር መሸሸግ አልፈልግም፡፡
‹‹ቤተሰቦቼ የሚገኙት ኦሬጎን ውስጥ ፖርትላንድ በሚባል ስፍራ ከማንቸስተር ትንሽ ወጣ ብሎ ፔሻዬር ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱም አካባቢውን የምወደው በፍቅር ነው፡፡ የሚፀፅተኝ ነገር ቢኖርም ማንቸስተር ሲቲ ታሪክ እንዲሰራ በመጠኑም ቢሆን እገዛ አድርጌያለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛ የፈፀምነው ነገር ዳግመኛ ይደረጋል ብዬ አላስብም›› ሲሉ በሲቲ ያሳኩት ገድል የማይረሳ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ለማንቸስተር ሲቲ ሃያል የእግር ኳስ ክለብ ሆኖ ብቅ ማለት የያያ ቱሬ አስተዋፅኦ የገዘፈ ነው፡፡ የቀድሞው ሲቲ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ጋሪ ኩክ በ2008 ሼክ ማንሱር ሲቲን መረከባቸውን ተከትሎ በበርካታ ተጨዋቾች ላይ ገንዘብ አፍስሰዋል፡፡ በዚያው ዓመት ብራዚላዊውን ሪቢንሆ በ32 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ሲቲ መቀላቀል የቻሉ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ካርሎስ ቴቪዝን አስፈርመዋል፡፡ ሆኖም ግን ኩክ ከፈፀሟቸው ዝውውሮች ሁሉ ያያ ቱሬን ያገኙበት ቀዳሚው እንደሆነ ያምናሉ፡፡ አይቮሪኮስታው ባርሳን የለቀቀው በሳምንት የሚያገኘውን 200 ሺ ፓውንድ ታሳቢ አድርጎ እንዳልሆነ ኩክ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡
‹‹ያያ ቱሬ በሲቲ የለውጥ ምክንያት ሆነ፡፡ ሮቢንሆን እና ካርሎስ ቴቪዝን ያስፈረምናቸው ሌሎች ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ ለመማረክ በማሰብ እንደሆነ የብዙሃኑ እምነት ነው፡፡ እውነት ለመናገር ሁለቱም ተጨዋቾች ሲቲን የተቀላቀሉት ለሲቲ ከሚያበረክቱት ይልቅ የሚያገኙትን ታሳቢ አድርገው ነው፡፡
‹‹ያያ ግን የተለየ ነው፡፡ እንደመጣም ይህን ክለብ ታላቅ አደርገዋለሁ ሲል ተናገረ፡፡ እንዳለውም አደረገ፡፡ እርሱን ካስፈረመን በኋላ ታላላቅ ተጨዋቾች በሙሉ ሲቲን መቀላቀል የሚችሉበት ዕድል መኖሩን መመርመር ጀመሩ፡፡ ለምሳሌ ያያን ባናስፈርም ኖሮ ዴቪድ ሲልቫ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ እርሱን ካስፈረምን በኋላ ሌሎቹ ተከታትለው መጡ››
ከአምስት ዓመት በፊት ሲቲ ከኤሲ ሚላን ካካን ለማዘዋወር ሙከራ አድርጎ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ የቀድሞው የሲቲ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ተጫዋቹ የዓለም ሪከርድ በሆነ 100 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ወደ ኢቲሃድ ሊያደርገው የነበረው ዝውውር ሳይሳካ መቅረቱ እንደፀፀተው እንደነገራቸው ተናግረዋል፡፡ በዚያው ክረምት ብራዚላዊው ለሪያል ማድሪድ ተሽጦ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ተመልሶ በሚላን በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡
ኩክ የዝውውሩን ሂደት በተቆጣጠሩበት መንገድ ወቀሳ ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ ነገር ግን የሚላን ባለቤት እና የጣሊያን ጠ/ሚኒስትር የሆኑት ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ዝውውሩን አገዱት እንጂ ተጫዋቹን የማዘዋወሩ ሂደቱ ተጠናቅቆ እንደነበር የሚያመላክቱ ጠንካራ ማስረጃዎች አሉ፡፡
‹‹ሚላን ተጫዋቹን ለመሸጥ ተስማምቶ እንደነበር የሚያረጋግጥ ሰነድ አሁንም ድረስ በእጄ ይገኛል፡፡ እኔ እና ካካ የሲቲን ማሊያ ይዘን ከኋላችን ደግሞ የሚላኑ ቼፍ ኤግዚኪዩቲቭ አድሪያኖ ጋሊያ ቆመው የሚያሳይ ፎቶ አለኝ፡፡ ይህን ያህል ተጉዘን ነበርር፡ ችግሩ የተፈጠረው ካካን መሸጥ ምን ያህል ደጋፊውን ሊያስከፋ እንደሚችል መጀመሪያ ላይ ከግምት ባለማስገባታቸው ነው፡፡ ከተጫዋቹ አባት ጋር ስለ ቆይታው እና ጥቅማ ጥቅሞች ለመነጋገር ባመራሁበት ወቅት የሆነ ችግር እንዳለ ተገለጠልኝ፡፡ እጅግ የተጋነኑ ጥያቄዎችን ይጠይቁ ጀመር፡፡ ያንን ማሟላት የምንችልበት ዕድል ደግሞ አልነበረም፡፡ በወቅቱ የተፈጠረው ችግር ምን እንደሆነ መጠየቄን አስታውሳለሁ፡፡
‹‹ካካ በረንዳ ላይ ቆሞ የሚላንን ማሊያ ሲያውለበልብ በቴሌቪዥን ስመለከት ከዚያ የመንቀሳቀሻ ጊዜዬ መሆኑን አወቅኩ፡፡ የማስበው ቤርሎስኮኒ አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት እንደፈለጉ ነው፡፡ ሚስተር ቤርሎስኮኒ ልምድ ያላቸው ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ አጋጣሚውን ከሚላን ነዋሪዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠንከር እና የሆነ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የተጠቀሙበት ይመስለኛል፡፡
‹‹ሚላን ካካን ሊሸጥልን ተስማምቶ ነበር፡፡ የደጋፊውን ተቃውሞ ሲመለከት ቃሉን አጠፈ፡፡ ከጊዜ በኋላ ካካን በሮቢንሆ ሰርግ ላይ አግኝቼው ነበር፡፡ ለሲቲ ፈርሞ ቢሆን ኖሮ ደስተኛ ይሆን እንደነበር ነግሮናል፡፡ ዳግም ልናስፈርመው የምንችልበት ዕድል መኖር አለመኖሩን ሲጠይቀኝም መርከቢቷ ትታው እንደተጓዘች ነግሬዋለሁ፡፡ በቅርቡም እጅጉን እንደሚቆጭ ነግሮኛል›› ሲሉ በሲቲ የነበራቸውን ቆይታ መለስ ብለው የቃኙበትን ሀሳብ ያጠናቅቃሉ፡፡