ለ፴(ሰላሣ) ቀናት በፆም እና በፀሎት ተወስናችሁ፣ ፈጣሪያችንን ስትለማመኑ የከረማችሁ የእስልምና ዕምነት ተከታይ ወገኖቻችን፦ ኢድ ሙባረክ!
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት
በመሠረቱ የረመዳን የፆም ወር በረከትን እና መተዛዘንን ይዞ እንደሚመጣ የሚታመንበት ወቅት ነው። ሙስሊሞች በዚህ ወቅት ራሣቸውን በፆም እና በፀሎት ወስነው፣ ፈጣሪያቸውን ከመለመን ባሻገር ለድሆች ሠደቃ (ምፅዋት) በመለገስ፣ ለሌሎች ሰዎች ውለታ በመዋል፣ ለተራቡ በማብላት፣ ለታረዙ በማልበስ፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ ሌሎችንም በጎ ተግባሮች በማከናወን ያሣልፉታል። ሆኖም ያለፉት ፳፬(ሃያ አራት) ዓመቶች ለኢትዮጵያውያን የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ታላቅ የሠቆቃ እና የሽብር ዓመታት ሆነው ዘልቀዋል። ገና ከጥንስሱ «በከፋፍለህ ግዛው» መሠሪ የአገዛዝ ዘዴ ኢትዮጵያውያንን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሣው የትግሬ-ወያኔ፣ ኃይማኖትን ለኢትዮጵያውያን የመፋጃ አጀንዳ ለማድረግ ያልፈነቀለው ድንጋይ፣ ያልማሰው ጉድጓድ የለም። ጥረቱ እንዳሰበው ባይሣካለትም፣ አንዳንድ የታሪክ ጠባሣዎችን ትቶ ማለፉ አልቀረም። ይህ የትግሬ-ወያኔዎች የአገዛዝ አቅጣጫ የባንዳ ወላጆቻቸው ጌቶች ከነበሩት ከፋሽስት ጣሊያኖች የተቀዳ ዘዬ ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የእስልምና ዕምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በጀመሩት «ድምፃችን ይሰማ» በተሰኘው ሰላማዊ የመብት ማስከበር ጥያቄ የተደናገጠው የትግሬ-ወያኔ አገዛዝ፣ አያሌ የዕምነቱን ተከታዮች ለእሥር ሲዳርግ ጥቂቶችንም በግፍ ገድሏል። ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት በኢትዮጵያውያን የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ላይ በትግሬ-ወያኔ አገዛዝ የሚፈፀመውን የጅምላ እሥር እና አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በከፍተኛ ሁኔታ ያወግዛል።
በዚህ አጋጣሚ በአስቸጋሪ ሁኔታ በእሥር ቤት ውስጥ ሆነው እንደዕምነታቸው ሥርዓት የኢድን በዓል ለማክበር ያልቻሉትን የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ሁላችንም በያለንበት እንድናስባቸው አደራ እንላለን።
ኢድ ሙባረክ!
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት