Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በዚህ ታላቅ ወር እጆቻችን ወደላይ ዘርግተን የተበዳይ ድምፃችንን እናሰማ!!! –ድምጻችን ይሰማ!

$
0
0

አርብ ሰኔ 12/2007
voice of peopleረመዳን የድል ወር ነው፡፡ ለየትኛውም ዓይነት ድል የመጀመሪያው እና ዋነኛው እርምጃ የሆነውን በራስ ላይ ድል የመቀዳጀትን ስኬት እውን ለማድረግ ደግሞ ከረመዳን የተሻለ አጋጣሚ የለም፡፡ ረመዳን የኢብሊስን መታሰር ተከትሎ የሰውን ልጅ ወደታች ከሚጎትተው ስጋዊ ሰሜት ጋር የሚያደርገው ትግል ቀላል የሚሆንበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ነፍስ ተገርታ፣ ባህሪዋ ተስተካክሎ በፅድቅ ስራዎች እንድትመጥቅ ከፍተኛ ልፋትና ትግል ይጠይቃል፤ መልካም ነገሮች ባጠቃላይ ያለልፋት አይገኙምና፡፡ ነፍስ በሰከነ እምነትና አመለካከት የበለፀገች፣ በመልካም ስብእና ላይ የረጋች ስትሆን የሰው ልጅ በየትኛውም የህይወት መስክ ስኬታማ እንዳይሆን እንቅፋት የሚሆኑበትን ነገሮች በቀላሉ የምትሻገርበት ጉልበት ይኖራታል፡፡


ረመዳን ማህበረሰባዊ ተጨባጭን ለመቀየር በሚደረግ ትግል ወሳኝ የሆኑትን ትዕግስት፣ ጽናት እና መስዋእትነትን ለነፍሳችን የምናስታጥቅበትን ምህዳር አመቻችቷል፡፡ ተጨባጩን ለመቀየር በሚደረገው ትግል ማሰብ የማይሰለቸው አዕምሮ፣ ድካም የማይሰማው ጉልበት፣ የማይበርድ ወኔና ስሜትን የተላበሰ ስብዕና ለመገንባት፣ በአስቸጋሪ መሰናክሎች የተሞላውን የጀነት ጉዞ በስኬታማነት ለማጠናቀቅ የሚያስችለውን የኢማን ስንቅ የምንሸምትበት ከአዛኙ ጌታችን የተቸረ መስተንግዶ ነው፡፡ እንግዲህ የወሮች ቁንጮ የሆነውና ታላላቅ ችሮታዎችን እና ትሩፋቶችን ጠቅልሎ የያዘው ረመዳን ከእነሙሉ ስጦታው በአላህ ፀጋዎች ደምቆ ልቦቻችንን በብርሀኑ ሊሞላን እነሆ አንድ ብሎ ጀምሯል፡፡ ከትሩፋቶቹ አንዱ ደግሞ ዱዓ ተቀባይነት በሚያገኝባቸው በርካታ ወቅቶች የታጨቀ መሆኑ ነው፡፡


ዱዓ ሰፊ የኸይር በርና በቀላሉ ወደ ስኬት መዳረሻ አቋራጭ መንገድ ነው፡፡ ዱዓ የነገሮች ባለቤትነት በእጁ ለሆነው አምላክ የሚደረግ መተናነስ፣ ደካማ ባሪያዎቹ መሆናችንን በተግባር የምናሳይበት የአምልኮ አስኳል ነው፡፡ በያዝነው የተከበረ ወር አላህን (ሱ.ወ) እያረፈብን ያለውን የበደል አለንጋ እንዲያስወግድልን፣ ችግሮቻችንን ቀርፎ ቃል የገባልንን ድል እንዲያወርድልን ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ልንማጸነው ይገባል፡፡ የምድር ተረኛ ገዢዎች ውክልናችንን እና ፊርማችንን በሰጠናቸው ወኪሎቻችን ላይ እኩይ ውሳኔ ለመስጠት የያዙት ቀጠሮ ሳምንት ብቻ የቀረው በመሆኑ በዛሬዋ የመጀመሪያ የረመዳን ጁሙዓ የምናደርጋት ዱዓ ትልቅ ዋጋ ይኖራታል፡፡ መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) በጁሙዓ ዱዓ ተቀባይነት የሚያገኝባት ወቅት መኖሯን ነግረውናል፡፡ ከረመዳን ጋር ሲደመር ደግሞ መቅቡልነቱ ይጨምራል፡፡ በመሆኑም ከፍትሐዊው አምላካችን አላህ (ሱ.ወ) ፍትሕን በመፈለግ እጆቻችን ወደላይ ዘርግተን የተበዳይ ድምፃችንን ልናሰማ ይገባል፡፡ ለአላህ ያለንን ክብርና መተናነስ፣ ኃይልም ብልሀትም የእርሱ ብቻ መሆኑን በዱዓችን ልንገልጽ ይገባል፡፡ አላህ ዱዓችንን ይቀበለን!


‹‹ባሮቼም ከእኔ በጠየቁህ ጊዜ (እንዲህ በላቸው)፡- እኔ ቅርብ ነኝ፡፡ የለማኝን ጸሎት በለመነኝ ጊዜ እቀበለዋለሁ፡፡ ስለዚህ ለኔ ይታዘዙ፤ በኔም ይመኑ፤ እነሱ ሊመሩ ይከጀላልና፡፡›› (ሱረቱል በቀራህ 2፡186)
‹‹‹አላህ በቂዬ ነው፡፡ በእርሱ ላይ ተመኪዎች ይመካሉ› በል፡፡››
(ሱረቱ ዙመር 38፡39)
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

The post በዚህ ታላቅ ወር እጆቻችን ወደላይ ዘርግተን የተበዳይ ድምፃችንን እናሰማ!!! – ድምጻችን ይሰማ! appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>