(ዘ-ሐበሻ) የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከሌሎች የግንቦት 7 አመራሮች ጋር በመሆን አስመራ መግባታቸውን የዘ-ሐበሻ ምንጮች አረጋገጡ:: ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር አቶ ነአምን ዘለቀም ተጉዘዋል እየተባለ ሲሆን ዘ-ሐበሻ ይህን በማጣራት ላይ ትገኛለች::
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ባለፈው ጁላይ 3 በዋሽንግተን ዲስ “ካሁን በኋላ ሕዝብን ሰብስቦ ማነጋገር ላቆም ነው” ማለታቸውን ዘ-ሐበሻ መዘገቧ አይዘነጋም::
የአርበኞች ግንቦት 7 ሰሞኑን የሕወሓት መንግስት ከትግራይ ክልል ጋር በግድ ቀላቀለው በሚባለው ወልቃይት አካባቢ ጥቃት ማድረሱን እና እስካሁንም ከ100 በላይ የሕወሓት መንግስት ወታደሮችን መገድሉን ሲያሳውቅ ከርሟል::
ከሰሞኑ እየተቀጣጠለ ያለው ትግል መድረሻውን አራት ኪሎ ቤተመንግስት ለማድረስ ነው ሲል አርበኞች ግንቦት 7 በተደጋጋሚ ሲገልጽ የቆየ ሲሆን ዶ/ር ብርሃኑ ነጋም ሆነ ሌሎች የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር አባላት የሕይወት መስእዋትነት ሳይቀር ለመክፈል ወደ ትግሉ ሜዳ መውረዳቸውን ከንቅናቄው አካባቢ ዘ-ሐበሻ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል::
ዘ-ሐበሻ ከዚህ ቀደም ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ አስመራ ሊሄዱ ነው ስትል መዘግቧ የሚታወስ ሲሆን በዚህም መሠረት ዶ/ሩ ትናንት ማምሻውን አስመራ መድረሳቸውን የዘ-ሐበሻ ምንጮች አርጋግጠዋል::
ሜዳ ላይ ሕይወታቸውን ለመስጠት የተዘጋጁት የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት አባላት የመሪዎቹ ድጋፍ ስለሚያስፈልገው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደዚያው ሄደዋል:: ዶ/ሩ ወደ አስመራ ከመሄዳቸው አስቀድሞ በዋሽንግተን ዲሲ ከሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተሰባሰበውን የመድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶችን መረከባቸውን ዘ-ሐበሻ ዘግባ ነበር::
ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር የንቅናቄው አመራር አባል የሆኑት አቶ ነአምን ዘለቀም ተጉዘዋል የሚሉ መረጃዎች ለዘ-ሐበሻ የመጡ ሲሆን ጉዳዩን ለማጣራት ወደ አቶ ነአምን ዘለቀ የሰሜን አሜሪካ ስልክ ስንደውል ስልካቸው ዝግ መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል:: 100% አስመራ ሄደዋል የሚለውን ለማረጋገጥም ዘ-ሐበሻ እየሰራች ትገኛለች::
የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ ትግሉ ሜዳ መውረድ ትግሉን የበለጠ ያፋፍመዋል የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ:: በተለይም ‘አሜሪካ ሆኖ መታገል አይቻልም” ለሚሉት ትችቶች ትክክለኛ ምላሽ ነው የሚሉ ተንታኞችም አሉ::
በዚህ ዙሪያ ዘ-ሐበሻ ተከታታይ መረጃዎችን ትለቃለች::