Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ባክኖ የቀረ  አየር ኃይል –ክንዴ ዳምጤ –ሲያትል

$
0
0

ውስጥ ውስጡን በድብቅ ሲብላላ የሰነበተውና በኋላ ቀስ በቀስ ወደ አደባባይ የወጣው የሻብያና ህውሃት ወዳጅነት ላይ ያንዣበበው ጥቁር ደመና ሞትን አርግዞ እያስገመገመና እያስፈራራ ሰነባብቷል ። እዚህ አስመራ ውስጥ ከወትሮው የተለየ ነገር ባይታይም አዲስ አበባ ላይ የኢትዮጵያን ፓርላማ የክተት አዋጅ ተከትሎ የጦርነቱ ከበሮ ተሟሙቆ ቀጥሏል ።

ethiopian airforceህውሃት አዲስ አበባና ደ/ዘ እንደደረሰ እጁ ያስገባቸውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት ወደ እስር ሲያግዝ እድል የቀናው ባገኘው ቀዳዳ ሁሉ አገር ጥሎ ተሰደደ ። እዚህ አስመራ ደግሞ ሙያችንን ፈልገው አዲስ እየተዋቀረ ባለው አየር ኃይላቸው ውስጥ እያሰሩን ያለን ኢትዮጵያውያን ቁጥራችን ቀላል አይደለም ። እንዲያውም ከ80 % በላይ የአዲሲቱን አገር ኤርትራን አየር ኃይል እያቋቋምን የምንገኘው በትውልድ ኤርትራዊ የሆኑትና እኛ ኢትዮጵያውያን የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላቶች ነን ። (ኤርትራውያኖች የቀድሞ አየር ኃይል አባላት እድለኞች ናቸው ። ኢትዮጵያ እንደተደረገው መሰደድና መጋዝ አላጋጠማቸውም ። ሙያቸው ለአገሪቷ እንደሚጠቅም የሚረዳ የሙያው ባለቤት የሆነ አዛዥ አላቸውና በቀጥታ ወደ ስራ ምድባቸው እንዲገቡ ተደርጓል ።)

በዕለተ ዓርብ ግንቦት 27, 1990 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) ሜይ 5, 1998 በፈረንጆች የአስመራ አየር ኃይል ቤዝን ለማውደም የተጀመረውን የአየር ድብደባ ተከትሎ የኤርትራ አየር ኃይል 100% የውጊያ ዝግጁነት ( 100 % Readiness ) ታዟል

ይህ የውጊያ ዝግጁነት እኛን ኢትዮጵያውያኖቹን የማይመለከተን ቢሆንም ከኰ/ል ታደሰ ሙሉነህ ጋር በነጋታው ጠዋት ወደ አስመራው የአየር ኃይል ግቢ አመራን ። (ኰ/ል ታደሰ ሙሉነህ ማለት ታዋቂ የአየር ኃይል ተዋጊ በራሪ የነበረና በኋላም የአርበኞች ግንባር መሪ ፣ በቅርቡ ደግሞ እዚያው ኤርትራ ውስጥ ለእስር ተጋልጧል የሚባለው)

አስመራ አየር ኃይል ቤዝ እንደደረስን በሁለት የኢትዮጵያ ሚግ – 23 ተዋጊ አውሮፕላኖች የደረሰውን የአየር ድብደባና በአካባቢው ላይ ያደረሱትን ጉዳት እየተዟዟርን ተመለከትን ።

አንድ የጥገና ጋራዥና አጠገቡ የነበረች ሻይ ቤት ሙሉ በሙሉ ወደመዋል ። ኰ/ል ታደሰ ተበታትነው ወደ ሚታዩት ፍንጣሪዎች በእጁ እያመለከተ “ ይሄ ክላስተር ቦምብ ነው ” አለኝ ። በድብደባውም ሻይ ቤቷ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሰራተኞች ከባድና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ፣ ፍፁም የሚባል የቀድሞው አየር ኃይል ባልደረባም እንደሞተ ሰማሁ ።

አለፍ ብሎ ደግሞ ሁለተኛው የአውሮፕላን ጥገና ጋራዥ ላይ የወደቀውንም ቦምብ ተመለከትን ። ይህ ደግሞ “ ናፓል ቦምብ ” ነው አለኝ ኰ/ል ታደሰ ሙሉነህ በድጋሚ ። እኔ ሁለቱንም ዓይነት ቦምቦች ሳይ ይህ የመጀመሪያዬ ነበር ።

በመቀጠል በረራ መስመር ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማየት አውሮፕላኖቹ ወደቆሙበት ስፍራ ስንጠጋ አካባቢው በአደጋ መከለያ አጥር ታጥሯል ። አጥሩን አሻግሬ ስመለከት ኰንክሪቱን ወደ አንድ ሜትር ያክል ሰርስሮ የገባው ባለ 500 ኪ/ግ ቦምብ ሳይፈነዳ ከነነፍሱ ቁጭ ብሏል ። አደጋ እንዳይደርስ ተብሎም ወደ ቦምቦቹ መቃረብን ለመከላከል እንደታጠረ ተረዳሁ ።

 

ይህንን ግዳጅ የሰሩት ኢትዮጵያውያን በራሪዎች አስመራን ጠንቅቀው የሚያውቁና ፤ የሚደነቅም ችሎታ ያላቸው ስለመሆኑ እኔና ኰ/ል ታደሰ ተስማማን ። ለነገሩ የአገርን አንድነት ለመታደግ ከሻብያ ጋር ግብ ግብ እንደገጠሙ እዚሁ አስመራ አይደል ዘመናቸውን የፈጁት ? አስመራ የአየር ኃይል ቤዝ ለእነዚህ በራሪዎች አዲስ ሊሆን አይችልም ። በአገር ቤት ከእስርና ከስደት ተርፈው በስራ ላይ ያሉት በራሪዎች እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉም አሰብን ። በይበልጥ እኔ አብሪያቸው ስስራ የቆየሁ በመሆኔ ለመገመት ብዙም አልተቸገርኩም ።

አካባቢውን ተመልክተን እንዳበቃን ቁርስ በመቀማመስ ወደ ሆስፒታል በመሄድ የተጐዱ አባላትን ጠየቅን ። ኤርትራና ኢትዮጵያ ከመለያየታቸው በፊት በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ ሁላችንም በአንድነት እንሰራ ነበርንና በአንድ እናት ልጆች መካከል የሚካሄድ ፋይዳ ቢስ ፀብ መሆኑ እየተሰማን የጦርነቱ አላስፈላጊነትና እየደረሰ ያለው መጐዳዳት በእጅጉ አሳዘነን ።

ረፋዱ ላይ አገር ያናወጠ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ጡሩንባ ( ሳይረን ) ደጋግሞ በረጅሙ አስተጋባ ። ይህ ሳይረን የጠላት ተዋጊ አውሮፕላኖች አደጋ ለማድረስ መቃረባቸውን የሚጠቁምና ማንኛውም ሰው መከላከያ ስፍራ እንዲይዝ የሚያስጠነቅቅ ነው ። በመሆኑም ሁሉም ሰው በደርግ የአስተዳደር ዘመን ወደተሰሩ የመሬት ስር ምሽጐች እየሮጠ መግባት ጀመረ ። እኔም ዘመቻ መምሪያ አቅራቢያ ወደ አለው ባንከር እየተጣደፍኩ አመራሁ ። ልክ ባንከሩ መግቢያ ደጃፍ ላይ ስደርስ በደርግ ዘመን ሻብያ ከርቀት የከባድ መሳሪያ አረሮችን ወደ አስመራው አየር ኃይል ካምፕ ያዘንብ በነበረበት ወቅት አንድ ም/መ/አለቃ ይኩኖ ታደሰ የሚባል ጓደኛችን ወደ እዚህ ባንከር ውስጥ ሊገባ ሲል ከእርቀት እየተተኰሰ ባለው የመድፍ አረር ፍንጣሪ አንገቱ ተቆርጦ መሞቱ ለአፍታ ወደ አዕምሮዬ በመምጣቱ ሰውነቴን ሁሉ እየዘገነነኝ እያማተብኩ ፈጠን ብዬ ወደ ባንከሩ ተወርውሬ ገባሁ ።  ወደ ውስጥ ስዘልቅ የአየር ኃይሉ ኰማንደርና የመከላከያ ሚንስትሩ ባንከሩ ውስጥ መኖራቸውን አስተዋልኩ ።

ደቂቃዎች ተከትሎ ለሰማይም ሆነ ለምድር የከበደ ከፍተኛ የተኩስና የፍንዳታ ጩሀት በተደጋጋሚ አገሩን አደበላለቀው ። የዓለም ፍፃሜ የሆነ ያክል ተሰማኝ ። በዚህ አስተማማኝ ባንከር ውስጥ ሆኜ ግን ሃሳቤና ስጋቴ ሁሉ አየር ላይ ሆነው ወደ ታች ስለሚተኩሱት በራሪዎች ነበር ። “ እነማን ይሆኑ ” ? ብዬ በረዥሙ እየተነፈስኩ እራሴን ጠየቅሁ ። ብርድ ቢጤ መላው አካላቴን ሲያንዘፈዝፈው ይሰማኛል ። ፓይለቶቹን በሙሉ አውቃቸዋለሁ ። ከሁሉም ጋር ከወዳጅነት የዘለለ ቅርበትና አብሮ መኖር አለኝ ።  በዚህ ቀውጢ ሰዓት በራሴው ወንድሞች ዒላማ ውስጥ መሆኔ እየተሰማኝ ቢሆንም መጥፎ ሃሳብ ወደ አዕምሮዬ ከቶ አልመጣም ፤ እንዲያውም ስለነሱ ደህንነት አብልጬ ተጨነቅሁ ። የአንድ እናት ልጆችን እርስ በርሳችን እያፋጁ ያሉትን ረገምኩ ።

 

መከላከያ ሚንስትሩና የአየር ኃይሉ አዛዥ ወደ አሉበት አካባቢ ቀረብ በማለት የሚያደርጉትን የሬዲዮ መልዕክት ልውውጦችን ማዳመጥ ጀመርኩ ። በትግሪኛ ቋንቋ መሆኑ ቢቸግረኝም እንዲሁ በደፈናው ግን ስለምን እንደሚያወሩ መረዳት ቀላል ነበር ። ከጥቂት የሬድዮ ንግግሮች በኋላ …. “አንዲት ሚግ -21 አውሮፕላን ተመታለች  ….. እየጨሰችም ነው ” የሚል መልዕክት ከወዲያኛው ጫፍ በሬዲዮው ውስጥ ጮክ ብሎ ተሰማ ። መድሃኒያለም ! እያልኩ ደጋግሜ ማማተቤን አስታውሳለሁ …. መላውን ሰውነቴን ነዘረኝ ፤ እንደፈራሁት ! አልኩኝ በውስጤ ።

ኰማንደሩም በመቻኰል ….” ወደቀች ! ” ? በማለት ጮክ ብሎ በጉጉት ጠየቀ ።

ከወዲያኛውም ጫፍ  “ አዎ ወድቃለች ” የሚል ተስፋ አስቆራጭ መልስ ሰጠ ።

ባንከሩ ውስጥ እኔ ካለሁበት በተቃራኒና ተማሪዎቹ ወደ አሉበት ጥግ የደስታና የጭብጨባ ድምፅ በከፍተኛው አስተጋባ ። የሚገርም ዓለም ነው ።  “ የአንዱ ቤት ሃዘን .. ለአንዱ ቤት ደስታ ነው ” አልኩኝ  አንገቴን ደፍቼ እያዘንኩ ። ሆዴ በእጅጉ ታወከብኝ …. አፌ በአንድ አፍታ ደረቀ ። ….. “ እግዚያብሄር ሆይ መጥፎ ነገር አታሰማኝ ! ” አልኩ በጉልህ በሚሰማ ድምፅ  ።

ኰማንደሩ በደስታ በሚመስል ፈጠን ያለ ድምፅ  …. “ ፓይለቱስ ? ”  ብሎ ጠየቀ ።

“ ፓይለቱ ዘሏል ! ”  የሚል ድምፅ ከወዲያኛው ጫፍ ከሬዲዮው ውስጥ አስተጋባ ። ቀጥሎም “ ወታደሮች ወደ ዘለለበት ስፍራ ተንቀሳቅሰዋል ”  አለ ።

…… “ የፈጣሪ ያለህ ! ” ….  አሁን እራሴን ማረጋጋት እንዳለብኝ ተገነዘብኩ ….. ነገሮች በቅፅበት እየተቀያየሩ ናቸው ።   ማን ሊሆን ይችላል ?  ብዬም ወደ ጥልቅ ሃሳብ ውስጥ ገባሁ ።

የማቃቸውን አራት የሚግ-21 በራሪዎችን ቆጠርኩ ። በእርግጥ ተፈትቶ ይሆናል ብዬ እንጂ አንዱ እስር ቤት እንዳለ አውቃለሁ ። ( እድለ ቢሱ መ/አ ደመላሽ መኰንን )

ለነገሩ እስር ቤቱማ የአገር ባለውለታ የሆኑትን የአየር ኃይል አባሎችን አጭቆ ይዞ የለ ? የነጠረ ችሎታ ፣ ለዘመናት የካበተ ልምድ ፣ በርካታ አዛውንት በራሪዎች በከንቱ ከተከረቸሙ 7ኛ አመታቸውን እያከበሩ አይደል ። በሃሳቤ የተሰደዱትንና በየሜዳው የተበተኑትን የአየር ኃይሉ ባለሙያተኞችን አስታወስኩ ። … “ያልታደለችና ባለቤት አልባ የሆነች አገር ”…. አልኩኝ ለራሴ ።

ከሁሉም ያስደነገጠኝ ነገር … ከቆጠርኳቸው አራት በራሪዎች ውስጥ ሶስቱ በወታደራዊው ስርዓት ዘመን ከሻብያ ጋር በጀግንነትና በቁርጠኝነት ሲዋጉ ( ዛሬ ያ ሁሉ መስዋዕትነት በዜሮ ቢባዛም ) በአማፅያኑ ተይዘው መጨረሻ ላይ ሻብያ ድል ሲያገኝ በምህረት የተለቀቁ ነበሩ ።

“ አምላኬ እባክህ ከሶስቱ መካከልስ አንዳቸውም አይሁኑ ” ….. ብዬ ፀለይኩ ። ከሶስቱ ውጪ ደግሞ አንዱ ወጣት በራሪ ነው …. የጊምቢ ልጅ ( ም/መ/አ እንደገና ታደሰ ) ።  በጣም ትሁትና ጨዋ ሰው ።

 

አንድ ጊዜ ባህር ዳር ከዚሁ ከጊምቢው ልጅ ም/መ/ እንደገና ጋር ከተማ ተያይዘን ወጣን ። የገበያ ዕለት በመሆኑ ብዙ ሰውና ግርግር በዝቷል ። አብዛኛው ሰው ጐስቋላና በየሚዲያው አማራ እየተባለው ከሚነገረው ፕሮፖጋንዳ ጋር በፍፁም አይጣጣምም ። መ/አ እንደገና የሚያየውና ስለ አማራ ነፍጠኛ ሲሰማ የነበረው ( ነፍጠኛ እየተባሉ የሚጠሩት አኗኗራቸው የተለየ ነው ብሎ ያምን ስለነበር ) አልገናኝ ብሎት ስሜን ጠርቶ … “ ወዳጄ ክንዴ ነፍጠኞቹ የታሉ … ? ” ብሎ ሲጠይቀኝ እነዚህ ሜዳው ላይ ፈሰው የምታያቸው ናቸው ብዬ በፈገግታ መለስኩለት ።  “ እነዚህ የማያቸውማ ከጊምቢ የባሱ ጐስቋላ ሰዎችን ብቻ ነው ….. ” ይልቅ ነፍጠኞቹን አሳየኝ ያለኝን አስታውሼ ነፍጠኛ ስለሚባሉት ምስኪን ህዝቦች ውስጤ አዘነ ።

ስለዚህ ቀደም ሲል ከሻብያ በምህረት የተለቀቁት በራሪዎች ክፉው ዕጣ የእነሱ እንዳይሆን የተመኘሁት በተቃራኒው ወጣቱ በራሪ ላይ ያሟረትኩበት መስሎኝ ተፀፀትኩ ።

እንዲሁ በሃሳብ እየባከንኩ ባለሁበት ቅፅበት ነበር “ ….. በራሪው በቁጥጥር ስር ውሏል ! ”  …. የሚል ጨካኝ መልዕክት በሬዲዮው ውስጥ የተሰማው ። ፈፅሞ የማላውቀው በራሪ እንዲሆን ተመኘሁ ። ለነገሩ የማላውቀው በራሪ ከየት ይመጣል ? ከማርስ …. ? እንዴት ሊሆን ይችላል ?

ኰማንደሩ ፈጠን ብሎ “  … ለመሆኑ ማን የሚባል ነው ? ” ብሎ ጠየቀ ። የልቤ ምት ተቀየረብኝ ….  ጆሬዬንና አፌን እንደከፈትኩ ከሬዲዮው ውስጥ የሚመጣውን መልዕክት ለማዳመጥ ጓጓሁ “ …. ያው ልማደኛው ነው …. ” አለ የሬዲዮው መልዕክት ። “ ….. ማ ! በዛብህ ?  …. ” …… “  በትክክል አውቀሀዋል …. ” አለ ያ ሟርተኝ ድምፅ በድጋሜ ።

ክፉኛ ደነገጥኩ …..  ። ኰ/ል በዛብህ ጴጥሮስ በእንደዚህ አይነት የልጆች የዕቃ ዕቃ ጨዋታ በሚመስል ፋይዳ ቢስ ጦርነት ውስጥ መሰለፍ እንደሌለበት ልቤ ያምናል ። ኰ/ል በዛብህ ለአገሪቷም ሆነ ለአየር ኃይሉ ትልቅ ኃብት ነው ። የአስተማሪዎች አስተማሪ ፣ እጅግ ልምድ ያለው አዛዥ መኰንን ነው ። የእርሱ አደጋ ላይ መውደቅ በእጅጉ ይጐዳል ። በእንደዚህ ዓይነት ኤርትራን በምታክል ገና ዳዴ በምትል አዲስ አገር ጋር በሚደረግ የጥጋበኞች ልፊያ ውስጥ ቢበዛ ወጣት በራሪዎችን ማሰለፍ ሲቻል ኰ/ል በዛብህን ከነሙሉ ልምዱና አዛዥነቱ በከንቱ ማጣት ምንኛ ያለመታደል እንደሆነ አሰብኩ ። ቀደም ሲል ስምንት ዓመታትን ሙሉ በሻብያ እስር ቤት አሳልፏል ። ከሻብያ ድል በኋላም በምህረት ተለቆ ወደ ቤተሰቦቹ በሰላም የተቀላቀለ ነው ። እግዚአብሄርም ዳግመኛ ባርኰት ልጅ ወልዶ ባላቤቱን እርጥብ አራስ ልጅ እንዳስታቀፈ ሳይመለስ የቀረውን ያልታደለውን ኰ/ል በዛብህን እንደገና አሰብኩ ? ለመሆኑ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ማነው ? የስንቱ ዜጋ ቤት ተዘግቶ ፣ ወጣት በራሪዎችን ሜዳ ላይ በትኖ ፣ አዛውንቶችን በየማጐሪያው እያሸ ያለ ጨካኝና ዘረኛ ስርዓት ። ፋይዳ ቢስ ጦርነት …. ከንቱ መስዋዕትነት …. ያልታደለችና እርግማን ያለባት አገር ።  አንጀቴ ተቃጠለ ።

 

በዛብህ ጴጥሮስ ሎዳሞ አልኩኝ አንገቴን እንደደፋሁ ። ምን ዓይነት ፍርጃ ነው ?  …. ጌታ እየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ “ አባት ሆይ … ፈቃድህ ቢሆን ይህቺ ፅዋ ከእኔ ትለፍ ” የሚለውን የመፅሃፍ ቅዱስ ትምህርት አሰብኩ ። ከምር ብርታትንና ፅናትን ተመኘሁለት ። የባለቤቱንና የልጆቹን ሃዘን አሰብኩ ። መጥፎ ቀን … መጥፎ ቦታ … መጥፎ አጋጣሚ ።

ቀና ስል ከአዛዡ ጋር ዓይን ለዓይን ግጥም አልን ። ለራሱ እየቀረበለት የነበረውን ቡና አስተናጋጇ ለእኔ እንድትሰጠኝ በጥቅሻ ወደ እኔ እያመለከተ ነበር ። አሁን ለእኔ ሁሉ ነገር መራራ ነው ፤ ነገር ግን የደረቀ አፌን ማርጠቢያ ባዶውን ቡና መጠጣት ጀመርኩ ። ሃሳቤን ግን ከኰ/ል በዛብህ ላይ ሊያነሳልኝ አልቻለም ። አሁን ምን ያስብ ይሆን አልኩኝ በውስጤ ።

በዛብህና የኤርትራው አየር ኃይል አዛዥ ኰማንደር ሃ/ፅዮን ሃድጐ ያላቸውን ጓደኝነትና ቀረቤታ አውቀዋለሁ ። አንድ ጊዜ አራት የኤርትራ አየር ኃይል የበረራ ተማሪዎች በኢትዮጵያ አየር ኃይል ስኰላር ሺፕ አግኝተው ወይም ለበረራ ስልጠና ዕድል አግኝተው ይመጣሉ ። ታድያ ተማሪዎቹን ደብረ ዘይት በረራ ት/ቤት አምጥቶ ያስረከበው አዛዡ ኰማንደር ሃ/ፅዮን ነበር ። ከስራ መውጫ ሰዓት እንደደረሰ ሃ/ፅዮን ለምን አንድ ላይ እራት አንበላም በሚል እዚያ ላለነው የበረራ አስተማሪዎች ግብዣ አቀረበ ። በሃሳቡም ተስማምተን ደ/ዘ ወደሚገኘው ሆራ ራስ ሆቴል አቀናን ። ኰ/ል በዛብህን ጨምሮ ስምንት የምንሆን የበረራ አስተማሪዎች ነበርን ። ሃ/ፂዮን ስለ ኰ/ል በዛብህ ተናግሮ አይጠግብም ። “ በጣም የምወደውና የማከብረው አስተማሪዬና ጓደኛዬ እያለ ያሞግሰዋል ። እኔ ጋ አስመራ ቢመጣ እንደዚህ ህውሃቶች እንዳደረጉት ተራ አስተማሪ አይደለም የማደርገው ። የአስተማሪዎች አስተማሪ በማድረግ ዘውድ ጭኜ በክብር የማስቀምጠው ሰው ነበር ” አለ ።

ታድያ አሁን በተፈጠረው አጋጣሚ ኰ/ል በዛብህን ምን ይለው ይሆን ? ። እንዴት ወንድምና ወንድም ፣ ጓደኛና ጓደኛ እንዲህ የመረረ የመጠፋፋትና የመተላለቅ ግጭት ውስጥ ይገባሉ ? በዚህስ ማን ተጠቃሚ ይሆናል ?  አድካሚ የሆኑ ከንቱ ሃሳቦችን ሳወጣና ሳወርድ ሰዓቱ መርፈዱንም ልብ ሳልል ቀረሁ ። ኰ/ል ታደሰ በሃሳብ ጭልጥ ብዬ ከሄድኩበት ቀስቅሶ እንሂድ ባይለኝ ኖሮ ምን ያክል እዚያው ፈዝዤ እንደምቆይ መገመት ይቸግረኛል ።

ከኰ/ል ታደሰ ጋር ተያይዘን እንደወጣን “ ቢ ዜድን አስበሉት አይደል ? ” አለኝ ኰ/ል ታደሰ ። (BZ ማለት ኰ/ል በዛብህ በረራ ምድብ ውስጥ የሚጠራበት የአህፅሮት ስሙ ነው) ። ለኰ/ል ታደሰ ምንም መልስ አልሰጠሁትም …. አሁንም ከራሴው የውስጥ ሃሳብ ጋር ሙግት ላይ ነኝ ። የኤርትራው አየር ኃይል ምክትል አዛዥን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ስታፎች የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባል በመሆናቸው ፣ በተጨማሪም እየተፈጠረ ያለው ግጭት በአንድ ወቅት አንድ ላይ በነበሩ ሰዎች መካከል በመሆኑ የሃዘኔታ መንፈስ ይታይባቸው ።

ከኰ/ል ታደሰ ጋር በዝምታ ተጉዘን ከቤቴ በራፍ ላይ ስደርስ ማ/ቴክ አርጃ ፔራን አገኘሁት ። (ማ/ቴክ አርጃ የታወቀ የአርማሜንት ስፔሽያሊስት ኢትዮጵያዊ ነው ፤ ነፍሱን በገነት ያኑራት አሁን በህይወት የለም) ።

ማ/ቴክ አርጃ ወደ ቴሌ ሄዶ ደ/ዘ ቤተሰቡ ጋ ስልክ ደውሎ እየተመለሰ ነበር ። ቤተሰብ እንዴት ነው ? ደ/ዘይትስ እንዴት ናት ? ብዬ ጠየቅኩት ። “ ቤተሰብ ደህና ነው …. ደ/ዘ ግን አንድ የሻብያ ሚግ አውሮፕላን መትተን ጥለናል ተብሎ እየተጨፈረ ነው ” አለኝ ። ሚግ ጥለናል የሚለው ጉዳይ ብዙም ትኩረቴን አልሳበም ፤ ምክንያቱም እዚህ ኤርትራ አየር ኃይል ውስጥ እየሰራ ያለ አንድም ሚግ የሚባል አውሮፕላን እንደሌላቸው አውቃለሁና ። ይልቅ የገረመኝ ከአንድ ቀን በፊት ዓርብ ዕለት እዚህ አስመራ ከተማ ውስጥ የመኪና ጥሩንባ እየተነፋ ቅልጥ ያለ ጭፈራና ደስታ ነበር ። ምክንያቱ ደግሞ ሁለት የኢትዮጵያ ሚግ-23 መትተን ጥለናል የሚል ነበር ። ሁለቱም ወገኖች አውሮፕላን መትተው እንደ ጣሉና ህዝባቸውም በደስታ እንዲጨፍር እያደረጉት ነው ። ሁኔታው ሁሉ ናላዬን እያዞረው በመሆኑ ሁሉንም ትቼ ወደ እቤቴ ገባሁና አልጋዬ ላይ ጋደም ብዬ እየተከሰተ ያለውን ትርምስ በአይነ ህሊናዬ እየመረመርኩ እንቅልፍ ጣለኝ ።

 

በነጋታው እሁድ ዕለት ማልጄ በመነሳት ኰ/ል ታደሰ በያዛት መኪና አስመራ አየር ኃይል ቤዝ ቀደም ብለን ደረስን ። የዘመቻ ጊዚያዊ ፅ/ቤት ከምድር በታች የተሰራው ባንከር ውስጥ ስለነበር ወደዚያው አመራን ። ዙርያውን መሬት ላይ በተደረደረው ፍራሽና ምንጣፍ ላይ ቁጥሩ በዛ ያለ ሰው ተኝቷል ። አዛዡ ኰ/ር ሃ/ፅዮን ወደ አለበት ጠጋ ብለን ሰላምታ አቀረብንለት ። አስከትዬም ውስጤን እያስጨነቀኝ ያደረውን ጉዳይ ኰ/ል በዛብህን አግኝቶት እንደሆነ ዓይን ዓይኑን እያየሁ ጠየኩት ። ሃ/ፅዮንም ቁጭትና ንዴት በተቀላቀለበት አንደበት “ አግኝቼዋለሁ …. የማይረባ ሰው ነው  ” አለኝ ። የኰማንደሩን ንዴት እንዳልገባኝ አልፌ “ ግን ደህና ነው ? ምን አለህ ለመሆኑ ” ? አልኩት ። “ በጣም ነው የተሳሳትከው …. እንዴት ትንሽ እንኳ አታስብም …. እንዴትስ በወያኔ ተልከህ ይህንን ትሰራለህ ” እንዳለውና  በዛብህም በበኩሉ “ አንተስ ብትሆን የሰራሀው ጥሩ ስራ ነው እንዴ ? አገር ጨርሰሃል እኰ ? ምን የተረፈህ ሰው አለ ? ብዙ ሰው ተጐድቷል ? አውሮፕላኖች ከጥቅም ውጪ ናቸው .. አንድም የተረፈ በራሪ የለም … ሁለታችን ብቻ ነን የተረፍነው … (እሱንና እንደገናን ማለቱ ነበር) ” እንዳለው ነገረኝ ።  ኰ/ር ሃ/ፅዮንም እየሳቀ መ/አ እንደገና (የኰ/ል በዛብህ ዊንግ ማን የነበረ ወይንም ከኰ/ል በዛብህ ጋር አስመራን ለመደብደብ አብሮት የበረረ ወጣት በራሪ) ትናንት ኰ/ል በዛብህ ተመትቶ ሲወድቅ ብቻውን ወደ መቀሌ ቤዝ ሲመለስ ወያኔዎች የሻብያ ሚግ መስሏቸው በሚሳኤል መትተው ጣሉት …. በጃንጥላ ወደ ምድር ከወረደም በኋላ የሻብያ በራሪ ያዝን ብለው ተሰብስበው ቀጠቀጡት …..  ” እያለ በጅልነታቸው ተገርሞ ጮክ ብሎ ይስቃል ። ማ/ቴክ አርጃ ፔራ ማታ ስለ ደ/ዘ የደስታ ጭፈራ የነገረኝን አስታወስኩና አሁን ኰማንደሩ ከሚነግረኝ አስቂኝ ሁኔታ ጋር አገጣጥሜ እኔም ሳልወድ በግድ ምን ያክል አየር ኃይላችን ወደ ኋላ እየወረደ እንዳለ እያሰብኩ ፈገግ አልኩኝ ። አዛዡ እንዲያውም “ ዘግይቶ የደረሰን ዜና ” በሚል በቴሌቪዥናቸውም አቅርበውታል ብሎ አከለልኝ ።

 

ኰማንደር ሃ/ፅዮን ከኰ/ል በዛብህ ጋር የተነጋገረውንና የሰማውን በመዘርዘር  .. አንድ ሚግ አውሮፕላን ለግዳጅ ወደ አስመራ እያቀና እያለ ባልታወቀ እክል በራሪው በጃንጥላ መውረዱንና አውሮፕላኑ መከስከሱን  የአብራሪው ስም ጨምሮ ነገረን ። 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከህውሃት በኩል 2 ሚግ-21 እና 1 ሚግ-23 አውሮፕላኖች መውደማቸውን ፣ በአየር በተደረገ ጥቃት ከህውሃት በኩል ሁሉም በራሪዎች መቁሰላቸውንና ከአሁን በኋላ አንድም በራሪ ግዳጅ ለመፈፀም የሚችል ያለመኖሩን ሲገልፅ በኩራትና በእርካታ ነበር ። አሁንም እያመነታሁ ቆይቼ “ አንተስ እንዴት ት/ቤት ትደበድባለህ ” ? ብዬ ጠየቅኩት ። ኰ/ር ሃ/ፂዮን ሲመልስም “ እናንተ ሰዎች መቼ እንደምትነቁ አይገባኝም ። እነዚህን ሰዎች (ህውሃት) አስከ አሁን አላወቃችኋቸውም ማለት ነው ። የመጨረሻ ውሸታሞች ናቸው ። የፖለቲካ ትርፍ የሚያስገኝ ከመሰላቸው ምንም ነገር ከማድረግና ከመናገር ወደ ኋላ አይሉም …. ማመዛዘን ፈፅሞ አልፈጠረባቸውም ። የሚያወሩትን ሁሉ ከሰማህማ አብደው ያሳብዱሃል ። እነሱ ያሰቡት የጦር ጀት የላቸውም እንደፈለግን እንቀጠቅጣቸዋለን ብለው ነበር ። እድሜ ለጆቤ ። ጆቤ አዛዥ መሆኑና ያንን አየር ኃይል እንዳልነበረ በማድረጉ ባለውለታችን ነው ። ከሁሉም በላይ የሚገርመኝ ግን እነ በዛብህ በጆቤ የመታዘዛቸው ጉዳይ ነው ። አዛዡ ታዛዥ …. ታዛዡ ደግሞ አዛዥ የሆነባት አገር ። አይነ ስውር አይን ያለውን እንደመምራት ማለት ነው ” አለኝ ። ቀጥሎም የኢትዮጵያ አየር ኃይልን መበተን በጣም እቃወም ነበር ። አምርሬም አወግዝ ነበር ። ያለውን ዕምቅ ኃይል አውቀዋለሁና ። አሁን ግን እንኳንም አፈረሱልን ። እንኳንም በተኑልን ። ባይበተኑ ኖሮ ምን ይውጠን ነበር ? …. አፈር ከድሜ ያስገቡን ነበር ። ከታሰሩትና ከተሰደዱት ግማሽ ያክሉ እንኳ ቢኖሩ ኖሮ ማን ያድነን ነበር ? ሳይደግስ አይጣላም አይደለም የሚባለው ?

….. በአንድ ወቅት እንደውም የታሰሩት ምንም አላጠፉም ልቀቋቸው … ቢደበድቡም የደበደቡት ሻብያን ነው …. ስለዚህ ፍቷቸውና ለእኛ ስጡን ብያቼው ነበር ። እነሱን ባገኝ ደግሞ ለመላው አፍሪቃ የሚሆን የአቪዬሽን ሴንተር እከፍት ነበር ። እነሱም ያልፍላቸዋል …. ሙያቸውም ሜዳ ላይ እንዳልባሌ አይባክንም ነበር ። ስለዚህ ጆቤ ባለውለታዬ ነው ። በዛብህ ከነጆቤ ቤት ርካሽ ሆነ እንጂ .. የከበረ ዕንቁ ማለት ነው ። ነብይ በአገሩ አይከበርም …. ጆቤ ትልቅ ባለውለታችን ነው ….. የዕውር መሪ …. ” ብሎ ቃላቶቹን ሳይጨርስ ድንገት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ መጡና ጨዋታችን በዚሁ አበቃ ። እኛም ከኰማንደሩ ጋር የነበረንን ጥልቅ ስሜትን ያዘለ ጭጭውውት በዚሁ ቋጭተን ከኰ/ል ታደሰ ጋ ወደ አንድ ጥግ ተጠግተን የራሳችንን ጨዋታ ጀመርን ።

3 ሚግ አውሮፕላኖች ሃያ አራት ሰዓት ሳይሞላ ወደቀ የሚባለው ዕውነት ነው ? ብዬ ኰ/ል ታደሰን ጠየቅኩት ። ኰ/ል ታደሰም ሲመልስ “ትልቁ ኪሳራ ሚግ አይደለም ..  በዛብህ ነው ” አለኝ ። … በመቀጠልም “ መንግስቱ ካሳ የወደቀ ጊዜ አስታውሳለሁ .. አየር ኃይል ጨላማ የዋጠው ያክል ሃዘን ወሮት ነበር  አለኝ ። “ ጥሩ በራሪ ስታጣ ጉዳቱ የቤተሰቡ አይደለም …. የአየር ኃይሉ ነው … የተቋሙ ነው ” በማለት ከልቡ በተቆጨ ስሜት ተናገረ ። “ የሚገርምህ ግን አሁን ጆቤ ጉዳቱን የሚረዳውም አይመስለኝ አለኝ ኰ/ል ታደሰ እንደተቆጨ ።  ” በማስከተለም “ ለመሆኑ የእነ በዛብህ ግዳጅ ምን ለማጥፋት ነው ? ዒላማቸውስ ምንድነው ? ይሄ ሁሉ መስዋዕትነትስ አስፈላጊ ነው ? ”  ። በአጠቃላይ የአውሮፕላኖቹም ሆነ የበዛብህ ለሁሉም ኪሳራ ተጠያቂው ጆቤ ነው ።  በሙያው የተቀመጠ አዛዥ ቢሆን ኖሮ በዚህ ሁሉ ኪሳራ ምክንያት ወዲያው ስራውን መልቀቅ ነበረበት ። አለኝ ኰ/ል ታደሰ አምርሮ ።

ይህ የኰ/ል ታደሰ አባባል ለአስርተ ዓመታት ከአዕሮዬ አልወጣም ። እውነት ነው ደግሞ … ጆቤ በሙያው ሳይሆን በፖለቲካ አቋሙ ነው አዛዥ ሆኖ የተመደበው ። አመራሩም ሆነ ውሳኔው ሁሉ ሙያዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው ። እንዲያውም ጆቤ ዘረኛ እንጂ የሰከነ ፖለቲከኛም ስለመሆኑ እጠራጠራለሁ ። ዘር በመሰረቱ የዜግነት እኩልነትን ያቃውሳል … መጨረሻውም ጥሩ አይሆንም ። ጆቤ በዘር በሽታ የተለከፈ ስለመሆኑ በስሩ በረዳትነት ያስቀመጣቸውን ሰዎች ለአፍታ በአይነ ህሊናዬ ቃኘኋቸው ዙርያውን የራሱን ቋንቋ ተናጋሪዎችን ብቻ ኰልኩሏል ። ይህ አደገኛ ዘረኝነት እንጂ ሌላ ስያሜ ሊሰጠው አይችልም ።

 

ያ ትውስታዬ ዛሬ 18 ዓመታትን አስቆጥሯል ። አስመራ ያለሁበትን ሁኔታ የተገነዘቡ ጓደኞቼ ሊታደጉኝ ወሰኑ ። በጉብኝት አሁን ወደምኖርበት ሰሜን አሜሪካ እንድመጣ ከፍተኛ እገዛ አደረጉልኝ ። ከመጣሁም በኋላ በአገር ቤት ተለይቻቸው እሩቅ ለእሩቅ እንኖር የነበሩትን ባለቤቴንና ልጄን አምጥቼ በሰላም እኖራለሁ ።

ኰ/ል በዛብህ የከፈለው ዋጋ ለአገሩ እንደሆነ አምናለሁ ። ቢያንስ ግን ክብር መስጠት አስፈላጊ ነበር ። በአንድ ወቅት አሉ የተባሉት አርቲስቶች ተሰብስበው አየር ኃይሉን እንዲጐበኙ ተደረገ ። አስጐብኚው ሻለቃም  “ የሞተና የበሰበሰ አየር ኃይል ነው የተረከብነው ” እያለ ደጋግሞ ይገልፃል ። ይህ አባባል እነ በዛብህን ሁለተኛ እንደ መግደል ይሰማኛል ። እንዲህ አይነቱን ሁኔታ አርቲስት ሜሮን ጌትነት “ ጠበል ጓሮ አግኝተው ቁርበት ነከሩበት ” በማለት ትቀኝበታለች ። ይህንን ታሪካዊ ስህተትና ዘለፋ ከአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጪ ማንም ደፍሮ ቆሞ ሊሞግት ድፍረት ማጣቱ ቢያሳዝነኝም አርቲስት ታማኝ በየነ ረዥም እድሜ ይስጠውና እንባ እየተናነቀው ለቀድሞ የስራ አጋሮቹ እውነታውን በድፍረት አሳውቋል ። በዕለቱ አየር ኃይሉን እንዲጐበኙ የተጋበዙት አርቲስቶችም ይህንን እውነታ ሳይገነዘቡ ይቀራሉ የሚል እምነት የለኝም ። ቢያንስ እነ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ እነ ጀነራል ፋንታ በላይን ከነሙያቸውና ዝናቸው ያውቁዋቸዋል የሚል እምነት አለኝ ። ጥላቻውና ዘረኝነቱ  ግን ልኩን ማለፉን በቀላሉ ማየት ይቻላል ።

 

በቅርቡም ገቢው ለአየር ኃይል ቬተራን አሶሴሽን ይውላል የተባለው የአየር ኃይል ታሪክ መፅሃፍ (ስለ ቬትራን ማህበር ያለኝን ጥያቄ ላቆየውና) በአየር ኃይሎች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረትን ስቦ ሰንብቷል ። አንድም ቀን ስለተሰደዱት ፣ በችግር ስለሚቆሉት ፣ ስለ ታሰሩት ፣ በእስር ላይ ህይወታቸው ላለፈ ፣ በስደት ህይወታቸው ላለፈ ፣ ስለ ተበተኑት ባለሙያዎች ድምፃቸውን አሰምተው የማያውቁት ሁሉ ዛሬ ሽር ጉድ ሲሉ ይስተዋላሉ  ። ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ .. ይህ ሁሉ የአገር ሃብት የፈሰሰባቸው ባለሙያዎች በከንቱ ሲበተኑ አንድም ቀን ያላስታወሱት ፤ እንዲያውም ሞትና እድሜ ልክ የተፈረደባቸውን የአየር ኃይል አባላት የፍርድ ሰነድ በፊርማቸው ያፀደቁት ፕሬዝዳንት አሁን የአየር ኃይሉ ታሪክ መፅሃፍ ሲመረቅ የክብር እንግዳና ፈራሚ መሆናቸው በእጅጉ የሚያስተዛዝብና ያስደነገጠኝ ክስተት ነው ።

በሸራተን የፊት መስመር ላይ የተሰለፉት ከፍተኛ የአየር ኃይል መኰንኖች አስተማሪዎቻችንና አለቆቻችን ሆነው ሳለ ምንም እንዳልተፈፀመ ፣ ዘግናኙ የብቀላ ጅራፍ ፈፅሞ እንደተረሳና የአየር ኃይሉን ጉዳይ ከብሄራዊ ጉዳይነት ወደ ተራ የግል ጉዳይ ዝቅ ያደረጉት በሚመስል ዓይነት በፕሬዝዳንቱ አማካኝነት የፖለቲካ ስሌት መጫወታቸው ታሪክ በትዝብት የሚመለከተው እንደሆነ ይሰማኛል ።  በመጨረሻም ለዚህ መፅሃፍ እውን መሆን ከመጀመሪያው ጀምሮ በቅንነት ጥረት ያደረጉትን ሁሉ ሳላመሰግን አላልፍም ።

 

ክንዴ ዳምጤ

 

The post ባክኖ የቀረ  አየር ኃይል – ክንዴ ዳምጤ – ሲያትል appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>