Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የልኂቃኖቻችን ማንነትና ያደረሱብን ኪሳራ!!!

$
0
0

ከአምሳሉ ገ/ኪዳን (ሰዓሊ)
Amsalu በጥንት ዘመን ላይ ነው የምግብ ጉዳይ የሰማይ አእዋፍንና የምድር እንስሳትን ለሞት ሽረት ጦርነት ዳርጎ ነበር፡፡ ለጦርነቱ መንስኤ የሆነባቸው ምክንያት እግዚአብሔር እንደ መና ያለ በጣም የሚጣፍጥና ተስማሚ መንጅ የሚባል ምግብ ለሁለቱም ወገኖች ባጠቃላይ ለፍጥረቱ ሁሉ በየዕለቱ ከሰማይ ያወርድላቸው ነበር፡፡ ታዲያ እላቹህ አንድ ወቅት ላይ መተሳሰቡ ጠፋና ሆዳምነት ሰፈነና የምድር እንስሳቱ አእዋፉን ሳያስቡ ድርሻቸውን ሳይተውላቸው ሁሉንም መንጅ ጠራርገው እየበሉባቸው አእዋፉ እጅግ በመቸገራቸው እራሳቸውን የምድር ታላላቅ እንስሳቱን ግልገሎችና እንደ እባብ አይጥ የመሳሰሉትን አነስተኛ እንስሳት እየሞጨለፉ በመውሰድ መብላት ጀመሩ፡፡ እንስሳቱ ደነገጡ በገዛ እጃቸው የማይቻል ባለጋራ እንደፈጠሩ ጠላት እንዳፈሩ ያኔ ገባቸው፡፡ ጥፋት እንደሠሩ ስሕተት እንደፈጸሙ አምነው ይቅርታ መበጠየቅ ከእንግዲህ የአእዋፉን ድርሻ እንደማይነኩባቸው ቃል በመግባት እርቅ እንዳያወርዱ በአራዊቱ ትዕቢትና እብሪት አሻፈረኝ ባይነት በእርቅ እናውርድ ጥያቄው ላይ መስማማት ባለመቻላቸው ምክንያት የእርቁ ጉዳይ ውድቅ ሆነና እጅግ ዘግናኙ የተራዘመ ጦርነት ተኪያሔደ፡፡ ከሁለቱም ወገን በርካታ ዝርያዎች ዝርያቸው ጨርሶ እስኪጠፉ ድረስ እጅግ ዘግናኝና አሰቃቂ ጦርነት ለተራዘመ ጊዜ ተደረገ፡፡ ማናቸውም ግን አሸናፊ ሆነው መውጣት አልቻሉም፡፡ የሁለቱም ቡድኖች ኃይላቸው ሲዳከም በራሳቸው ጊዜ ጦርነቱን እስከተውበት ጊዜ ድረስ ያንን ጦርነት ያደረጉ እንጅ መጨረሻ ላይ የደረሱበት ስምምነት ወይም እርቅ ኖሮ አልነበረም ጦርነቱን ያቆሙት፡፡

ፈጣሪም የሰጣቸውን ጸጋ በፍቅር በስምምነት በመተሳሰብ ሊጠቀሙበት ሊመገቡት ባለመቻላቸውና ለዘግናኙ እልቂት መንስኤም ስላደረጉት ወዲያውኑ ነበር መንጁን ከሰማይ ማውረዱን ያቆመው፡፡ ጦርነቱ ያንን ያህል ዘግናኝና አሰቃቂ ሊያደርገው የቻለው ከሰማይ የሚወርደው መንጅ ስለቆመና አንደኛው ሌላኛውን ለምግብነት ከመጠቀም አልፎ እዛው እርስ በርስም አንዱ ሌላውን ለምግብነት ፍጆታ የመጠቃቃት አዙሪት ውስጥም በመግባታቸውም ጭምር ምክንያት ነበር፡፡ እግዚአብሔር ምግባቸውን ያቆመባቸው እሱ የሚገኘው ከመሀከልም የሚኖረው በረከትን ረድኤትን ጸጋውምን የሚሰጠው ፍቅር ስምምነት መተሳሰብ ባለበት ቦታና ሁኔታ እንጅ መለያየት ጸብ ክርክር ፍጅት ራስ ወዳድነት ስግብግብነት ባለበት ቦታና ሁኔታ እንዳልሆነ እንዲረዱ እንዲገነዘቡ ተገንዝበውም ሰላም ፍቅር ስምምነት መተሳሰብ እንዲያሰፍኑ ለማስተማር ለማሳወቅ ነበር፡፡ እነሱ ግን የሠሩት ስሕተት ምን ያህል ከባድ ማስተዋል አርቆ ማሰብ የጎደለው እንደሆነ በርካታ ዝርያዎቻቸው እስኪጠፉ ድረስ ከመተላለቅና ለምግብነት እራስበራሳቸው እስኪባሉ ድረስ የተጎዱበት እንጅ ምንም ያላተረፉበት እንደሆነ መረዳት ተስኗቸው እርቁን ስምምነቱን ሳያወርዱ ሳይፈጥሩ እንደቀሩ ቀሩ፡፡ ይሄው ይህ ሁኔታም እስከአሁን ድረስ ዘልቆ ለምግብ ፍጆታነት ሲባል እርስ በእርስ ይበላላሉ፡፡

ጦርነቱ ለከፋ መተላለቅ የዳረጋቸው ምክንያት ከሰማይ ይወርድላቸው የነበረው ምግባቸው በመቆሙ እርስ በራሳቸው ለምግብ ፍጆታነት የመጠቀም ግዴታ ውስጥ ከመግባታቸው በተጨማሪ ያ አስከፊ ጦርነት በዚያ መልኩ ተጠናቆ አስከፊ ውድመት ለመከሰቱ አንድ ሌላ ጠንቀኛ ምክንያት ነበር፡፡ እሱም ያ የተራዘመ ጦርነት በሚደረግበት ወቅት የኃይል ሚዛኑን ዕያየች ወደሚያደላው እየተሰለፈች እንስሳቱ ያሸነፉ ሲመስላት እንስሳ ነኝ፤ እእዋፉ ያሸነፉ ሲመስላት ደግሞ ወፍ ነኝ የምትል አንዲት ፍጥረት ነበረች፡፡ የሌሊት ወፍ ትባላለች፡፡ የሌሊት ወፍ ከወገቧ በላይ አይጥ ከወገቧ በታች ደግሞ ወፍ ናት፡፡ ይህች ወፍ ጦርነቱ እንደዚያ ዓይነት ውድመት ለማድረሱ ከፍተኛ ድርሻ ነበራት፡፡ እንዴት መሰላቹህ፡- አንድ ጊዜ ከአእዋፉ ሌላ ጊዜ ከእንስሳቱ በምትሆንበት ወቅት የአንደኛውን ቡድን የጦር አሰላለፍና የውጊያ ስልት (ስትራቴጂ) አቅድ ለሌላኛው እያቀበለች ነበር ጦርነቱ አሸናፊ ሳይኖረው ተራዝሞ በመኪያሔድ እንዲያ ዓይነት ውድመት ልታደርስ የቻለችው፡፡ በመጨረሻ ላይ ግን መጽሐፉም እንደሚል “የማይታወቅ የተሰወረ የማይገለጥ የተከደነ ነገር የለምና” ሁለቱም ወገኖች የየሽንፈታቸውን ምክንያት በሚያጣሩበት በሚገመግሙበት ምሥጢራቸውን ማን አሳልፎ እንደሰጠ እንዳቀበለ በሚመረምሩበት ጊዜ የሌሊት ወፍ ሆና አገኟት፡፡ ሁለቱም ሞት ፈረዱባትና የሌሊት ወፎችን ማግኘት የቻሉትን ያህል ገደሉ፡፡ ሊያገኟቸው ያልቻሏቸውንና ያመለጡትን የሌሊት ወፍዘሮች ደግሞ የሁለቱም ወገኖት አረጋዊያን በየባሕላቸውና እምነታቸው የእርግማን መዓት አወረዱባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የሌሊት ወፍ ከሁለቱም ወገኖች ውጭ የተገለለች ስደተኛ የተነጠለች ሆና ጨለማ ለብሳ ጠቁራ የወፍ ሠራዊት በማይበርበት በማይኖርበት ሰዓት ሌሊት ሌሊት በራሪና ቀን ቀን ደግሞ በዋሻዎችና ዛፎች ላይ ተዘቅዝቃ ተንጠልጣይ ሆና ቀረች ይባላል፡፡

የዚህችን የሌሊት ወፍ ግብር ስታዩ ምን ተምሳሌትነት ያለው ይመስላቹሀል? የእሷን ማንነት የተላበሱ በርካታ ሰዎች በመሃላችን እንዳሉ ልብ አላላቹህም? አልታዩዋቹህም? እስኪ ዘወር ዘወር በሉና አማትሩ ብዙ ሳትቆዩ ከፍ ከፍ ያለ ቦታ የያዙ ከባለጸጋ እስከ ዳኛ ከምሁር እስከ የሀገር ሽማግሌ ከሃይማኖት መሪ እስከ የጎሳ መሪ ከሁሉም ዓይነት ጎራ ጎላ ጎላ ብለው የሚታዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች (ልኂቃን) በጭንቅላታቹህ ተግተልትለው ይመጡላቹሀል፡፡ በተለይ ይሄ ዘመን በርካታ የሌሊት ወፎችን ፈጥሯል፡፡ ብዙ አሉ ከወገባቸው በላይ ወያኔ ከወገባቸው በታች ሕዝብ ሆነው አንዱንም የሆኑ ሳይመስሉ በሕዝብ ሕይዎት ድራማ (ትውንተ ኩነት) የሚሠሩ የሚቀልዱ፣ ለወያኔ ምርኩዝ ድጋፍ እስትንፋስ በመሆን የሕዝብን የመከራ ዘመን የሚያራዝሙ፣ በሕዝብና በወያኔ መሀከል በሚደረገው ፍልሚያ የኃይል ሚዛኑን ዕያዩ ወያኔ ያየለ ሲመስላቸው ከወያኔ ጋር የሚለጠፉ ወያኔን የሚያገለግሉ ሕዝብ ያየለ ሲመስላቸው ደግሞ በአለብላቢት ምላሳቸው የሕዝቡን ዜማ የሚያቀነቅኑና “ካንተ ጋር እኮ ነን! ያንተ ደጋፊ እኮ ነን!” ለማለት ጥረት የሚያደርጉ፤ በዚህም የሌሊት ወፋዊ ማንነታቸውና ግብራቸው በሕዝብና በሀገር ላይ የሚደርሰውን ጉዳት የከፋና የከበደ የሚያደርጉ፤ ከየማኅበራዊ አገልግሎቱ ኃላፊነትና ከየሙያ ዘርፉ በርካታ የሌሊት ወፎች አሉ፡፡ በዚህ ርካሽ ሰብእናቸው የጎደፈ የተመረዘ ሥራቸውን ዘወትር በየብዙኃን መገናኛው ተዘግቦና ተጽፎ ታገኙታላቹህ ሕዝብ በሚሰባሰብበት መድረኮች ሁሉ እራሳቸውን በአካል ሲቀባጥሩ ታገኟቸዋላቹህ፡፡

እነኝህ ወገኖች እውነት ከየትኛው ወገን እንዳለች አጥተውት እንዳይመስላቹህ እንዲህ የሚሆኑት፡፡ ነገር ግን በተለያዬ ርካሽና ነውረኛ ምክንያቶቻቸው እውነቱ ካለው ከሕዝብ ጋር አያብሩም አስመሳዮችና አድር ባዮች ናቸው፡፡ እውነቱ ያለው የሕዝብ ወገን እንዳይቀየማቸውና ቀንቶት ያሸነፈ እንደሆነ ያኔ እንዳይገለሉ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ በግልጽ ሳይሆን በቅኔ በተረትና ምሳሌ በሚናገሩትና በሚጽፉት ነገር ቁስሉን እያከኩ እያስተዛዘኑ አንጀቱን ለመብላትና ከሱ ጋር እንደሆኑ እንዲያስብ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ የፈለገ ቢሆን ግን የሚናገሩትንና የሚጽፉትን ተረትና ምሳሌ እንዲሁም ቅኔ በጥሬው ያስቀምጡታል እንጅ በምንም ተአምር እንደ ብሒሉ ተርጉመው በማስረዳት መልእክቱን የተሟላ አያደርጉትም፡፡ ተረትና ምሳሌውን ቅኔውን ተርጉመው ነገሩን ሊሉ የፈለጉትን ግልጽ ካደረጉት በሁለት ቢላ መብላቱ ስለሚቀርባቸውና እውነት በመናገራቸው ዋጋ ስለሚያስከፍላቸው ይህ እንዲሆንባቸው ደግሞ ፈጽሞ ስለማይፈልጉ ነው የሚናገሩትንና የሚጽፉትን ተረትና ምሳሌ እንዲሁም ቅኔ እዛው ላይ ተርጉመው በመናገር እንደ ጌታ ወንጌል እንደ ሊቃውንቱ ምክር የተሟላ የማያደርጉት፡፡

የሚሉትን በተረትና ምሳሌ በቅኔ ካሉ በኋላ ደግሞ በስውር አንዳንዴም በይፋ በሥራዎቻቸው ያኛውን ወገን (ወያኔን) ያወድሳሉ ያበረታታሉ ያከብራሉ ያገለግላሉ ሕዝቡ የሚጠቃበትን መንገድ ይጠቁማሉ ይመክራሉ፡፡ እራሳቸውን የማኅበረሰባችን ልኂቃን እንደሆኑ የሚቆጥሩ የእነዚህ እኩያንና እርኩሳን ግለሰቦች ድርጊት በሀገርና በሕዝብ ጥቅም ላይ ያደረሱትና የሚያደርሱት ጉዳት በዚህ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህ ርካሽ ነውረኛና ጸያፍ ማንነታቸው ወይም ሰብእናቸው እንደ ብልጠት ዘመናዊነትና አስተዋይነት ተቆጥሮ እንደ መልካም ነገር በሕዝባችን ዘንድ በአርዓያነት በምሳሌነት እየተወሰደ የሕዝባችን ባሕርይ ወደ እነሱው በመለወጡና ለመብቱ ደፍሮና እራሱን ገልጦ እንዳይታገል የአስመሳይነትን የአድር ባይነትን ሰብእና ሞያየ ብሎ እንዲላበስ እያደረገው በመሆኑም ጉዳቱን ድርብ ድርብርብ እያደረገው ይገኛል፡፡ እነኝህ ግለሰቦች እንደያዙትና እንዳለባቸው ማኅበራዊ ኃላፊነት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በታማኝነትና በቁርጠኝነት አለመወጣት በአዎንታዊ ጎን ምሳሌ አርዓያ ሆነው አለመገኘትና በአሉታዊ ጎን ምሳሌ አርዓያ ሆነው መገኘት ሕዝባችን በራሱ ጉዳይ ላይ የማያገባው አድርጎ እንዲያስብ ራሱን እንዲያገል በውጤቱም የምናየውን ያህል እንዲጎዳ አድርገውታል እያደረጉትም ይገኛሉ፡፡

ይህ ጉዳይም በአጭሩ “የፖለቲካ ጉዳይ አያገባኝም!” በሚል ድንቁርና የተሞላበት ቃል ይገለጻል፡፡ እኔ ይሄንን የሚሉ ሰዎች ፖለቲካ ማለት ምን ማለት መስሎ እንደሚታያቸው አይገባኝም፡፡ አንድ ዜጋ የሀገሩ የራሱ ጉዳይ ካላገባው ማን ይሆን ታዲያ የሚያገባው? አንድ ዜጋ በራሱ እጣ ፋንታ ላይ የሚወስነው መንግሥቱ ማንነትና ምንነት ጉዳይ ካላገባው ማን ነው እሱ የሚያገባው? የሰው ልጅ እስከበላ እስከጠጣ በዚህች ምድር ላይ ስፍራ ይዞ እስከኖረ ጊዜ ድረስ ራሱን ከፖለቲካ ገለልተኛ ወይም ነጻ አድርጎ ማኖር ይችላል ወይ? በዚህ ጉዳይ ላይ እጅግ በጣም የሚገርመኝ ምን እንደሆነ ታውቃላቹህ? የከፍተኛ ትምህርት ተማርን የሚሉ ሰዎች ሳይቀር እንዲህ ማሰባቸው ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ይቅር እነሱ አጭር ወይም ረጅም ጥቁር ወይም ነጭ እንትን ወይም እንትን በመሆናቸው ብቻ አላግባብ ከሕግ ውጪ የዜግነት መብታቸው ከሆኑ ጥቅሞች መገለላቸው ወይም እንዳያገኙ መደረጋቸው መከልከላቸው ከዚያም አልፎ እንዲጠፉ መደረጋቸው እንዴት ነው የማያገባቸው? “ፖለቲካ አያገባኝም” ማለት እኮ በዜግነቴ በሀገሬ ላገኝ ሊከበርልኝ የሚገባኝ ጥቅም ሁሉ ማለትም የመኖር፣ ሠርቶ የማደር፣ የመማር፣ በእኩል የመስተናገድ፣ ሰብአዊ መብቱን ያለማጣት የመሳሰሉት መብቶች ቢነፈጉኝ፣ ቢጣሱብኝ፣ ብከለከል አይገደኝም አይሰማኝም አያገባኝም አይመለከተኝም አይጨንቀኝም ማለት እኮ ነው፡፡ ሰው ሆኖ ተፈጥሮ እነዚህን መሠረታዊ ጥቅሞቹንና መብቶቹን አጥቶ የማይከፋ ቅር የማይሰኝ የማይጎዳ እነኝህን ያጣቸውንም ጥቅምና መብቶቹን ለማስጠበቅ የማይፈልግ የማይጥር የማይመኝ ይኖራል? ካለ እሱ ሰው የሰው ልጅ ነኝ አይበል! ምን ነኝ እንደሚልም አላውቅለትም! “እንስሳ ነኝ” ይበል እንዳልልም እንስሳትም እራሳቸው እነኝህን መሠረታዊ መብቶችና ጥቅሞች አጥተው ዝም ጸጥ የሚሉ አይደሉምና ነው፡፡ ግዑዝ ነገር ድንጋይ እንዳልለውም ደግሞ ይተነፍሳል ይንቀሳቀሳል ይበላል ይጠጣል፡፡ ታዲያ ይሄንን ሰው ምን እንበለው?

እንዲህ የሚሉ ሰዎች ታግለው የፖለቲካ ምኅዳራቸውን ባስተካከሉ ሕዝቦች አይቀኑም ወይ? እንደነሱ ለመሆንስ አይመኙም ወይ? ከተመኙ ከፈለጉስ ይህ ስኬት በምን የሚመጣ መስሎ ነው የሚታሰባቸው? ፖለቲካ ሲባል ሌላ ምን መስሏቸው ነው? ግብግቡ ፍልሚያው ምን ሆነና? “የለም አይደለም እንዲህ መሆን የለበትም! ፍትሐዊ ሚዛናዊና ትክክል አይደለም ይስተካከል! በሚልና አይ! አይስተካከልም መብትህን እንጀራህን ነጥቄ ወደህ ሳይሆን ተገደህ ተረግጠህ እንደዜጋ ሳይሆን እንደ ባሪያ ትኖራታለህ!” በሚለው መሀከል አይደለም ወይ ግብግቡና ፍልሚያው? እነዚህ ሰዎች በዜግነታቸው በኢትዮጵያዊነታቸው የሀገሪቱንና የሕዝቧን ሁለንተናዊ ደኅንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው ጨርሶ አያውቁም ማለት ነው? የአንዲትን ሀገርና ደኅንነት ዜጋዋ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ማን ከየት መጥቶ ነው የሚያስጠብቅላት? ይህችን ሀገርና ሕዝቧን እራሳቸው ዜጎቿ ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ማን ከየት መጥቶ ነው ደህንነታቸውን የሚያስጠብቅላቸው? ይሄንን አለመረዳት ምን ይሉታል? ድንቁርና፣ አለቅጥ ከልክ በላይ የተጫነ ፍርሐት፣ የገዘፈ ራስ ወዳድነት፣ ሆዳምነት፣ አድር ባይነት፣ ኅሊና ቢስነት ወይስ ሌላ ምን?

በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ፖለቲካ የምሁራን ተሳትፎ ምን ያህል መንማና እንደሆነና የዳር ተመልካቾች እንደሆኑ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የተማሩ ፊደል የቆጠሩ ከባድ ማኅበራዊ ኃላፊነት የተጫነባቸው የተባሉ ሰዎች የፖለቲካን ምንነት በዚህ መልኩ ተረድተው ይሄንን ያህል ዘቅጠው እንዲህ ካሰቡ ያልተማረ በሚሉት ሕዝባችን ላይ በምንም ጉዳይ ላይ ቢሆን እንዴት ሆኖ ነው ጣት ለመጠቆም የሚያበቃ የሞራል (የቅስም) ብቃት አለን ብለው የሚስቡት? ወጣም ወረደ ፖለቲካ ማለት ሌላ ምንም ማለት ሳይሆን የዜጎች ሕይዎት የሀገር ደኅንነት ማለት ነው፡፡ አንድ ዜጋ እነኝህን ጉዳዮች አያገቡኝም ሊል አይችልም፡፡ ወይም ደግሞ የእነኝህ ነገሮች ምንነት የማይገቡኝ ደንቆሮ፣ ፈሪ፣ ራስ ወዳድ፣ አድር ባይ፣ ሆዳም፣ ኅሊና ቢስ ነኝ ብሎ በራሱ ላይ እየመሰከረ እንዲህ መሆኑን እያረጋገጠ ነው ማለት ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ “ከፖለቲካ ነጻ ወይም ገለልተኛ የሆነ” እየተባሉ የሚቋቋሙ ማኅበራት “ዋነኛ ሥራችን በቀጥታ ፖለቲካዊ አይደለም ማኅበራዊ ነው” ይበሉ እንጅ “ከፖለቲካ ነጻ ወይም ገለልተኛ” የሚባል ነገር ባለመኖሩና አማርኛው ፍጹም የተሳሳተና ቀደም ሲል ካወራነው መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም በመሆኑ ይሄንን ቃል ከመጠቀምና ሕዝብን ከማደንቆር ቢቆጠቡና ቢታረሙ መልካም ነው ለማለት እወዳለሁ፡፡ ማንኛውም ነገር ከፖለቲካ ነጻ ወይም ገለልተኛ በፍጹም ሊሆን አይችልም (physically impossible)፡፡ እውነት ከአንደኛው ወገን ላይ መሆኗ አይቀርምና ይሄ ከሆነ ዘንዳ ደግሞ የእውነት ደጋፊና ጠበቃ የመሆን ሞራላዊ (ቅስማዊ) ሃይማኖታዊም ግዴታ በሁሉም ሰው ላይ የተጣለ ነውና “ነጻ” ወይም “ገለልተኛ” የሚለው ቃል አያስኬድም ወይም ትክክል አይደለም፡፡ ምንጊዜም ቢሆን እውነት ከሕዝብ ጋር ናት፡፡ “ሕዝባዊ ወይም ማኅበራዊ ነን” የሚል ማኅበር የሕዝቡ የማኅበረሰቡ ደኅንነት ከምንም ጉዳይ በላይ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳትና ችግር የሚፈጥርበት ይህ ፖለቲካዊ ጉዳይ የማይመለከተው ሊሆን አይችልም አይገባምም፡፡ ማኅበራዊ ነው ብላቹህ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ስለ ሕዝባችንና ስለ ሀገራችን ደኅንነት ጉዳይ እኮ ማንሣታቹህ አይቀርም፡፡ ካነሣቹህ ደግሞ በቃ እኮ መሰላቹህ እንጅ ፖለቲካ ማለት እኮ እሱ ነው ሌላ አይደለም፡፡ በመሆኑም “ሕዝባዊ ወይም ማኅበራዊ ነን” ሲሉ “ከእውነት ጋር የቆምን ነን” እንዳሉ ያስቡ እንጅ “ከፖለቲካ ነጻ ወይም ገለልተኛ” እንዳሉ በማሰብ “አያገባንም” ሊሉ በምንም ተአምር አይገባም አይቻልምም፡፡ የቃሉ አጠቃቀም አስቀድሜ እንደገለጽኩት ማንም ሰው በዚህች ምድር እስካለ ጊዜ ድረስ ከፖለቲካ ነጻ ወይም ገለልተኛ መሆን ስለማይቻል የደነቆረና የተሳሳተ አገላለጽ በመሆኑ እንዲታረም ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

በመጨረሻም በእኩይ ነውረኛ ርካሽና ጠንቀኛ የማንነት ተግባሮቻቸው የመከራ ዘመናችንን ያራዘሙትን ጉዳታችንን ኪሳራዎቻችንን ያበራከቱብንን ያከበዱብንን እራሳቸውን እንደ የማኅበረሰባችን ልኂቃን (Elites) አድርገው የሚቆጥሩትን ከወገብ በላይ ወያኔ ከወገብ በታች ሕዝብ የሆኑ የሌሊት በራሪ የሌሊት ወፎቻችንን እረግሜ ልቋጭ፡- የዕውነት አምላክ ልዑል እግዚአብሔር እጣ ፋንታቹህን ዕድል ተርታቹህን መጨረሻቹህን እንደ የሌሊት ወፎቹ ያድርግባቹህ!!!

በአንጻሩ ደግሞ ሀገርን ከራስ በላይ ዐይታቹህ ሀገርን ከምንም ነገር አስቀድማቹህ መተኪያ የሌላት ነፍሳቹህን ሰጥታቹህላት ይህችን ጠብቃቹህ ያስረከባቹህንን ሀገር እንዳስረከባቹህን ጠብቀን ማስቀጠል ቢያቅተንምና ሀገር በየአቅጣጫው በሰሜን በምዕራብ በምሥራቅ ነገ ደግሞ በየት እንደሚቀጥል አናውቅም እንደቂጣ እየተሸራረፈች ስትሰጥ ስትሸጥ ጸጥ ብለን በማየት፤ ግን ምን እናድርግ? እናንተ እኮ! ነፍሳቹህን እስከመስጠት ቁርጠኛ ሆናቹህ መሥዋዕትነት ብትከፍሉ በዘመናቹህ ሀገር ወዳድ የሀገሩን ጉዳይ ፈጽሞ ለድርድር የማያቀርብ ከሀገራችንና ከሕዝቧ በላይ የሚያየው ምንም ነገር የሌለው ኢትዮጵያዊ መንግሥት ቢኖራቹህና ቢያዘምታቹህ ነው፡፡ እኛ እኮ! የተቸገርነውና አደራቹህንም ለመጠበቅ እንዳንችል ያደረገን ይህች ሀገር ዐይታው የማታውቀው ኢትዮጵያዊ ስሜት፣ ወኔ፣ የሀገር ፍቅር፣ ተቆርቋሪነት ቅንጣት እንኳ የሌለው ለሀገርና ለሕዝቧ ሳይሆን ለባዕዳንና ለጠላቶቻችን ታጥቀው ተግተው የሚሠሩ ከሀዲያን የእፉኝት ልጆች መንግሥት ሆን ብለው ተቀምጠውብን እንዴት ብለን በየት በኩል ማን አዝምቶን? ማን አስተባብሮን? ማን አስታጥቆን? ድንበራችንን ከጠላት እንከላከል? እንጠብቅ? እሱ ራሱ ጠላትና የጠላት ቅጥረኛ ሆኖብን?

“ድንበር የሚደፍር ሀገር የሚፃረር ጠላት መጥቶብሀል ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት!” ብሎ አውጆ ሀገራችንን ከጠላት እንድንጠብቅ ሊያስታጥቀን ሊያዘምተን ሊያስተባብረን የሚገባው መንግሥት ተብየ እሱ ራሱ ድንበር የሚያፈርስ መሬት የሚቆርስ ሀገር የሚያምስ አንድነታችንን የሚያፈራርስ በዘር በሃይማኖት እየከፋፈለ ሊያባላን ሴራ የሚጠነስስ ጉድጓዳችንን የሚምስ ጠላት ከጠላትም ጠላት ሲሆንብን እንዴትና በየት በኩል አደራቹህን እንጠብቅ? ችግራችን ይሄ መሆኑ ምንም እንኳን ከተጠያቂነት ባያድነንም የገጠመን ችግር እኮ እንኳን በሀገራችን በዓለማችን እንኳ አንድ መንግሥት በገዛ ሀገሩ ሲያደርገው ታይቶ የማይታወቅ በዐይነቱ የተለየና ትንግርት በመሆኑ እኮ ነው ነገሩን የባሰ አስቸጋሪ ያደረገው፡፡ ለማንኛውም ለውዲቷ ሀገራችን ነጻነትና ህልውና በአርበኝነት ከተጋደላቹህት ጀምሮ በጊዜና በቦታ ሳትወሰኑ መቸም የትም ለእውነት በመቆማቹህ እውነትን በመመስከራቹህ ልትከፍሉት የምትችሉት ዋጋ መሥዋዕትነት ሳያሳስባቹህ ሳያስጨንቃቹህ ሳያንበረክካቹህ ሰው የመሆንን ዋጋ በሚገባ ተረድታቹህ ሆድን፣ የግል ጥቅምን፣ ራስ ወዳድነትን፣ አድር ባይነት፣ ፍርሐትን አሸንፋቹህ ሥጋን ከነ ክፉ መሻቱ በመስቀል ለኅሊናቹህ ለእውነትና ለአምላክ ታላቅ ዋጋና ክብር በመስጠት ለዚህች ብርቅየ ሀገርና ለዚህ ውድ ሕዝብ ዋጋ መሥዋዕትነት የከፈላቹህ ዋኖቻችንን ጀግኖቻችንን ደግሞ ውኃ ሽቅብ አይፈስምና ምንም ብየ ልመርቃቹህ ባይቻለኝም ለከፈላቹህልን ዋጋና መሥዋዕትነት ላበረከታቹህልን ትሩፋት ሁሉ ልዑል እግዚአብሔር ይስጥልን!!! እጅግ እጅግ እጅግ እናመሰግናለን!!!

ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! እባክህን ለዚህች ብርቅ ሀገርና ውድ ሕዝቧ ልዕልና ነጻነት ደኅንነትና ህልውና ሲሉ መራር ዋጋ መሥዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖቻችን ዋኖቻችን ድካምና መሥዋዕትነት ከንቱ ሆኖ ይቀር ዘንድ አትፍቀድ? “የእሳት ልጅ አመድ” ሆነና ተረቱ ስንት ታሪክ የሠራ ሕዝብ ለስንቶች ስንት ያደረገ ስንት የሆነ ሕዝብ ጠላቶቻችን በምን በኩል እንዴት ሆነው ቢገቡብን ውጤታማ እንደሚሆኑ ተረድተው በደናቁርቱ በባንዶቹ በደካሞቹ ላይ ተጭነው በመግባታቸው ያ ታላቅ ሕዝብ ዛሬ ለራሱ እንኳን ሳይሆን ቀርቶ ለመፍረስ ገሐድ አደጋ በመጋለጡ ተጨነቅን ፍርሐትና ሥጋት እረፍት ነሳን፡፡ እውን ሥጋታችን ተግባራዊ ይሆናል? አንተን ከመበደላችን ከዐመፃ ሥራችን የተነሣ የጠላቶቻችን ጥረትና ምኞት ሠምሮ እውን ሀገራችን እንድትፈርስ ሕዝባችን እንዲጠፋ ትፈቅዳለህ?
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገብረ ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

The post የልኂቃኖቻችን ማንነትና ያደረሱብን ኪሳራ!!! appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>