Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ላይ እስከሞት ሊያስቀጣ የሚችል ረቂቅ ህግ ወጣ

$
0
0

 

መታሰቢያ ካሳዬ

8cf0b7d1151c50109f60fcd52cca9a8e_Mበህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ላይ ከፍተኛ ቅጣት የሚያስጥል አዲስ ረቂቅ ህግ ወጣ፡፡
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውና ትናንት በምክር ቤቱ ውይይት የተደረገበት ረቂቅ አዋጅ፤ በወንጀለኞች ላይ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት የሚያስቀጣ አንቀፅ ተካትቶበታል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና ስር እየሰደደ ዜጎችን ለአስከፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና እንግልት እየዳረገ በመሆኑ በወንጀለኞች ላይ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት ለመጣል የሚያስችል ህግ ማውጣት በማስፈለጉ ረቂቅ ህጉ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
ረቂቅ ህጉ በማንኛውም ህገወጥ መንገድ ስደተኞችን ወደአገር ውስጥ ማስገባትም ሆነ ከአገሪቱ ግዛት ማስወጣት ከ15-20 ዓመት ለሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ150ሺ – 300ሺ ብር ለሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይዳርጋል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው በስፋትና በበርካታ ሰዎች ላይ ከሆነ አሊያም የወንጀል ድርጊቱ በተጎጂው ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ወይም ሞት ያስከተለ ቅጣቱ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም ሞት ሊሆን ይችላል፡፡
ማንኛውም ሰው ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ለማስገባት ወይም ከኢትዮጵያ ግዛት ለማስወጣት የተጭበረበረ ወይም ሀሰተኛ መታወቂያ ካርድና የጉዞ ሰነዶችን ካዘጋጀ፣ ይዞ ከተገኘ፣ ካቀረበ ወይም ካስተላለፈ ከ10 ዓመት በማያንስ ከ20 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና እስከ 200ሺ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይቀጣል፡፡
በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወይም ስደተኞችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለ ተጠርጣሪ እስከ አራት ወራት የሚደርስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊጠየቅበት እንደሚችል የሚደነግገው ረቂቅ ህጉ፤ በወንጀሉ ላይ የሚቀርቡ ክሶች ወይም ቅጣቶች በይርጋ እንደማይታገዱም ያዝዛል፡፡
የህገወጥ ስደቱ ተጎጂ የሆኑ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ፈንድ መቋቋሙም በረቂቅ ህጉ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይህንኑ ወንጀል ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችልና የተጎጂዎችን መልስ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍና ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ኮሚቴ የሆነ የፀረ ህገ ወጥ ሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር የጋራ የግብረ ኃይል መቋቋም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡
ፍርድ ቤት በጥፋተኛው ላይ ከሚወስነው ቅጣትና መቀጫ በተጨማሪ ለተጎጂው ወይም በተጎጂው ስም ወጭ ላወጡ ሌሎች ሰዎች ወይም ድርጅቶች ካሳ እንዲከፍል ሊወስን ይችላል ያለው ረቂቅ ህጉ፤ ካሳው እንደነገሩ ለህገወጥ ደላላ ከከፈለው ገንዘብ፣ በወንጀል ድርጊቱ ምክንያት ተጎጂው ካጣው ወይም ህገወጥ ደላላው ካገኘው ጥቅም መጠን ያነሰ መሆን የለበትም፡፡
ተጐጂው ከወንጀል ፈፃሚው  ካሳ ማግኘት ካልቻለ የማካካሻ ክፍያ ከፈንዱ እንዲከፈለው ይደረጋል የሚለው ረቂቅ ህጉ፤ ይህም የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ላላቸው ተጎጂዎች ብቻ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

ምንጭ – አዲስ አድማስ

The post በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ላይ እስከሞት ሊያስቀጣ የሚችል ረቂቅ ህግ ወጣ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles