Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ውስጤ! – (ሥርጉተ ሥላሴ)

$
0
0

ሥርጉተ ሥላሴ 06.07.2015 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

ጤናይስጥልኝ ወንድሜ ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ እንዴት ሰነበትክልኝ። መልክትህ ከደረሰኝ ወራት – አስቆጥሯል። የጹሑፌ ታዳሚ በመሆንህ ልገልጸው የማልችለው ደስታ – ተስምቶኛል። ስልክህም ተስጥቶኝ ነበር። ነገር ግን እኔ የስልክ ሰው ስላልሆንኩ ብቻ ነው – ያልደወልኩልህ። ባለመደወሌም ይቅርታ – እጠይቅኃለሁ። የተሰጠኝን ስልክ ቁጥር ግን በክብር ስልኬ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። መጸሐፍቶቼን ብትገዛቸው ደግሞ የበለጠ እኔን ውስጤን ማዬት – ትችላለህ። ትንሽ ማስታወቂያ ቢጤ … ሽልንግ አሰኝቶኝ።

አሁን ወደ ተነሳሁበት መሰረታዊ ጉዳይ ….

የማከብርህ ወንድሜ ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ ከልብ ሆኜ ነበር ጹሑፍህን – ያነበብኩት። በመናገር – በማሰብ – በመጻፍ ነፃነት ላይ ነበር – ያተኮርከው። ትክክል ነው። ትግሉም ለዚህ ነው። ነገር ግን ጋዜጠኝነት ሙያ እና ካድሬነት እጅግ የማይቀራረቡ መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው። ባይገርምህ ወንድምዓለም እኔ ሁሉንም ሆኜ – አይቸዋለሁ።

  1. የኢሠፓ ፓርቲ ካድሬ ሆኜ – ሳይከፈለኝ።
  2. መደበኛ የፖለቲካ ቋሚ ሠራተኛ ወይንም ፋንክሽነሪ ሆኜ – እዬተከፈለኝ።
  3. ዬዬትኛውም የፓርቲ አባል ሳልሆን በጋዜጠኛነት ከፍተኛ አበል – እዬተከፈለኝ።
  4. ዬዬትኛውም ፓለቲካ ፓርቲ አባል ሳልሆን በጋዜጠኝነት በራሴ ወጪ – ሳይከፈለኝ

የኢሠፓ ፓርቲ አባል ሆኜ በካድሬነት ሥሠራ በነበረበት ጊዜ እማስበው የፓርቲዬን ፕሮግራም ዓላማና ግብ ተፈጻሚነት ብቻ ነበር። ጉዞዬ አንድ አቅጣጫ ግቤም አንድ ብቻ ነበር። ጋሬ – ዓይነት። መደበኛ የፖለቲካ ፓርቲ ሠራተኛ በሆንኩበት ጊዜ ግን ከካድሬነት መንፈስ ጋር በፍጹም ሁኔታ ነበር – የተለያዬነው። ዬተለዬ ሁኔታ ነበር ማለት – እችላለሁ። ተከታታይ ስልጠናዎችና የተፈጠሩልኝ ሌሎች በርካታ አጋጣሚዎች ታክለው ወጣትነቴን ታግሎ አሸንፎልኛል። አለቆቼ ደግሞ ዘመን የማይተካቸው እንደነ ጓድ ገ/ መድህን በርጋ ዓይነት – ነበሩ። እራሳቸው ድርጅት – የሆኑ። በፓርቲዬ ፕሮግራምና ደንብ አፈፃፀም በሚመለከት በአባልነቴ በፓርቲዬ መሠረታዊ ድርጅት ያለብኝን ግዴታ እዬፈጸምኩኝ ግን በማደረጀት ከፍተኛ ዬኃላፊነት ተግባሬ የበለጠውን እጅ ለሙያው ሥነ ምግባር ኃይሌን በመገበር – ነበር።

በጋዜጠኝነት ሙያ እዬተከፈለኝ ሥሠራ የተቃዋሚው ጎራና የገዢው ድርጅት ጎራ በሚመለከት ወገናዊነቱ ለተቃዋሚው ቢያጋድልም ግን ሌላውንም መንፈስ በቅንነት እከውን ነበር። ምርጫ አልነበረኝም በማልፈልገው ቦታ አልገኝም – የማለት። በምታዘዘው ቦታ ሁሉ መገኘት ግዴታዬ ነበር። ነገር ግን ያዬሁትን በትክክል ሳላጋንን ሳልቀንስ ሳልጨምር አስተላልፍ – ነበር። በምልሰት ሳስበው የነበረብኝን ኃላፊነት ከሃቅ ጋር ሳልጣለ ስለነበር ጸጸት ኖሮብኝ – አያውቅም። እንዲያውም የተቃዋሚ ኃይሎችም እኩል ድርሻ እንዲኖራቸው፤ እኩል የአዬር ጊዜ እንዲኖራቸው በጣሙን – ጥሬያለሁ፤ እኩልም አገልግያለሁ ማለት – እችላለሁ። ነፃነቱ ምን ነበር ብትለኝ የተጎዳውን ስሜቴ ለመግለጽ አቅም ነበረው። በሌላ በኩል የምንም ፓርቲ አባል ባልሆንም ግን ህዝቡ የወያኔ ሃርነት ትግራይን መሰሪ ደባ ያለወቀበት ጮርቃ ላይ ስለነበር እኔ ደግሞ በተለያዬ ሁኔታ ስለታገልኩት መጪው ጨላማ ጊዜ በሚመለከት አምቄ የምዬዘው አመክንዮ ስለነበረ መንፈሴ ምቾት በፍጹም ሁኔታ አይሰማውም – ነበር። እርግጥ ሰፊ ተግባር – ከውኝበታለሁ። ሰፊ ልምድም ከአዛውንታት ሊቃናት ባለሙያዎች – ቀስሜበታለሁ። ቀደምቶቹ ቅኝታቸው ቅኔነት ነበር። ቀደምቶቹ ፓን አፍሪካንስት ነበሩና።

ሳይከፈለኝና የፓርቲ አባል ሳልሆን የምሠራው የጋዜጠኝነት ተግባር ግን ወጪው፤ እረፍት – ማጣቴ፤ የሚገጥሙኝ የማያልቁ መከራዎች መጠነ ሰፊም ቢሆኑም በተግባሬ ሆነ በተልዕኮዬ በሙያው ሥነ ምግባር ውስጥ መኖሬ በራሱ ገነት ነው። አብሶ ማንም የማያዝበት የወልዮሽ ያልሆነ፤ የግል መተንፈሻ ቧንባዬን ከአደራጀሁ በኋላ እጅግ ሰላም፤ ጸጥታ፤ መረጋጋት፤ ፍጹም የሆነ ደስታ አለኝ። እማስበውን፤ የሆንኩትን፤ ህመሞችን ካላንዳች ማዕቅብ – እግልጻቸዋለሁ። ፍጹም የሆነ የነፃነት – የጤንነት – መንፈስን ተጎናጽፌያለሁ ማለት – እችላለሁ። ይህ የምድር ጽድቅም ነው። እርግጥ ቲፎዞ – የለኝም። ወይንም ደጋፊ – የለኝም። ወይንም የሚረዳኝ የለም። ወይንም አይዞሽ ባይ – የለኝም። እንኳንም ልታገዝ እልቀተ ቢስ እንቅፋቱን ታሪክ አንድ ቀን ይዘግበዋል። ዛሬ እንዲያውም አንድ ቃለ ምልልስ ነበረኝ። የገጠሙኝን ፈተናዎች ላልተወለዱኝ ስገልጽላቸው እንዴት በተመስጦ እንዳደመጡኝ ለአንድ ዓመት ስንቅ – ይሆነኛል። በእቅፋቸው ውስጥም ህቅታዬን እስክሰበሰብ ስላቆዬዩኝም አምላኬን – አመስግኜበታለሁ።

የሆኖ ሆኖ ፍጹም የሆነ እንክን የለሽ ውሳኔዬ የሐሤቴ ጌታ እንድሆን – አድርጎኛል። ይህ ጉዞዬ ሌላም ነገር – ሸልሞኛል። በተለይ „ሰው“ በሚለው ማዕከላዊ አጀንዳ ላይ ተግቼ እንዳተኩር መሆኔ በራሱ አዲስ የተመቸ አለም ውስጥ እንድኖር ባለ አዲስ መንፈስ ሙሉዑ ሰው እንድሆን – አድርጎኛል። ዛሬ ሃይማኖቴ – ፓርቲዬ – ኑሮዬ – ተስፋዬ „ሰው“ ብቻ ነው። እውነት እውነትነቱ ሊረጋገጥ የሚችለው „ሰው“ በሚለው አምክንዮ ውስጥ መኖር ስትፈቅድ ብቻ ነው። መጀመሪያ „ሰው“ ይተርጎም። „ሰውን“ የተረጎመ እሱ የሁሉም ሙያ ባለቤት ይሆናል። ፍርድ ላይ ቢቀመጥ፤ ወንበር ላይ ቢቀመጥ፤ አዬር ላይ ቢቀመጥ፤ ብቻ ምን አለፋህ ወንድምዓለም „ሰውን“ ማዬት ያስችለዋል። እራሱንም ሰው ነኝ ማለት ይቻለዋል።

ከዚህ ላይ አንድ ነገር ልከልልህ አያቶቼ የቤተ ክህንት ዓራት ዓይናማ ሊቃናት ነበሩና እናቴ ስትነግረኝ ሲያድጉ መሬትን ሲረገጡ መሬት የታመመች ያህል ወይንም የቆሰለች ያህል እንዲጠነቀቁላት ይቆጣጠሯቸው ነበር። መሬት ላይ መዝለል አይፈቅድላቸውም ነበር። አሞከሞም – ሰኞ ማክሰኞም አይፈቀድላቸውም ነበር። ሌላው ቀርቶ ገበጣ ቆፍረው እንዲጫወቱ ማዕቀብ – ነበረባቸው። እኛም ስናድግ ጠረኑ እንዲኖር ተደርጎ ቢሆንም፤ አሁን የሚገርምህ ነገር የበለጠ በላቀ ሁኔታ ተፈጥሮን እማይበት መንፈስ ያ የአያት ቅድመ አያቶቼ መንፈስ አፅመ ቅዱስ ቅርስ የላክልኝ – ይመስለኛል። መሬትን ስረግጥም – የበለጠ ከልጅነቴ ጊዜ ተጠንቅቄ ነው።

አሁን ወደ አነሳኸው ነጥብ ልመጣ አቶ ሄኖክ ሰማእግዚር ለእኔ ጋዜጠኛ ነው ለማለት እጅግ – ይከብደኛል። ራሱ የድምጹ ምቱ ትንት – አለበት። ኢትዮጵያዊ ጠረን የሌለበት መሆኑ መንፈሱን – ይተርጉምልሃል። ምክንያቱም በሙያው ሥነ ምግባር ውስጥ ስሌለ። ጋዜጠኝነት የጎጥ ችግኝ – አይደለም። ጋዜጠኝነት የመንደር እርሾ – አይደለም። ጋዜጠኝነት የበቀል ተክል – አይደለም። ጋዜጠኝነት የቁርሾ ቁርስ – አይደለም። ጋዜጠኝነት ሲሞቅና ሲቀዘቅዝ „በስብዕ ተፈጥሮ ላይ“ ሙከራ የሚሠራም – አይደለም። ጋዜጠኝነት የሰውን ልጅ ተፈጥሮ የመተርጎም ልዩ የመንፈስ ብጡል አቅምና ልቅና ነው። ይህን አመክንዮ በአቶ ሄኖክ ሰማእግዚር አላዬሁበትም። እሱ ካድሬ ነው።

… ካድሬነቱ ደግሞ ለፋሽስቱ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ አስፈጻሚነት ጠበቃ፤ ድልዳል፤ ሽፋን በመሆን በግንባር ቀደምትንት የሙያውን ሥነ ምግባር በመርገጥ የጎጡን ዓላማ አስፈጻሚ በመሆን ነው። እሱ እራሱ ገና ካላደገው አስተሳሰብ ላይ ነው ያለው። ጎጠኝነት መንደርተኝነት ማለት እኮ ያልተመጣጠነ የአስተሳሰብ እድገት ማለት ነው። ያልተመጣጠነ የአስተሳስብ እድገት ማለት ደግሞ የአስተሳሰብ ድህነት ነውና ከጋዜጠኝነት ሥነምግባር ጋር አይተዋወቅም ማለት ነው። ካድሬ ነው፤ የካድሬነቱን ተግባር በዚህ ታላቅ ክቡር ሙያ ሽፋንነት ሊሸቅጥበትና ሊመቅጥበት አይችልም። ስለዚህ ምርጫው አንድ ነው። በሙያው ለመቆዬት የካድሬነቱን ውስጥነት – መርገጥ። ወይንም በካድሬነት ለመቀጠል የጋዜጠኝነቱን ጭንብል – ማውለቅ። በሁለቱ ሥም መነገድ – አይቻልም። እኔ እንደ ሥርጉተ ጋዜጠኝነትን የመረጠ ዜጋ ከብዙ ነገር እራሱን ማቀብ እንዳለበት ነው የማምነው። በስተቀር እውነቱን የማዬት አቅም – ያንሰዋል። መንፈሱ ስስ ስለሚሆን ያገኘ – ይበሳዋል። የመንፈሱ ሰበል የማደግ አቅም አይኖረውም – በአረም ስለሚዋጥ። ከእውነትም በጣም እጅግ በጣም – ይርቃል። ስለዚህ የሙያው መንፈስ መንገድ አዳሪ ይሆናል …..

ጋዜጠኛ ለተገፋ፤ ለተበደለ፤ ለታፈነ፤ ለሚገደል፤ ለሚሞት፤ ለሚደበደብ፤ ለሚደፈር፤ ለሚፈናቅል፤ አድሎ ለሚፈጽምበት፤ ለሚታሰር፤ በግፍ ለሚሰደድ መቆም አለበት። ለነዚህ ምንዱባን ግን ጠበቃ ነው ጋዜጠኛ። አንድ ጋዜጠኛ ይህን ፍላጎቱን ለማስፈጸም ፈቃድ ከማንም መጠበቅ – የለበትም። ሙያው እኮ መከራን አብዝቶ የሚቀበለው፤ የሰቆቃ ኑሮን ፈቅዶ ማድመጥ መቻሉ ነው። የሰቆቃን ኑሮ ማድመጥ መቻል ደግሞ በውስጥ አንጀት ላይ ከፍተኛ ህውከት – ይፈጥራል። ስለምን? ጫናው ሁሉ የሚያርፈው አንጀት ላይ ነውና። ከዚህ መስፈርት በዜሮ ፐርሰንት ላይ የሚገኘው አቶ ሄኖክ ሰማእግዚር እራሱን ያጣው ዛሬ ሳይሆን ከሙያው ሥነ ምግባር ሲወጣ ነው። እራሱን የደበደበው ከተከበረውና ከተቀደሰው የጋዜጠኝነት ሙያዊ ሥነምግባር ይልቅ የጎጥ ካድሬነቱን የመረጠ ዕለት ነው። ከሙያው ዓለም ዐቀፍ ህግጋት ይልቅ መንደር ላይ ከተቀረቀረ የጎጥ ካርድ ላይ ሲወድቅ ነው። ያን ጊዜ ነው ከባህር የወጣ አሳ የሆነው።

የሃሳብ ነፃነት፤ የመናገር ነፃነት፤ የመፃፍ ነፃነት በሰው ስቃይና መከራ እዬተደነሰ ወይንም ፈንድሻ እዬተረጨ – አይደለም። ሰሞኑን አንድ አውዴዎ ወጥቶልሃል። ሊንኩን አልጥፍልህም፤ የቤት ሥራ ነው ፈልገህ አድምጠው ማንና መቼ እንደ ተነገረ „ ብዙ የውጭ ጋዜጠኞች ስለሚመጡ እንዳትደናገጡ!“ ይህ መልዕክት ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲነገር ዕድምታው ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኛ የለም። ያሉን ካድሬዎች ብቻ ናቸው ነው። ነፃ ጋዜጠኞቹ ደግሞ እስር ቤት ጉድጓድ ወስጥ የተጨመሩ – ናቸው። ይህም ብቻም አይደለም ጋዜጠኝነት ሙያው ማስፈራሪያ ስለመሆኑ ነበር የወያኔ ሃርነት ትግራይ በሚ/ር ደረጃ ያሉ – የገለጹት። ያሳፍራል። ኢትዮጵያ የምትመራው ዓለም ዓቀፍ በሚመራው ህገ – መግስት ድንጋጌ በ1948 ሳይሆን የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሲመሰረት በተፈጠረው ናዚያዊ መርዝ ማኒፌስቶ ነው። ውጪ ወያኔ ያሰማራቸው ካድሬዎችም ከኢትዮጵያ ጋር ንኪኪ ያላቸውን ተቋማት ሁለ በዚህ መስፈርት እንዲሄድ ነው ዘመቻው ትልሙም። ኢሳትም ተፈትኖ ነበር … ስላልተደፈረና ስላለፈ – ይረሳልን? በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ለሚኖር ባለሙያ ሙያውም የሙያው ታዳሚም ቦታ የላቸውም። የተከበሩ ዶር ወ/ሮ አንጅላ ሜርክል የጀርመን የመጀመሪያዋ ሴት ጠንካራ ጠ/ሚር 70ኛውን ዓመት የቤተ ይሁዳን ጭፍጫፋ በሚመለከት በተዘጋጀው ህዝባዊ ስበስባ ላይ ውስጠ መንፈሱ „ ለዛ ናዚያዊ አስተሳሰብ ዛሬ ቦታ የለንም“ ይል ነበር። እኛም ለእነሱ ቦታ የለንም።

ሌላው ያነሳኽው ሰላማዊ ሰልፍን በሚመለከት ነው። ሰላማዊ ሰልፍ የተፈቀደ አመጽ ማለት ነው። ህግ የለውም። ጥሰት ሊኖር ይችላል። እንዲያውም – ምረውታል። ፍቅር እኮ አይገዛም። የህዝብ ፍቅር አሽዋ አይደለም ከመሬት – የምታፍሰው። የህዝብ ፍቅር ወንዝ ሄደህ የምታወጣው – አሳም አይደለም። የህዝብ ፍቅር ህግ ደንግገህ የምትሸምተው አይደለም። የህዝብ ፍቅር ዋርካ ላይ ወጥተህ የምትለቅመው ፍሬ – አይደለም። በተግባርህ ልክ የምታገኘው ከሃብቶች ሁሉ ሃብት የሆነ የመንፈስህ ሰብል ነው። ስለዚህ የጠላኸውን፣ አንደበትህ ያልሆነውን ለዛውም በከፋህ ቀን መከፈታህን ሊረግጥ፣ ሊሳለቅበት፣ ሊጠቀጥቀው፣ ሳያፍር ሲመጣ አንገቱን ማስደፋትና ከባህር የወጣ አሳ ስለመሆኑ ማሳዬት የነፃነት ትግሉ አንዱ ዘርፍ ነው። ጋዜጠኛ በጠባቂ – በጠበንጃ ታጅቦ ሳይሆን ጋዜጠኛ በህዝብ ፍቅር ታጅቦ ነው የኖረው።

እንዲሁም – „ለከፋው ማጭድ አትዋስው“ ይባላል። የእነዛ ሰማዕታት ደም በሀገር ውስጥም ተደግሞ ደም እዬፈሰሰ፤ በታመቀ የሃዝን ቁስላዊ ምጥ ውስጥ ላለ ሥጋ ሌላ ጠቅጣቂና ፌዘኛ ማስተናገድ አቅም ያነሰዋል እጬጌው ዕውነት። ይወቀው ሃቅን እስከዳ ድረስ ነገም መጠጊያ የሌለው – እርቃኑን ስለመሆኑ። ነብዬ እግዚአብሄር ዳዊት „ሐገርን ህዝብ ካልጠበቀ ሠራዊቱ በከንቱ ይደክማል“ ብሏል። አጋዚ አሜሪካን የለም – እንዳይከላከልለት። ለጽንስ የማያዝኑ አውሬዎች፤ „ምን አለሽ መቲ“ አንድ ድንቅ ዝግጅት ነበራት። ከወርቆቻችን ጋር አዳምጠው ወይንዬ ያለችውን … 15 ጊዜ ሰምቼዋለሁ እንባዬ እንደ ጎርፍ እዬወረደ „ እኔ ሞቼ፤ እኔ ታስሬ፤ እኔ ተንገላትቼ“ ትላለች ያቺ የነፃነት ቀንበጥ …. ያን ሁሉ አሳር ነፍሰጡሯ ችላ፤ ገና መንፈሱ ከእንሰሳነት ከትንሿ ጉልት ላልወጣ፣ ያ ታላቅ ሙያ እንደ እሱ ላለ በጎጥ በሽታ ላበደ ጥንዝልና ዝንጥል ቦታ – የለውም። ሙያውም ጥብቅናም – አይቆምም። ጋዜጠኛ አብርሃ ደስታ ነው የእኛ። ሁሉ ሲቻለው መከራን ለመቀበል በቃኝን በአሳር – ያቀለመው። ናፍቆቴና ውዴ … የ እነሱን መታሰር ለ አምንስት ኢንተርናሽናል ስልክ የቀደመኝ እንደሌለ በጣም እርግጠኛ ነኝ። አዬህ ለእውነት አርበኞቻችን ፈጣኖች ነን። ለካህዲዎችና ለባንዳዎች ደግሞ ጦሮዎች።

በተጨማሪ ያነሳኸው ነጥብ አለ። አዎን የተወጣው መሰረታዊ ምክንያት ዕንባችን – ይደመጥ ነው። ስለዚህ ወሰን ደንበር ተሰርቶለት በዚህ ብቻ በዛኛው ብቻ ሊባል – አይችልም። አኔ አንድ ነገር ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ መላክ ስፈልግ ተያያዥ ሊንኮችን ጨምሬ ነው – እምልከው። ጥያቄ ስለ ድምጽ አልባዎቹ መከረኛ እህቶቼ ሊሆን ይችላል። ግን ሌለችንም አክዬ – እልካለሁ። ሊንኮችም ዕውቅና እንዲያገኙ ስለምፈልግ። አዬህ አባትዬ ግፉ በዝቶ ተርፎ ፈሶል …. አቅም የለም ህግ የምንሠራበት – ይህን አትንኩ ያኛውን ብቻ የሚባልበት – ጊዜ ላይ አይደለም። ሰላማዊ ስለፈኛን ማስተዳደር – አይቻልም። ለዛውም – የተከፋን፤ በሃዘን – የተረመጠ፤ በዕንባ – የተቃጠለ ….. ብሶተኛ ሰላማዊ ጦረኛ ነውና!

ወንድምዬ ስለ አቤ በለውም አንስተሃል። አቤን ማንም – አልተጋፋውም። ራዲዮ ፕሮግራሙ አማርጭ ነው። በከፍተኛ ደረጃ ሲደመጥ – ኖሯል። ሰፊ ተከታይና አድናቂም – ነበረው። ያቀረበውን ቢያቀርብ፣ የጠዬቀውን ቢጠይቅ ማን ተናግሮት ያውቃል? እንዲያውም አንድ ጊዜ እኔ „ቤት አለው“ በሚል አንድ ጹሑፍ አንብቤ የጻፍኩት ነበር። ተከላካይ ሆኜ። ይሄ ብቻ አይደለም የልጅነት ፍቅር እስከ የሰብዕ መብት ጠበቃነት በሚል ለልጆች በጻፍኩት ላይ ስልማውቃቸው መንትያ ወንድሞቼ ስለ ታማኝና ስለ እሱ – ጽፌያለሁ። ታትሟል መጸሐፉ። እንዲህ ዓይነት ሰብዕና ሲያመጣ – አመመኝ። ስለ – አዋረደኝ። አንድ ጋዜጠኛ በአድማ መግባት – በፍጹም የለበትም። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለዛውም በታላቋ አሜሪካ በአንድ እንፍራዝ ላይ እንደሚካሄድ ስብሰባ በዛ ነክና ውሎ ጉዞ የሌለው ማይክራፎን ይቅርታ ሲጠይቅ ድምጹን – ሰምቼያለሁ። ይቅርታ መጠዬቁ መልካም ነው። ግን ችግሩ ማይክ ነበርን? ቦታ – ቅጥል ሥም ነውን የሚያሰኘው? ምን ያደርግለታል – ለአንድ ሞት ለተፈረደበት ጋዜጠኛ? …. ይሄን ነበርን የሚፈልገው ወይንም የከነከነው? እኔ እንደማስበው ለጋዜጠኛ ወንበር ቦዶ …. ቦደ ወና ነው። ሥልጣን ጭድ – ምደረ በዳ ነው ነው። ክብርም – ልጥፍ ነው። እኔ ሀገሬ ኢትዮጵያ በህዝብ ፈቃድ ምርጫ ብታካሄድ የምርጫ ካርድ – አልወስድም? ለምን? ሚዛኔን – አጣለሁ። ክብሬን እሸጣለኋ! ምርጫው – ቢዛባ፤ ቢጨበረበር በምን አንደበቴ – እናገራለሁ? እኔም ተሳታፊ ነኝና። እኔም ታዳሚ ነኝና። እኔም ድምጽ ሰጥቻለሁ፤ እና ነፃ ጋዜጠኛ የመክሊቱ ዳር ድንበር አሁን በከፈተው ዘመቻ መሆን አይገባውም።

ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ የጋዜጠኛ ኃላፊነት ዕውነት መሆን ይገባዋል። ጋዜጠኝነት የዕንባ ተጠሪነት ነው። ለዛውም አማራጭ የሆነ ራዲዮ በብዙ መልኩ በሁሉም ዘርፍ ተሸሎ ሠልጥኖ መገኘት አለበት። የአቲካራ ቤትም መሆን የለበትም። ቤተ – እርቅ ነው መሆን ያለበት። የእሱ ደግሞ ቤተ – እሳት – ነዲድ፤ ቤተ አድማ – አደረገው። ሌላው ያነሳኸው መልስ አልተሰጠም ብለህ የወቀስከው ነገር አለ። እኔ ለአቤ አንድ ችግር ገጥሞኝ ጽፌለት ነበር በአንድ ወቅት እሱ እራሱ መልስ – አልሰጠኝም። መልስ በመስጠት፤ መልእክት በማድመጥ – በማክበር ከማንም ያላገኘሁትን፣ ያለዬሁትም የሰጠኝ ጋዜጠኛ አበበ ገላውን ብቻ ናሙና ማድረግ ይቻላል። በስተቀር የትም ቦታ ጽፈህ መልስ – የለም። ሆም ፔጆች ሁሉ። ተባባሩን ይላሉ፣ ስትጽፍላቸው መልስ የለም። አንድ ጹሑፍ ገርሞኝ አደባባይ ላይ ከምወርፋቸው ብዬ ለቀድሞው ብቸኛ የፓርላማ ተመራጭ ለአቶ ግርማ ጽፌ ነበር – መልስ አልሰጡኝም። ምን አልባት እኛ እምንፈልገው ክረት እንጂ ለዘብ ማደረግ ስላልሆነ እንዲሁም ቶሎ ሆድ ስለሚበስን እንጂ ብዙ ሰው ባህሉ አይደለም። ታላላቅ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ግን መለስ ይሰጡኃል። ወይ ደውለው – ያነጋግሩሃል። ወይ በኢሜልህ መልስ – ይልኩልሃል። ለማንኛውም እምትፈልጉትን ለአቤዋ ገላው – ላኩለት። ለምትፈልጉት አካል – ይልክላችኋል። አንድ ዓመት ሙሉ ስሜቴን፣ ቅሬታዬን፣ የማጠናከሪያ ሃሳቤን – እንደዛሬው ቤቴን ዘሃበሻን ሳላገኝ ለእሱ ነበር – እምልከው። ደከመኝ አይልም፤ ሰለቸኝ አይልም፤ በዛብኝም አይልም፤ አይቆጣኝም፤ ሁሉንም እንደምፈልገው በፈለግኩት ደረጃ አስተናግዶልኛል። አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም የላከበትን ጨምሮ ይልክልኝ ነበር። እኔ ጽፌለት መልስ ሳይሰጠኝ የቀረበት አንዳችም ጊዜ – የለም። የዘሃበሻ መኖር እኔም የማይደክመኝ ሰውንም ይደክመዋል የማይመስለኝ ስለሆንኩኝ አሁን እርግጥ ጫናው  – ተቃሎለታል። አስቸግሬው አላውቅም።

ክንዴ! – ከዚህ በተረፈ የሰው ተፈጥሮ የተለያዬ ነው። የእኔን – ልንገርህ። ስልክ – አልመልስም። አራት የእጅ ስልክ አለኝ። ሲዊዝ ጓደኞቼ ገዝተው – የሰጡኝ። እውነት ልንገርህ – የሁለቱን ቁጥር – አላወቀውም። የቤትም አለኝ። አስቤም – አልደውልም። ሲደወልልኝም – አላነሳም። በቃ ተፈጥሮዬ ነው። ኢሜል ከሆነ ብቻ አፋጣኝ መልስ – እሰጣለሁ። ስለዚህ ከመናቅ ወይንም ቸል ከማለት ወይንም አልደፈርም ከማለት ላይሆን – ይችላል። የሰው ልጅ ሴሎች ህወሶች ከአንዱ ሰው የሌላኛው የተለዬ ነው። የጭንቅላታችን፤ የእግራችን፤ ዬእጃችን አሻራዎች ኮፒ የላቸውም። በቃ ሃቁ ይሄ ነው። አንድ ሰው እራሱን ሆኖ ነው – የተፈጠረው። ሌላው ስለሚያደርገው ነገር የእሱ አይደለም። በእሱ ውስጥ ያለው እሱ ብቻ ነው። ስለዚህ ወቃሽም ተወቃሽም ሊኖር አይገባም። ባህሬው ሊሆን ይችላል።

አሜሪካኖችን ጠባይም የጠቋቋምከው አለ። የተዘጋ በር እኮ ከፍተውላቸዋል። መከራ የበዛበት ህዝብ ደግሞ የዕንባ መውረጃ ቦይ እንጂ በዛች ቅጽበት ይሄን የሚያገናዝበብት አቅም ካላመጣህ ተብሎ ሊወቀስ አይገባም። ስለምን? ሃዘናቸው – ሃዘናችን ነው። እኛ ባልተገኘንበት ቦታ ሁሉንም ሆነው የዕንባችን ተጠሪ መሆናቸው ሊያስመሰግናቸው እንጂ ሊያስወቅሳቸው – አይገባም። አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ የተሠሩ ጊዜ በተባባሩት መንግሥታት ቢሮ ፊት ለፊት የወያኔ ሃርነት ትግራይ አርማ ተቃጥሏል። በዛን ጊዜ ለተወሰነ ጊዜ ራስን መግዛት – ይሳናል። አማትፈልገውን ነገር እንድታደርግ የሚያሰገድዱህ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች  – ናቸው። ስለዚህ – አይፈረደም። ለተወሰነ ጊዜ ሌላ ሰው ትሆናለህ። ከተረጋጋው ሰብናህ ጋርም ልትተላለፍ ትችላለህ። አቅደው ደግሞ አልሠሩትም ድንገት የተፈጠረ ነው።

ክወና …. እኔ ቅጣት ነው አልልም። ትምህርት ነው። ሀገር ቤት ያሉትም የኢትዮጵያ ህዝብ አጋጣሚ ቢያገኝና ቢፈቀድለት ከቤተ ክርስትያን እንደገባ ውሻ እንደሚያደርጋቸው – አትጠራጠር። 24 ዓመት ሙሉ በአግላይ ፖለቲካ የተቀጠቀጠ የህዝብ አካል …? ወደ አሜሪካ ከሚላኩትና ከሚዋረዱት ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ አስፈጻሚዎች አቶ ሄኖክ ሰማእግዚር ከቶ በምን ይለያል? በምንም ነው – ለእኔ። ለዛውም በነፃነት ሀገር – ተቀምጦ። ማዬቱን ሰጥቶት ከውሳኔ ላይ ያደርሰው፤ እንደ ሥሙ ለመሆን ያብቃለት የምህረት አባት ቻይ ነውና አዲስ ልብ ይላክለት። አሁንም አልመሸም ይቅርታ ጠይቆ ሥጋና ደምን ከዕንባ ጋር ለማጋባት። ቢያንስ የሚያነብበትን ቶኑን ትንሽ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ እንዲሸት ይታደገው – አንድዬ። ጉድፍና ግድፈት ይናኘኝ ካለም ከዛሬ የባሰም ሊገጥመው – ይችላል። የሰማይ ቅጣትም እኮ አለ። ለማንኛውም ወደ ልቦናው ድንግል ትመልሰው። እሷ የይቅርታ እመቤት ናትና!

ውዶቼ ሳላስበው ነው ዛሬ ከች ያልኩት፤ መሸቢያ ሰሞናት። ክብሮቼ – ዘሃበሻ ኑሩልኝ ውድድድ …..

ኃላፊነቴን የገደልኩት ቀን አኔን ቀድመህ ውሰደኝ – ፈጣሪዬ።

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል!

 

 

The post ውስጤ! – (ሥርጉተ ሥላሴ) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>