እየጎመዘዘኝ የሰማሁት ዜና ነው!!
ወጣቱ ፖለቲከኛ ዳዊት አስራደ የሚወዳቸውን ቤተሰቡንና ልጁን ትቶ ከሀገር መሰደዱ ተሰምቷል፡፡ ዳዊት ከ13ቱ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ እንዲሁም የብሄራዊ ምክር ቤት አባልና የአንድነትን የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድም ከሌሎች የፓርቲው አመራሮች ጋር በመሆን የነደፈ ሙሉ ማንነቱን ለሀገር ትግል የሰጠ ቁርጥ ኢትዮጵያዊ ልጅ ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም በአማራ ክልል ምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያለ በመኪና ተገጭቶ ለ6 ወራት ተኝቶ ከሞት ድኗል፡፡
በ97 ዓ.ም በቅንጅት ፓርቲ ውስጥ ፖለቲካዊ ተሳትፎውን የጀመረው ዳዊት አስራደ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መስራች አባልም ነበር፡፡ ዳዊት በፓርቲው የተለያዩ ሓላፊነቶች ላይ የሰራ ሲሆን ለአብነትም
– በወጣቶች የትምህርትና ስልጠና ዘረፍ
– የብሄራዊ ምክር ቤት ቋሚ አባል
– የብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና ዋና ጸሀፊ
– የኢኪኖሚ ጉዳዮች ሃላፊና በተለያዩ የአድሆክ ኮሚቴዎች ውስጥ በሀላፊነትና በአባልነት ሰርቷል፡፡
የአንድነትን የ5 አመት እቅድና ስትራቴጂ ከነደፉት ሰዎች መካከልም ዳዊት አለበት፡፡ በ2002 ምርጫ አንድነት መድረክን ወክሎ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በምዕራብ ጎጃም ዞን በፍኖተ ሰላም ከተማ ተወዳዳሪ ነበር፡፡ ሆኖም በ2007 የአንድነት ፓርቲ በምርጮ ቦርድ ለነ ትግስቱ አወል መሰጠቱን በመቃወም ከፓርቲው ሙሉ በሙሉ ቢገለልም በገጠመው ተደጋጋሚ እስርና እንግልት ምክንያት ሀገሩን ትቶ ሂዷል፡፡
መንግስት በሽብር ቡድኖች በሊቢያ የተቀጠፉ ኢትዮጵያውያንን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ ‹‹ቪዲዮ ቀርጻሃል›› በሚል ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በፖሊስ ተይዞ ቄራ ፖሊስ ጣቢያ ገባ፡፡ ሰልፉን በሞባይል በቀረጸበት የ25000.00 ብር ዋስ እንዲለቀቅ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአቃቂ ምድብ ችሎት ወሰነ፡፡ ሆኖም አቃቢ ህግ ወዲያውኑ በ14 የተደረገውን ሰልፍ ለማወክ በ13 ከ200-300 የሚሆኑ ወጣቶችን አደራጅተሃል የሚል ተጨማሪ ክስ መሰረተበት፡፡ ይህን ክስ ደግሞ በ6000.00 ብር መያዣ ይፈታ ሲባል በእለቱ ስብሰባው ላይ ችግር ፈጥረሃል የሚል ክስ ታከለለት፡፡ ለዚህ ደግሞ 5000.00 ብር አስይዝ ተባለ፡፡
ሚያዚያ 14 በቄራ፣ ከሚያዚያ 15- 21 በፔፕሲ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስሮ ቆየ፡፡ ሚዚያ 21 ቀን ባስያዘው ገንዘብ ተፈቶ ሳይሰደድ ሲቀር ይምሰላል በግንቦት 3 ቀን ከፔፕሲ ፖሊስ ጣቢያ ተደወለለት፡፡ ያስያዝከውን ንብረት ውሰድ ነጻ ነህ አሉት፡፡ ሲሄድ ግን ታሰረ፡፡ ሶስት ቀን ፔፕሲ ፖሊስ ጣቢያ ከቆየ በኋላ ወደ ማእከላዊ ተወሰደ፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዘያት እስከ ሰኔ 5 ቀን በማእከላዊ እስር ላይ ቆይቶ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአቃቂ ምድብ ችሎት በእለቱ እንዲፈታ ወሰነ፡፡ እስካሁን ያዝያዘው 36000.00 ያልተመለሰለት ሲሆን ሰኔ 19 ቀን ፍርድ ቤት እንዲገኘ ሌላ ቀጠሮ ተሰጠው፡፡
ዳዊት በሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች ባሉ መርማሪ ፖሊሶች ከኢህአዴግ ጋር እንዲሰራ ግብዣ ቀርቦለት ነበር፡፡
ዳዊት አስራደ በተለያዩ ባንኮች በተለያየ የሃላፊነት ቦታ ላይ ሰርቷል፡፡ አገር ጥሎ በወጣበት ወቅትም በህብረት ባንክ ዋና መስሪያ ቤት የአንድ ክፍል ዋና ሓላፊ እና ጥሩ ደመዝ ተከፋይም ነበር፡፡ ዳዊት የአንድ ልጅ አባትና ባለትዳር ነው፡፡
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስርዓቱ እግር ተወርች አስሮ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ በዚህ ሳምንት አገሩን ጥሎ መጥፋቱ ተገልጧል፡፡
(ዛሬ የሰማሁት መራር ዜና ነው- የዳዊት አስራደ ስደት፡፡ ይህን ቆራጥ ሰላማዊ የዲሞክራሲ ታጋይ በቅርበት አውቀዋለሁ፡፡ የሚወደውን ልጁን፣ የሚያፈቅራትን ሚስቱን እና ሀገሩን ትቶ መሰደዱን ስሰማ ከልቤ አነባሁ፡፡ )
– See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/8067#sthash.3jr38q3y.dpuf
The post ቆራጡ የዲሞክራሲ ታጋይ ዳዊት አስራደ ከሀገር ተሰደደ!! appeared first on Zehabesha Amharic.