Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

መድረክ በኦሮሚያ 2፣ በደቡብ 1 እንዲሁም በትግራይ 1 አባላቶቹ መገደላቸውን ይፋ አደረገ

$
0
0

በኦሮሚያ 2 አባላት ተገድለዋል፤ 640 ታስረዋል ብሏል

(አዲስ አድማስ) መድረክ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞንና በትግራይ ክልል ሁለት አባላቱ በ3 ቀናት ልዩነት እንደተገደሉበት አስታወቀ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በትግራይ ክልል የመድረክ አባል የነበረው አቶ ታደሰ አብርሃ እንደተገደለበት በመግለጫው ያስታወቀ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ደግሞ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን አቶ ብርሃኒ ኤረቦ የተባሉ የመድረኩ አባል ተገድለው ትናንት ጠዋት አስከሬናቸው መገኘቱን የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በምዕራብ ትግራይ ዞን የአረና/መድረክ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው በዘንድሮው ምርጫ በዞኑ የምርጫውን ሥራ በማደራጀት፣ በመቀስቀስና ታዛቢዎችን በመመደብ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ የቆዩት አቶ ታደሰ አብርሃ አርአያ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተደብድበው መገደላቸውን መድረክ አስታውቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ ለጊዜው ማንነታቸው በግልጽ ተለይቶ ያልታወቁ 3 ሰዎች ወደ ቤታቸው በመግባት በተፈጸመባቸው አሰቃቂ ድብደባ ሕይወታቸውን ያጡት አቶ ታደሰ፤ በምርጫው ቅስቀሳ ወቅትም በኢህአዴግ ካድሬዎችና ታጣቂዎች ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል ያለው መድረክ፤ “ምርጫውሲያልፍ አንድ በአንድ እንለቅማችኋለን፤ የትም አታመልጡንም” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያም ደርሶባቸው ነበር ብሏል፡፡
beyene_petros
በዞኑ በሚገኘው ማይካድራ ከተማ ነዋሪ የነበሩት አቶ ታደሰ አብርሃ፤ ድብደባው እንደተፈጸመባቸው ጉዳዩን የሰሙት አቶ መሰለ ገ/ሚካኤል /በዞኑ የአረና/መድረክ ተወካይ/ ለጉዳተኛው የሕክምና ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ለማስተባበርና ወንጀለኞችንም ተከታትሎ ለማስያዝ ከቤታቸው በሞተር ብስክሌት ወጥተው ሲንቀሳቀሱ ፖሊሶች ይዘው “መንጃ ፈቃድ በእጅህ አልያዝክም” በሚል ሰበብ ሞተር ብስክሌታቸውን ወስደው ፖሊስ ጣቢያ በማስገባታቸው፣ለተጎጂው ከመድረሳቸው በፊት ሕይወታቸው ማለፉን መድረክ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የ48 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ታደሰ አብርሃ፤ ባለትዳርና የአንድ ሴት ልጅ አባት የነበሩ ሲሆን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም በነጋታው ረቡዕ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች በተገኙበት ተፈጽሟል ብሏል፡፡በሌላ በኩል በትግራይ ክልል በምርጫው ሰሞን ዕጩዎች በሚቀርቡበት ወቅት የታሰሩ 17 የአረና/መድረክ አባላት አሁንም በመቀሌ ወሕኒ ቤት ታስረው እንደሚገኙ መድረክ አስታውቋል፡፡ በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎችም በአባላቱና በምርጫው ወቅት በታዛቢነት ያገለገሉ ግለሰቦች ላይ የተለያዩ መከራዎችና እንግልቶች እየተፈፀሙ መሆኑን የፓርቲው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ በእሳት ቤት ንብረትን ማቀጠልን ጨምሮ ከቤት ማፈናቀልና እስራት በአባላትና ደጋፊዎች ላይ እየተፈፀመ ነው ያለው መድረኩ፤ “ተቃዋሚዎችን መርጣችኋል ወይም ህዝቡ እንዲመርጣቸው ቀስቅሳችኋል” በሚል ግለሰቦችን ማሰቃየቱና ማዋከቡ ተጠናክሮ እንደቀጠለ አስታውቋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎችም ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ እስካሁን 640 አባላትና ደጋፊዎቹ መታሰራቸውን የጠቀሰው መድረኩ ሁለት አባላት ሲገደሉ 66 መደብደባቸውን፣ 7 አባላቱም በጥይት ተመተው እንደቆሰሉ መድረክ በመግለጫው አመልክቷል፡፡ በመድረኩ አባላት ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ፣ እንግልትና ስቃይ በተመለከተ በዝርዝር ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ ማቅረባቸውን የጠቆሙት የፓርቲው ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ “በአባላቶቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ግድያ የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም እየሆነብን ችግር ላይ ነው ያለነው” ብለዋል፡፡

መንግስት በጉዳዩ ላይ ሊያነጋግራቸው እንደሚገባ ያሳሰቡት ፕ/ር በየነ፤ መድረኩ በአባላቱ ላይ እየደረሱ ነው ላለው በደል ድምፁን ከማሰማት ወደኋላ እንደማይል ገልፀዋል፡፡ አክለውም ከትናንት በስቲያ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን የመድረክ አባል የሆነና በምርጫው ጉልህ
ተሣትፎ የነበረው አቶ ብርሃኑ ኤረቦ፣ ፖሊሶች ከቤት አስገድደው ከወሰዱት በኋላ ወንዝ ውስጥ
ሞቶ አስከሬኑ አርብ ጠዋት እንደተገኘ ፕ/ር በየነ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

The post መድረክ በኦሮሚያ 2፣ በደቡብ 1 እንዲሁም በትግራይ 1 አባላቶቹ መገደላቸውን ይፋ አደረገ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>