Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: ‹‹አርሰናል ከህይወቴ ጋር ተቆራኝቷል›› –ካዞርላ

$
0
0

Arsenal's Santi Cazorla reacts after scoring against Aston Villa, during their English Premier League soccer match, at the Emirates Stadium, in London, Saturday, Feb. 23, 2013. (AP Photo/Bogdan Maran)

Arsenal’s Santi Cazorla reacts after scoring against Aston Villa, during their English Premier League soccer match, at the Emirates Stadium, in London, Saturday, Feb. 23, 2013. (AP Photo/Bogdan Maran)


አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ብቃታቸውን ያስመሰከሩ እና በቴክኒክ ተሰጧቸው ጎልተው የወጡ የላ ሊጋ ተጨዋቾችን ለማስፈረም ያላቸው ብልሃት አስገራሚ ነው፡፡ ግለሰቡ በተደጋጋሚ ይህንን ፈፅመዋል፡፡ ማንም ሳያውቃቸው እርሳቸው እነኚህን ተጨዋቾችን ለማስፈረም አይቸገሩም፡፡

ቬንገር ባለፉት ሶስት የዝውውር ጊዜያቶች በዚህ አይነት መልኩ ተጨዋቾችን አስፈርመዋል፡፡ በ2013 አርሰናል የአማካይ ክፍሉን ማጠናከር ነበረበት፡፡ ቬንገር በተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነው በመጨረሻም በሪያል ማድሪድ የተገፋውን ሜሱት ኦዚልን አስፈርመዋል፡፡ በወቅቱ የሊቨርፑሉን አጥቂ ሉዊስ ሱዋሬዝን ለማስፈረም ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ኡራጓዊውን አጥቂ ማግኘት የተሳናቸው ፈረንሳዊው አሰልጣኝ በመጨረሻም ሳይጠበቁ 42.5 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍለው ጀርመናዊውን አማካይ የግላቸው አድርገውታል፣ ይህ ክፍያ ለአርሰናል በተጨዋቾች የዝውውር ሪከርድ ታሪክ ቀዳሚውን ቦታ ይወስዳል፡፡

ቬንገር በሌሎች ክለቦች የዝውውር ረድፍ ውስጥ ያልገቡ ተጨዋቾችን ማስፈረማቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከብራዚሉ የዓለም ዋንጫ መልስ ባርሴሎና ሱዋሬዝን ሊያስፈርም በአጥቂ መስመሩ ከሚገኙ ተጨዋቾች መሀከል አንዱን መልቀቅ ነበረበት፡፡ ሊዮኔል ሜሲ የባርሴሎና ምልክት በመሆኑ ይህንን ማሰብ አይቻልም፡፡ ኔይማር ወደ ባርሴሎና ካመራ የተቆጠሩት የወራት ጊዜ ብቻ መሆናቸው እንዲሁም የወጣበት ከፍተኛ ክፍያ ይህንን እንድናስብ የሚያስችል አይመስልም፡፡ ስለዚህ የባርሴሎና አመራሮች የነበራቸው አማራጭ አሌክሲስ ሳንቼዝን ማሰናበት ነበር፡፡

ሳንቼዝን ለማስፈረም ሊቨርፑል ከፍ ያለ ፍላጎት ነበረው፡፡ አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ከሱዋሬዝ ዝውውር ያገኙትን 75 ሚሊዮን ፓውንድ ተጠቅመው ቺሊያዊውን ለማስፈረም ከፍ ያለ ፍላጎት ቢያሳዩትም ቬንገር የተጨዋቾቹን ፍላጎት ተጠቅመው በመጨረሻም ግን ኢምሬትስ አምጥተውታል፡፡ በወቅቱ ለዝውውሩ የወጣበት ክፍያ ከኦዚል ያነሰ ቢሆንም በክለቡ ታሪክ ከውድ ተጨዋቾች ተርታ የሚቀመጥ ነው፡፡ 35 ሚሊን ፓውንድ የወጣበት አጭሩ አጥቂ ከአርሰናል የአንድ ዓመት ቆይታው አስደናቂ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ያነሳው ሳንቼዝ በ52 ጨዋታዎች 25 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ያስቆጠራቸው ሊጉ ተሳታፊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የአርሰናል ተጨዋቾች በተመሳሳይ ወቅት ምርጥ ብቃታቸውን አውጥተው ቢጠቀሙም ቬንገር ግን ካዞርላን ያስቀድማሉ፣ ሁለገቡ ተጨዋች ሜዳውን አካልሎ የሚጫወትበት መንገድ በጣም ይገርማል፣ በአማካይ ተከላካይ ላይ ከፍራንሷ ኮክለ ፊት ተጫውቷል፣ ተደራቢ አጥቂ እና በሁለቱም መስመሮ ተጫውቷል፡፡
ቬንገርም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ያሳየውን ብቃት በጣም በጥንቃቄ እና በጥልቀት ተመልክተው ‹‹ሳንቲ ካዞርላ ከውድድር ዓመቱ ጅማሮ አንስቶ እስከመጨረሻው ድረስ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል›› ብለው መስክረውለታል፡፡

ቬንገር ሌሎች ተጨዋቾች በግል ያሳዩትን ብቃት አጥተውት አይደለም፡፡ ካዞርላን በቀዳሚነት ሲያስቀምጡ ምክንያታቸው ተጫዋቹ በዙሪያው የሚገኙ ተጨዋቾች ያላቸውን ብቃት አውጥተው እንዲጠቀሙ ባበረከተው አስተዋፅኦ ነው፡፡

የአርሰናል አማካይ ክፍል እስትንፋስ ኮክለ ቢሆንም ከእርሱ ጎን ተሰልፎ የማጥቃቱን እንቅስቃሴ የሚያስጀምረው እና በመጨረሻዎቹ 30 ሜትሮች ላይ የጨዋታውን እንቅስቃሴ የሚያፈጥነው ካዞርላ ነው፡፡ ትልልቅ ቡድኖች ሚዛናዊነትን የሚጠብቁት በዚህ አይነት መልኩ ነው፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት አርሰናልን ሲቀላቀል በቅንጦት መልክ ያልታየው ካዞርላ በአሁኑ ሰዓት የአርሰናል መሪ ሆኗል፡፡

ካዞርላን ከሌሎች ተጨዋቾች ለየት የሚያደርገው በየትኛው እግሩ እንደሚጫወት ግራ እስኪያጋባ ድረስ በሁለቱም እግሮቹ መጫወቱ ነው፡፡ ሆኖም የዚህ ምክንያት ከጉዳቱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

‹‹ሁልጊዜም ቢሆን እግር ኳስ እጫወት የነበረው በቀኝ እግሬ ነበር፡፡ በአንድ አጋጣሚ የቀኝ እግሬ ጉልበቴ ላይ መጠነኛ ጉዳት አስተናገድኩኝ፤ ይህ ደግሞ በግራ እግሬም እንድጫወት አስገደደኝ፣ በዚህም ይበልጥ በግራ እግሬ መጫወት ጀመርኩኝ፡፡

‹‹በግራ እግሬ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ከመደበኛ ልምምድ መልስ በተደጋጋሚ ግድግዳ ላይ ኳስን እመታ ነበር፡፡ ይህንን ደጋግሜ በመፈፀም የምመታው ምት ጠንካራ ስለመሆኑ አረጋግጥ ነበር፡፡ ወጣት ተጨዋቾች ሁሉም ነገር የሚሳካው በጠንካራ ሥራ እንደሆነ መረዳት አለባቸው፡፡ ስለዚህ በመጨረሻ ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም፡፡
‹‹እግርኳስን መጫወት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ በሁለቱም እግሮቼ መጫወት ተፈጥሯዊ ልማዴ ሆኗል፡፡ ነገር ግን በሁለቱም እግሮቼ እኩል ለመጫወት (አንዱን ከአንዱ ላለማበላለጥ) ጠንክሬ መሥራት ነበረብኝ፡፡ በመጨረሻም ይህንን ማሳካት ችያለሁኝ›› በማለት ተፈጥሯዊው እግሩ የትኛው እንደሆነ ግራ እስኪያጋባ ድረስ በሁለቱም እግሮቹ መጫወት የቻለበትን ምስጢር አስረድቷል፡፡

30 ዓመቱን የደፈነው ካዞርላ በእግርኳስ ህይወቱ አስደሳች አጋጣሚ ቢያሳልፍም አሁንም ቁርጠኝነቱ በጣም ይገርማል፡፡ አርሰናልን ከተቀላቀለ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት (2013 እና 2015) ያሳካቸው የኤፍ.ኤ.ካፕ ድሎች ቀዳሚውን ቦታ ይወስዳሉ፡፡ እነኚህ ሁለት ዋንጫዎች ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ከ2004/05 የውድድር ዘመን በኋላ ምንም ዋንጫ ላላገኙት ቬንገርም ሆነ ደጋፊዎቹ ወሳኝ ናቸው፡፡

በስፔን ብሔራዊ ቡድን ግን ውጤታማ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡ ለአገሩ 73 ጨዋታዎችን የፈፀመው አማካይ በ2008 እና 2012 የአውሮፓ ዋንጫ ላነሳችው ስፔን ወጣ ገባ እያለ ተጫውቷል፡፡ ስፔን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫውን ስታነሳ ግን በአንጀት ህመም ምክንያት የቡድኑ አካል አልነበረም፡፡
የሳንቲ ህልም አንድ ቦታ ላይ የሚቆም አይመስልም፡፡ ጫማውን ከመስቀሉ በፊት ተጨማሪ ድሎችን ማሳካት ይፈልጋል፡፡

‹‹የውድድር ዓመቱን የፈፀምነው አስደሳች በሆነ መልኩ ነው›› የሚል አስተያየትን የሚሰጠው የቀድሞው የማላጋ ኮከብ ‹‹በቀጣዩ ዓመት ይበልጥ ተጠናክረን መቅረብ አለብን፣ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ‹‹ስለማንሳት እና በቻምፒዮንስ ሊጉ ረጅም ርቀትን ስለመጓዝ ማሰብ አለብን›› ጠንካራ ቡድን እንዳለን ይሰማኛል፣ ተግተን መስራት ያለብን ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት ላይ ነው፡፡ ጠንካራ አዕምሮዎችን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ያሸጋግረናል፡፡ ቼልሲ ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ አዎን ይህ በግልፅ የሚታይ ነው፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ሆነዋል፤ የእኛም ቡድን ቢሆን ያለጥርጥር ጠንካራ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጨዋታ አንስቶ ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ በአውሮፓ ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎናን የመሳሰሉ ክለቦች የዓለማችን ምርጥ ተጨዋቾች ይዘዋል፡፡ እኛም ብንሆን በእነርሱ ደረጃ ስለመገኘት ማሰብ አለብን›› በማለት ሁልጊዜም ቢሆን መዳረሻቸው በትልቅ ደረጃ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

ካዞርላ ደረጃቸው የላቁ ተጨዋቾች መፈረማቸው አርሰናልን እንደሚያጠናክረው ያምናል፡፡ የሳንቼዝ እና ኦዚል ዝውውር ምን ያህል በግል ደረጃውን እንዳሻሻለው ጠንቅቆ ይረዳል፡፡ በቀጣዩ ዓመትም በተመሳሳይ ደረጃቸው የላቀ ተጨዋች እንዲመጡ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡

‹‹ስም ያላቸው ተጨዋቾች መፈረማቸው ያስደስታል፣ ሁሉም ተጨዋቾች ያላቸው ስሜት ተመሳሳይነት አለው›› ይላል ሳንቲ፡፡ ‹‹እንደ አሌክሲስ እና ሜሱት አይነት ምርጥ ተጨዋቾች ወደዚህ መምጣታቸው ብቃቴን አውጥቼ እንድጠቀምና እንዳሻሽል አግዞኛል፤ የሁለቱ ተጨዋቾች ጥምረት ቡድናችንን ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህ ላይ የአጨዋወት ዘይቤያቸው ከቡድኑ ጋር በፍጥነት የሚዋሃድ አይነት ነው››

አርሰናል ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ድረስ ሙሉ የሆነ ቡድን ይመላል፡፡ ይበልጥ በአማካይ ስፍራ ላይ በርካታ አማራጮችን ይዟል፣ በዚህ ቦታ ላይ ከሚጫወቱ ተጨዋቾች መሀከል አንዱ የሆነው ጃክ ዊልሸር በውድድር ዓመቱ ከጉዳት ጋር እየታገለ በአርሰናል ማልያ በቂ ጨዋታዎችን ቢያከናውንም ባለፈው ዓመት መጨረሻ ተስፋ ሰጪ ነገር አሳይቷል፡፡
እንግሊዝ በቅርቡ ከሶሎቬንያ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ላይ ያሳየው ብቃት እና ጎል ማስቆጠሩ ሁሉንም ነገር ሊነግረን ይችላል፣ ካዞርላ የቡድን ጓደኛው ከእንግሊዛውያን ተጨዋቾች በተቃራኒ በላ ሊጋው መጫወት የሚያስችል ኳሊቲ እንዳለው ጠቅሷል፡፡

‹‹ጃክ ያለጥርጥር በስፔን መጫወት የሚያስችል ኳሊቲ አለው›› ይላል ካዞርላ፡፡ ‹‹ተሰጥኦ ያለው ታላቅ ተጨዋች ነው፡፡ እርሱን የመሰለ ተጨዋች መያዛችን እድለኞች ነን፤ የእግር ኳስ ህይወቱን ወደላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ከሆነ በስፔን ላ ሊጋ የመጫወት አቅም እና ብቃት እንዳለው እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁኝ፡፡
‹‹እንግሊዛውያን ተጨዋቾች ግን ስፔን ላ ሊጋ ተጉዘው የማይጫወቱበት ምክንያት አይገባኝም፡፡ ነገሩን ሳስበው እግረማለሁኝ፤ እርግጥ ነው ከዚህ ቀደም ስቲቭ ማከማናማን፣ ዴቪድ ቤካም እና ማይክል ኦዌን በላ ሊጋው ተጫውተዋል፡፡ ሆኖም ግን ቁጥራቸው ብዙ የሚባል አይነት አይደለም›› በማለት የእንግሊዛውያን ተጨዋቾች በላ ሊጋው ያለመታየታቸው ምክንያት እንዳልገባው ያስረዳል፡፡

የላ ሊጋ ክለቦች የካዞርላን በድጋሚ ወደ ስፔን መመለስ አጥብቀው ይመኛሉ፤ በቀጣይ አማካዩን ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን አርሰናልን ለመልቀቅ የሚደፍር አይመስልም፡፡ እርሱም ቢሆን ከኢምሬትስ መልቀቅ የሚፈልግ አይነት አይደለም፡፡

‹‹ለጊዜው አርሰናል ቤቴ ነው፡፡ የምኖረው የዕለት ህይወቴን እንጂ መጪውን ዘመን አሻግሬ አልመለከትም፣ በአሁኑ ሰዓት ከአርሰናል ጋር ስኬትን እንጂ ከዚያ ተቃራኒ የሆነ ነገር ማሰብ አልፈልግም፤ አርሰናል አቅጣጫዬን የሚጠቁምልኝ መንገዴ ነው፡፡ ከምንም በላይ ከህይወቴ ጋር የተዋሃደ ጉዳይ ሆኗል›› በማለት በኢምሬትስ ቆይታው ስኬታማ መሆንን እንጂ ከክለቡ ጋር ስለመለያየት በጭራሽ እንደማያስብ ጠቁሟል፡፡

ስፔናዊውን ተጨዋቾች በፕሪሚየር ሊጉ ለረጅም ጊዜ ቆይተው ስኬታማ የሆኑበትን ጊዜ ማስታወስ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሴስክ ፋብሪጋዝ በአርሰናል ስምንት ዓመት ቢቆይም አንድም ዋንጫ አላነሳም፤ ካዞርላ በሶስት ዓመት ቆይታው ሁለት ጊዜ የኤፍ.ኤ ካፕ ዋንጫዎችን አንስቷል፤ እንደ ፋብሪጋዝ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ለመሆን ቀጣዩ ዓመት የምርጥ አጋጣሚ ይመስላል፡፡

አርሰናል ከ2003/04 የውድድር ዘመን በኃላ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ምን ያስፈልገዋል? ካዞርላ እንዳለው ጠንካራ አዕምሮ፣ ወጥ አቋም እና ደረጃቸው የላቁ ተጨዋቾችን ማስፈረም ይህ ብቻውን በቂ አይመስልም፣ ሻምፒዮን የሚሆኑ ቡድኖች ጠንካራ የተከላካይ መስመር አላቸው፡፡

‹‹በቀጣዩ ዓመት አስተካክለን መቅረብ ከሚገባን ግብአቶች መሀከል ቀዳሚውን ቦታ የሚወስደው የተከላካይ መስመሩ ጥንካሬ ሊሆን ይገባል›› የሚል መረጃን ሰጥቶ ‹‹ይህንን ማስተካከል ከቻልን የአጥቂ መስመራችን ጠንካራ ይሆናል፡፡ ባለፈው ዓመት በሜዳችን ሳይቀር በትንንሽ ቡድኖች ነጥብ የመጣላችን ምስጢር ይኸው የተከላካይ መስመራችን የቦታ አጠባበቅ ወሳኝነት አለው›› ይላል፡፡

የሰሜን ለንደኑ ክለብ በቀጣይ አዳዲስ ተጨዋቾችን የሚያስፈርም ከሆነ ፔትር ቼክ እና የፖርቶው አጥቂ ጃክሰን ማርቲኔዝ በአማራጭነት ይቀርባሉ፡፡ ኮሎምቢያዊው አጥቂ ለዝውውር 25 ሚሊዮን ፓውንድ ተጠይቆበታል፡፡ የቼክ ዝውውር ደግሞ ውስብስብነት በዝቶበታል፡፡

‹‹ይህ ፈታኝ ውሳኔ ነው፡፡ አርሰን ቬንገር ውሳኔውን እንደሚያሳልፍ ይሰማኛል፣ የእርሱ ውሳኔ ለቡድኑ የላቀ ጠቀሜታ አለው፣ የትኛውም ተጨዋች ቢመጣ ወሳኙ ነገር የቡድኑን ደረጃ የሚያጎለብት መሆን አለበት፡፡ በየትኛው ቦታ ተጨዋቾች እንዲመጡ ብትጠይቁኝ ቅድሚያ የምሰጠው በአጥቂ ቦታ ላይ የሚጫወት መሆን አለበት፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ተጫውቶ ቡድኑን ውጤታማ የሚያደርግ ቢሆን ደስ ይለኛል›› ይላል፡፡

የተከላካይ መስመሩ ግን አሁንም ትኩረት ይሻዋል በመሀከል ተከላካይነት ቦታ ላይ አስተማማኝ ሊባል የሚችለው ሎሮ ኮሲዬልኒ ነው፣ ፔር ሜርትሳከር ዕድሜው ገፍቷል፡፡ ከጉዳት ጋር በተያያዘ በእርሱ ላይ እርግጠና መሆን አይቻልም፡፡ ማቲዮ ዴቡቼም ለጉዳት ቅርብ ተጨዋች ሆኗል፡፡ በክረምቱ ከሳውዝአምፕተን አርሰናልን የተቀላቀለው ካሉም ቼምበርስ የመሀል ተከላካይ ሆኖ መጫወት ቢችልም በውጤታማነቱ ላይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

የካርል ጄንኪንሰን ቆይታ አስተማማኝ የሚባል አይነት አይደለም፡፡ እንግሊዛዊውን ተከላካይ በውሰት ለመውሰድ ዌስትሃም ዩናይትድ እና ሳውዛመውተን ጥያቄ ቢያቀርቡም አርሰናል ያቀረበውን የ15 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡ ምናልባት የቀድሞው የቻርልተን አትሌቲክ ተከላካይ በቀጣይ ወደ ሰንደርላንድ ሊያመራ ይችላል፡፡
እንደ ካዞርላ እምነት ጠንካራ አዕምሮ፣ ወጥ የሆነ አቋምና ደረጃቸው የላቁ ተጨዋቾች ማስፈረም እና ጠንካራ የተከላካይ መስመር መገንባት በቀጣዩ ሲዝን አርሰናልን ለፕሪሚየር ሊጉ ስኬት አብቅቶ ለቻምፒዮንስ ሊግ ተፎካካሪነት ያበቃዋል፡፡
ሳንቲ ካርላን እንወቅ
ሙሉ ስም፡- ሳንቲያጎ ካዞርላ ጎንዛሌዝ
የትውልድ ዘመን፡- ዲሴምበር 13/1984
ዕድሜ፡- 30
የትውልድ ቦታ፡- ሊያኔራ (ስፔን)
ቁመት፡- 1.68 ሜትር
ቦታ፡- የመስመር አማካይ (የአማካይ አጥቂ)
ክለብ፡- አርሰናል
የማልያ ቁጥር፡- 19


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>