* እናት አንጀቷን አስራ የፍትህ ያለህ ስትል ዛሬም ታነባለች
* ፍትህ ዘግይቶ ጎድቷታል …አለፋ ስቅተቷ በዝቷል
* ፍትህ የሚያስገኛት ፣ ግፉን የሚያስቆመው ጠፍቷልየ4 ዓመት ደልዳላ እያለ ድክ ድክ እያለ ሮጦ ለቀላል ህክምና ከጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት አፍንጫ ስር በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ገባ ። ብዙም ሳይቆይ ከሰመመን መንቃት አልችል አለ ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከሰመመን አልነቃም ፣ በሃኪሞች ስህተት ብላቴናው መሀመድ ህይዎቱ ተሰናክሎ ላለፉት 9 ዓመታት የአልጋ ቁራኛ ሆነል። ትናንትም ሆነ ከትናንት በስቲያም መሀመድና ቤተሰቦቹ ፍትህ ርትዕ ያገኙ ዘንድ ደጋግሜ ጠይቄያለሁ ፣ ዛሬም እጠይቃለሁ ! ላለፉት በዘጠኝ አመታይ ከጅዳ ቆንስል ኃላፊዎች ጀምሮ ሳይኖር ” አለሁ ” እስከሚለን የሴቶች ማህበር ተወካዮች ፍትህን ለመሀመድ ያስገኙ ዘንድ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦ ፍትህ ማስገኘት ገዷቸዋል ፣ ተበዳዮች ፍትህ ርቋቸዋል … !
ክልትሙ ተንከባሎ ዛሬ ላይ ሲደርስ …
========================
ታሪኩን ከመሀመድ እናት ቃል በቃል ስሙት ፣ እኔ መግቢያየን አጠር ላድርገው … ከዚህ ሁሉ አመት በኋላ የብላቴናው መሀመድ አብድልአዚዝ ቤተሰቦች ደጋግመው ያደረጉት ውትወታ በቀደም የጅዳ ቆንስል ኃላፊዎች ተቀባይነት አግኝቶ አያውቅም ። ለአዲሱ አንባሳደር የቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አገኘና በጉዳዩ ላይ ክትትል መጀመሩን ተመለከትን ። ቆንስል መስሪያ ቤቱ ጉዳዩን በያዘው ማግስት ደግሞ ለ9 ዓመት የዋለለው የፍትህ ጥያቄ መልስ አገኘ ! አዎ … በአሳር በመከራ ለመሃመድ ቤተሰቦች ያለማሰለስ ባደረጉት ጉትጎታ 2.5 ሚሊዮን የሳውዲ ሪያል ካሳ እንደሚሰጥ በሳውዲ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር አንድ አጣሪ ኮሚቴ ውሳኔ ተላለፈ ። ውሳኔው ባይከፋም ለሰዓታት ከመተንፈሻ መሳሪያ ውጭ መንቀሳቀስ የማይችለው ብላቴ ቤተሰቦች የተወሰነውን ካሳ ተቀብለው ከሀኪም ቤቱ እንዲለቁ የተላለፈውን ፍርደ ገምድል የወላጅ ቤተሰቦች ተቃወሙት! በሰጠናቸው መረጃ መሰረት በውሳኔ አሰጣጡ ሂደት የተገኙት የጅዳ ቆንስል ተወካይም የወላጆችን ውሳኔ በመደገፍ የውሳኔውን ፍትሃዊ አለመሆን ሳይቀበሉ ቀረ ! ውሳኔ ያሳለፈው ኮሚቴ በህክምና ስህተት መሀመድ በደል የደረሰበት መሆኑን የሚያረጋግጠው ሰነድና ሙሉ ውሳኔ በአስር ቀናት ውስጥ ለወላጅና ለቆንስል መስሪያ ቤቱ እንደሚሰጥ ፣ አስፈላጊ ነው ካሉ ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ እንደሚቻል ተገልጾ ጉዳዩ በተያዘው ቀጠሮ ተዘጋ … ይህ የሆነው ከወራት በፊት ነበር !
ህግ አስከባሪ የማጣት እንቆቅልሽ !
======================
ዛሬስ ? ዛሬ የተገባው ቃል የማይጨበጥ ፣ የማይዳሰስ ጉም ሆኗል ፣ ቆንስል መስሪያ ቤቱ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል አቀርብኩት ያለው አቤቱታ መልስ አላገኘም ፣ ወላጆች ላፍታ ከመድሃኒትና ከህክምና ውጭ መቆየት የማይችለውን መሀመድን ይዘው እንዲዎጡ እየተወተወቱ ነው! እናት ልጇቸውን በቅርብ እንዲያስታምሙ ከተሰጣቸው ማደሪያ በኃይል እንዲለቁ ተገደዋል ፣ መጠለያውን በጸጥታ አስከባሪዎች እንዲለቁ ሲደረግ ለቆንስል መስሪያ ቤቱ ቢያመለክቱም መጠለያውን ከመልቀቅ አልታደጓቸውም ! የሳውዲ መንግስት የጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት አጣሪ ቡድን ያረጋገጡት ግፍ ተፈጽሞ የመሀመድ ቤተሰቦች በተለይም ብርቱዋ እናት ዛሬም ድረሱልኝ እያሉ ነው ! ቆንስል መስሪያ ቤቱም ፣ የተላለፈውን የውሳኔ ሰነድ ተረክቦ ጉዳዩን ወደ ፍትህ አካላት ማቅረብ ተስኖታል ! የጎደለባቸው ፍትህ እንዲሰፍን ዛሬም ተገፊዋ ይጮሃሉ … “ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም !” የሆነበት እንቆቅልሽ ግን አልገባን ብሏል !
እንኳንስ ይህም መሰል ግፍ ተሰርቶ በአደባባይ ተፈጽሞባቸው ፣ በከባድ የሳውዲ መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች የተፈጸመ የህግ ጥሰት የሚሸፋፍን የህግ ስርአት ሳላለመኖሩ ብዙ መረጃ ማቅረብ ይቻላል ። የቀደመውን ትተን ዛሬ የወጣውን የሳውዲ ጋዜጥ ብንመለከት ያን ሰሞን በሳውዲ አየር መንገድ ተጓዠ የነበሩ ሁለት ታዳጊዎችን ደፍረው የተመሰከረባቸው ሁለት የአየር መንገዱ የጸጥታ ሰራተኞች የአራት አመት እስራትና 1000 ጅራፍ ተፈርዶባቸዋል ! የእኛ ብላቴና መሀመድ ስቃይና የወላጆቹ አቤቱታ ጉዳይ ግን ጠያቂ አጧቷልና ህግ ፊት እንኳ የሚያቀርበው ጠፍቷል ! ስለሆነም የዜጎች መብት የሚያገባቸው አካላት የት አሉ ? ብለን እንጠይቅ ዘንድ እንገደዳለን !
ስለ ጎደለብን ፍትህ መከበር እንናገር !
=========================
ለሰብዕናና ለፍትህ ቀናኢ አይደለንም ፣ በሳውዲ አረቢያ የከተመው ነዋሪ ከኮሚኒቲ አባልነት ሸሸቷል ፣ የጅዳና የሪያድ ኮሚኒቲዎች የአባላት ድርቅ የመመታታቸው ሚስጥር ተአማኒነት ማጣት እንጅ ” ቡዳ ” በልቷቸው አይደለም ፣ ባሳለፍናቸው በርካታ አመታት ተወካዬዮቻችን ማህበራት ምስረታ አድርተው ትልቁን ኮሚኒቲ አኮላሸተውታል ፣ እናም እላችኋለሁ ፣ ለሰው መብት መቆምን ፈነጋግላችሁ የልማት ማህበራት እንደ እንጉይ የመፈልፈሉ የመጠመዳችሁን አደጋ ዛሬም በውል ያልታያችሁ ጉዳይ ፈጻሚ የመንግስት አካልት አካሄዳችሁን ልትገመግሙ ግድ ይላል ። ከምንም በላይ ዘንድሮ በተሃድሶ ላይ ነው የምንለው ቆንስል መስሪያ ቤት መመሪያ ወርዶ እያስፈጸመ ቢሆንም መልሶ ከዳጡ ወደ ማጡ እንዳይወድቅ እሰጋለሁ ! ለተገፊው መሀመድ ፍትህ ማግኘት ሁላችን ልንተጋ ግድ ይለናል ፣ ቢያንስ ጉዳዩን ወደ ፍትህ አካል ይቀርብ ዘንድ ሁላችንም የቻልነውን ከማድረግ ጎን ለጎን መሀመድን በጸሎት ታስቡት ዘንድ አደራየ የጠበቀ ነው !
ተወካዮቻችን የግፉአንን እንባ በመጥረጉና መብትታቸውን በማስከበሩ ሰናይ ምግባር ቆመው አለማየታችን የምስኪኗ የመሀመድ አብድልአዚዝ እናት እንባ የሚነግረን እውነታ አይጠፋም ! ” ስለ እውነት እንመስክርና የመጣው ይምጣ ! ” ማለትን ለደፈረ ባለፉት በርካታ አመታት በዋነኛነት የዜጎች መብት የቆሙት ተወካዮቻችንም ሆነ የሚያደራጇቸው ማህበራት ድግስ እየደገሱ በስሙ ገንዘብ ከመሰብሰብ ያለፈ ስራ ሰሩ ቢባል ለህዳሴውን ግድብ አደረጉ የሚባለውን ድጋድ ብቻ ነው የምናገኘው ! ለሀገር ግንባታ ፣ ለልማትና ድንበሩ ተደፈረ ሲባል ለሀገሩ ቀናኢነት የሚያሳየው ዜጋ ፍትህ እጦት ግን ዛሬም ተዘንግቷል …! ይህ በጣሙን የሚያም ፣ ሲነገሩት እንኳ መስዋዕትነትን የሚያስለፍል እውነታ ቢሆንም ነግ በኔ ነውና እኔ የምፈራው መከፈል ያለበት መስዋዕትነት የለም ፣ ከልጆቸ ፣ ከሞቀው ቤቴና ከከባቢው የተረጋጋ ኑሮየ እሰናከል ይሆናል ፣ ይህ ሁሉ ግን እውነቱን በተጨባጭ መረጃ ከመናገር ላፍታም ያህል አይገታኝም ! እውነቱን ተናግረን ከመሸበት እንደር …ስለ ፍትህ መከበር እናገራለሁ ! እናንተም ተናገሩ !
በእሱ ስራ አንገባም ፣ የዘገየው ፍትህ ይሰፍን ዘንድ ለፈጣሪ አቤት እንላለን ፣ መልስም እናገኛለን ! ምድራዊ ነንና የተወካዮቻችን ጀሮ የተፊዎችን ድምጽ ይሰማ ዘንድ ከመማለዱ ጎን እንደ ፍጡር የፍትህ ማስከበር ጥሪያችን ትሰሙ ዘንድ እንማለዳችኋለን !
የየራስ ፍርዳችሁን ስጡ ፣ እኔ እንዳገባኝ እናንተም ያገባኛል ካላችሁ ፣ የማቀርበውን ጭብጥ መረጃ ፣ ስለ ሰነብአዊ መከበርና ስለ ፍትህ መረጃውን እየተቀባበላችሁ ጩኹት … የተነፈግነውን ፍትህ ማግኘት እስክንችል :( የእናት ፍቅርን የምታውቁትም ሆነ የማታውቁ ፣ የእናት አንጀትን መላወስ ህመም ጠልቆ የሚሰማችሁትም ሆነ ስሜቱን የማይገባችሁ ፣ የምትወዱትን ነገር በግፍ ስለመነጠቃችሁ እያሰባችሁ ስለ መሀመድና ስለ ግፉአን ቤተሰቡ ፍትህ ማግኘት አቤት ትሉ ዘንድ አደራ እላችኃለሁ . .. !
በሳውዲ መንግስት ጤና ጥበቃ ሚኒስትር አጣሪ ኮሚቴ በህክምና መሰናከሉ የተረጋገጠው የብላቴናው ጉዳት ዛሬ ላይ ሲደርስ ፍትህ እጦቱ አንገሽግሾናል ፣ ብላቴናውና ቤተሰቦቹ ፍትህ ይሻሉ ፣ እኛ የወገናችን ጉዳይ ያገባናልና ፍትህ ፣ እንሻለን ፣ ፍትህ ናፍቆናል ! ጉዳዩን ወደ ፍትህ አቅርቡልን !
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓም
The post የማለዳ ወግ … በብላቴናው ላይ የዘገየው ፍትህ ! (ነቢዩ ሲራክ) appeared first on Zehabesha Amharic.