Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሻእቢያ ለምን ? ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ

$
0
0
ከቀደሙ ልምዶች መማር መጠየቅ ወይም መረዳት ተመሳሳይ ስህተቶች ተደጋግመው እንዳይፈፀሙ ይረዳል በተለያዩአጋጣሚዎች ባለፈው አሰርተ -አመት በጣት የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች ወደ አስመራ ተጉዘዋል ። ከነዚህም ውስጥ አንዱና ቀዳሚው እኔ ነኝ ብል ማጋነን አይሆንብኝም ። ደጋግሜም ወደ ኤርትራ ተጉዣለሁ ።
ከአርበኞቹ ጋር ሰላምታ ስለዋወጥ ። በተለይ ሰላምታ እየሰጠሁት ያለው አርበኛ ካሳሁን ሁንዴ ኢትዮጵያዊ የግንባሩ አመራር ይጠናከር በማለቱ በሻእቢያ ጉርጓድ ወስጥ ታስሮ ለወራት ሲሰቅይ ከቆየ በኋላ የተረሸነ ።
ወድ አንባቢዬ ሆይ!
 
እነዚህ ከአሁን ጀምሮ በተከታታይ የማቀርባቸውን የጉዞ ማስታወሻዎቼ እንዲያተኩሩ የምፈልገው በኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ላይ ብቻ ነበር ። ሆኖም ግን ስለአርበኞች ግንባር መከታተል ስጀምር ህይወት በራሷ መንገድ ይዛኝ የነጎደችባቸው ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴዎች ነበሯትና እግረ መንገዴን ያየሁቸውና ያስተዋልኳቸው ብዙ ሁኔታዎች አጋጥመውኛል ።
 
 demisይህ ፅሁፌ የማንንም ወገን ወይም ቡድን የመጥቀምም ሆነ የመጉዳት አላማ የለውም ። ምናልባት ባቀራረቤ ከረር ወይም ለስለስ ያደረኩ ከመሰላችሁ ትኩረቴ እውነታው ላይ ብቻ ስለሆነ ፋክት መሆኑን ብቻ ተመልከቱልኝ ። ለወጣቱና በቦታው ላልነበርው የሃገሬ ዜጋ ሁሉ በጉዞዬ ላይ ያየሁትንና የሰማሁትን ማካፈል ግዴታየ ነው ። ሁሉም ሰው የሃገሩ ጉዳይ እኩል ይመለከተዋል ። አንድ ዜጋ ብሄራዊ ጥቅሙን ከማስጠበቅ አልፎ ለወደፊቷ የሃገሪቷ መፃኢ ትውልድ ሰላማዊት  ሃገር ማስተላለፍ ይችል ዘንድ ትክክለኛ መረጃ  ሊኖረው ይገባል ። በሰከነ መንፈስ ተረጋግቶ መርጃን የሚመዝን ሰው ፤ በቀላሉ ስህተት ውስጥ አይዘፈቅም ።
 
ወገኖቻችንና  ዜጎቻችን ከየትኛውም የአገራችን ክፍሎች ይምጡ፤ አምነውብውትም ይሁን ሳያምኑበት እየከፈሉት ያሉት መስዋእትነት አለ ።  መስዋእትነቱን ለመክፈል በፈቃደኝነት የሄዱት የጠበቃቸውና ያገኙት እንዳሰቡት ነበር ወይ ? ያለፈቃዳቸው በምርኮ የሄዱትስ ኑሯቸው እንዴት ነው ? ይህን ማንም ዜጋ ሊያጤነው ይገባል ብየ አስባለሁ ። በኤርትራው ተደጋጋሚ ጉዞዬ መልካምና ቅን የሆኑ ኤርትራውያን ተዋውቄአለሁ ።  በዚያው ልክ ደግሞ የሰው ልጅ ስቃይና መከራ ውስጣቸውን በሃሴት የሚያለመልምላቸው ቂመኛና ጥቅመኛ ኤርትራውያንም አጋጥመውኛል ። በኤርትራው ጉዞየ ላይ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ዘላለማዊ  ወንድሞችም አትርፌአለሁ ። ተኮራርፈን የቀረንም ወገኖች አለን ። ብንኮራረፍም ዛሬ ላይ ሆነን ሁላችንም የነበረውን ሁኔታ ስናጤነው ፤ የችግሮቻችን ምንጮች ምንና እነማን እንደነበሩም የተረዳን ይመስለኛል ። ያም ሆኖ አብዛኛዎቻችሁ  የሃገራችሁ ክብርና ፍቅር ልባችሁ ወስጥ እንደሚነድድ ተረድቻለሁ ። መንገዶቻችን የተለያዩ  ቢሆኑም በቅን ልቦና ለአርበኞቹ ትለፉ እንደነበር ግን ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለኝም ። ስለዚህም በዚህ አጋጣሚ ዘላለማዊ አክብሮቴን ልገልፅላችሁ እወዳለሁ ።         
 
ለምን ይህን ጊዜ መረጥክ የሚል ጥያቄ ልታነሱ የምትችሉ ወገኖች እንዳላችሁ አውቃለሁ ። እኔም ሆንኩ አብረውኝ የነበሩ ሰዎች ስለዚህ ጉዳይ ሳንወተውት ያሳለፍንበት ጊዜ አልነበረም ። አንዳንዴ  ጊዜው ሌሎች ሁኔታዎች ላይ ያተኩርና የህዝቡን የማስተዋል አቅጣጫ ወደ ሌላ መስመር ይዞት ይነጉዳል  ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ጊዜው ያመጣቸው የፖለቲካ ሾፌሮች የግል ፍላጎት ስለአርበኞች ግንባር መነጋገር ፤ የነሱን የፖለቲካ ስራ የሚያደናቅፍባቸው ወይም ጥላ የሚያጠላበት መስሎ ስለሚታያቸው እንዳይነገር እንዳይሰማ መሰናክል ይፈጥሩ ነበር ። ከዚህ ሌላ ደግሞ በነፃነት አስተያየትን መግለፅ ትክክል ነው ብለው የሚያምኑ በጣም ጥቂት ሚዲያዎች  እንዳሉ ሁሉ ፤   አብዛኛዎቹ ድጋፍ እናጣለን ከሚል ስጋት ማንም ሳያስገድዳቸው ራሳቸው ላይ ግለ-ሳንሱር (self censorship) ይጥላሉ  ።  እና መረጃዎች በትክክል እንዳይደርሱ ምክንያት  ይሆናሉ ።
አንድ ፀሃፊ በስሙ እስከፃፈ ድረስ የፅሁፉ ባለቤትነትና ሃላፊነት የራሱ ይሆናል ። የሚዲያዎቹ ሃላፊነት የመነጋገሪያ ፤ የመወያያና የመከራከሪያ መድረኩን ማዘጋጀት ብቻ መሆን ይኖርበታል ።    ስለዚህ በዚህና በመሳሰሉት ጉዳዮች ምክንያቶች  ሳላቀርባቸው ቆይቻለሁ ።ከብዙው በጥቂቱ ምክንያቶቼ እነዚህ ነበሩ ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ዛሬ  አፍጥጦና ገጦ የወጣ ጉዳይ አለ ። የኢትዮጵያ ጉዳይ እየተመራ ያለው በኢትዮጵያውያን አይደለም ብዬ አምናለሁ ። የትእዛዝ ሰጪነትና ተቀባይነት ግንኙነት የሎሌነት ግንኙነት ነው ። ይህ ደግሞ አገራችንንና ህዝባችንን ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፍላቸዋል ። ይህን መስል ግንኙነቶችም ወያኔና ህዝባችንን ያስከፈለው ዋጋ  የቅርብ ጊዜ ትዝታዎቻችን ናቸው ። አሁን ግን ጊዜው የደረሰ ስለመሰለኝ ፤ በተከታታይ አቀርበዋለሁ ።
 
  ስለ ኤርትራና  ስለኢትዮጵያ  ህዝቦች ባህላዊ ፤ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ግንኙነት እዚህ ላይ መጥቀሱ አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም ። የዛሬው ጎልማሳ ትውልድ የአንድነቱንም ሆነ የልዩነቱን ዘመን በሚገባ ያውቀዋልና ።
 
በረራ ወደ አስመራ!
 
        የአስመራው በረራዬ  ከፍራንክፈርት ጀርመን የተነሳው አመሻሽ ላይ ነበር ። ወደ ደቡብ ምስራቃዊ አቅጣጫ አፍንጫውን የደገነው የተሳፈርኩበት አውሮፕላን የአውሮፓን ሰማይ እየሰነጠቀ ነጎደ ። በአውሮፕላኑ መስኮት አይን አስከሚደርስበት ድረስ የአውሮፓን ምድር ሳይ  አንዳንድ ቦታ ክምችት ክምችት ብለው ሌላ ቦታ ደግሞ ብትንትን ብለው የሚታዩት የኤሌክትሪክ ብርሃኖች ፤ ጥቁር ምንጣፍ ላይ የተበተኑ የአልማዝ ቁርጥራጮች ይመስላሉ ። የአልማዞቹ ምንጣፍ ወደኋላ እየቀረ የሜዲትራኒያን ባህር አየር ላይ መግባቱን የሉፍታንዛው አውሮፕላን የካርታ ማሳያ ጠቆመ ።
 
ሜዲትራኒያን ሲነሳ ሃሳቤ ከመፃህፍቱ አለም ካገኘኋቸው  የታሪክ እውቀቶች ጋር ለምዕተ- አመታት ወደኋላ ይዞኝ ነጎደ ። የዛሬዎቹ የመካከለኛው ምስራቅና የውሮፓው ቋንቋዎች ፊደላት ድምፀት በፊንቃውያን (Phoenicians)  የተጨለፈበት ባህር ነው ሜዲትራኒያን ።  የግርኮች ስልጣኔ ወርሶች የለመለሙትና ፍሬ ያፈሩት የዚህን ባህር ውሃ እየጠጡ ነው ። የካርታጎው አፍሪቃዊ የጦር ሰው ሃኒባል አውሮፓ ላይ በዝሆኖች በመዝመት ሮምን ያስጨነቀው ይህንኑ  ባህር በመሻገር ነበር ። ሮማውያን የሃኒባልን ጦር አሸንፈው ሰሜን አፍሪቃን በመቆጣጠር ቄሳራዊ ግዛታቸውን  የመሰረቱት በዚሁ ባህር ላይ  ።  ክሊዮፓትራና ግብፃዊ ህዝቧ በተለይ የማርክ አንቶኒና የክሊዎፓትራ ፍቅርና ትራጀዲ መድረክም ይኸው ባህር ነው ።  በሃዋርያዊ ጉዞ ለክርስትና መስፋፋት  ታላቁን ሚና በመጫወትም ይታወቃል ሚዲትራንያን ።  አረባውያኑ የነቢዩ ሞሃመድ ተከታዮችም መካከለኛው ምስራቅን አልፈው ሰሜን አፍሪቃን ተቆጣጥረው ስፔንንና ደቡባዊ ፈረንሳይ ድረስ የዘለቁት ይህንኑ ባህር ተሻግረው ነው ። ኦቶማን ቱርኮችም ፤ ተራቸውን እንዲሁ እየጠበቁ በአዕምሮየ ተመላለሱብኝ። በአለማችን ላይ ካሉት ባህሮች ሁሉ እንደሜዲትራንያን ባህር ሰፊ የሰው ልጆች ታሪካዊ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በስተጋብሮችና ግንኙነቶችን ብሎም ጦርነቶች የተካሄዱበት ባህር የለም ማለት እችላለሁ ።  
 
 ምናቤን ከነዚህ የታሪክ ዘመናት አውጥቶ  ወደ ጉዞየ አቅጣጫ የመለሰው የፓይለቱ እወጃ ነበር ። በመጀመሪያ በጀርመንኛ ከዚያም በእንግሊዝኛ በአፍሪካ ሰማይ ላይ መሆናችንን አበሰረ ። ድሮ ድሮ አፍሪካ  “ጨለማው ክፍለ-አለም” ሲባል የትምህርት እጦት ጨለምተኝነት ብቻ ይመስለኝ ነበር ። የአፍሪካ ምድር ምሽት ድቅድቅ ጨለማ ነው ። የአፍሪካ የእውቀት ኋላ ቀርነት የብርሃንም  ጨለማ አድርጓታል ። ለምን እንደሆነ ባላውቅም ወደአስመራ የበረርኩባቸው ከአውሮፓ የተነሱ አውሮፕላኖች ሁሉ ወደ ኤርትራ ከመብረራቸው በፊት በጅዳ ሰማይ ላይ አንዣበው ነው የአስመራን አቅጣጫ የሚይዙት  ። ጅዳም ታዲያ ከአሮፓው ምድር ባልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ ማለት እችላለሁ ብርሃን ለብሳለች ። የነቢዩ ሞሃመድ አገር መሆኗና የህዝቡ ሃይማኖቱን አክባሪነት ብሎም ፀሎተኝነት ፤ ጭው ባለው በረሃ ፤ ከከርሰ ምድሯ ጥቁር ወርቅ እንዲፈልቅላት እግዚአብሄር ፈቅዶ በብርሃን ተፍለቅልቃለች ።
 
ቀይ ባህርን ተሻገረ አውሮፕላናችን ። ብርሃን ግን የለም ።  አስመራ ስንደርስ ኤሌክትሪኩ ፏ ብሎ እንደሚጠብቀኝ ተስፋ አድረኩ ።  ቀድሞ የኢትዮጵያ አካል የነበረችውና ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ሁለተኛዋን ከተማ ትባል የነበረችውን አስመራ ለመጀመሪያ ጊዜ ላያት ነው ። በተለይ ወላጆቻቸው ከኤርትራ የነበሩ አብረውን ያደጉና የተማሩ አምቼዎች ስለአስመራ ሲያሞጋግሱና ትላልቆቹም ትውልደ-ኤርትራውያን እንዲሁ አፍሪቃዊቷ ሮም እያሉ ሲያንቆላጵሷት እየሰማሁ በአይምሮየ የቀረፅኳት አስመራ ለየት ያለች ነበረች ። ልቤ በሃይል መምታት ጀምሯል ። መንፈሴም ተነቃቅቷል ። አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ቆንጆ ነገር ተደረገ ብለህ ስታወራ ፤ የኤርትራ ትውልድ ያላቸው ልጆች አስመራ ጣሊያን የሰራው እንዲህ እንዲህ የሚባል ቦታ ከዚህ የበለጠ አለ ።ድሮ ድሮ  ነው የተሰራው ብለው በደቦ እየተቀባበሉ የሚነግሩን ሁሉ ታወሰኝ ። “አደየ አስመራ ! አደየ ኤርትራ”
 
 አስመራንም አይቼ የአርበኞቹንም እንቅስቃሴ ተመልክቼ የምሰራው  ጋዜጣዊ ሪፖርት እየታየኝም ወስጤ በደስታ ሞልቷል ።በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፎች መምታት ይቻላል የሚባለው ለዚህ ይሆን?  አውሮፕላኑ ለመውረድ ማኮብኮብ ጀመረና ዝቅ እያልን ስንሄድ የመንደርደሪያው ማሳያ ሰልፈኛ ብርሃኖች ታዩኝ ። ከአገሬ ከወጣሁ ረዘም ያለ ጊዜ ስላለፈና የአገሬ አካል የነበረችውን የአስመራን መሬት የአውሮፕላኑ ጎማ ሲነካ የተደበላለቀ ስሜት ነበር የተሰማኝ ። ደስታ ይሁን ሃዘን ፤ ፍርሃት ይሁን ስጋት ወይም ጥንቃቄ ሁሉም በአንድነት ይተረማመሱብኛል፤ ምን ነካኝ? ስል ራሴን ጠየቅሁ ። ቀደም አድርጌ ደጋግሜ ያሰብኩበት ቢሆንም ፤ ያደረከው ውሳኔ ትክክል ነው ወይ ሲል ህሊናዬ እንደገና ራሴን ጠየቀኝ ። ትክክለኛም ሆነ አልሆነ አንዴ መጥተሃል  የመጥህበትን ጉዳዮች ፈፅም ሲልም መከረኝ ።
 
“…..አንታ ሃላፋይ መንገዲ እንተረኪብካያ ንመለይ፤
 ሰላም በልለይ።…..”
 
 ትርጉም                                  
“…..አንተ በመንገድ አላፊው ቆንጂትን ካገኘህልኝ ፡
 ሰላም በልልኝ።…… “ 
 
እያልኩ የአስመራን መሬት ረገጥኩ ።
 
   ከአውሮፕላን እንደወረድኩ እኔን ሊቀበሉ የመጡጥ ሰዎች አውሮፕላኑ ድረስ መጥተው ተቀበሉኝ ። ሁለት ነበሩ ። ሃላፊነታቸውንና የየትኛውመስሪያ ቤት ተወካይ እንደሆኑ ሳይነግሩኝ ስማቸውን  ብቻ በመግለፅ ተዋወቁኝ ። ሻእቢያዎች ናቸው በሚል ግምት እኔም ተዋወቅኳቸው ። ኤርፖርቱን በአይኔ ለመቃኘት ሞከርኩ ። ተርሚናሉ እዚህ አሜሪካን አገር አንድ መካከለኛ ገቢ ያለው ሰው ሊሰራው ከሚችለው ቤት አይበልጥም ። ከተርሚናሉ ትይዩ  በቆርቆሮ የተሰራ መኪና ቤት ውስጥ አንድ  የእሳት አደጋ መኪና ቆሟል ። ሊቀበሉኝ የመጡት ሰዎች ከሌሎቹ ተሳፋሪዎች ነጥለው ወደሌላ አቅጣጫ ወሰዱኝ ። በኔና በሌሎቹ ተሳፋሪዎች መካከልም የባላ ቅርፅ ያለው መንገድ ተፈጠረና እኔ ሌላ በር ሌሎቹን ተሳፋሪዎች ደግሞ ሌላ በር ዋጠን ። እኔ የገባሁበት በር ትላልቅ እንግዶች የሚገቡበት VIP በር ነበርና የክፍሉ ወለል ከዳር እስከዳር በቀይ ምንጣፍ ተሸፍኗል ። ሶፋዎቹም እንደዚሁ ቀያዮች ናቸው ። ይሁንና የወለሉ ምንጣፎች በጣም ያረጁ ናቸው ። ሶፋዎቹም እንደዚሁ ያረጁ ስለሆኑ  መዳፍ ፤ ክንድና ጭንቅላት የሚያርፍባቸው ቦታዎች  በሳሙናና በቡርሽ ከመታጠብ ብዛት የሶፋዎቹ ፀጉሮች አልቀው ድርና ማጋቸው ተጋልጦ ቀለማቸውን ለውጠዋል ። ከድዩቲ ፍሪ (Duty free) መግዛት የምትፈልገው እንዳለ ጠይቀውኝ ፤ ማየቱ አይከፋም በሚል በኮሪደሮች ውስጥ እያቆራረጥን ወደሱቁ ገባን ።  ኮሪደሮቹ  ወስጥ ከሶስት ኢንች ያልበለጠ ውፍረት ያላቸው የስፖንጅ ፍራሾች መሸፈኛ ጨርቆቻቸው የተቀዳደዱ ፤  በየቦታው ተበታትነው እንሱን እየዘለልንና እየተራመድን ነው ወደሱቁ የገባነው ። እነዚህን ፍራሾች ማንኛውም ወደ ኤርትራ ለስራም ሆነ ለጉብኝት ከሚመጣ ቱሪስት አይን የተሰወሩ አይደሉም ። እንግዶች እየጋበዝክ መግቢያህ ላይ ያለውን ቆሻሻ እንዳለማፅዳት ይቆጠራል ።  ከኤርፖርቱ  በአንዲት አሮጌ ቶዮታ ኮሮላ መኪና ከሁለቱ ተቀባዮቼ ጋር ወጣን ።  ከተማይቱ ምንም አይነት የመንገድ መብራትም ሆነ የቤቶች መብራቶች አይታዩባትም ፤ ጨለማ ውጧታል ። የኤርፖርቱ ኤሌክትሪክም በጀኔረተር እንደሚሰራ ተረዳሁ ።  ከኋላ ተቀምጬ የሚታየኝ የመኪናዋ መብራት  ማሳየት የሚችለውን ብቻ ነበር ። አቆራርጠን ተጣጥፈን  ከተማው መሃል ገባን  ። በኋላ ላይ እንዳረጋገጥኩት ከተማዋ መሃል ላይ በምትገኝ አንድ ተራ ካርቱም ሆቴል የምትባል  ውስጥ ነው መኝታው  የተያዘልኝ ። ወደክፍሌ ስገባ ኮሞው ላይ( White Horse) ውስኪ ተቀምጣል ። አማራ ውስኪና ጥሬ ስጋ ላይ ሲንደፋደፍ ፤ እኛ ኤርትራውያን ጥሬ ቆሎ እየበላን አሸንፈነው ነፃነታችንን ተቀዳጀን እያሉ ይፎክሩ የነበርው አባባላቸው ውስኪዋን ዘወር ብዬም እንዳያት አላደረገኝም  ። ክፍሉ ውስጥ ያሉ ሮቾች ግን ሰላም አልሰጡኝም ። ሲተረማመሱ  ስላይኋቸው እየቀፈፈኝም ቢሆን ተኛሁ ። ንጋት ላይ ከእንቅልፌ ተነስቼ መስኮቱን ከፈትኩ ። የውጪውን ቀዝቃዛ አየር ሳምባዬ እስከሚችለው ድረስ ሳብኩት ። ያደኩባት አገሬ አየር ሰውነቴን እስኪወጣጠር  ድረስ የሞላው መሰለኝ ።  ፀሃይ ገና አልወጣች ነበርና ደስታየን የተሟላ ያደርገው ዘንድ የወፎቹን የጠዋት ዝማሬ ማዳመጥ ተመኘሁ ። ምንም አይነት ዝማሬ የለም ። በቀጣዮቹ ማለዳዎችም የወፍ ዝማሬ የለም ። ወፎች አስመራ ውስጥ ለምን እንደሌሉ እስካሁን ሊገለፅልኝ  አልቻለም ። የወቅት ነው እንዳይባል በተለያዩ ወቅቶች ደጋግሜ ሄጃለሁ ፤ ወፎች የሉም ። አሽሟጠጠ አትበሉኝና  ለኤርትራ ወጣቶች የስደት መንገዱን (ስግረዶም) ያሳዩአቸው ወፎቹ ሳይሆኑ አይቀሩም ።  ዛሬ ወፎቹም የሉም ፤ ወጣቶችም የሉም ኦሮማይ! ። ስደቱ  ወደ ታዳጊዎችም እየተዛመተ ነው ። ሱዳን ሸገራብ ፤ ኢትዮጵያ እንዳባጉና የስደተኞች መቀበያ ማእከላትን በመመልከት የታዳጊዎቹን እድሜ ማወቅ ይቻላል ።  ሰሃራ ሳይናይና ሊቢያም ምስክሮች ናቸው ።
  
 ከተማዋን ለማየት ከሆቴሉ ወጣሁ ።  ሆቴሌ የሚገኝበትን መንገድ ላይ ወደ ግራ ታጠፍኩና መቶ ሜትር ያህል እንደሄድኩ  ኮምፔሽታቶ ላይ “ሲኒማ ኢምፔሮ” ከሮማዊ ፅሁፉ ጋር ፊትለፊቴ አገኘሁት ይህ ሲኒማ ቤት በጣሊያኖቹ ዘመን  ለነጮቹ መዝናኛ ከተከፈቱት ሲኒማ ቤቶች አንዱ ነው ። ከሲኒማ ቤቱ በስተቀኝ የአስመራ ከተማ ምልክት የሆነችውን የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ካቴድራልን ታገኛላችሁ ። ይህቺ ቤተ-ክርስቲያን በጣሊያኖች ቅኝ ግዛት ዘመን የኤርትራን የዘመኑ  ጌቶች ነጮችን  ከክርስቶስ ጋር የምታገናኝ ብቸኛ መንገድ ነበረች ። ስጋ-ወደሙም የሚቀበሉት የታላቂቱ ሮማ ዜጎች ብቻ ነበሩ ።  የአስመራ ከተማ መስራች የገበሬው የእንግዳ ቁቢ ልጅ አሉላ አባ ነጋ ይህን ሳያይ ቀድሞ መሞቱ ጠቀመው ። (ይህን የአስመራ ከተማ አመሰራረት ታሪክ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ) ።
  
  ከዚያ በተረፈ የከተማዋ ቤቶቹ የስሚንቶ ምርጎች በየቦታው ተቦዳድሰው  የቆመ የገበጣ  ገበታ ይመስላሉ ።  ቀለም የሚባል ነገር ካረፈባቸው ዘመናት ስለተቆጠሩ  የቀድሞ ቀለማቸውን አንኳ ማወቅ አይቻልም ። የአስፋልቶቹ እድሳቶች ያለእውቀት ወይም ለግብር ይውጣ አለያም በችኮላ የተሰሩ ሆነው ፤ አሮጌው ወይም ያረጀው ሬንጅ ሳይነሳ በላዩ ላይ አዲሱ ተመርጎበታል ።  በዚህም ምክንያት ሬንጁ እየቀለጠ ቀስ እያለ በመውረድ የውሃ መፋሰሻውን ደፍኖታል ። ጠዋት ነውና አስመራ እንደተኛች ነበረች ። በኋላ ላይ ስትነቃ ግን የሰዉ እንቅስቃሴ ይህን ሁሉ ትዕይንት ይጋርደዋል ።  
 
ከዚህ በኋላ አስፈላጊ ሆኖ ሳገኘው ወደ አስመራ ወጣ ገባ እያልኩ የማጫውታችሁ ይኖረኛል ።
 
አሁን ወደ አርበኞች ግንባር ።                
     
ኮለኔል ፍፁም ይስሃቅ በቅፅል ስሙ “ሌኒን’ የአርበኞች ግንባር ፤ የድምሕትና ፤ የግንቦት 7 ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጉዳይዋና አዛዥ ። በወታደራዊ ሰንሰለቱ “በስሪት አሃደ” በጀነራል ተክሌ ማንጁስ ስር መተዳደር የሚገባው ። ግን ከወታደራዊ ሰንሰለት ውጪ በቀጥታ ከፕሬዚደንቱ ፅ/ቤት ዋና ሹም ከኮለኔል ተስፋ ልደት ተ/ስላሴ ጋር የመገናኘት ስልጣን ያለው ።
ሻለቃ ሓድጎ የአርበኛችና የግንቦት ሰባት ተዋጊዎች ጋር አብሮ የሚኖር የእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸውን ተቆጣጣሪና በአርበኞቹ ላይ ያለገደብ ሙሉ ስልጣን የነበርው ።( ከኮለኔል ፍፁም ይስሃቅ ጋር ባለመግባባት ከስልጣኑ የተነሳ) ።
ሻለቃ ዳዊት የዲምህት TPDM ተዋጊዎች ጋር አብሮ የሚኖር የእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸውን ተቆጣጣሪና በተዋጊዎቹ ላይ ያለገደብ ሙሉ ስልጣን ያለው ። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከሻለቃ ሓድጎ መባረር በኋላ የአርበኞች ግንቦት 7ና የድምህት ተዋጊዎች ላይ ሙሉ ስልጣን ያለው ።
ኮለኔል ተስፋ ልደት የፕሬዚደንቱ ፅ/ቤት ዋና ሹም ።
( እኔ በነበርኩበት ጊዜ) ኮለኔል ጣእመ አብርሃ ጎይቶም በቅፅል ስሙ “መቀለ” የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ወታደራዊናፖለቲካዊ ጉዳይ ዋና አዛዥ የነበረይህ ሰው ኮለኔል መንግስቱ ኅይለ ማርያምን ለመግደል በሻእቢያ ወደዚምባቡዌ ተልኮ ተነቅቶበት ተይዞ የተመለሰ ነው ።
እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው የሻእቢያ ወታደራዊ የጦር መኮንኖች ፤ቀጥታ ግንኙነት ከሌለው ከኮለኔል ተስፋልደት ተ/ስላሴ በስተቀር ሁሉም ፈላጭ ቆራጭ አዛዦች ናቸው ። በህይወት ላሉትም ሆነ ህይወታቸው ላለፈው ሰዎች ቀጥታ ተጠያቂዎች ናቸው
ከነዚህ ከላይ ከጠቀስኳቸው ሌላ የየድርጅቱን ሰራዊት ለውጊያ ወደ አገር ውስጥ ይዘው የሚገቡ መስመራዊ አዝማች የበታች ሹማምንት አሉ ።
በምንም መልኩ ጦርነት ከተነሳ አገራችን የምትወረረው በሻእቢያ ነው ። አዝማቾቹ ደግሞ እነዚሁ ከላይ የጠቀስኳቸው ወታደራዊ ሹማምንቶች ናቸው ። በሻእቢያ ቅኝት የሚራመዱት ደግሞ እንደ ባንዳ ወይም የሻእቢያ አጋሚዶ ሊቆጠሩ ይገባል ። እኔ እስከማውቀው ድረስ በሻእቢያ አመራር የሚዋጉ ፤ በራሳቸው ጦርነት የማንሳትም ሆነ የመዋጋት ወታደራዊ ብቃትም ችሎታም እንዲኖራቸው አይደረግም ፤ አይፈቀድምም ።
ይህ እየተሰማ ያለው  የጦርነት ነጋሪት ተጋግሎ ጦርንርት በሁለቱ አገሮች መካከል ቢነሳ አሁን ሻእቢያን አመራር የሚከተለው ሁሉ ሻእቢያን ደግፎ ሊሰለፍ ነው ማለት ነው? ተጨባጭ ማስረጃ እስካሁን ድረስ ባላገኝም ፤ በታሪካችን በሶማሊያ ጦርነት ጊዜ ሶማሊያን ደገፉ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ያንን እድፍ እስከዛሬ ድረስ አጥቦ ማፅዳት አልተሳካላችውም ። ዛሬም ሻእቢያን የሚደግፉ ወገኖች ቆም ብለው ሊያጤኑ ይገባቸዋል እላለሁ ።
አርበኞች ግንባር ቀድሞ ከነበረው ሃይል ሆን ተብሎ በየጊዜው እንዲመናመን ተደርጓል ። ምክንያቱም በውስጡ ያሉት ሰዎች በአብዛኛው አማሮች ናቸውና ። በሻእቢያ ህሳቤ አማራ ማለት የኢትዮጵያዊነት ቫይረስ ተሸካሚ ማለት ነው ። ሻእቢያ ደግሞ ኢትዮጵያ እስካልፈራረሰች ድረስ ኤርትራ ሙሉ ነፃነቷን ገና አላገኘችም ብሎ የሚያስብ ድርጅት ነው ። ስለዚህ የአማሮች መጠናከር አደጋ ያመጣል ብሎ ያስባል ። አማራ ያልሆኑ ሰዎችን ግን እንደፈለኩ አሽከረክራቸዋለሁ ብሎ ያምናል ።
ግንቦት 7 በሰው ሃይል አኳያ ከአንድ ሰው የእጅ ጣት በማይበልጥ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ነው መሰብሰብ ችሎ የነበረው ። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ያለፍላጎታቸው ወደአውሮፓ ትሄዳላችሁ ። እዚያም የግንቦት ሰባትን አላማ ታስተምራላችሁ ። በመጀመሪያ ግን ኤርትራ ስልጠና ትወስዳላችሁ ተብለው ባዶ የውሸት ተስፋ ተሰጥቷቸው ከመጡ በኋላ እዚያው ሓሬና ማሰልጠኛ ጣቢያ ለሻእቢያ ባሪያ አስዳሪዎች መጫወቻ ሆነው የቀሩ ሰዎች ናቸው ። ስለዚህ አርበኞች ግንቦት 7 የተባለው ውህደት ትልቁን ቁጥር ልስጠውና ቢበዛ ከመቶ ሃምሳ  በላይ ተዋጊ የለውም ።። በነገራችን ላይ የግንቦት ሰባት ተዋጊዎች ናቸው ተብለው ፤ አይደለም ከፊት ለፊት ፤ ከኋላ እንኳን የተነሱትን ፎቶ ድርጅታቸው እስከዛሬ አሳይቶን አያውቅም ። የሌሎችን ድርጅቶች ፎቶዎችና ፊልሞች በገደምዳሜ የራሱ ለማድረግ ሲሞክርና ሲያሳይ ግን አውቃለሁ።
 ኦብነግ ( የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር) ከሌሎች የኢትዮጵያ ተዋጊ ሃይሎችና ድርጅቶች ለምሳሌ ከአርበኛችግንባር ድምሕት ወይም ከኦሮሞ ነፃ-አውጭ ርድጅት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖረው ተደርጎ ተነጥሎ ለብቻው ቀይ ባህር ላይ የተቀመጠና ልዩ ቁጥጥር የሚደረግበት ድርጅት ነው ።
 ያም ሆነ ይህ ኤርትራ ውስጥ ተዋሃደ የሚባለው አርበኞች ግንቦት 7 ፤ ብቻውን በራሱ ለውጊያ ብቃት አለው አልልም ።
የጦርነቱን ዜና እኛ አደረግነው እያለ አርበኞች ግንቦት 7 በራሱ ሚዲያ ቢወተውትም ፤ እየተዋጉ ነው ተብለው የምናያቸውና የምንሰማው ግን ድምህትቶ ናቸው ። የትግራዩ ድርጅትም ተዋህዷል እንዴ?


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>