(ዘ-ሐበሻ) ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከሦስት ዐሥርት ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ በሚሌኒየሙ መባቻ ወደ አገራቸው ተመልሰው ላለፉት ሰባት ዓመታት በማስተማር ሥራ ላይ ቆይተዋል፡፡ ምሁሩ በዋናነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ቢኾኑም በሕግ ፋክልቲ፣ በሴንተር ፎር ሂዩማን ራይትስ፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ በአምስት ኪሎ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋክልቲ፣ በቴአትሪካል አርትስና በያሬድ የሙዚቃ ት/ቤትም አስተምረዋል፡፡ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በተጠቀሱት የትምህርት መስኮች በተለያየ ጊዜ ሲያስተምሩ ቢቆዩም ከጠየቁት የዓመት ዕረፍት(sabbatical leave)ን እንደምክንያት በማድረግ ለሃገራቸውን ለወገናቸው ያላቸው ተቆርቋሪነት በስር ዓቱ አልወደድ በማለቱ ከዩኒቨርስቲው መሰናበታቸው ይታወቃል::
አሁን ደግሞ ግንቦት 29 በተጻፈ ደብዳቤ ዩኒቨርሲቲው የሰጣቸውን ቤት በ15 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ የሚያሳስብ ደብዳቤ ደርሷቸዋል:: (ደብዳቤውን ይመልከቱና ከታች የዶ/ር ዳኛቸውን ምላሽ ያንብቡ)
ዶ/ር ዳኛቸዉ አሰፋ ለዩኒቨርሲቲው ቤቶች አስተዳደር ያስገቡት ደብዳቤ፣
ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም
ለ፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቤቶች አስተዳደር መምሪያ
አዲስ አበባ
ከ፦ ዶ/ር ዳኛቸዉ አሰፋ
ጉዳዩ፦ ቤት የማስረከብን ሁኔታ ይመለከታል፡፡
ከሁሉ አስቀድሞ “ከመስከረም 2002 ዓ.ም ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዉ እንደማንኛዉም የዬኒቨርሲቲዉ መምህራን ቤት ሰጥተዎት” የሚለዉ ገለፃ በከፊል እዉነት ሲሆን የገባሁበት ቀንና ዓመተምህረት የናንተዉ መስሪያ ቤት ባዘጋጀዉ ሰነድ ላይ ተመዝግቦ እያለ፤ “ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ” የዩኒቨርሲቲዉ ቤት ዉስጥ ትኖር ነበር ብላችሁ የተሳሳተ የግዜ አሃዝ ማስቀመጣችሁ ግምታዊና ሙያዉ የሚጠይቀዉን አሰራር እንደማታሟሉ ይጠቁማል፡፡
ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ.ም በቁጥር ቤአ/259/2007 በተጻፈ ደብዳቤ የምኖርበትን ቤት እስከ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ማለትም በ15 ቀን ዉስጥ እንዳስረክብ የጠበቀ ማሳሰቢያ ደርሶኛል፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማደረግ እንደምክንያት የቀረበዉ ዩኒቨርሲቲዉ በ15/01/2015 በተመራ ደብዳቤ “በጡረታ የተገለልህ” በመሆንህ በሚል ሰበብ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ደብዳቤ በጣም አስገራሚ እና ከእውነት የራቀ የሚያደርገዉ ከላይ በተጠቀሰዉ ቀንም ሆነ ይህንን ደብዳቤ እስካረቀቅሁበት ጊዜ ድረስ ለእኔም ሆነ ለትምህርት ክፍሉ ኃላፊ እንዲሁም ለማህበራዊ ሳይንስ ኮላጅ ዲን ጡረታ መዉጣቴን እና ኮንትራቴ እንዳማይራዘም የሚያበስር ደብዳቤ እንዳልተፃፈ እና እንዳልደረሰ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ እዉነታዉ ይህ ሆኖ እያለ ተፃፈ የተባለዉ ደብዳቤ ለእኔ ለባለጉዳዩና ኮንትራቴ እንዲራዘምልኝ በአጽንኦት ለጠየቁልኝ የትምህርት ክፍልና ለማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ሳይደርስ ለእናንተ አስተዳደር (ቤቶች አስተዳደር መምሪያ) ደርሶናል ማለታችሁ እንቆቅልሽ ነዉ፡፡ በመሆኑም ለእኔ ባልደረሰኝና በማላውቀው፣ ምንአልባትም እርስ በርሳችሁ በተጻጻፋችሁት ሰነድ ላይ ተመርኩዛችሁ በ15 ቀን ዉስጥ ቤቱንና ቁልፉን በአስቸኳይ አስረክበህ ዉጣ የሚል አስተዳደራዊ ደብዳቤ መጻፋችሁ ለህግና ለሞራል ተገዥ አለመሆናችሁን ያሳያል፡፡
በተጨማሪም በ15 ቀን ዉስጥ የተባለዉን ዉዝፍ የቤት ኪራይ (3‚300 ብር) እና መብራትና የዉሃ ፍጆታ ከፍዬ እንድወጣ ከላይ እንደጠቀስኩት ትዕዛዝ ተሰጥቶኛል፡፡ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ሦስት ነጥቦችን አቅርቤ ደብዳቤዬን መዝጋት እፈልጋለሁ፦
1ኛ/ እንደሚታወቀዉ ቤት አከራይ ተከራዩን ከተከራየዉ ቤት ለማስለቀቅ ቢያንስ 3 ወራት ያህል ጊዜ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ይሁን እንጂ ለእኔ የተሰጠኝ ጊዜ ከላይ የተጠቀሰዉን ትዕዛዝ ለመፈጸም በቂ ስላልሆነ ህግና ደንቡ በሚፈቅደዉ መሰረት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠኝ ስል እጠይቃለሁ፡፡
2ኛ/ ከላይ አለብህ ተብሎ የተጠቀሰዉን ገንዘብ ለመክፈል ፈቃደኛ መሆኔን እየገለጽሁ ዶ/ር ሁሴን ጀማ (አካዳሚክ ስታፍ አፌርስ ዳይሬክተር) ጡረታ የወጣህበትን ወረቀት ካላመጣህ በሚል ፈሊጥ ያስተማርኩበትን ገንዘብ (14ሺህ) እና ዶ/ር ተመስገን ቡርቃ (አሶሺዬት ዲን እና የ2007 ዓ.ም የኢህአዴግ ለፓርላማ ምክር ቤት ተመራጭ) አግባብ በሌለዉ መንገድ የያዙብኝን ተጨማሪ 14ሺህ ብር ፣እንዲሁም ሁለት በድህረ-ምረቃ ፕሮግራም ያስተማርኩበትን ተጨማሪ 28ሺ ብር፤ በድምሩ 56 ሺህ ብር ዩኒቨርሲቲው ቢከፍለኝ ያለብኝን ኃላፊነት በጊዜዉ መወጣት ያስችለኝ ነበር፡፡
3ኛ/ ከላይ ያቀረብኳቸው ሁለት ነጥቦች መሠረታዊ ቢሆኑም እጅግ የሚያሳዝነው ጉዳይ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በዜጎች መካከል የሚፈጥረው ልዩነትና እድሎ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ እኔ በምኖርበት ህንጻ ላይ በተለያየ ምክንያት ከዩኒቨርሲቲው ለቀው እንዲያውም የተሻለ ገቢ የሚያገኙ ሰዎች፣ ከዩኒቨርሲቲው ቤት እንዲለቁ ሳይደረግ በዩኒቨርሲቲው ድጎማ እየኖሩ፤ በተናጠል እኔ ከቤት በጥቂት ቀናት ውስጥ ለማባረር መደረጉ ነው፡፡በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የመንግሥትን ንብረት እንደራሱ በመቁጠር በፖለቲካ የሚጠላቸዉን ዜጎች ማጥቂያ ማድረጉን ማቆም እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ ሆኖም ግን ሹመኞቹ ከኢሞራላዊ አሰራር የፀዱ እንዳይሆኑ በላያቸዉ ላይ የሰፈረዉ የትዕዛዝና የጥቅም መስተጋብር እንደሚከለክላችዉ መረዳቱ አያዳግትም፡፡በጎ ነገሮች ይመጣሉ በሚል በተስፋ ላይ ተስፋ ሰንቀን ብንጓዝም ከዩኒቨርሲቲው የአመራር ለውጥ ጋር ተያይዞ የሥርዓት ለውጥ ይመጣ እንደሁ እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማይመጣ ልቦናችን ይነግረናል፡፡
ከሰላምታ ጋር
ግልባጭ
• ለፕሬዝዳንት ጽ/ቤት
• ለአስተዳደር እና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት
• ለፋሲሊቲ ማኔጂንግ ዳይሬክተር
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
The post ዶ/ር ዳኛቸዉ አሰፋ በ15 ቀናት ውስጥ የዩኒቨርሲቲውን ቤት እንዲያስረክቡ ደብዳቤ ደረሳቸው appeared first on Zehabesha Amharic.