Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ጥያቄው ሻዕቢያን ማመን አለማመን ሳይሆን ከወያኔ አገዛዝ እንዴት እንላቀቅ ነው፡፡  –ይገረም አለሙ

$
0
0

 

eri_tigrayወያኔን በማያውቀው ሰላማዊ ትግል አሸንፈው  በህዝብ ለተመረጡበት ቦታ ሳይሆን ለወህኒ የተዳጉት ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ በሊቀመንበርነት የሚመሩት አርበኞች ግንቦት 7  ወያኔን ማነጋገር በሚገባው ቋንቋ ነው  ብሎ መዘጋጃና መነሻ ቦታውን ኤርትራ ውስጥ ማድረጉ በአንዳንድ ወገኖች እየተነቀፈ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደውም  ከነቀፋና ተቃውሞ አልፈው ሀገር መሸጥ ነው እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡

ሁሉም ድርጊቱን የሚኮንኑ የሚያወግዙ  ሰዎች ኢትዮጵያ ከወያኔ የግፍ አገዛዝ መገላገል አንዳለባት የሚያምኑ ናቸው፡፡ወይም ይመስላሉ፡ ግንቦት 7 የመረጠውን የትግል ስትራቴጂም በጥቅሉ ሲያወግዙ አይታዩም፡፡ ችግራቸው ሻዕቢያ አይታመንም፣ ሻዕቢያ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ጠላት ነው ወዘተ የሚል ነው፡፡ እንዲህ አታድርጉ፣እንዲህ መሆን የለበትም የሚል በአንጻሩ መሆን አለበት የሚለውን መጠቆም ማመላከት ይኖርበታል፡፡

ወያኔ በአገዛዝ መቀጠል የለበትም ከተባለ ለዚህ የሚያበቃውን የትግል አይነትና ስልት ማሳየት ይገባል፡፡ ሻዕቢያ አይታመንም ከተባለ ወያኔን በሚገባው ቋንቋ አነጋግሮ ኢትዮጵያን ከአገዛዝ ሊያወጣት የሚችል ትግል ከየት ሊጀመር እንደሚችል ማመላከት ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ በተቃውሞ ብቻ አማራጮችን ማጨለምና መንገድ መዝጋት የምናምነው ጎረቤት እስከሚገኝ ወያኔ ይግዛኝ ማለት ይሆናል፡፡

እኔ የሻዕቢያ አፍቃሪም አድናቂም አይደለሁም፤ ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ ነው፡፡ የኤርትራንና የኤርትራዉያንን ኢትጵያዊነት ግን በጥብቅ አምናለሁ፡፡ መሬቱም ሰዉም ማለቴ ነው፡፡ የበርሊን ግንብ ፈርሶ ጀርመኖችም አንድ ሆነዋል፡፡ ሻዕቢያና የኤርትራ ሕዝብ አንድና አንድ ናቸው የሚል እምነትም የለኝም፡፡አንዳንደ ሰዎች ሸዕቢያን ቅዱስ ኢሳይያስን መልዐክ ለማስመስል በሚቃጣ መልኩ የሚየሰሙት ድምጽም ተገቢም አስፈላጊም አይደለም እላለሁ፤

ሻዕቢያን ማመን አይገባም የሚሉ ወገኖች  የዛሬ ሰላሳና አርባ አመት ወደ ኋላ ተጉዘው ሻዕቢያ በኢህአፓ ላይ ፈጸመው ያሉትን ድርጊት በመከራከሪያነት ያቀርባሉ፡፡ ትናንት የነገረ የተደረገን  ነገር አስታውሶ ዛሬ መሰል ድርጊት እንዳይፈጸም መጠንቀቅ ብልህነት ነው፡፡ ሌሎች ከዛ እንዲማሩ መምከርም አርቆ አስተዋይነት ነው፡፡ ያን እያሰቡ በስጋት መፍራትና ፈርቶ ማስፈራራት ግን የሚጠቅም አይደለም፡፡

ትናንት ዛሬ አይደለም ነገም ዛሬን ሊሆን አይችልም፡፡ እያንንዱ ግዜ የራሱ ነባራዊ ሁኔታዎች ይኖሩታል፡፡ ያንን ተረድቶ ዓላማና  ፍላጎትን ለማሳካት የሚያስችሉ እቅድና ስትራቴጂዎችን ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞና መንገድን አመቻችቶ መሄድ ነው ከውጤት የሚያደርሰው፡፡

ሻዕቢያም ሆነ ወያኔ ኢህአፓን ሲያጠቁ አበይት ምክንያታቸው የዓላማ ልዩነት ነው፡፡ የኢህአፓ ዓላማ ከመገንጠል ማስገንጠል ዓላማቸው ተቃራኒ በመሆኑ ለትግላቸው ስኬትም ሆነ ተሳክቶላቸው ስልጣን ቢይዙ ለመንግስታቸው መርጋት እንቅፋት አድርገው ስላዩት ኢህአፓን ሳይቃጠል በቅጠል በማለት አጠቁት፡፡ እውነትን በድፍረት እንነጋገር ከተባለ ኢህአፓ የተጠቃው በወያኔና በሻዕቢያ ብቻ አልነበረም፡፡ ርስ በርስ በመጠቃቃትና በመከዳዳት ለሻዕቢያና ወያኔ ጥቃት ራሱን አመቻችቷል፡፡

ሻዕቢያና ወያኔ በየግል የፈለጉትን የሁለት ሀገር መንግስትነት ሲያገኙ በጋራ ያለሙት ኢትዮጵያን የመቦጥቦጥ  የጫካ ስምምነታቸው ግን በተለይ ወያኔ ቤተ መንግሥት ተቀምጦ ሊፈጽመው የሚችል አልሆን አለና ይሄው ሰበብ ሆኖ አያሌ ኢትዮጵያዉያን ( ኤርትራዉያንም  ማለቴ ነው) ላለቁበት ጦርነት ዳረጉን፡፡ ይህም ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅነትም ሆነ ጠላትነት የለም የሚለውን አባባል ትክክለኛነት ያሳያል፡፡

ስለሆነም አሁን ያለውን ሁኔታ መገምገምና የመፍትሄ ሀሳብ መለገስ  ኢትዮጵያን ከወያኔ አገዛዝ ለማላቀቅ ከምናካሂደው ትግል አንጻር የኤርትራ ጠቃሚነትና ጎጂነት በሚል ቢሆን ይመረጣል፡፡ ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር  ያለው ምርጫ ሁለት ነው፡፡ ወያኔ በሰላማዊ ትግል በምርጫ ሥልጣን መልቀቅ አይደለም አንድም የፓርላማ ወንበር ለተቀዋሚ እንደማይሰጥ አረጋግጧል፡፡ ይሄ ደግሞ የ ዛሬ ብቻ አይደለም እድሜ ከሰጠው የዛሬ አምስት አመትም ይደገማል፡፡ማስረጃ የሚፈልግ የወያኔን ልሳን አዲስ ራዕይ መጽሄት የሀምሌ 2002 ዕትምን ማንበብ ይችላል፡፡

“ጸረ ሕገ መንግሥታዊ አቋማቸውን እስካልቀየሩ ድረስ መብታቸውን በጥብቅ አክብረን በማያቋርጥ ዴሞክራሲያዊ ትግል አሁን ከደረሱበት ደረጃ አንዳያልፉና እንዳያንሰራሩም በርትተን መስራት ይጠበቅብናል” ይላል (አዲስ ራዕይ Ñê 27)

ይህ በምርጫ 2002 ማገስት የተጻፈ ነገር ምን ማለት አንደሆነ ዛሬ አሁን በምርጫ 2007 በተግባር ያየነው ይመስለኛል፡፡ስለሆነም ከላይ እንዳኩልት ያለው ምርጫ ሁለት ነው፡፡ከወያኔ አገዛዝ ለመላቀቅ ከምናደርገው  ትግል ጠቃሚነት አንጻር ኤርትራን  እንዴት በምን ሁኔታና እስከ ምን ድረስ  መጠቀም እንችላልን ብሎ የአጭርና የረዥም ግዜ ስትራቲጂ ነድፎ በጥንቃቄና በጥንካሬ ትግሉን መቀጠል፡፡ የወያኔ አገዛዝ ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ መቆየት የለበትም የሚል ወገን ሁሉ በሚችለው መንገድና አቅም  ትግሉን ማገዝ፤( ምክር መለገስ፣ ልምድ ማካፈል፣ ድክመትን መጠቆም፣ የመፍትሄ ሀሳብ መስጠት፣ መንገድ ማመላከት ወዘተ) ይህን ለማድረግ ፍላጎቱም ፈቃደኝነቱም ሆነ አቅሙ ከሌለ  ከማደናቀፍ መቆጠብ፡፡

ሁለተኛው ምርጫ ሻዕቢያ አይታመንም ብሎ ቀን እባብ ያያ ማታ በለልጥ በረየ እንዲሉ ሆኖ ለትግሉ መነሻ የሚሆን የሚታመን ጎረቤት ሀገር እስኪገኝ ወያኔ ይግዛኝ ብሎ  ቡራኬ መስጠትና ያዋጣል ብለው በአመኑበት መንገድ ትግል የጀመሩትን ወገኖች እያወገዙና እየኮነኑ መቀጠል፡፡ ይህኛው ተመራጭም አዋጭም አይመስለኝም፡፡

አንድየ የማሪያም ልጅ ኢትዮጵያን ይጠብቃት

The post ጥያቄው ሻዕቢያን ማመን አለማመን ሳይሆን ከወያኔ አገዛዝ እንዴት እንላቀቅ ነው፡፡  – ይገረም አለሙ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>