በዘውዲቱ ሆስፒታል የመህፀን እጢ እንዳለባቸው የተነገራቸው የ 5 ልጆች እናት እጢው ወደ ካንሰር እንዳይለወጥ አስቸኳይ ቀዶ ጥገና እንዲደረጉ ይታዘዛሉ ። ለዚህም ቀዶ ጥገና ሆስፒታሉ መሳሪያ ስለሌለው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የምርመራ ውጤታቸውን አባሪ በማድረግ ይልካቸዋል። የተጠቀስው ሆስፒታል እደደረሱም እናት ለህክምና ከአቅማቸው በላይ የሆነ ክፍያ ሰለተጠየቁ «ያለአባት የሚያሳድጓቸው የ 5 ልጆች እናትና የቤተሰብ ሃላፊ መሆናቸውን ጭምር በመግለጽ ሆስፒታሉ ከሞት እንዲታደጋቸው ይማፀናሉ ። የሆስፒታሉ አስተዳደር እናት ከቀበሌ ደብዳቤ ካመጡ በነጻ ህክምና የሚያገኙበትን መላምታ እንደሚያመቻቹላቸው ቃል በመግባት ያሰናብቷቸዋል። የጤና ጉዳይ ነውና እናት የተባለውን ሁሉ አሞልተው ዳግም ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በማቅናት ለነጻው ህክምና ተራ ያሲዛሉ ። ከወራት ቆይታ በኃላ እናት የቴሌፎን ጥሪ ከሆስፒታል ይደርሳቸዋል « ተራዎ ስለደረሰ መጥትው ነጻ ህክምናውን ይውሰዱ የሚል» ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በቁሙ የገባ ታካሚ እንደዋዛ በሬሳ ሳጥን ታሽጎ በአስከሬን በር የሚወጣበት ፤ የመኪና ግጨትን ጨምሮ በተለያያ ድንገተኛ አደጋዎች እግርጥሎት ወደ ሆስፒታሉ ያቀና «ዘመድ አዝማድ የሌለው የኔ ቢጤ » የሰውነት ክፍሉ ተበልቷ ለሃብታሞች ጫራታ የሚቀርብበት ፡ በአጠቃላይ ሆስፒታሉ ወደ ሰው ቄራነት የተለወጠ ፤ የህክምና መሳሪያን ጨምሮ በ መደሃኒትና በባለሙያ እጠረት ያለበት መሆኑን ቀደም ብለው የተረዱ እናት ሁኔታው ደስ ስላላቸው « እሱ እንደፈጠረኝ እሱ ይግደለኝ » ብለው ምንም አይነት የህመም እንደማይሰማቸው ገልጸው የቀዶ ጥገና ሃሳባቸውን መለወጣቸውን ለሆስፒታሉ ያስረዳሉ። የኚህን እናት ሙሉ መረጃ የያዙ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዶ/ሮች በተደጋጋሚ ስልክ በመደውል እጢው ቀላል እንደሆነና በዛው ልክ ቀዶ ጥገና እንደሚያደርጉላቸው ያግባቦቸዋል።
እናት ያለአባት የቀሩ ልጆቼን ላሳድግ ኽረ ! ጉድ ታደርጉኛላችሁ ! ቢሉ ማን ሊሰማ ። በዶ/ክተሮች ተማጽኖ ሆስፒታል የገቡት እናት ግን የፈሩት አልቀረላቸውም። ዕለቱ ማክሰኞ ረፋዱ ላይ ነው ። ከሶስት ቀን በፊት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አልጋ ተይዞላቸው የቀዶጥገና ቀናቸውን የሚጠብቁት የ 5 ልጆች እናት ስጋታቸው ጨምሯል። እናት ፍረሃት ፍረሃት እንዳልቸው ለገኙት ሁሉ ቢገልጹም ደሃ ታሞ በማይድንባት ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም እንደሆነ የሚነገርለትን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ባዶ ህንጻና ነጫጭ ገዋን በለበሱ የጤና ባለሙያዎች በተማረኩ ወገኖች አበረታችነት እናት በተጠቀሰው ቀን ከቀኑ 8 ሰዓት ልጆቻቸውን ተሰናብተው ወትሮም ወደ አላመኑበት ቀዶ ጥገና ክፍል ገቡ ። ልጆቻቸውን ጨምሮ ሁሉም ቤተሰብ ቀዶ ጥገና ክፍል በሩ ላይ በጭንቀት ተውጦ ፈጣሪውን ይማፀናል ። የቀዶ ጥገና ክፍሉ መግቢያ ላይ ዶ/ሮቹ ቀዶ ጠገናውን መጀመራቸውን የሚያመላክተው ቀይ መብራት በርቷል ።ሶስት ሰዓት ይፈጃል ይተባለለት ቀዶ ጥገና ሳይጥናቀቅ ከቀዶ ጥገና ክፍሉ አንድ በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ የህክምና ባለሙያ እይተቻኮለ ወጣ ፤ በጭንቀት ተመስጥው በር ላይ ለታደሙት ቤተሰቦች በተርበተበተ አንደበት « ሴትየዎ ብዙ ደም ስለፈሰሳቸው ደም ስለሚያስፈልግ ፈልጋችሁ አምጡ » የሚል ትዕዛዝ ቢጤ አስተላልፎ እየተቻኮለ ወደ መጣበት ክፍል ተመለስ ።ሁሉም ቤተሰብ በየአቅጣጫው ደም ፍለጋ ከተማ ውስጥ ያሉትን ሆስፒታሎች ማካለል ጀመር ወትሮስ ምክንያት እንጂ ችግሩ የደም አልነበረም ። የናታቸው ህይወት አደጋ ውስጥ መውደቅ የተነገራቸው ልጆች እሪታቸውን አቀለጡት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህንጻ እንደዚህ አይነት ጩህቶችን በየግዜው መስተናገድ የተለመደ ቢሆንም የልጆቹ ጩኽት ግን ከወትሮው ለየት ያለ ነበር ፤ በአካባቢ የነበረውን ሁሉ ደረት በማስደቃት የሆስፒታሉን ድባብ ለወጠው ።በሁኔታው የተደናገጡት ዶ/ር ተብዬዎች ከአካባቢው ተሰወሩ ችግሩ ወደ ተፈጠረበት የቀዶ ትገና ክፍል የመጡ የሆስፒታሉ ህላፊዎች በቀዶ ጥገና ወቅት በደም ስር ላይ ጉዳት ሳይደርስ እንዳልቀረና ሴትየዋ የማይተርፉ መሆናቸውን ቢረዱም የዜጎች ህይወት በተደጋጋሚ በቀዶ ጥገና ስህተት መጥፋት የተለመደ ነውና በአካባቢ የነበረውን ቤተሰብ ከማስተዛዘን ውጭ ዴታም አልነበራቸውም ፤ በተለይ ልጆቻቸውን ለማረጋጋት በእድሜ የገፋውን ልጅ ቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ ይዘውት በመግባት ከማደነዘዣ የነቁትን እናት እንዲያይ ፈቀዱለታል ።
የአባት ፍቀር እንደተራበ እናቱን ለማየት ወደ ቀዶ ጠገና ክፍል የዘለቀው ልጅ ከእናቱ አንደበት « ብርድ ብርድ አለኝ ፤ ተጫወቱብኝ የሚለውን ቃል ከመስማት ባሻገር »እናት ጤና እያሉ ይለግሱት የነበረውን የእናትነት ፍቅር ዳግም መስማት አለታደለም ። የማህጸን እጢ አለባቸው ተብለው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተለምነው የገቡት እናት ይህይወት ፍጻሜ በቀዶ ጠገና ስህተት ሁሉም ነገር አበቃ ። በዛው ቅጽፈት የቀዶ ጠገና ክፍሉ ዘግናኝ የደውል ድምጽ አቃጨለ ተጠያቂነትና የህግ የበላይነት በሌለበት ሃገር ተተኪ የሌላት የ 5 ልጆች እናት ላትመለስ እስከ ወዲያኛው አሸለበች ። በፖለቲካ አመመለካከታቸው አያሌ የሃገሪቷን እውቅ ዶክተሮች ከሃገር እንዲሰደዱ ያደረገው « የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት » በጤና ፖሊሲው የፖለቲካ ቱሩፋት ለማግበስበስ ያለ በቂ ባለሙያ ፤ የህክምና መሳሪያና መደሃኒት በየክልሉ ለይስሙላ ባስገነባቸው ባዶ ህንጻዎች ውስጥ ህይወታቸው እንደዋዛ ያጡትን ዜጎቻችንን ቤት ይቁጠራቸው::
The post በዘውዲቱ ሆስፒታል የ5 ልጆች እናት በህክምና ስህተት ሕይወቷ አለፈ appeared first on Zehabesha Amharic.