Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ስለ ህዝብ የሚያስብ  ማን ይሆን? –ከተማ ዋቅጅራ

$
0
0

Ketemaእኔ ከሞትኩኝ ሰርዶ  አይብቀል የሚል የአህያ  ተረት አለ። በኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለው ይሄ ነው። እኔ…እኔ ለኔ…..ለኔ የሚል ትውልድ መነሳቱ ያሳዝናል። በርግጥ ማንም ለራሱ ቢያስብ ለራሱ ቢኖር ምንም አልነበረም መጥፎነቱ እራሱን ከፍ አድርጎ ለማኖር ሌላውን መበደል ግን አግባብነት የለውም። ሌላውን ገድሎ ወይም አጥፍቶ እራስን ለማኖር መፍቀድ ተገቢ አይደለም። ይህ ሃሳብ ፈጽሞ ከኢትዮጵያ ምድር መጥፋት ያለበት ድውይ ሃሳብ ነው።

የአንድ አገር ለውጥ አምጪ አልያም የሞተሩ ሃይል ያለው በመንግስት ደረጃ ነው። የመጀመሪያው አሜሪካ መሪ ጆርጅ ዋሽንግተን ለአገሩ ነጻነት ከታገለ በኋላ የሚከፈለውን መሰዋትነት ከፍለው አገራቸውን ነጻ ካወጡ በኋላ ታግዬ የመጣው ስለሆነ የስልጣን ወንበሩ ለኔ ብቻ ነው የሚገባው እስከምሞትም መምራት አለብኝ አገሪቷን እኔ ካልመራኋት ትፈራርሳለች ወደ ባሰም ችግር ታመራለች የሚል የደካማ አስተሳሰብ እና የራስ ወዳድ አመለካከት ስሌላቸው <<እኔ ወደቀድሞ ሰራዬ ተመልሻለው አገሪቷን በዲሞክራሲ የሚመሯት እና ወደተሻለ ደረጃ ሊያደርሷት የሚችሉ ልጆች ስላሏት እነሱ ያስተዳድሯት>> በሚል የጠለቀ ሃሳብ ሰጥተው የአገሪቷን የሁል ግዜ ሰላም አብስረዋል። ከዛን ግዜ ጀምሮ ህዝቡ የመረጠው መሪ እያነገሰች እድገቷ ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ የአለማችን ትልቋ አገር ለመሆን በቅታለች። አሜሪካ  ውስጥ የአንድ ተራው ዜጋ መብት እና የመሪው መብት እኩል እስኪሆን ድረስ የሁሉም መብት እኩል የተከበረባት አገር እንድትሆን ያስቻሏት እና የነጻነት መሰረቱን የጣሉት ጆርጅ ዋሽንግተን ናቸው።

ኢትዮጵያ  ውስጥ ግን እንደዚህ አይደለም። አንዱ ከመጣ ውረድ…..አልወርድም። አትጨቁን…..እጨቁናለው።  አትግደል……እገድላለው።  የህዝብ መብት አትርገጥ…….እረግጣለው።  እኩልነት ይስፈን…..እኩልነት የለም። በእንደዚህ አይነት ጥያቄ እና መልስ ተወጥራ የመከራ ዘመኗን ትገፋለች። አንድ ጠቢብ ሰው ምን አለ የሰው ልጅ አእምሮ  መጠቀም ከሚችለው 100% ትላልቅ ፈላስፎች የተጠቀሙበት 13%ቱን ነው 13% ጭንቅላታቸውን ተጠቅመው ለአለማችን ትላልቅ ስራዎች ሰርተው አልፈዋል እኛ ግን 3% ብቻ ነው የተጠቀምንበት ብለው ሲናገሩ ሰምቻለው። የሚገርመው ደግሞ  ስለሰው ክፋትና ጥፋት እራሳቸውን ብቻ በመውደድ በተሻለ ነገር ለማኖር ህዝብን የሚበድሉ ህዝብን የሚያጠፉ አካሎች ደግሞ 0% ነው የተጠቀሙበት ገና ጭንቅላታቸው መስራት አልጀመረም ልክ እንደ  እንስሳ አልያም እንደጋሪ ፈረስ ፊት ለፊታቸውን ብቻ የሚያዩ መልካምነት፣ የሰዋዊ ተፈጥሮ  እና ሰበአዊነት ያልፈጠረባቸው እርምጃ ወሳጆች ናቸው። ግደለው፣ አስወግደው፣ አምጣው፣ አባረው፣ ምን ያመጣል፣ የትም አይደርስም፣ አቃጥለው፣ ጨርሰው፣ አፍርሰው፣ ደርምሰው  የሚሉ ብቻ  የእንደዚህ አይነት ሰው ጭንቅላት ለመቀየር አይቻልም እንጂ ቢቻል ኖሮ አቃቂ ብረታ ብረት ገብተው ቀልጠው እንደገና በአዲስ መልክ ካልወጡ በስተቀር የነዚህ አይነት ሰዎች ጭንቅላት እንደሰው ማሰብ ለመጀመር በጣም ይከብዳቸዋል።

አንበሳ  በጫካ ውስጥ የሱ ግዛት የሚለውን በሙሉ በትንፋሹ በጠረኑ ያጥረዋል እዛ ግዛት ውስጥ የገቡትን በሙላ ያጠቃል ያጠፋል። እርስ ባራሱም ሲኖር የመንጋው መሪ ለመሆን ይፋለማል ያሸነፈም መንጋውን ይመራል። ያ የመንጋው መሪ የሆነ አንበሳ ወንድ የሆኑትን እና ቀና ቀና ያሉትን አንበሳዎች በሙሉ ማባረር ማጥፋት ይፈልጋል ምክንያቱም ስላጣኔን ይቀሙኛል ስለሚል። ይሄ እንስሳዊ ጸባይ ነው። በሁሉም የእንስሳት ዘር ተመሳሳይ ድርጊት ይከናወናል። ምክንያቱም አእምሮአቸው 0% ስለሚያስብ ነው። ታዲያ የኛ መሪ ተብዬዎች ቀና ቀና ያለውን ለአገር አሳቢውን ለህዝቡ ነጻነት አላሚውን በእውቀት የበሰሉ አእምሮአቸውን ማሰራት የሚችሉ ፍቅር መዝራት የሚችሉትን ሰላምን ማምጣት የሚችሉትን የለውጥ ገበሬ የሆኑትን በሙሉ እያሳደደ  ያጠፋል ያስራል ይገድላል ታዲያ ይህ እንስሳዊ ባህሪም አይደለምን? ያው 0% ውስጥ አይደሉምን?

ሞኝ የተከለውን ብልህ አይነቅለውም ይባላል እነዚህ ሰዎች የሚያውቁት ምንም ነገር ስለሌለ የተማረ ሰው ከመጣ የኔን ቦታ ይወስደዋል ስልጣኔን ያሳጣኛል በሚል እንስሳዊ ባህሪ ሃገር ተበደለ ህዝባችን ሰላም አጥቷል አገዛዙ ልክ አይደለም የሚለውን በሙሉ ሲያሳድዱ ይኖራሉ። አንዴ እነሱ እዛ ቦታ ላይ ተተክለዋልና መሳሪያ አላቸውና የሚያጅባቸው ወታደር አላቸውና አድርግ ሲባል የሚያደርግ ፈጽም ሲባል የሚፈጽም አዛዙ ሞኝ ቅጥረኛውም ሞኝ አገልጋይ አንድ ላይ ሆነው መኖር እስከሚያስጠላው ህዝችን በምድሩ ላይ በደልን በማድረስ የስልጣን ዘመናቸውን ይቆጥራሉ።

ታዲያ እውነተኛ ለአገሩ አሳቢ ማን ይሆን? ለህዝቡስ የሚጨነቅ የትኛው ይሆን? ኬኒያ ላይ ህዝባችን በደል እየደረሰበት ነው፣ ሱዳን ላይ፣ ደቡብ አፍሪካ ላይ፣ የመን ላይ፣ ሊቢያ ላይ፣ ሳውዲ አረቢያ ላይ፣ ቤሩት ላይ፣ አረብ አገራት ላይ፣ አገር ውስጥም ውጪም በህዝባችን ላይ ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸው ነው ብለህ ስትናገር የመንግስት አካል የሆኑት የነሱን ፖለቲካ ስለማይነካ የራሳቸው ጉዳይ ነው በሚል በንቀት እና በጥላቻ ስሜት መግለጫ፣ ዜና፣ አልያም ንግግር እንደሰማናቸው ይናገራሉ። ከሌላውም አካል ደግሞ የኔ ወገን ስላልሆነ አይመለከተኝም ይላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ለግንባታ ተብለው በተቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ ህጻናት እየገቡ እየሞቱ ነው በተለያየ ቦታ ላይ ለመንገድ ለተለያየ ነገር የሚቆፈሩት ጉድጓዶች በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን መንግስት እያወቀ ስለጠፋው የሰው ህይወት ሳይሆን ባለሃብቶቹ እንዳይቀየሙ የውጪ ዜጋም ከሆነ ዲፕሎማሲ ግንኙነቱ እንዳይበላችበት በማሰብ ለዜጋው ያለውን ጥላቻ  እና ንቀት እንዲሁም ያነሰ ግምት በየግዜው ይገልጻሉ። ምዕራብያዊያን ግን እንዲህ አይደለም አንድን ስራ ሲሰራ ሰው ላይ ጉዳት እንዳያደረስ የመከላከያ ምልክቶችን እና ጥንቃቄዎችን ያደርጋሉ። ምክንያቱም በሚከሰተው አደጋ ተጠያቂ ስለሆነ እና ከሚሰራው ስራ በላይ ስለዜጋው ስለሚጨነቅ ቅድመ ጥንቃቄ ያደርጋል። ጥንቃቄ ሳያደርግና ምልክቶችን  ሳይጠቀም  የሚሰራ ማንኛውም የስራ ድርጅት ከተጠያቂነት አልፎ የስራ ፍቃዱ እስከመነጠቅ የሚያደርስ ከፍተኛ እርምጃ በመንግስት ይወሰዳል።

በኛ አገር ግን ለስራ ተብለው በሚከወኑ ክንውኖች ከጥንቃቄ ጉድለት እና ከእንዝላለኝነት የሰው ህይወት ይጠፋል መንግስትንም የተቹ በሙሉ ታድነው ይታሰራሉ ባልታወቀ  ምክንያትም ይገደላሉ ዜጋችን በየግዜው ይሞታል። ታዲያ መቼ ይሆን ስለ ህዝባችን ህይወት የምናስበው? ዜጋው ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት በምንም መልኩ በሚሰራው ስራ እና ባለው የተለየ ሃሳብ ስለ አገሩ ነው የሚሰራው ተብሎ አመለካከቱ ተከብሮለት የምንኖረው መቼ ይሆን? መንግስት ተሳስቷል ባለስልጣኖችም ወንጀል ሰርተዋል ተብሎ ሲነገር ድምጻችን ተሰምቶ ስተቱ የሚታረምበት ወንጀል የሰራውም ባለስልጣን የሚቀጣበት መቼ ይሆን? የመንግስት ስህተት በህዝብ ጥያቄ የሚፈረድበት የባለስልጣንም ጥፋት በህዝብ ዳኝነት የሚታይበት ግዜ ይመጣል። ያኔ የህዝብ የበላይነት ሲታወጅ በነጻነት መንግስትን እና የምንግስት አካላትን እንደምዕራብያዊያኑ እየተቸህ ስህተቶችንም እያጋለጥክ ካለምንም ፍራቻ በሰላም የምንኖርባት አገር ከፊለፊታችን  ትመጣለች።ያኔ ዜጋዬ የሚል መንግስት ይኖረናል እንኳን በአገር ውስጥ ይቅርና በውጪ አገር ሺዎች ሰበደሉ እና ሲገደሉ ዝም የሚል መንግስት የሺ ኢትዮጵያንን በዳይና ገዳይ መንግስት ሲሞት የአገሩን ክብር አዋርዶ የሞቱትን እና የተጎዱትን ህዝባችንን ንቆ ለሆድ በማደር የገዳይን አገር መንግስት ገዳይን በክብር ለመቅበር የሚሄደውን ሳይሆን አንድ ዜጋችን በውጪ አገር  ሲታሰር የታሰረውን በክብር ለማስፈታት ወታደር የሚልከውን ለህዝብ እና ለአገሩ ክብር የቆመው መንግስት ከፊታችን ይመጣል። እድሜ መስታወት ነው ሁሉን ያሳያል ይባል የለ ይህንን ጉድ መንግስት እንዳየን በድንቅ አገር ድንቅ መንግስት ኖሮን እናያለን።

ቸር  እንሰንብት።

 

ከተማ ዋቅጅራ

Email- waqjirak@yahoo.com

01.07.2015

The post ስለ ህዝብ የሚያስብ  ማን ይሆን? – ከተማ ዋቅጅራ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>