Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ከመስፍን ወልደማርያም (ፕሮፍ) ምን እንማር? (ኤልያስ ገብሩ ጎዳና)

$
0
0
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ

ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ

ሚያዚያ 16 ቀን 2007 ዓ.ም 85 ዓመት ለሆናቸው መስፍን ወልደማሪያም (ፕሮፌሰር)፣ ደጋግሞ ታላቅ ክብር መስጠት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ዕድሜ ስለሀገር እና ህዝብ የሚያምኑበትን፣ የሚታዘቡትን፣ የሚያዝኑበትን፣ የሚደሰቱበትን፣ …ሀሳብ መሰረት በማድረግ ብዕርን ከወረቀት ወይም ጣቶችን ከኮምፒውተር ኪቦርድ ጋር አገናኝቶ ለህትመት እና ለማኅበራዊ ድረ-ገጽ አንባቢያን ማቅረብ መቻል የሚያስመሰገን ተግባር ነው፡፡

ሀገራችን በተለያዩ የሙያ እና የዕውቀት ዘርፎች ያፈራቻቸው እጅግ በርካታ ምሁራኖች እንዳሏት ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ፣ ሀገር እና ህዝብ (ከሚያውቁት አኳያ) ብዙ ሲጠብቅባቸው የጋን ውስጥ መብራት ሆነው፣ አይተው እንደላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ፣ ታዝበው እንዳልታዘቡ፣ አውቀው እንዳላወቁ በመሆን አንድም በፍርሃት አሊያም የሥርዓቱ አሸብሻቢ መሆንን መርጠው አድርባይነት መገለጫቸው ሆኗል፡፡ ይህ የሚያሳዝን አካሄድ ፕሮፍን አይመለከትም፡፡ ሥርዓቱ ተከፋ አልተከፋ፣ ተቆጣ አልተቆጣ፣ አሰረ አላሰረ፣ አስፈራራ አላስፈራራ ፕሮፍ ያመኑበትን በድፍረት ሲነገሩ እና ሲጽፉ ኖረዋል፡፡ ፈጣሪ ጤናና ዕድሜ ይስጣቸው፣ በዚህ መንገድ ዛሬም ነገም ይኖሩታል፡፡ ፕሮፍን ብዙ በጽሑፋቸው፣ ጥቂት በአካል ከማውቃቸው አኳያ፣ እንደዛሬ ትውልድ አባልነቴ ‹‹ከእሳቸው ብንማር ይጠቅሙናል›› ብዬ ከማስባቸው ነገሮች መካከል የተወሰኑትን ከዚህ በታች ልጥቀስ፡-

ተፈጥሮን መኖር
——
በዓለማችን ላሙኑበት ዓላማ፣ እስከመጨረሻው ድረስ ከመንገዳቸው ሳይዛነፉ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ይመስሉኛል [ጥናት ላይ የተመረኮዘ ጽሑፍ ስላልሆነ ነው]፡፡ ላመኑበት እውነት የሚኖሩ ሰዎች፣ በውስጣቸው የሚለዋወጥ ፍላጎት ሳይሆን ረግቶ የሚኖር መሻት አላቸው፡፡ ይህም ነው፣ በዋነኝነት ጽኑ የሚያደርጋቸው፡፡ በሁኔታዎች እና በጊዜያቶች የሚዋልል ፈላጎት ያላቸው ሰዎች ቆምንለት ላሉት ሀሳብ ሩቡን ወይም ገሚሱን እንኳን ሳይጓዙ ማሊያቸውን ለውጠው የመገለባበጥ ጅምናስቲክ ሲሰሩ ይገኛሉ፡፡ በሀገራችንም ቢሆን ይሄን ትናንት አይተናል፤ ዛሬም ሆነ ነገ እናይ ይሆናል፡፡ ከዚህ ረገድ፣ ፕሮፍ ካሏቸው ጽኑ መሻቶች መካከል አንዱ፤ በሀገራችን የሰብዓዊ መብት ተከብሮ ማየት መሆኑን ከተግባራዊ እንቅስቃሴዎቻቸው በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡ ሰመጉ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ፕሮፍ፣ ስለፍትህ መጓደል፣ ስለ ዴሞክራሲ ንፍገት፣ ስለነጻነት ዕጦት፣ ስለችጋር፣ ስለትውልዱ ችግር፣ …ወዘተ ያለመታከት ጽፈዋል፡፡ ይሄ እንግዲህ በሀገራችን የሚታዩ ወሳኝ ችግሮችን ለማጋለጥ ጠንክሮ መቆምን ያሳያል፡፡

እኔ እና አቤል አለማየሁ በ2005 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በጋራ አዘጋጅተነው በነበረው ‹‹ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?›› መጽሐፍ ላይ እንዲህ ገልጸው ነበር፡- ‹‹የተፈጠርኩለትን ዓላማ ምን እንደሆነ በእውነት አላውቅም፡፡ [ፈገግታ ያጀበው ሳቅ] በአዕምሮህ ‹ይህ ተፈጥሮዬ ነው› ልትል ትችላለህ፡፡ አዕምሮህን ስለህ፣ እያሰብኩ ‹ይሄ ትክክለኛ መንገድ ነው፤ በአስተሳሰብ፣ በሕግ ሀልዮት ደረጃ ይሄ ትክክል ነው› ብለህ የምትሄድበት መንገድ አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በልብህ፣ በህሊናህና በስሜትህ መጥፎ፣ ክፉ ነገር ስታይ ያን መጥላትህ፣ ‹‹እንደዚህ ዓይነት ነገር በሰው ላይ መፈጸም የለበትም›› ብለህ ራስህን አጋልጠህ መኖርህ፣ ሐሳብ እና ስሜትህ በተገናኙበት መንገድ ለመሄድ መቻልህ ተፈጥሮዬ ነው ልትል ትችላለህ፡፡ እምነትም እዚህ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ራስህን ብቻ አውጥተህ፣ ጥቅም ብቻ እያሳደድክ የምትኖረው ኑሮ ለእኔ በፍጹም ሕይወት አይደለም፡፡ በአከባቢዬ ያለው፣ በመስኮት ስመለከት የማየው ነገር ሁሉ እንዲነካኝ፤ የሌላው ችግር እንዲቸግረኝ፣ የሌላው ሰቆቃ እና ጭቆና እንዲሰማኝ እፈልጋለሁ፡፡ የሰውየውን ያህል ችግሩ ላይሰማኝ ቢችልም ትንሽም ቢሆን እንዲነካኝ ካላደረኩኝ ለእኔ ሕይወት ምንም ትርጉም የለውም፡፡›› በዚህ ገለጻ ውስጥ፣ በተፈጥሮ መንገዳቸው መሄዳቸውን እና ለሰብዓዊነት ተቆርቋሪነታቸውን በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡

ድፍረት
—–
በሕይወት፣ የሚያምኑበትን ነገር መለየት እና ለተግባራዊነቱ መወሰን፣ መንቀሳቀስ መጀመርና ላመኑበት ነገር መኖር ድፍረትን ይጠይቃል፡፡ በአጭሩ ፕሮፍን ድፍረት ይገልጻቸዋል፡፡ ያመኑበትን በግልጽ አማርኛ ይናገራሉ፡፡ ይሄንን ለመረዳት እና ለማረጋጋጥ የጻፏቸውን መጽሐፎች፣ ግጥሞች፣ ግለ-ሀሳቦች መለስ ብሎ ማየት ነው፡፡ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ ውስጥ፣ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ስላሉ ሰዎች ሀሳብ እንዲሰጡን ለፕሮፍ ጥያቄ እንስቼላቸው፣ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ፍርሃቱን ልትነግረው ‹‹ተው አትፍራ›› ብትለው አትችልም፤ የማይቻል ነው፡፡ ፍርሃት በጣም የግል (Subjective) ነው፡፡

ፍርሃቱ እስኪተውው ድረስ ‹‹አትፍራ›› ልትለው አትችልም፡፡ አንተ ባለመፍራት አንዳንድ ነገር ስታደርግ እሱ ስለሚፈራ ‹‹ቂል›› ይልህ ይሆናል፡፡ ፈሪ ሆኖ ጥሩ ፎቅ ቤት ውስጥ ይኖራል፡፡ ጥሩ ኑሮ ይሆናል፡፡ አንተ ያልሆነ አልባሌ፣ ዓይነት ኑሮ በመኖርህ ‹‹ይሄ ቂል አርፎ ቢቀመጥ፣ እንደ እኔ እንዲህ መኖር ይችል ነበር›› ይልሃል፡፡ ይሄን መቻል አለብህ፡፡ ነገ፣ ከነገወዲያ፣ ሁልጊዜ በአንድ መስመር እንድትሄድ የሚደርግህ እንዳልኩህ ሚዛንህን መያዝህ ነው፡፡›› የዛሬ ወር ገደማ ፕሮፍ በማኅበራዊ ድረ-ገጽ (በፌስ ቡካቸው) ላይ ባሰፈሩት አጭር ጽሑፋቸው ውስጥ ኑሯቸውም ሆነ ሞታቸውም በሀገራቸው መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ሀገር ጥለው እንዲወጡ እየተነኳኮሷቸው ላሉት ካድሬዎች የሰጡት አጭር ምላሽ በድፍረት የታጀበ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ በቤታቸው የሚገኙት የገብረ-ክርስቶስ ደስታ ስዕሎች መሆናቸውን ጠቅሰው ‹‹በዚህ አጋጣሚ ሥዕሎቹን የሚገዛ…›› ያሏት አገላለጽ ደስ እና ፈገግ አስደርጋኛለች፡፡

አድናቆት እና ትችትን መቻል
——-
ለፕሮፍ የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት አድናቆትን በቃላትና በጽሑፍ ሰጥተዋቸው ያውቃሉ፡፡እንዲሁም ፕሮፍ በጋዜጦች/በመጽሔቶች/በመጽሐፎቻቸው ባነሷቸው ሀሳቦች ላይ ተንተርሰው የተለያዩ ሰዎች ትችትን በጽሑፍ አቅርበውባቸውም አንብበናል፡፡ ለተቿቸው ሁሉ ግን መልስ አይሰጡም፡፡ ምሳሌ ለማንሳት ያህል፣ ‹‹መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ›› ለተሰኘው አነጋጋሪ መጽሐፋቸው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላነሳባቸው ትችት መልስ ሰጥተውታል፡፡ የኢዴፓ አመራር የነበረው አብዱራህማን መሐመድ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ሰፊ ጽሑፍ ፕሮፍ ላይ ቢጽፍም አጸፋዊ መልስ ነፍገውታል፡፡ ስለዚህ ፕሮፍ መልስ የሚሰጡበትና የማይሰጡበት የትችት ዓይነት እንዲሁም ሰዎች ስለመኖራቸው የሚያሳይ ነው፡፡ እሳቸው ቢሆኑ አድናቆቱም ሆነ ትችቱ አልጣላቸውም፡፡ እዚህ ጋር፣ ‹‹አድናቆት ይጥላል ወይ?›› የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችል ይሆናል፡፡ መልሴ አዎን ነው፡፡ አድናቆትን መቆጣጠር የሚችሉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፤ በአድናቆት ሰክረው ከመንገዳቸው የሚንሸራተቱ ሰዎች መኖራቸውን ማወቅም ተገቢ ነው፡፡ በትችት መንፈሳቸው በቀላሉ የሚሰበሩ ሰዎች አሉ፤ አይተናልም፡፡ ፕሮፍም ቢሆኑ ለሰዎች አድናቆት ሲሰጡ እና ጠንካራ ትችትን ሲሰነዝሩም እናውቃቸዋለን፡፡ አንድ ሰው ራሱን አደባባይ ላይ በተለያየ መንገድ አውጥቶ ልተች አይገባም ሊል እንደማይችል በአንድ ወቅት ከሰጡት ቃለ-ምልልስ ተረድቻለሁ፡፡ ስለዚህ አድናቆትንም ሆነ ትችትን መቻል ትልቅ ጥበብ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡

ተስፋ አለመቁረጥ
—–
በሀገራችን የፖለቲካው መስክ፣ ይበልጥ የተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያ በብዙዎች ላይ በገሃድ ይንጸባረቃል፡፡ አፍ አውጥተው ተስፋ መቁረጣቸውን የሚናገሩም አሉ፡፡ ይህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት በተለይ ወጣቶች ላይ ሲታይ ያስጨንቃል፤ ያሳዝናልም፡፡ ለሥርዓቱ የጭካኔ በትር በአንድ ጊዜ የሚንበረከኩ ሰዎች መኖራቸውንም በግል ታዝቤያለሁ፡፡ ይህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ‹‹መስመራችን ነው›› ካሉት ጎዳና አስወጥቶ እስከወዲያኛው ያርቃቸዋል፡፡ ከዚያም አይተው እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ፣ አውቀው እንዳላወቁ ወደመሆን ያመራሉ፡፡

ፕሮፍ ግን፣ ሀገሪቷ በተለያዩ አስቸጋሪ ሁነት ውስጥ እየኖረች መሆኑን ተገንዝበው፤ አይተው እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ፣ አውቀው እንዳላወቁ መሆን አልቻሉም፡፡ ባለፈው ዓመት መጨረሻ አካባቢ ‹‹ፋክት›› መጽሔት ከመዘጋቷ በፊት በየመጽሔቷ አምደኛ ሆነው በየሳምንቱ ሀሳባቸውን ይሰነዝሩ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን፣ በማኅበራዊ ድረ-ገጽ በፌስ ቡክ ገጻቸው አልፎ አልፎም ቢሆን ሃሳባቸውን እየጻፉ ማስነበባቸውን ቀጥለዋል፡ች በሀገራችን ብዙ አሳዛኝ ድርጊቶች መፈጸማቸው ቀጥለዋል፡፡ በእነዚህ አሳዛኝ ሆነቶች ፕሮፍ ተስፋ ቢቆርጡ ኖሮ ሀሳባቸውን በአንድም ይሆን በሌላ መንገድ ባላየን ነበር፡፡ ይህ፣ በሀገር ጉዳይ ተስፋ ያለመቁረጥ ስሜት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ተስፋ ስንቆርጥ እንቅስቃሴያችን ይገታል፡፡ ስለዚህ፣ ሰዎች በሕይወት እስካለን ድረስ ተስፈኛ መሆን ይገባናል፡፡

እንግዲህ በግሌ ከፕሮፍ ብንማራቸው ይጠቅሙናል ያልኳቸውን እራት ነጥቦች በአጭሩ ለማቅረብ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ሌሎችም ፕሮፍን ከማወቅ አኳያ፣ አስተማሪ ናቸው የምትሏቸው ሀሳቦች ካሉ ሀሳባችሁን ሰንዝሩና አብረን እንማማር፡፡

(በዘንድሮው የፋሲካ ዕለት፣ ሚያዚያ 4 ቀን 2007 ዓ.ም የተጻፈ)

በዚህ አጋጣሚ፣ ፈጣሪ ዕድሜ እና ጤናን ለፕሮፍ ይስጥ ብያለሁ!

ቸር እንሰንብት!

The post ከመስፍን ወልደማርያም (ፕሮፍ) ምን እንማር? (ኤልያስ ገብሩ ጎዳና) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>