ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው
በሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ እንዲቻል፣ ‹‹ኢትዮጵያ ራይዚንግ›› በሚባል መጠሪያ በተካሄደ የተጓዳኝ ስብሰባ ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ለውጭ ባንኮች ክፍት እንደማይሆን አረጋገጡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የባንክ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች ክፍት እንዲደረግ ጥያቄ የቀረበላቸው ከኢስላሚክ ባንክ በኩል ሲሆን፣ ‹‹የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ ክፍት በማድረግ የውጭ ባንኮችን የምናስገባበት ጊዜ ላይ አይደለንም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹አውሮፓውያኑ አሁን የደረሱበት ደረጃ ላይ ደርሰው ነው ባንኮቻቸውን ለውጭ ክፍት ያደረጉት፡፡ እኛ እነሱ የደረሱበት ደረጃ ላይ አልደረስንም፤›› በማለት የባንክ ኢንዱስትሪው አሁን ክፍት ቢደረግ፣ የአገር ውስጥ ባንኮች ባዶአቸውን እንደሚቀሩ፣ ለአገር ውስጥ የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚቀርብ ገንዘብ ማግኘት ከባድ እንደሚሆን በመግለጽ ዘርፉ ክፍት አይሆንም ብለዋል፡፡
የውጭ ባንኮች ቢመጡ ለአገር ውስጥ ተበዳሪዎች ምንም ገንዘብ አያቀርቡም ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ለአገር ውስጥ አነስተኛና መካከለኛ ተበዳሪዎች ከምታበድሩት ሃምሳ በመቶውን እናቀርባለን ካላችሁ ያን ጊዜ እከፍትላችኋለሁ፤›› ከማለታቸውም በላይ፣ ‹‹በአፍሪካ የባንክ ኢንዲስትሪውን ለውጭ ክፍት አድርጎ የተጠቀመ አገር ካለ ጥሩልኝ፤›› በማለትም ጥያቄያዊ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በመድረኩ ከቀረቡላቸው ሌሎች ጥያቄዎች መካከል በአሜሪካ የሃርለም ኮሚዩኒቲ ከንቲባና የአፍሪካ ስደተኞች የክብር አምባሳደር ‹‹ንግሥቷ እናት›› በሚል የተለምዶ መጠሪያ የሚታወቁት ዶ/ር ዴሊዎስ ብላክሊ ያቀረቧቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ንግሥቷ አቶ ኃይለ ማርያምን በመሬት ሽሚያና በተማሩ ሰዎች ፍልሰት ላይ ጠይቀዋቸዋል፡፡ በአፍሪካ የመሬት መቀራመት እንዲቀር፣ ‹‹አፍሪካ አትሸጥም›› በማለት ጠንካራ ንግግር ጋር ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በርካታ የተማሩ ሰዎች ወደ አገራቸው በመመለስ ባህላቸውን እየጠበቁ እንዲኖሩ የሚያስችላቸው አሠራር እንዲኖርም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡
አቶ ኃይለ ማርያም በበኩላቸው፣ የመሬት ሽያሚያ የሚለው አገላለጽ የተሳሳተ መሆኑንና የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች የሚያራግቡት ርዕዮተ ዓለም ነው በማለት ተችተዋል፡፡ ‹‹ሰዎችን አናፈናቅልም፡፡ ባዶ መሬት ነው የምናቀርበው፡፡ ባዶ መሬት እንዲሁ መተው የለበትም፣ መልማት አለበት፤›› በማለት ተከራክረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ‹‹የምዕራባውያን ኩባንያዎች መጥተው ኢንቨስት ሲያደርጉ ማንም አይናገርም፡፡ የቻይናና የህንድ ኢንቨስተሮች ሲመጡ ግን ሁሉም ይቃወማል፤›› ካሉ በኋላ፣ ይህ ፍትሐዊነት የሌለው ርዕዮተ ዓለም መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ መብት እንዳለው፣ እስካሁንም በአገልግሎት መስክ መልካም የሚባለውን አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የአሜሪካ ዳያስፖራ አባላት አገር ውስጥ እንዳሉም ለ‹‹ንግሥቷ›› አስረድተዋል፡፡
በአገሪቱ የኢንቨስትመንት መስህቦች ላይ የኧርነስት ኤንድ ያንግ ማኔጂንግ ፓርነትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ እንዲሁም የሶል ሬቤልስ ኩባንያ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ቤተልሔም ጥላሁን ንግግር አድርገዋል፡፡ አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ያላትን አመቺነትና በአፍሪካ እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚ የበላይነቷን በማስመልከት አቶ ዘመዴነህ እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ሦስተኛዋ ትልቅ ኢኮኖሚ ያላት አገር ለመሆን ተቃርባለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ከናይጄሪያ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከአንጎላ ቀጥላ በአራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ አንጎላን ወደኋላ ልታደርግ ከምትችልባቸው አጋጣሚዎች አንዱ እያደገ የመጣው የውጭ ኢንቨስትመንት ነው ብለዋል፡፡
የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጂም ዮንግ ኪም በኢትዮጵያ በርካታ ተስፋ የሚጣልባቸው ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት እሳቸውን ጨምሮ ማንም ሰው ኢትዮጵያ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች ለማሳካት ይቻላታል ብሎ ያሰበም የተነበየም እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡