ዘመድኩን በቀለ
እስቲ ዛሬ ደግሞ ከነገረ ተሐድሶ ወጣ እንበልና ባለፈው በደቡብ አፍሪካ በተነሳው ብጥብጥ አሳዛኝ የሆነ አደጋ ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አንዱን ገጠር ድረስ በመሄድ አፈላልጌ አግኝቸዋለሁ እና ታሪኩን ላጫውታችሁ ።
ይህን ልጅ አግኝቼ እንዳወራው በብርቱ የደከመውን እና ጊዜውን መኪናውን በመስጠት ጭምር የተባበረኝን የደርባኑ አሸናፊን ሳላመሰግን አላልፍም ።
አደጋው የደረሰበትን ልጅ ለማግኘት አስቸጋሪ የነበረው በቅርብ ልጁን ማግኘት አለመቻሉ ነው ። ምክንያቱም በአስገዳጅ ምክንያት አሁንም ይህ ልጅ ወደዚያው አደጋው ወደ ደረሰበት ስፍራ በመመለሱና ስልኩም አልሰራ ብሎኝ ስለነበር ነው ።
እኔም ከትናንት ወዲያ የአገልግሎት እረፍት ስለነበረኝ ልጁን አሸናፊ በዘመዶቹ አማካኝነት ደርባን ድረስ አስመጥቶት ስለነበር ለመገናኘትና ታሪኩን ለመስማት ወደተቀጣጠርንበት የህንድ ውቅያኖስ የባህር ዳርቻ አመራን ። ከባህሩ ላይ የሚመጣው ነፋስ ደስ የሚያሰኝ ፣ ማእበሉም የሚማርክ ነው ።
ተጎጂው እያነከሰ ፣ የሀገሬን የአድአ በርጋን ነጭ ማኛ ጤፍ የመሰለን አሸዋ እየረገጥን ቀስብለን ወደ ባህሩ ዳርቻ ደርሰን በመቀመጥ ቦታ ይዘን በመቀጥ ወጋችንን ጀመርን ።
ኤልያስ ማርቆስ ይባላል ። ተወልዶ ያደገው በደቡብ ክልል ጊቤ ወረዳ ሜጋቶ ቀበሌ ውስጥ ነው ። በ1979 ዓም ከአቶ ማርቆስ ማንጉዶ እና ከወይዘሮ መረጠት አቢኮ የተወለደው ኤልያስ በዚያው የሜጋቶ ቀበሌ ዘመናዊ ትምህርቱን እስከ 10 ኛው ክፍል ድረስ ተከታትሏል ።
በዚያ ቤተሰብ ውስጥ ከተወለዱት 9 ልጆች መካከል አንዱ እዚሁ በእሳት ተቃጥሎ ሲሞት 8ቱ በህይወት ይገኛሉ ። በደቡብ ክልል በከምባታ አካባቢ ቀደም ብለው ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጡ የአካባቢው ልጆች የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ መለወጣቸውን የተመለከተው ኤልያስ የገበሬ ቤተሰቡን ህይወት ለመለወጥ በሚል አደገኛና ከባድ ውሳኔ በመወሰን በወለድ እግድ 60 አፄ የኢትዮጵያ ብር በመበደር በደላሎች አማካኝነት በመጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ ከዚያም ወደ ሞያሌ ከሞያሌ ናይሮቢ ድረስ ተጓዘ ።
ኤልያስ እስከ ሞያሌ ድረስ ምንም አልመሰለውም ። በመኪና ስለሄደ እስከ ደቡብ አፍሪካም ድረስ እንዲሁ የሚሄድ መስሎትም ነበር ። ግና ከሞያሌ በኋላ ደላሎቹ እንክብካቤያቸውን በመቀነሳቸው መኪና መጠቀምም ቀርቶ ጉዞው በእግር ሆነ ።
ከናይሮቢ ታንዛኒያ ። ከታንዛኒያ ማላዊ ። ከማላዊ ሞዛምቢክ ። ከሞዛምቢክ ዚምባቡዌ ። ከዚምባቡዌ በመጨረሻ ከ8 ወር አድካሚና አሰቃቂ የእግር ጉዞ በኋላ 60 ሆነው ወጥተው 4 መንገድ ላይ በረሐብ ሲሞቱ ኤልያስን ጨምሮ 56ቱ ሰው ያለበት ሲደርሱ ከሀገሬው ሰው እየለመኑ ። ሰው በሌለበት ደግሞ ሳርና ቅጠል እየበሉ ያገኙትን ውሃ እየጠጡ ተስፋ ወዳደረጓት ምድር ደቡብ አፍሪካ ገቡ ። በመንገድ ላይ የአውሬው የሽፍታው የዝናቡ የፀሀዩ ነገር አይነገርም ።
በደቡብ አፍሪካ ኤልያስ ከተማው አከባቢ ተቀጥሮ ጥቂት ጊዜ ከሰራ በኋላ ወደ ገጠር በመግባት በመጀመሪያ መደብ ላይ በመቀጠል ትንሽዬ ኮንቴነር በመከራየት ሌት ተቀን በመስራት በመጀመሪያ ሐገር ቤት ያለበትን እዳ ከፈለ ። ሲያስበው በዚህ አይነት የሚረዳው የራሱ ሰው ቢያገኝ የበለጠ በቶሎ እንደሚለወጥ በማሰብ ወንድሙን በ100 ሺህ ብር ወለድ አግድ ከፍሎ በ2012 ዓመተ ምህረት ወደ ደቡብ አፍሪካ አስመጣው ።
ወንድሙ የእድል ጉዳይ ሆኖ በዚያው ኤልያስ በመጣበት መንገድ 4 ወር ፈጅቶበት ነው የደረሰው ። አሁን ኤልያስ ደስ አለው ። በመጀመሪያ ዕዳውን ለመክፈል እቅድ አወጡ እሱና ወንድሙ ። ወንድሙ ተሰማ ማርቆስ የ5 ተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ነው የመጣው ። ኦምላዚ ሴክሽን ደብሊው የሚባል ለህይወት አደገኛ የሆነስፍራ በዚያችው ኮንቴነር ውስጥ ሥራቸውን በትጋት ማካሄድም ጀምረዋል ።
ከእለታት በአንዱ ቀን ። በቀን ጎዶሎ ይለዋል ኤሊያስ ያን እለት አርብ ሲያስታውሰው ። ከምሽቱ 1 ሰዓት አካባቢ በድንገት ገጀራ ፣ ሽጉጥ ፣ ጋዝ ፣ እሳት ፣ ፔትሮሊየም ቦምቦች የያዙ አስፈሪ ሰዎች ድንገት እነሱ በሱቋ ውስጥ እንዳሉ ከውጭ በሩን ቆለፉባቸውና ቤንዚን አርከፍክፈው እሳት ለቀቁባቸው ። ቤቱን ያከራያቸው ሰው ቢደርስም እንዳያድናቸው ጎረምሶቹ እጁን ወጥረው በመያዝ ከለከሉት ።
ኤልያስ ይቀጥላል ። እኔ እንደ አጋጣሚ በደመ ነፍስ ስወራጭ ቆርቆሮ የያዙ ካርቶኖች በላዬ ላይ ወደቀብኝ ። ሱቋ በጭስ ተሸፍና ስለነበር የወንድሜን ዋይታ እሰማለሁ እኔም ጆሮዬ ስር የሚነደውን እሳት ለማጥፋት ስታገል እግሬ መንደድ ይጀምራል ። እግሬን ስታገል ወገቤ ይነዳል ። ወንድሜ ግን ከእግር ፍሩ እስከ ራሱ ድረስ ተያይዞ እንደ ጧፍ ይነዳል ። ልቅሶ ።
ከዚያ ገዳዮቹ የኛ ነገር ያለቀ መስሎአቸው ሌላ የሚገድሉት ፍለጋ ሲሄዱ ሱቁን ያከራየን ሰው መዶሻ አምጥቶ ሰብሮ በመግባት እኔንም ወንድሜንም አወጡን ። ወንድሜ 85% የሰውነት ክፍሉ ተቃጥሎ ። የውስጥ እቃዎቹም እንዲሁ ተቃጥለው ስለነበር በፍጥነት ወደ ሐኪም ቤት ቢወስዱትም ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም ።
እኔ ግን ራሴን ያወቅሁት እና የነቃሁት በ4 ተኛ ቀኑ የወንድሜ አስከሬን ወደ ሐገር ቤት ሊሸኝ በዝግጅት ላይ እያሉ ነበር ።
ኤልያስ አሁን በምድር ላይ በፀፀት እየተቃጠለ እንደሚኖር ነው የሚሰማው ። ብዙ ነገር ያስጨንቀዋል ። ምንም እንኳን ወንድሙን ይህ መከራ ይገጥመዋል ብሎ አስቦ ባያመጣውም ምክንያቱ ግን እሱ እንደሆነ ሲያስብ እረፍት ያጣል ። ሟች ወንድሙ በእዳ ነው የመጣው አበዳሪዎች ሐገር ቤት ናቸው ። ካልከፈለ ቤተሰቡን ያስጨንቁበታል ። ይሄንንም ባሰበ ጊዜ ይጨንቀዋል ። ደህናውን ልጅ ከቤት አስወጥቶ የተቃጠለ አስከሬን ለእናትና አባቱ መላኩን ባሰቡት ጊዜም ይጨንቀዋል ።
አሁን ቁስሉ እያመመው ነው ። እንደወጉ ቢሆን አገግሞ ትንሽ ማረፍ ነበረበት ። ግን የሚያስጨንቀው ነገር ስለበዛ እረፍት ማድረጉን ትቶ እንደገና ወደ ገጠር ገብቶ በዚያው አደገኛ ሎኬሽን ውስጥ በሰው ቤት ተቀጥሮ በመስራት ላይ ይገኛል ።
ኤልያስ እንደሚለው በህይወት ከቆየሁ እንደምንም ጥቂት ሰርቼ መጀመሪያ እዳዬን መክፈል ነው የምፈልገው ። አሁን ጥቂት ሥራ መጀመሪያ ሳንቲም ባገኝ እርግጠኛ ነኝ በቶሎ እነሳለሁ ። ሥራውን እንዴት እንደምሰራውም አውቃለሁ ። አሁን ከህመሜም ጋር እየተሰቃየሁም ቢሆን እንዲህ መከራ ያየሁበትን ሐገር ሳልሰራና ጥሪት ሳልይዝማ አልወጣም ።
ሞትን በጉዞዬ አይቸዋለሁ ። ወንድሜን አይኔ እያየ ታቃጥሎ ሲሞት ተመልክቻለሁ ። ስለዚህ ጤናም የለኝ እናቴንም አባቴንም ብዙ ኪሳራ ላይ ጥዬማ እኔም ባዶ እጄን ሐገር ቤት አልመለስም ። እዳዬን እከፍላለሁ ። ከዚያም ለእናትና አባቴ መጦሪያ የምትሆን ነገር ሰርቼ እልካለሁ ። ከዚያ ብሞትም አይቆጨኝም ።
አፍፍፍፍፍ እኔን ጨነቀኝ ። አብሬው አለቀስኩ ። ድህነትን ረገምኩት ። ምን አይነት ጨካኝና ክፉ ነው ይሄ ድህነት ይሉት ነገር ክፋቱ ። በሱዳን በረሃ መደፈሩ መገደሉ ፣ በሊቢያ በረሃ መታረዱ መረሸኑ ፣ በሜዲትራንያን ባህርና በቀይ ባህር መስጠሙ ፣ በየመን በቦንብ ፣ በሳውዲ በጅራፍ ፣ በሊባኖስ ከፎቅ መወርወሪያ ፣ በኬንያ በጅቡቲ መሰቃየቱ ፣ በደቡብ አፍሪካም በቁም መቃጠሉ መቼ ይሆን የሚያበቃው ። አረ ያንድዬ እናት ተማለጂን ። ምነው የአስራት ሀገርሽን ጨከንሽባት ።
አሁን ከኤልያስ ጋር አብረውት ከመጡት ልጆች ላይ 400 ራንድ ከአሹ ከጓደኛዬ 100 ራንድ እኔም ራሴ ከአሹ ተበድሬ መቼ እንደምከፍለው ባላውቅም 50 ራንድ በአጠቃላይ 550 ራንድ ሰጥቼው ደግሞ ይህን ያነበቡ ሰዎች ማን ያውቃል ሊረዳህ የሚችል አታጣ ይሆናል ? ብዬ ሥራ መስጀመሪያው ባይሆንም ለዳቦ መግዣ የምትሆነውን ሰጥቼው ፣በተረፈ ደጋግ ጓደኞች ስላሉኝ እነግርልሃለሁ ። ሐገር ቤት ስገባም አባትህንና እናትህን እጠይቃቸዋለሁ ብዬ ስልካቸውንም ተቀብዬ ተለያየን እኔና ኤልያስ ።
አሸናፊ ማለት በደቡብ አፍሪካ ችግሩ ሲነሳ ከእሱ ሱቅ ፊት ለፊት ነበር ። እሱም በቦታው ላይ ነበር ። እሱም በተአምር ነው የተረፈው ።
እናም ውድ ጓደኞቼ ምን አስባችሁ ? ይህን ወገናችንን የቻላችሁ እርዱት ። ያልቻላችሁ ደግሞም አቅሙ የሌላችሁ ደውሉለትና አይዞህ በሉት ። ኢትዮ ዙሪክ የእግር ኳስ ቡድን አባላት ይሰማችኋል አይደል ? ጴጥሮስ አሸናፊ ወንድሜ ለቡድኑ አስተባባሪ ለሬዲዮ ንገረው አደራ ።
አማርኛ መናገር ሰለሚቸግረው በተለይ ሀድይኛ የምትናገሩ በ +27742508476 ደውሉለት ።
አማርኛ ተናጋሪዎች ደግሞ በ +27842145850 ላይ ሰላሙ ብላችሁ ደውሉለት ።
በተረፈ ጆሃንስበርግ ከደረስኩ ደግሞ ሌላ አንድ የተጎዳ ልጅ ተቃጥሎ ከሞት ተርፎ በሕይወት የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ወገኔን ስልኩን ስላገኘሁ እንዲሁ ላገኘው እናፍቃለሁ ። ሰላም ሁኑልኝ ።
+251911608054 በ Viber አሁን የምገኝበት የእጅ ስልኬ ነው ። የደቡብ አፍሪካው ጊዜአዊ ስልኬም እነሆ ይኸውላችሁ +27 74 243 3712
ይህ ጽሑፍ ሼር መደረግን አጥብቆ ይፈልጋል ። ምን አልባት ድንገት ኤልያስን ሊረዳው የሚችል ደገኛ ሰው ቢገኝ ። ይቆየን ።
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ሰኔ 24/10/2007 ዓም
ደርባን – ደቡብ አፍሪካ
The post ከመቃጠል ያተረፈችው ነፍስ ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ (አሳዛኝ ታሪክ) – ወንድም ያላችሁ በትእግስት አንብቡት appeared first on Zehabesha Amharic.