Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሙታንን የከፋፈለው የህወሓት ‹‹ብሄርተኝነት››

$
0
0

hawzen
ከጌታቸው ሽፈራው

ጀርመን ውስጥ በነበረበት ወቅት ጠባብ ብሄርተኝነት ምን እንደሆነ በተግባር የተገነዘበው የሳይንሱ ሊቅ አልበርት አንስታይን ጠባብ ብሄርተኝነትን የሰው ልጅ አጥፊ በሽታ ነው ይለዋል፡፡ አውቁ ሳይንቲስት ይህን በሽታ በቀላሉ የማይድን፣ የሰውን መላ ሰውነት የሚያበላሽ እከክ አይነት ወረርሽኝ ጋር ያመስለዋል፡፡ የህወሓት በሽታም ይህ የኑክሊየር ፊዚክስ ቀመሩ ባለቤት የገለጸው ጠባብ ብሄርተኝነት ነው፡፡ ደርግ በትግራይ ጨምሮ በሁሉም የአገራችን ክፍሎች ህዝብ ጨፍጭፏል፡፡ ይህን ጭፍጨፋ በኢትዮጵያውያን ላይ የተደረገ በደል አድርጎ ከመቁጠር ይልቅ በብሄር አይን መንዝሮታል፡፡ እናም ሰኔ 15 ‹‹የትግራይ የሰማዕታት ቀን›› በሚል ለ26ኛ ጊዜ አክብሯል፡፡

እንግዲህ ትግራይ ውስጥ ደርግ የጨፈጨፋቸውን ኢትዮጵያውያን ከሞቱ በኋላም እንደ ኢትዮጵያውያን እንዳናስባቸው በቋንቋ መስመር ታጥረናል ማለት ነው፡፡ በመላው አገሪቱ ጭፍጨፋዎች ነበሩና ሌሎች ከ80 በላይ ‹‹ብሄሮች››ም የየራሳቸውን ሰዕማታት ቀን ሊያከብሩ መሆኑ ነው፡፡ ደርግ አሁን ትግራይ ተብሎ በተከለለው የኢትዮጵያ ክፍል ባደረገው ጭፍጨፋ አፋርኛ፣ አማርኛ፣ ኦሮምኛ….ሌሎችም ቋንቋ ተናጋሪዎች ለገበያ አሊያም በሌላ ምክንያት በአካባቢው በመገኘታቸው የጭፍጨፋው ሰለባ የሆኑት ነፍሳቸው የሰው ነፍስ አይደለም ማለት ነው፡፡

በተመሳሳይ በሌሎች አካባቢዎች በተደረጉ ጭፍጨፋዎች ትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን የጭፍጨፋው ሰለባ ሆነዋል፡፡ ሆኖም ህወሓት ሀውዜንም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች በተደረጉት ጭፍጨፋዎች ሰለባ የሆኑት ‹‹ትግሬዎች ብቻ ናቸው!›› ብሎ ለብቻው የሙት አመት እያከበረ ነው፡፡ በዚህም ትግራይ ውስጥ በደርግ የተጨፈጨፉ ሌላ ቋንቋ ተናገሪዎች ደመ ከልቦች ሆነዋል፡፡

ህወሓት ማንን ያስቀድማል?

አንድ ሀቀኛ ፓርቲ ከስልጣን ይልቅ ሊያስቀድመው የሚገባው ወክየዋለሁ የሚለውን ህዝብ ነው፡፡ ሆኖም አንዳንድ ፓርቲዎች በስም ወክለነዋል የሚሉትን ህዝብ እንዳስቀደሙ በማስመሰል ቅድሚያ የሚሰጡት ስልጣናቸውን ነው፡፡ ከዚህ ሲከፋ ደግሞ ስልጣናቸው በራሱ ወክየዋለሁ የሚሉትን ህዝብ ከመውደድ ይልቅ ሌላ ህዝብን በመጥላት ላይ ሊመሰረት ይችላል፡፡ አጠቃላይ የአገሪቱን ህዝብ የሚጠሉ ከሆነ ደግሞ የሚወዱት ስልጣንን ብቻ ይሆናል፡፡ የህወሓት ስልጣን የተመሰረተው ሌሎችን በመጥላት ላይ ነው፡፡ ህወሓት የትግራይን ህዝብ ቢወድ ኖሮ በጠባብ ብሄርተኝነት ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠል ባልጣረ ነበር፡፡ በመላ ኢትዮጵያ የሞቱትን ትግርኛ ተናጋሪዎች ሞት ረስቶ ክልሉ ውስጥ የሞቱትን የሚረሳበት አጋጣሚ አይፈጠርም ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅር ቢኖረው ደግሞ ትግራይ ውስጥ የተጨፈጨፉትን ኢትዮጵያውያን ከሰው ሳይቆጥር የእኔ ነው ያለውን ህዝብ ብቻ በቋንቋ ለይቶ ባላስታወሰ ነበር፡፡

ህወሓት ይህን ጥላቻን መሰረት ያደረገ ጉዞውን አርበኝነት ይለዋል፡፡ ስሙ እንኳ ይህን ለትግራይ ህዝብ አርነት የቆመ መሆኑን ያስረዳል፡፡ የፈረንሳ ቻረለስ ዲ ጎል ህወሓትን አይነት አካሄድ አርበኝነት ሳይሆን በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ጠባብ ብሄርተኝነት አድርጎ ይወስደዋል፡፡ እንደ ቻረለስ ዲ ጎል አርበኝነት ማለት የህዝብን ፍቅር ስታስቀድም የሚመመጣ ነው፡፡ በተቃራኒው ጠባብ ብሄርተኝነት ለራስህ ህዝብ ያለህን ፍቅር በመቅደሙ ሳይሆን ለሌሎች ህዝቦች ያለህን ጥላቻ ስታስቀድም የሚመጣ ክስተት ነው፡፡ ይህ የፈረንሳይ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ህወሓትን በስርዓት የገለጸው ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም ህወሓት ወክየዋለሁ የሚለውን የትግራይን ህዝብም አይደለም፡፡ ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይማ ዲ ጎል እንደሚለው ጥላቸው የከረረ ነው፡፡ በዚህ መሃል የቀረው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ስልጣን! ከሁሉም አስቀድመዋለሁ የሚለውን የትግራይ ህዝብም የስልጣን መጠቀሚያ ነው፡፡ ‹‹የትግራይ ሰማዕታ ቀን›› ብሎ ሲያውጅም ‹‹የሞትነው እኛ ነን፡፡ በመሆኑም ስልጣን ላይ መቆየት ያለብን እኛ ነን›› ብሎ ለስልጣን ምሽግ መቆፈሩ ነው፡፡
ኦስካር ስትራውስ የተባሉ ሌላ ሰውም እንደ ዲ ጎል ሁሉ ብሄርተኝነት አርበኝነት ሆኖ አያውቅም ይላሉ፡፡ ከብሄርተኝነት በእጅጉ የተሻለና ድንበርና ሌሎች መከለያዎች የማይገድቡት አርበኝነት አለ የሚሉት እኝህ ሰው አርበኝነትን የቋንቋም ሆነ ሌላ ድንበር ሊለየው አይገባም ባይ ናቸው፡፡ ይህ አርበኝነት ድንበር ሳይገድበው የሰው ልጅ ስልጣኔ የሰጠውን ተስፋ የሚያስቀጥለበት ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ድንበር የሚገድበው አርበኝነት ከዚህ በተቃራኒ የሰው ልጅን ስልጣኔ የሚያከስም እኩይነት ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ምሁራን እንደ ህወሓት ያሉትን የፖለቲካ ሀይሎች ላይ በተመሳሳይ የሚዘምቱ ናቸው፡፡

ለምሳሌ ያህል ቶርሰሪን ቬብለን ጠባብ ብሄርተኝነትን ሞራል ባጣ መንገድ የተወለደ እና ሰይጣናዊ በሆነ መንገድ የሚመለክ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ አስቀጥለውም ይህ መስረቱ እኩይ የሆነ አስተሳሰስ የሰው ልጅን ተቋማትና አጠቃላይ ኑሮ በአለመግባባትና በጭንቀት ከመወጠር አልቆመመም ሲሉ ኢትዮጵያ ያለችበትን አይነት ሁኔታ ቀድመው የተገነዘቡ ያስመስላቸዋል፡፡

በአገራችን ብሄር ‹‹ከሲቪል›› ተቋማት አልፎ ቤተ እምነት ውስጥ አለመግባባትና አለመተማመን እየፈጠረ ቀጥሏል፡፡ ቀበሌ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ ውስጥም ሳያዩ ያምናሉ በሚባሉት ኢትዮጵያውያን ላይ ‹‹ብሄር›› የልዩነት ምክንያት ሆኗል፡፡ ከአመታት በፊት ጳጳስ ከተቀናቃኞቻቸው ግብጽ ሲመጣ በፍቅር ይቀበሉ የነበሩት ኢትዮጵያውያን አሁን የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በ‹‹ብሄር›› አይን እንዲያዩ ተገድደዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ህወሓት ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ የድርጅቱ የቀድሞ ሊቀመንበር በመጽሃፋቸው እነ ስብሃት ነጋ ደብረ ዳሞን የመሳሰሉ ገዳማት ሳይቀሩ የህወሓትን አባላት አስርገው ሲያስገቡ መቆየታቸውንና በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ የሚሰራበት መሆኑን አምነዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም የእምነት፣ የቋንቋና ሌሎችም ሳይወስኗቸው ከሚገናኙባቸው ነገሮች አንዱ ሀዘን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን የሆነን ልዩ ማህበራዊ መሰረትና ተቋማት መስርተዋል፡፡ አሁን ግን ሟች በ‹‹ብሄር›› አጥር ታጥሯል፡፡ ሁሉም ‹‹ሟችህን በየ ቋንቋህ አስብ›› ተብሎ መከለል ተጀምሯል፡፡ ይህ እንግዲህ ቶርሰሪን ቬብለን መሰረቱ አሉታዊ መሆኑን የሚገልጹት ጠባብ ብሄርተኝነት እስከ ለቅሶና ቀብርም ወርዶ የኢትዮጵያውያንን ማህበራዊ ትስስርና ተቋማት ማንኮታኮቱን ነው የምንረዳው፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ ቀናት የሚከበሩት በአለም አቀፍ ደረጃ ነው፡፡ የሴቶች፣ የሰራተኞች፣ የጋዜጠኞች… ብቻ በርካታ ቀናት የሚታሰቡት በአለም አቀፍ ደረጃ ነው፡፡ ምክንያቱም ዘመኑ በአገር ብቻ የሚታጠርበት ባለመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ በርካታ ህዝቦች በሩዋንዳና በሌሎች አገራት የተፈጸሙን ጭፍጨፋዎች ያወግዛሉ፡፡ ጭፍጨፋን በተመለከተም አለማቀፍ ቀናት ይከበራሉ፡፡ አሁን በአገራችን እየተደረገ ያለው ግን ከአለም አቀፍም ወርዶ በ‹‹ብሄር›› ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያውያን ቋንቋውን ካልተናገሩ በስተቀር የተጨፈጨፉ ወንድሞቻቸውን ቀን ለማስብ እንዳይችሉ የ‹‹ብሄር›› አጥር ታጥሮባቸዋል፡፡

The post ሙታንን የከፋፈለው የህወሓት ‹‹ብሄርተኝነት›› appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>