Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“የፍርድ ቤት ብያኔው መንግስት ከሙስሊሙ ጋር ያለውን ቅራኔ ለመፍታት እያሰበ እንዳልሆነ የሚያሳብቅ እርምጃ ነው –ድምፃችን ይሰማ

$
0
0

ወቅታዊውን የሕዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች የፍርድ ሂደት አስመልክቶ ከ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› የተሰጠ መግለጫ
ሰኔ 29/2007፤ አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ
በሙስሊሙ ህብረተሰብ ወኪሎች ላይ የተላለፈውን የግፍ ፖለቲካዊ ፍርድ አንቀበልም!
በአንድነት በመቆም ለረጅም የትግል ጉዞ በአዲስ መንፈስ እንነሳ!

ላለፉት ሶስት ዓመታት በበርካታ አስቂኝ እና አሳዛኝ ድራማዎች ታጅቦ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ ዳዒዎች፣ ጋዜጠኞች እና አርቲስቶች የፍርድ ስነ-ስርዓት እንደተጠበቀው የኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት የደረሰበትን ዝቅጠት በሚያሳይ መልኩ እነሆ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ኮሚቴዎቻችንም በግልፅ ከችሎት ፊት ‹‹አሁን ባለው የፍትህ ስርዓት ሚዛናዊ የሆነ ፍትህ እናገኛለን ብለን ሳይሆን ለታሪካዊ እማኝነቱ ብለን ቀርበናል›› ሲሉ የተቹት የችሎት ክርክር መንግስት ራሱ ከሳሽ ራሱ ዳኛ የሆነበት እና ፍትህ የተዘነበለበት አሳዛኝ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ ሂደቱ የተጠርጣሪዎች ከፍርድ በፊት እንደ ነፃ የመታየት መብት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተጣሰበት፣ መንግስት የሃሰት ምስክሮችን በፕሮጀክተር ታግዞ በግልጽ ያሰለጠነበት፣ አቃቤ ህግ የዳኞች አለቃ መሆኑ የታየበት እና ዳኞች ማረሚያ ቤቱን እንኳን ማዘዝ እንደማይችሉ የታዘብንበት ትልቅ የፍትህ ክስረት ነበር፡፡
muslim
መንግስት ላለፉት ሶስት ዓመታት ይህንን ሰላማዊ እና ህገ-መንግስታዊ የሃይማኖት ነፃነት ትግል በኮሚቴው ላይ ከሚበየነው የፖለቲካ ፍርድ በፊት ለማኮላሸት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ከማንኛውም ታዛቢ የሚደበቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ እንቅስቃሴው ሙስሊም ባልሆኑ ወገኖቻችን ላይ የተቃጣ ሴራ እንደሆነ በማስመሰል እና የኢትዮጵያውያንን ተቻችሎ የመኖር ባህል አደጋ ውስጥ ሊከት በሚችል መልኩ ትግሉን ለማጠልሸት ሲጥር ቆይቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ በኮሚቴው እና በእንቅስቃሴው ላይ እንዲዘምት ሰላማዊ ሰልፍ ከማስጠራትም ባለፈ የኮሚቴውን እና የእንቅስቃሴውን ህልውና ለመናድ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም፡፡ በአላህ እርዳታ፣ ከዚያም ሙስሊሙ ማህበረሰብ በተከተለው ውጤታማ የትግል ስልት ምክንያት ሁለቱም የመንግስት እኩይ ዓላማዎች ሳይሳኩ የቀሩ ሲሆን እንቅስቃሴው ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሱን እያሰፋ እና በዳዮችን እያሳፈረ አሁን ካለንበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እንቅስቃሴው በጥቅሉ የሙስሊሙን አንድነት ከማጠናከሩም በተጨማሪ የመንግስትን የጥፋት ፕሮፓጋንዳ ባዶ በማስቀረት ሙስሊም ያልሆነውን ኢትዮጵያዊ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ ከእንቅስቃሴው ጎን ማሰለፍ ችሏል፡፡

እንቅስቃሴውን እና ኮሚቴውን ከህዝብ መነጠል ያልቻለው መንግስት እንደ 1987ቱ የአንዋር መስጂድ ግርግር ሙስሊሞችን የመከፋፈልና የማዳከም ሴራውን በመቀጠል ኮሚቴውን ለመሰንጠቅ ከመባከን አልታቀበም ነበር፡፡ በመላው የኮሚቴው አባላት ላይ ማስፈራሪያዎች እና የግድያ ዛቻዎች መሰንዘር የጀመሩትም ገና ከመነሾው ነበር፡፡ የተወሰኑትን የኮሚቴ አባላት በቁም እስር አቆይቶ ሌሎቹን ማዕካላዊ ሲያሰቃይ፤ ለአንድ ዓላማ በአንድ ላይ ሲሰሩ ከነበሩት ታሳሪዎች የተወሰኑትን በነፃ አሰናብቶ የተወሰኑትን ተከላከሉ ሲል የመንግስት ስሌት ኮሚቴውን በመክፈል ህዝቡንም በዚያው ልክ አቅጣጫ ለማሳት ያለመ ነበር፡፡ በእስር ላይ ያሉትን የኮሚቴው አባላት ስብዕና በሚጎዳ ኢሰብዓዊ አያያዝ በመያዝ፣ በቁም እስር ያሉትንም መፈናፈኛ በማሳጣት ህዝቡ እና ኮሚቴው ተስፋ እንዲቆርጥ ለማድረግም አድካሚ ጉዞ ተጉዟል፡፡ ይሁንና ህዝቡም ሆነ መላው የኮሚቴው አባላት ይህንን እኩይ ሴራ አስቀድመው በመገንዘባቸው የመንግስትን ስሌት ፉርሽ ማድረግ ተችሏል፡፡ ዛሬ በፍርድ ቤት ሽፋን የተላለፈው የፖለቲካ ብይን የእስካሁኑን ሂደት በጥሞና ለተከታተሉ ከዚህ ያለፈ ትርጉም እና ፋይዳ የለውም፡፡ ህዝቡ ደግሞ የኮሚቴዎቹን ማንነት ከማንም በላይ የሚያውቅ እንደመሆኑ ወኪሎቹ በእስር እስካሉ ድረስ ህዝበ-ሙስሊሙ ራሱ እንደታሰረ መቆጠሩ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡

መንግስት ሊያውቀው የሚገባው መሰረታዊ ነጥብ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነት ንቅናቄ በኮሚቴው ላይ በሚተላለፍ ማንኛውም ዓይነት ፍርድ እንደማይገታ ነው፡፡ እንቅስቃሴው ኮሚቴውን ወለደ እንጂ ኮሚቴው እንቅስቃሴውን አልወለደም፡፡ እንቅስቃሴው ያለ ኮሚቴው ራሱን ችሎ ከመቆም የሚያግደው አንዳችም ምድራዊ ሃይል እንደሌለ ለማሳየትም ያለፉት ሶስት ዓመታት ህዝባዊ ትግል ህያው ምስክር ነው፡፡ ኮሚቴውን በማሰር፣ የእንቅስቃሴውን አራማጆች በማሳደድ፣ በሰላማዊ መንገድ ብሶቱን በሚገልፀው ማህበረሰብ ላይ የጥይት ቃታ በመሳብ እና በመደብደብ ህዝባዊውን እንቅስቃሴ ከቶም ቢሆን ማስቆም አልተቻለም፤ አይቻልምም! ንቅናቄው የህዝባዊ ብሶት ውጤት እንደመሆኑ ማቆሚያውም ብሶቱን አድምጦ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ብቻ ነው፡፡ ‹‹ኮሚቴው ይፈታ!›› የሚለው ጥያቄም ተጨማሪ ጥያቄ እንጂ የንቅናቄው መነሻ አለመሆኑን ደጋግመን እናረጋግጣለን፡፡

ላለፉት ሶስት ዓመታት ሰላማዊ እና ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ጥያቄያችንን ለመንግስት በተለያዩ መንገዶች ስናቀርብ ቆይተናል። መንግስት የመጅሊሱን ምርጫ በሚፈልገው መንገድ ጠፍጥፎ ከጋገረው በኋላ እንኳን የተካሄደው ሹም ሽር፣ በሙስሊም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ጫና፣ በሴት ሙስሊም ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው የሂጃብ ገፈፋ፣ በመስጂድ ኢማሞች እና በዳዒዎች ላይ እየተሰራ ያለው ማፈናቀል እና ማስፈራራት፣ በኢስላማዊ ጋዜጦች እና መፅሄቶች ላይ የተወሰደው እርምጃ… ይህ ሁሉ መንግስት ለኢትዮጵያ ሙስሊም ካሰበለት እኩይ ዓላማ ጥቂቱ እና መሬት ላይ የዋለው ነው፡፡ ለዚህ ሰላማዊና ህጋዊ ጥያቄያችን የመንግስት ምላሽ ስም ማጥፋት፣ እስር፣ ድብደባ፣ እና ግድያ በመሆኑም ነበር ከመብት ጠያቂነት ወደ መብት ማስከበር የትግል ምእራፍ የተሸጋገርነው፡፡

አዎን! ያለፉት ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢስላማዊ አንድነቱን ያጠናከረባቸው፤ መንግስት ለክቶ የሰፋለት የሃይማኖት ነጻነት መብቱ እስከምን እንደሆነ በግልፅ ያየባቸው፣ እንዲሁም የወደፊቱን የትግል አቅጣጫ መስመር ያሰመረባቸው ወሳኝ የትግል አመታት ሆነው አልፈዋል፡፡ በየትኛውም መመዘኛ የዛሬ ሶስት ዓመት ከነበርንበት በተሻለ ማኅበረሰባዊ ንቃት ላይ እንደመሆናችን በኮሚቴዎቻችን ላይ የተበየነው የፖለቲካ ፍርድ ያለንን ሃይል በሙሉ አሟጠን እንድንታገል ቢያደርገን እንጂ አንድ ጋት እንኳ ወደ ኋላ ሊያፈገፍገን እንደማይችል እንገልጻለን፡፡ ህገ መንግስታዊ ሃይማኖታዊ መብቶቻችንን ከጥቃት ለመጠበቅ የአምባገነኖችን እርምጃ ፈርተን የምንሸበብበትም አንዳች ምክንያት አይኖረንም፤ እምነታችን በእኛ ዘንድ ከደማችን እና ከአጥንታችን በላይ ውድ ነውና!

ውድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሆይ!

በአምባገነን ስርዓት ውስጥ አንገትን ሰብሮ፤ ውርደትን ተከናንቦ ከመኖር ባህል ውጪ በሆነና በሚያኮራ አኳኋን ላለፉት ሶስት ዓመታት ‹‹እምቢ ለእምነቴ!›› ብለን በሰለጠነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሃይማኖት ነፃነታችን መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት ያለምንም ስስት እየከፈልን እዚህ ደርሰናል፡፡ ትእግስትን የሚፈታተኑና ጠብ አጫሪነት የተሞላባቸውን የመንግስት ትንኮሳዎች እና እርምጃዎች አልፈን ያልተቆጠበ የህይወት፣ የጉልበት፣ የሃሳብ እና የገንዘብ መስዋዕትነት ያለ ዘር፣ እድሜ እና ፆታ ልዩነት ስንከፍል ቆይተናል፡፡ ሶስት ቀላል የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄዎችን ያቀረብንለት መንግስት ላለፉት ሶስት ዓመታት የመለሰልን መልስ ይበልጥ ወኔ እና ቁርጠኝነት ቢጨምርልን እንጂ አንገታችንን አያስደፋንም፡፡ በመሆኑም የትግላችንን አድማስ በማስፋት በአዲስ መንፈስ ረጅሙ የትግል ጉዟችን የሚቀጥል ይሆናል። ሁሉን አቀፍ የሆነ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄያችንን አጠናክረን ከመቀጠል ውጪም ሌላ እርምጃ አይኖረንም፡፡ ድክመቶቻችንን አርመን፣ ጠንካራ ጎኖቻችንን አጠናክረን፣ በአላህ የእምነት ገመድ ተሳስረን ቃል የተጋባንበትን የትግላችንን ግብ በአላህ ፍቃድ እናሳካለን፡፡

የፍርድ ቤት ብያኔው መንግስት ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ጋር ያለውን ቅራኔ ለመፍታት እያሰበ እንዳልሆነ የሚያሳብቅ እርምጃ እንደመሆኑ የመብት ጥሰቱን ሂደት እና ውጤቱን በትክክል ያሳየ ነው፡፡ መንግስት የሙስሊሙን እንቅስቃሴ ከመጨፍለቅም አልፎ ሙስሊሙ በገዛ አገሩ ላይ የይገባኛል ጥያቄ እንዳያነሳ እና ሁልጊዜም ተጨቋኝ ሆኖ እንዲቀር የሚያስችል የረጅም ጊዜ እቅድ እንዳለው የሚያሳብቅ ግልጽ በደል ነው፡፡ ለዚያም ነው ለእንቅስቃሴው የጀርባ አጥንት፣ ለመንግስት ደግሞ ራስ ምታት የሆነውን አንድነታችንን ለመፈረካከስ የሚጥረው፡፡ በመሆኑም ካሁን ቀደም የተደረጉ የመከፋፈል ሙከራዎችን እንደህዝብ እንዳከሸፍን ሁሉ አሁንም ይህንን የፍርድ ሂደት በማስታከክ በመንግስት በኩል የተጠነሰሰልንን የመከፋፈል ሴራ በመገንዘብ ሁላችንም በአንድነት ለረጅሙ ጉዞ በተጠንቀቅ መቆም ይኖርብናል። እስከዛሬ በነበረው በሳል ሂደት ያካበትናቸውን ልምዶች መሰረት በማድረግ በተጠናከረ ውሳኔ ሰጪነት መብቶቻችን እስኪከበሩና ወኪሎቻችን፣ እንዲሁም በትግሉ ስም የታሰሩ ጀግኖች ሁሉ እስኪፈቱ ድረስ ሕዝባዊ ሰላማዊ ትግላችን በአላህ ፈቃድ እስከድል ደጃፎች ድረስ ይቀጥላል። ህብረተሰባችንም ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት ራሱን የማንቃትና የማጎልበት ስራ እየሰራ በትእግስት ቀጣይ መልእክቶችን እንዲጠባበቅ በአላህ ስም እንጠይቃለን።

የትግሉ ሰማዕታት፣ እስረኞቻችን እና የአካል ጉዳተኞቻችን ሆይ!

አላህ መስዋዕትነታችሁን ተቀብሎ ምንዳችሁን አጥፍ ድርብ ያበዛላችሁ ዘንድ ዱዓችን ነው! እኛም በእናንተ ፋና እየተጓዝን አብረን የጀመርነውን ትግል ሳናሳካ ከቶም እንደማንመለስ ቃል እንገባላችኋለን፡፡ እስካሁን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከጎናችን ለቆማችሁ፣ የመንግስትን አጥፊ ፕሮፓጋንዳ ችላ በማለት ድምፃችንን ስታሰሙልን ለነበራችሁ ክርስቲያን እና የሌሎችም ሃይማኖቶች ተከታይ ወንድም እና እህቶቻችን፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እና ለመላው የአገራችን ህዝቦች በሙሉ የአክብሮት ምስጋናችንን እናቀርባለን! ወገናዊ አጋርነታችሁ ወደፊትም እንደማይለየንም ተስፋ እናደርጋለን!

በአንድነት በመቆም ለረጅም የትግል ጉዞ በአዲስ መንፈስ እንነሳ!
ትግላችን በአላህ ፈቃድ አስከድል ደጃፎች ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

The post “የፍርድ ቤት ብያኔው መንግስት ከሙስሊሙ ጋር ያለውን ቅራኔ ለመፍታት እያሰበ እንዳልሆነ የሚያሳብቅ እርምጃ ነው – ድምፃችን ይሰማ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>