የአርበኞች ግንቦት 7 ህዝብ ግንኙነት ጋዜጣዊ መግለጫ:-
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ በህወሓት አገዛዝ ላይ ተከታታይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከጀመረ ወዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተነቃቅቶ ለለውጥ መነሳሳቱ ታውቋል፡፡ ስልጣኔን አጣለሁ ብሎ ትልቅ ስጋት ላይ የወደቀው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ዘረኛ ቡድን በበኩሉ ደግሞ ህዝቡን እያፈሰ ወደ ወህኒ ማጋዙን ተያይዞታል፡፡
በራሪ ወረቀቶችን ለህዝብ የማሰራጨቱ ተግባር ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ ደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል መሸጋገር ችሎ በአርባ ምንጭ ከተማ የትግል ጥሪ የያዙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወረቀቶች ተበትነዋል፡፡ በተጨማሪም በየምሰሶዎች፣ አጥሮችና የህንፃ ግድግዳዎች ላይ ህዝቡን ለትግል የሚያነሳሱ ፅሁፎች የሰፈረባቸው ወረቀቶች ተለጥፈዋል፡፡
በተለይም ድል ፋና ቀበሌ አስተዳደር ፅ/ቤት በር ላይ “ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ወደፊት” የሚል ፅሁፍ በጉልህ ሰፍሮ በመለጠፉ አካባቢው በፌደራል ፖሊስ ሰራዊት ተወሮ ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ በጦር ሜዳ እየደረሰበት የሚገኘውን መራራ ሽንፈት ቁጫኝ በህዝቡ ላይ እየተወጣ እንደሚገኝ የአርበኞች ግንቦት 7 ድፅ ሬድዮ ዜና ምንጮች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡
በተለይም በሰሜን ጎንደር እና በደቡብ ኢትዮጵያዋ አርባ ምንጭ አፈናውና እስሩ በእጅጉ በርትቷል፡፡ ህዝብ በገፍ ወደ ወህኒ እየተጋዘ ይገኛል፡፡
በሰሜን ጎንደር ቋራ ወረዳ ደለጎ “በመንግስት” ሰራተኝነት አገዛዙን የሚያገለግሉ ከ15 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከየቢሯቸው በደህንነት እየተለቀሙ ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደዋል፡፡ በአርባ ምንጭም እንዲሁ በርካታ ወጣቶች በደህንነቶችና በህወሓት የታጠቁ ኃይሎች እየታፈኑ በመሰወር ላይ ናቸው፡፡
የአፈናው አና የእስሩ ምክንያት ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላችሁ የሚል ሲሆን በተለይም ከሀምሌ 5 2007 ዓ.ም ጀምሮ በህወሓት ደህንነቶች ቁጥጥር ስር በዋሉት ሀብታሙ ዶልቻ እና ሲሳይ አምባው በተባሉት የአርባ ምንጭ ወጣቶች ላይ ከፍተኛ ሰቆቃ እየተፈፀመ እንደሚገኝ የደረሰን መረጃ ያረጋግጣል፡፡