Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ፍሬ ከሌለው (ይገረም አለሙ)

$
0
0

{ህይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው ምላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኮል ከመናገር ይከልክል፣ (የጴጥሮስ መልእክት 3፣10)

ይገረም አለሙ

ሰሞኑን ሁለት ነገሮች ጎን ለጎን እየተሰሙ ነው፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያን ከወያኔ የግፍ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ሁሉን አቀፍ ትግል ማድረግ ግድ ነው ያሉና ለዚሁ እየተዘጋጁ እንደሆነ ሲገልጹ የቆዩት ኃይሎች ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መሸጋገራቸውን ከማወጅ አልፈው ሊቀመንበሩ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ ትግሉ ወደተጀመረበት አካባቢ መሄዳቸው ሲሆን ሁለተኛው በተለያየ መንገድ ይህን ትግል የሚቃወሙ ድምጾች ናቸው፡፡ የወያኔን አገዛዝ እንታገላለን በሚሉ መካከል እንዲህ አይነት የነጻነት ትግልን ለማደናቀፍ ያለመ ልዩነት መታየቱ አሳዛኝ ነው፡፡

በቅዱሱ መጽኃፍ ጢሞቲዎስ 2፣2፣20 {በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፡፡እኩሌቶቹም ለክብር እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፡፡እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ ለክብርም የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎ ስራ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል፡፡} ተብሎ እንደተጻፈው እንዲህ ወሳኝ ቀን ሲመጣ መፈተኛው ተግባር ሲሆን በአንድ ጎራ የተሰለፉት ወርቅና ብሩ እንጨትና ሸክለው ግልጽ ብለው ይታያሉ፣ይለያሉ ይታወቃሉ፡፡

ሁሉም እንደ አቅሙ በአንድ ሀገር ልጅነቱ ተግባብቶና እንደ እውቀት ዝንባሌው፣እንደ ሙያና ችሎታው ተሰልፎ ሲሆን ተባብሮ ካልሆነም ተከባብሮ ቢጓዝ ለሀገርም ለሕዝብም የሚጠቅም በጎ ተግባር መከወን ይቻል ነበር፡፡ የወያኔ አገዛዝ ዘመንም እንዲህ ባረዘመ ነበር፡፡ መነጋገሩ ከሌለ መግባባቱ ከጠፋ እንዲህ ስታዩኝ ሸክላ ወይንም እንጨት ብመስላችሁም እኔ ወርቅ ነኝ ብሎ መኮፈስና ያልሆኑትን ለመሆን መዳከር ካለ፣ መልካም ቀኖችን ማየት የሚቻል አይሆንም፡፡ ማንነታችንን አውቀን አቅማችንን ተረድተን የምንችለውንና የሚገባንን እየሰራን ለበጎ ምግባር የተዘጋጀን እንሁን ሲባል ደግሞ የለም ወርቅ ባልሆንም ወርቅ ነህ ብላችሁ ካልተቀበላችሁኝ አይሞከርም ከተባለ በታሪካችን ተደጋግሞ እንደታየው እነዚህ ሰዎች የሚማሩም የሚመከሩም አይደሉምና {ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኩሱንም አትንኩ} (ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፣6፣17) ተብሎ እንደተጻፈው  የሚበጀው መለየቱ ነው፡፡

ነገር ግን መለየቱ  ብቻውን ለክብር አያበቃም፣ በዮሐንስ መልእክት (1፣3፣17) {እንግዲህ እናንተ ወዳጆች ሆይ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ በአመጸኞች ስህተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት አንዳትወድቁ ተጠንቀቁ}፡ ተብሎ እንደተጻፈው በመሰሪዎቹ ሴራ ተጠልፎ ሳይወድቁ፣ በስብከታቸው ተስቦ መንገድ ሳይስቱ፣ ለመለየት ምክንያት የሆነውን ዓላማ ከዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት መሰለፍ ነው የሚያስከብረው፡፡

ዛሬ በተለይ የነጻነት ትግሉ ወደ ተግባር ተሸጋገረ ከተባለበት እለት አንስቶ የምንሰማቸው ነገሮች ሁሉ ከመልካም እሳቤ የመነጩና ለበጎ ተብሎ የሚቀርቡ ቢሆኑ ኖሮ ከሁለትና ሶስት አመት ጀምሮ በሰማናቸውና ዛሬ የመለያያ ሳይሆን የመስማሚያ፣የመነታረኪያ ሳይሆን የመፍትሄ ሀሳቦች በሆኑ ነበር፡፡ ነገር ግን በታላቁ መጽሀፍ 1ኛ ጢሞቲዎስ 1፣5-7፣{የትዕዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹህ ልብና ከበጎ ህሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፡፡ ከእነዚህም አንዳንዶቹ ስተው የሚሉትን ወይንም እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ የህግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ ወደ ክፉ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል፣} ተብሎ እንደተገለጸው ሆነና  ንጹህ ልብ፣ በጎ ህሊና፣ እምነትና ፍቅር የሚባሉ ነገሮች ጠፍተው ለጥፋት የተነሳሳ ልብና ተንኮል ያረገዘ ህሊና በመግነኑ በአንድ ወይንም በሌላ መልኩ ድጋፍ መስጠት በሚገባበት ሰአት የነጻነት ትግሉን ለማደናቀፍ ያለሙ ድምጾች እዚህም እዛም ይሰማሉ፡፡፡

በማቲዎስ ወንጌል 23፣3-8 {ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፣ እነርሱ ግን በጣታቸው እንኳን ሊነኩት አይወዱም ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ አሸንክታባቸውን ያሰፋሉ፣ዘርፉንም ያስረዝማሉ፣ በምሳም የከበሬታ ሥፍራ በምኩራብም የከበሬታ ወንበር በገበያም ሠላምታና መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው መጠራትን ይወዳሉ} እንደተባለው እነርሱ አስበው ያልተሳካላቸውን፣ሞክረው ያልሆነላቸውን፣ወይንም ሊነኩት ያልደፈሩትን ሊሄዱበት ያልመረጡትን ወዘተ ሌላው ሲጀምረው ለማሳካትም ስንዝር ሲራመድ የሆነ ያልሆነ ሰበብ ደርድረው አፍራሽ ጩኸታቸውን ያሰማሉ፡፡ ትግለው ውጤት ለማሳየት ከመጣር ራሳቸውን  በመካብ በየመድረኩና በየመገናኛ ብዙኃኑ ክቡር እየተባሉ ያለስራቸው መሞገስን፣ ወርቅ ሳይሆኑ ወርቅ መባልን ይሻሉ፡፡

ስለሆነም {እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ ለክብርም የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎ ስራ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል፡፡} ተብሎ በሁለተኛይቱ የሐዋሪያው ጳውሎስ መልእክት ወደ ጢሞቲዎስ ሰዎች ምእራፍ 2 ቁጥር 20 ላይ እንደተጻፈው ከእነዚህ ሰዎች ጋር ንትርክና አንካ ሰላንትያ ማብዛት ሳያስፈልግ መለየትና ራስን አንጽቶ በሚቻለውና በሚመርጠው መንገድ የድርሻን ማበርከት ነው የነጻነቱን ቀን ሊያፋጥን የሚችለው፡፡

መጽሀፍ ቅዱስ {ህይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው ምላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኮል ከመናገር ይከልክል፣ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፣መልካምንም ያድርግ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፡} ይላል፡፡ (የጴጥሮስ መልእክት 3፣10) ኢትዮጵያ ከወያኔ አገዛዝ የምትላቀቅበትን ቀን ማየት እንደሚፈልጉ የሚነጋሩ ሰዎች ዛሬ የሚናገሩት ክፉ ነገርና የሚሰሩት ተንኮል እውነት ያችን መልካም ቀን ለማየት የሚናፍቁ ናቸውን የሚል ጣያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡

{ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ ይልቁን ግለጡት እንጂ፣ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳን ነውር ነውና ሁሉ ግን በብርሀን ነውና } ( ኤፌሶን 5፣11-13) ተብሎ እንደተጻፈው የተለያየ ሰበብ እየተጠቀሰ የነጻነት ትግሉን ለማደናቀፍ የሚደረገውን ስውር ሴራ  አለመተባበር ብቻ ሳይሆን በግልጽ እንዲታወቅ ከጓዳ ወደ አደባባይ ከጨለማ ወደ ብርሀን እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ {ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን በገበያም ሰላምታን፣ በምኩራብም የከበሬታን ወንበር፣ በግብርም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ} ( የማርቆስ ወንጌል 12፣38/39) በማለት እየሱስ እንዳስተማረው ከእንዲህ አይነት ሰዎች መለየትም መጠበቅም ያስፈልጋል፡፡ታላቁ መጽሀፍም ይላል፡ {ቅንአትና አድመኝነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽህት ናት፡፡ በኋላም ታራቂ፣ ገር፣ እሺ ባይ፣ ምህረትና በጎ ፍሬ የሞላባት ጥርጣሬና ግብዝነት የሌለባት ናት ፡፡ የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዞራል፡፡} ያዕቆብ 3፣16-18)      አንድየ የማሪያም ልጅ ለክፉዎች ልብ፣ ለበጎዎች ጽናት፣ ለእናት ኢትዮጵያ ነጻነት፣ለኢትዮጵያዉያን ፍቅር ይስጥ….አሜን…

Comment


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>