Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ዘሚ የኑስ –የኦቲዝሟ «አምባሳደር»

$
0
0

በልጅነት ዕድሜያቸው በደማቸው ውስጥ በሰረፀው የሥነ ውበት (ኮዝሞቶሎጂትምህርት በመታነፅ በሙያው በመካን አገራቸው ላይ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የሥልጠና ማዕከል በመክፈት ከስድስት ሺ በላይ ባለሙያዎችን ማፍራት ችለዋል።

zemi yenusበተጓዳኝም ችግረኛ ወጣት ሴቶችንና በሴተኛ አዳሪነት ለሚተዳደሩ ሴቶች በሚሰጡት ነፃ የትምህርት ዕድል በሥነ ውበት ሙያና የሕይወት ክህሎት ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ሥራ ፈጥረው ራሳቸውን እንዲረዱና የኢኮኖሚያዊ ነፃነት እንዲቀዳጁ በማድረግ የመልካም ስም ባለቤት ለመሆንም በቅተዋል። 

የውበትን ማራኪነት በመጠቀምና በመገንዘብ በዓይነቱና በይዘቱ የመጀመሪያ የሆነ የብሔር ብሔረሰቦችን አልባሳትንና ባህልን የሚያሳይ ኤግዚቢሽን በማሳየት ለአገራችን አልባሳት የተሐድሶ ዘመን ብርሃን በመፈንጠቅም የዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ባለቤት ለመሆን ችለዋል።

በልዩ ልዩ ምክንያት ትዳራቸውን ፈተውና ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ወደ አዲስ አበባ እየፈለሱ የሚመጡ በተለይ ዕድሜያቸው እስከ ሃያ አራት ዓመት የሚሆናቸው ወጣት ሴቶች በችግር ምክንያት ወደ ሴተኛ አዳሪነት እንዳያመሩ የሚያደርግ የባልትና እና የሕይወት ክህሎት የሚቀስሙበት «ስንቅ ቤት» የሚል ፕሮጀክት በመክፍት የወገን አለኝታነትን አትርፈዋል ።

ከሁሉም በላይ እንደ እራሳቸው ልጅ የኦቲዚም ችግር ያለባቸውን ልጆች በልዩ ፕሮግራም በመከታተልና በማስተማር ለተሻለ ህይወት በማዘጋጀት ብቁ ዜጐች እንዲሆኑ የሚረዳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ «ጆይ የኦውቲስቲክ ልጆች ማዕከል» የተባለ ተቋም መክፈት ችለዋል። በዚህም በአንዳንድ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቤቶች ትምህርትና አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ ህዝባዊ ዕውቅናንና አንቱታን ለማትረፍም በቅተዋል።

በሌላ በኩል በኦቲዝም ምክንያት የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑ እናቶችን በማደራጀትና በማሰልጠን የገቢ ማስገኛ ሥራ በመፍጠርና ለተጠቃሚነት በማብቃት ለኦቲስቲክ ልጆች እናቶችም አጋርነታቸውን በተግባር ለማረጋገጥ ችለዋል።

ይህ ብቻ አይደለም በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ኅብረተሰቡን የሚያወያይና ግንዛቤን የሚያሳድግ «ያገባኛል» የሚል ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በመክፈት በ«ጋዜጠኝነት» ሙያም በመሰለፍ አውቀው በማሳወቅ ላይ ይገኛሉ።

የእነዚህና የሌሎችም ታሪኮች ባለቤት ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በውጭ አገር ተሰደው በልጅነት ዝንባሌያቸው በሥነ ውበት ትምህርት በመሰልጠን ለኮዝሞሎጅስትነት የበቁት በአገራችን የመጀመሪያው የውበት ስራ ሥልጠና ማዕከል ባለቤት እንዲሁም የኒያ ፋውንዴሽን (የጆይ የአውቲስቲክ ልጆች ማዕከልመስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዘሚ የኑስ ይባላሉ።

የካቴድራሏ ዕምቡጥ

ዛሬ የመልካም ስም ባለቤት ለመሆን የበቁት ወይዘሮ ዘሚ የተወለዱት የዛሬ ሃምሳ አምስት ዓመት በፊት ጥቅምት ቀን 1951 .ም በአዲስ አበባ ከተማ ጣሊያን ሰፈር በሚባለው መንደር ነው። የአቶ አህመድ የኑስና የወይዘሮ ድሐብ ፎሌ አምስተኛ ልጅ የሆኑት የዚያን ጊዜዋ እምቦቅቅላ ህፃን ዘምዘም በካቴድራል ሴቶች ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን የጀመሩት ገና በስድስት ዓመታቸው ነበር።

በወቅቱ እንደማንኛውም ተማሪ ትምህርታቸውን በአግባቡና በትጋት የመከታተላቸውን ያህል በተለይ እናታቸው ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ሥራን ባህላቸው አድርገው፣ በሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ በማድረጋቸው በየምዕራፉ ለተሸጋገሩት ዘርፈ ብዙ የሕይወት ጉዞ በእጅጉ እንደጠቀማቸው ይናገራሉ። ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ከአደጉበት በቅሎ ቤት አካባቢ እየተመላለሱ ካቴድራል እየተመላለሱ ትምህርታቸውን የተከታተሉት የዜያን ጊዜዋ ሕፃኗ ዘምዘም በዕውቀት እየተኮተኮቱ ከክፍል ክፍል እየተዘዋወሩ በእድሜያቸውም እየደረጁ ሲሄዱ የሥነ ጥበብ (አርትዝንባሌ በውስጣቸው ሰረጸ። ይሁን እንጂ የነበረው ሥርዓተ ትምህርት ከዝንባሌያቸው ጋር ሆድ እና ጀርባ ሆነው ፍጹም ሳይገናኙ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል። የስምንተኛ ክፍልን ብሔራዊ ፈተና አልፈው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገቡ እንኳን በዝንባሌያቸው ለመማር አልቻሉም።

በእርግጥ ዲዛይነሩና ልብስ ሰፊው አባታቸው (ከገጠራማው የአገራችን ክፍል የእረኝነት ሥራቸውን በመተው ከጣሊያኖች ዘንድ ተጠግተው በቀሰሙት ሙያ የታላላቅ ባለሥልጣኖችንና የአምባሳደሮችን ሙሉ ልብስ ዲዛይን አውጥተው በመስፋት እውቅና የአተረፉልጆቻቸውን ለማስተማር ልዩ ትኩረት ነበራቸው። እናም ውሳኔያቸው ልጃቸውን ናዝሬት ትምህርት ቤት ለማስገባት ቢሆንም የዚያን ጊዜዋ ተማሪ ዘምዘም ግን ከጓደኞቻቸው «አልለይም» በማለታቸው የእቴጌ መነን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ ተማሪ ዘምዘም በመማር ማስተማሩ ሂደት የቆዩት ለሦስት ወራት ብቻ ይሆናል። 

ነገሩ እንዲህ ነው፤ በወቅቱ የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ መምህር የነበሩት «ሴቶችን የሚያንቋሽሹና የሚያዋርዱ» ምሳሊያዊ አባባሎችን እንዲነግሯቸው ወይም በጽሑፍ እንዲሰጧቸው ይጠይቋቸዋል። የመምህሩ ዕኩይ ጥያቄ ያናደዳቸውና ያበሳጫቸው ለግላጋዋ ተማሪ ፊት ለፊት ለመቃወም እንደማይችሉ ያምናሉ። ከጓደኞቻቸው ጋር ግን «በያገባኛል» ስሜት ይወያያሉ። ጉዳዩን ለትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ቢከሱም ተደማጩ አስተማሪው ስለሆኑ ውጤቱ ጉንጫ አልፋ መሆኑንም ጓደኛሞቹ ይገባቸዋል። የመምህሩ ፀረእኩልነት አስተሳሰብ ያስቆጣቸው የካቴድራሏ ዕምቡጥ ጉዳዩን ለአባታቸው በመንገር የሚወዱትን የአማርኛ ትምህርት በአግባቡ ይከታተሉ ዘንድ ሌላ ትምህርት ቤት እንዲያስገቧቸው ይጠይቋቸዋል። በልጃቸው መልካም አስተሳሰብ የተስማሙት አባትም በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ በሚገኘው ንፋስ ስልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ያደርጓቸዋል። በዚሁ ትምህርት ቤት እስከ አስራ አንደኛ ክፍል ድረስ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እያሉ ያልጠበቁትና ሕሊናቸው የማይቀበለው ሁኔታ ይከሰታል።

ወቅቱ የአብዮት ጊዜ ስለነበር ወጣቱ በተለይም ተማሪው እንደወንጀኛ ተቆጥሮ በፀረሕዝብነት ተፈረጀ። እናም ተማሪ ዘምዘም በወጣቶች ላይ የሚደርሰው ወከባ አስፈሪ ይሆንባቸዋል። የትምህርት ቤታቸው መዘጋትና መከፈት ያበሳጫቸዋል። ተማሪዎች እየተያዙ ወደ እስር ቤት ሲወሰድ በማየታቸው ስጋት ውስጥ ይገባሉ። ልጃገረዶች ቀበሌ እየተወሰዱ እንደሚደፈሩ ሲሰሙ ደግሞ ይበልጥ በፍርሐት ይርዳሉ። በእርሳቸው ዕድሜ የሚገኙ ተማሪዎች እየተገደሉ መሆኑን ሲሰሙም ሕሊናቸው በሐዘን ይሞላል። በእርግጥ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ባይገቡም ተማሪዎች የሚያነሱትን ጥያቄም ያምኑበታል። ነገር ግን ብጥብጡንና የሚያስከተለውን ችግር አይወዱትም። እናም የትግል ምርጫቸው ሰላማዊ ይሆናል። በወጣቱ ላይ ያንዣበበውን ዕልቂት የተገነዘቡት ተማሪ ዘምዘም ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ ታላቅ እህታቸው በፈጠሩላቸው ምቹ ሁኔታ ከሚያፈቅሯቸው እናትና አባታቸው፣ እህትና ወንድሞቻቸው፣ እንዲሁም ከሚወዷት አገራቸው ተለይተው በ1969 .ም ወደ ኢጣሊያ በረሩ። እናም በአስራ ሰባት ዓመት ዕድሜያቸው የስደት ኑሮአቸውን አሀዱ ብለው ይጀምራሉ።

የቤት ሠራተኛዋ 

እነሆ ገና በአስራ አራት ዓመት ዕድሜያቸው ለሴቶች እኩልነትና መብት ተቆርቁረው «በፆታ ዕኩልነት የማያምን መምህር አያስተምረኝም» የሚል የፀና አቋም የያዙት፤ ወጣትነት ወንጀል በሆነበትና የደርግን ጭፍጨፋ በመፍራት ለስደት የተዳረጉት ወጣት ዘምዘም ከኑሮ ጋር ግብግብ ይዘዋል። ፈረንጅ አገር « ዓለም ነው» ሲባል የሰሙት የተጋነነ ወሬ ውሸት ስለመሆኑ ሮም ከተማ ላይ በቀናት ውስጥ እውነታውን ያረጋግጣሉ።

ምንም እንኳ ታላቅ እህታቸው ወደ ጣሊያን እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ ቢፈጥሩላቸውም ምግብና መጠለያ እንዲሁም አልባሳትን ለማግኘት የግድ መሥራት እንዳለባቸው ያስገነዝቧቸዋል። እናም ቅምጥሏ የአቶ አህመድና የወይዘሮ ድሀብ ልጅ በምግብ አብሳይነትና በሞግዚትነት ለማገልገል የቤት ሠራተኛ ሆነው ይቀጠራሉ።

አዎ እናታቸው ገና በልጅነታቸው ያስተማሯቸው የባልትና ሙያ፣ ቤት አያያዝና ልጅ አስተዳደግ በእጅጉ ጠቅሟቸዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥም የሚሰሩት ምግብ ተወዳጅና ተመራጭ ይሆናል። «እጅሽን ከቁርጥማት ያድነው» አይነት አድናቆታቸውን ይገልጹላቸዋል። በሞግዚትነታቸውም ሩህሩህና ልጅ አፍቃሪ መሆናቸውም በእጅጉ ይወደድላቸዋል። በሌላም በኩል በትርፍ ጊዜአቸው ታይፕ እና አረፍተ ነገርን ወይም ቃላትን በአጭር የመጻፍ (shorthand) ትምህርት መከታተል ይጀምራሉ። 

በቤት ሠራተኛነትና በሞግዚትነት በሚያገኙት ገንዘብ እራሳቸውን በፀሐፊነት ከአሰለጠኑ በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል የቆዩበትን ሥራ በማቋረጥ በአንድ የስደተኞች ዕርዳታ ድርጅት ተቀጣሪ ይሆናሉ። በአጭር ጊዜ ውስጥም የፀሐፊነት ሥራቸውን በብቃት ይወጣሉ። በሥራቸው ያሳዩትን ቅልጥፍናና ትጋት የተመለከቱ የድርጅቱ አመራሮችም የድርጅቱን ሥራ በጉዳይ አስፈፃሚ መኮንንነት እንዲሰሩ የደረጃ ዕድገት በመስጠት ከጣሊያኖች እኩል ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያደርጋሉ።

በኢጣሊያ ቆይታቸው በተለይ ወደ ሥራ ዓለም ከመግባታቸው በፊት በተለያየ ምክንያት በመጠለያ እጦትና በርሃብ አለንጋ የመመታቱን የስደተኞችን ሕይወት ቀምሰውታል። ከእናታቸው የቀሰሙትን የሥራ ክቡርነት አስተሳሰብ የሕይወት ዘመን መመሪያቸው በማድረግ ከቤት ሠራተኛነት ተነስተው በአሥራ ዘጠኝ ዓመታቸው የዕርዳታ ድርጅቱን ከፍተኛ ኃላፊነት ለመሸከም ይበቃሉ። ይህም በመሆኑ ከጉዳይ አስፈፃሚ መኮንንነት በላይ የድርጅቱን ኃላፊ ወክለው ለመሥራትና አመራር ለመስጠትም ይበቃሉ። 

በሌላም በኩል ሊመረቁ ወራት ሲቀራቸው ቢያቋርጡትም የሆቴል አስተዳደር (ሆቴል ማኔጅመንትትምህርት መከታተል ጀምረው እንደነበር ያስታውሳሉ። የካቴድራሏ እምቡጥ፤ የመነኗ የመብት ተሟጋች ዘምዘም አንፃራዊ በሆነ መልኩ የተደላደለ ኑሮ ቢጅምሩም የእናታቸውን፣ የእህቶቻቸውንና የወንድሞቻቸውን እንዲሁም የአገራቸውን ናፍቆት ለማስታገስ ወደ አገራቸው መመለስ እንዳለባቸው ይወስናሉ። እናም የመሄዳቸውን ጉዳይ ኢጣሊያ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳውቀው አዲስ አበባ ይገባሉ።

ይሁን እንጂ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ አገራቸው የገቡት ስደተኛዋ ወይዘሪት ያላሰቡትና ያላለሙት አስደንጋጭ ችግር ይጋረጥባቸዋል። ቀደም ሲል ፈርተውት የወጡት ደርግ «ኢጣሊያን አገር በምትሠራበት የዕርዳታ ድርጅት ለወንበዴዎች ቪዛ እያዘጋጀት ትሰጣለች» በማለት ፓስፖርታቸውን ይነጥቋቸዋል። ይህም በመሆኑ ፓስፖርት አልባ የሆኑት ወጣት ተወልደው በአደጉበት ከተማ እንኳን እንደልባቸው ለመንቀሳቀስ ይሳናቸዋል። 

ቆፍጣናዋ ወጣት ግን የደርግ ጥርጣሬ መሠረተ ቢስ መሆኑንና ሰላማዊ ሰው መሆናቸውን በማስረዳት ይህንንም ኢጣሊያን አገር የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጠይቀው እንዲረዱ አቤት ይላሉ። አዎ ኤምባሲውም ዘምዘም ሰላማዊ መሆናቸውን ያረጋግጥና ፓስፖርታቸውን ያገኛሉ። በአዲስ አበባ የመቆያ ጊዜያቸውን በማሳጠር ወደ ሮም ይመለሳሉ። እንደተመለሱም ከኢጣሊያ እርቀው ለመሰደድ ይወስናሉ። «ዘምዘም» የሚለውን መጠሪያ ስማቸውን ቤት ውስጥ ይጠሩበት በነበረው ስማቸው በሕጋዊ መንገድ አስቀይረው «ዘሚ» በሚል አዲስ ስም ወደ አሜሪካን አገር ተሸጋገሩ። ከአምስት ዓመት የሮም ቆይታ በኋላ በሃያ ሁለት ዓመት ዕድሜያቸው አሜሪካን አገር የሎስ አንጀለስ ከተማ ነዋሪ ለመሆን ይበቃሉ።

ኮዝሞቶሎጂስቷ

እነሆ ወጣት ዘሚ የኑስ ዳግም ለስደት ቢዳረጉም የአገረ አሜሪካ የኑሮ ዘይቤ እምብዛም እንግዳ አልሆነባቸውም። የካቴድራል ተማሪ ስለነበሩም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችግር ስላልነበረባቸው ከሕዝቡ ጋር ለመግባባትም አላዳገታቸውም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢጣሊያን አገር ይሰሩበት በነበረው ድርጅት ተባባሪ በነበረው የካቶሊክ ወጣት ማዕከል በፀሐፊነት እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ ስለተፈጠረላቸው በሥራ ፍለጋም አልተንገላቱም። 

በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ከልጅነታቸው ጀምሮ በውስጣቸው ከሰረፀው ዝንባሌያቸው ጋር መገናኘት እንዳለባቸው ይወስናሉ፤ ከራሳቸው ጋርም ትግል ይገጥማሉ። እናም የሥነጥበብ አንዱ የሙያ ዘርፍ በሆነው በሥነውበት ጥበብ መማር እንዳለባቸው ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ። ጊዜ ሳይሰጡም የዝንባሌያቸው ባለቤት ወደሚያደርጋቸው የሥነውበት የትምህርት ተቋም በመግባት የሙሉ ጊዜ ተማሪ ይሆናሉ። ፍላጐታቸውን ለማሳካት በፅናትና በትጋት ትምህርቱን በመከታተላቸውም ሦስት ዓመት የሚፈጀውን ትምህርት በአንድ ዓመት በማጠናቀቅ በዲፕሎማ ይመረቃሉ።

የተፈጥሮ ውበት እንዴት እንደሚጠበቅ፣ እንዴትስ መንከባከብ እንደሚገባ፣ የተጐዳውንስ እንዴት ማስተካከልና ማስዋብ እንደሚቻል፣ ስለ ቆዳ እንክብካቤ፣ ስለፀጉር ውበት፣ ስለፀጉር ኬሚካል አጠቃቀም፣ ሳይንሱን በንድፈ ሃሳብ ደረጃ በሚገባ መቅሰም ቻሉ። ተግባራዊ ልምድ ለመጋራት ደግሞ በሎስ አንጀለስ ከተማ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑና ታላላቅ የውበት ሳሎን ካላቸውና የዘርፉ ሊቃውንት ከሆኑት እነ ዥዋን ዥዋን፤ እነ ጀምስ ጊብሰን፣ እነ ጀምስ ካናርና እና ሪኒ ዘንድ በመቀጠር በሙያው ያላቸውን ዕውቀት ያጐለብታሉ። 

ከውስጣዊ ዝንባሌያቸው ጋር በመገናኘት በተግባራዊ ሥራውም አቅማቸውን ያጐለበቱት የዚያ ጊዜዋ ወጣት በሁለት እግራቸው በሚገባ መቆማቸውን በፅናት በማመን «ኒያና ኢንተርናሽናል» የሚባል የውበት ሳሎን በሎሳንጀለስ ይከፍታሉ። ኒያ» የአረብኛ ቃል ሲሆን «መልካም መንፈስ፣ መልካም ዕቅድ…» የሚል ትርጓሜ አለውለስምንት ሰዎች የሥራ ዕድል ይከፍታሉ። በአጭር ጊዜ ውስጥም የወጣቷ ኢትዮጵያዊት የውበት ሳሎን በርካታ ደንበኞችን ያፈራል፤ ገበያውም ይደራል። ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውም ይጐለብታል። 

ከጥረታቸው ተጠቃሚ የሆኑት የሥነውበት ሙያተኛዋ ሥራቸውን የማጠናከራቸውን ያህል በፀጉር ኬሚካል አጠቃቀም፣ በቆዳ እንክብካቤና አያያዝ ላይ የስፔሻላይዜሽን ትምህርታቸውን በመቀጠል ስፔሻሊስት ያደርጋቸውን የምስክር ወረቀት ለመቀበል በቅተዋል። 

ለአሥራ አራት ዓመታት አሜሪካን አገር ሲኖሩ ቤተሰቦቻቸውን ከመርዳት ባይቆጠቡም በተለይ ደርግ ከወደቀ በኋላ አገራቸው በመግባት ከሚወዷት አገራቸውና ከሚያፈቅሯቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ብርቱ ፍላጎት ስለነበራቸው ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ያደርጋሉ። ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አሜሪካ ከመመለሳቸው በፊትም እትብታቸው ወደተቀበረባት አዲስ አበባ በመመለስ በሚችሉት ሁሉ ለአገራቸው ዕድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ የፀና አቋምና ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ። 

አገራዊ ትሩፋት

አዎ «ሰው ከተሰማራ እንደየስሜቱ በዋለበት ቦታ አይቀርም ማፍራቱ» እንዲሉ ሆነና በልጅነት የሙያ ዝንባሌያቸው በዕውቀት የታነጹትና በኢኮኖሚ አቅማቸው የደረጁት ወይዘሮ ዘሚ የኑስ «ማን እንዳገር» በማለት ከአስራ ዘጠኝ ዓመት በኋላ ጓዛቸውን ጠቅልለው በ1987.ም በሙሉ ፍላጐትና ከልብ በመነጨ ደስታ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ። 

ረዘም ያለ ጊዜም ሳይወስዱ የላቀ እውቀትና ዕውቅናን በተቀዳጁበት በሥነውበት (ኮስሜቶሎጂሙያ በአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን «ኒያና የውበት ሥራ የሥልጠና ማዕከል» የተባለ ትምህርት ቤት በመክፈት ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ያስመዘግባሉ። ለሰባ አምስት ወገኖቻቸው የሥራ ዕድል ከመክፈታቸው ባለፈም ትምህርት ቤቱን ለጊዜውም ቢሆን እስከአቋረጡበት 2004 .ም ድረስ ከስድስት ሺ በላይ የሥነውበት ባለሙያዎችን ማፍራት ችለዋል። በአስራ ስድስት ዓመት የትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሂደት ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ ዜጐቻችን ቢሆኑም ከናይጄሪያ፣ ከኬንያ፣ ከዛምቢያ… የመጡ ተማሪዎችንም በሙያው እንዲካኑ አድርገዋል።

«…እኔ ፈጣን ሥራ ፈጣሪ ነኝ፤ የፈጠራ ውጤቱን ተግባራዊ ከአደረጉ በኋላ የሥራ ዕድሉን ሌሎች እንዲቀጥሉበትና እንዲጠቀሙበት እየተውኩ በመውጣት ወደ ሌላ አዲስ የፈጠራ ሥራ ላይ ነው የማተኩረው፤ በአንድ ሥራ ላይ ብዙ ጊዜ ማጥፋት አያስደስተኝም…» የሚሉት የሥነ ውበት ጠቢቧ፤ ይህም በመሆኑ ከኒያና የውበት ሥራ ሥልጠና ማዕከል የተመረቁ ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ሠልጣኞቻቸው በቀሰሙት ትምህርት በመጠቀም በዕድገት ጐዳና በመገስገስ ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ። ከሁሉም በላይ የሙያ ልጆቻቸው አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮች ጭምር የሥነ ውበት ትምህርት ቤት መክፈት መቻላቸው ያስደስታቸዋል። የውበት ሳሎንና ስፓ እንዲሁም የባህል «ጭስ ቤትም» ከፍተዋል። አፍሪካውያን ተመራቂዎቻቸውም በየአገራቸው ውበት ሳሎንና ትምህርት ቤት ለመክፈት በቅተዋል። 

ኒያና የውበት ሥራ ሥልጠና ማዕከል ዓላማው በሙያው ለመሰልጠን የሚፈልጉ ወገኖቻችንን በማብቃት ተጠቃሚ እንደሆኑ ማድረግ የመሆኑን ያህል ለጊዜው ሥልጠናውን ቢያቋርጡትም በአጭር ጊዜ ውስጥ አደረጃጀቱንና ሥርዓተ ትምህርቱንም ከፍ አድርጐ እንደገና የመማር ማስተማሩን ሂደት እንደሚጀምር ይናገራሉ። የሥልጠና ማዕከሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በአደረገባቸው ዓመታት በተለይ ችግረኛ ወጣት ሴቶችንና በሴተኛ አዳሪነት ለተሰማሩ ወገኖች ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት ከችግራቸው እንዲላቀቁ በማድረግ የወገን አለኝታነታቸውን አረጋግጠዋል። በተጨማሪም ከሚሰጡት ሙያዊ ሥልጠና ባለፈ ኤች አይ ቪን በመከላከሉ ረገድ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አስተዋፅኦ አድርገዋል። እንዲሁም ወቅታዊ በሆኑ አገራዊ ችግሮች ላይም በንቃት በመሣተፍ በጐ ተግባራትን ፈጽመዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ የሙያው አፍቃሪዎችን በሥነውበት ሙያ ከማነፅ ባሻገር የውበትን ማራኪነት በመጠቀም «… በአይነቱ የተለየ በአገራችንም የመጀመሪያ የሆነ የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ባህልና አልባሳት የሚያስተዋውቅ አውደ ርዕይ በ1997 .ም አዘጋጅቼ በኤግዚቢሽን ማዕከል በሕዝብ እንዲታይ አደረኩ። ይህን በማድረጌም የአገራችንን አልባሳትና ቱባ ባህል አስተዋወኩ። የሸማ ሥራ ውጤትን ይበልጥ በማስተዋወቅ ሙያው የበለጠ እንዲስፋፋና ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻም አመላከትኩ። የአገሪቱንም ገፅታ ለመገንባት ሞከርኩ። የኤግዚቢሽኑን ውጤታማነትም በአጭር ጊዜ ውስጥ የአልባሳትን ተፈላጊነትና ተወዳጅነት ጨምሮ ለመመልከት አስችሎኛል…» የሚሉት የሥነውበት ምሁሯ በሌላም በኩል ኤግዚቢሽኑ ዛሬ እርካታን ለተጐናፀፉበት ታሪካዊ ምዕራፍ እንዳሸጋገራቸው ያስታውሳሉ።

የኦቲዝሟ «አምባሳደር»

በሌላ ህይወታቸው ደግሞ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ለመሆን የበቁት ሥራ ፈጣሪዋና ችግር ፈችዋ ወይዘሮ ዘሚ ከአሜሪካ ከመጡ በኋላ ልጃቸው የኦውቲዝም እክል እንዳለበት ያረጋግጣሉ። በዚህ ምክንያት ሕብረተሰቡ ስለኦቲዝም ማወቅ እንዳለበት ያሰባሉ። እናም በተደራጀ መልክ ያንን ማራኪ ኤግዚቢሽን በመጠቀም ለዛ በአለው የአነጋገር ብቃታቸው ስለኦውቲዝም ያወቁትን ያሳውቃሉ። መገናኛ ብዙኃንም የኦውቲዝሟን «አምባሳደር» ተከትለው ስለ ኦውቲዝም አስተጋቡ።

በእርግጥ ወይዘሮ ዘሚ የኑስ የኦቲዝም እክል ያለበትን ልጃቸውን አሜሪካን አገር ማስተማር እንደሚችሉ ያምናሉ። ግን ደግሞ ልጃቸው ከመሰል አቻዎቹ ጋር በአገሩና በወገኑ መካከል እንክብካቤና ትምህርት ማግኘት አለበት የሚል የፀና አቋም ይይዛሉ። ገና አዳጊ ወጣት በነበሩበት ወቅት የደርግን ጭፍጨፋና ሰቆቃ ፈርተው ቢሰደዱም በልጃቸው ምክንያት ዳግም መሰደድ እንደሌለባቸው ይወስናሉ። እናም «…ልዩውንና ፈታኙን የኦቲዝም መጋረጃ በመግለጥ ለምን የብርሃን ጮራ እንዲፈነጥቅ አላደርግም…?» በማለት ወላጆች ለልጆቻቸው ትልቅ ነገር እንደሚመኙላቸው ሁሉ በኦቲዝም ምክንያት ልጅን በእግር ብረት ማሰር ምን ያህል ዘግናኝና ኢሰብአዊ መሆኑን በየአጋጣሚው ማስተማሩን በትጋት ተያያዙት። ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶም የሕዝብ ንቅናቄ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። መንግሥትም ድጋፉን ቸራቸው። እናም የሥነ ውበት ሥራ ሥልጠናውን እያካሄዱ በነበረበት ወቅት በተጓዳኝ የኦውቲዝምን ጉዳይ ወደ አንድ ታላቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ያሸጋግሩታል።

«ጐሽ ለልጇ ስትል ተወጋች» እንዲሉ ሆነና ወይዘሮ ዘሚም አገራዊ አጀንዳቸውን ዕውን ለማድረግ ሰለቸኝና ደከመኝ ሳይሉ እልክ አስጨራሽ ውጣ ውረዶችን በማለፍ «ኒያ ፋውንዴሽን» የሚል ተቋም መሰረቱ። በስሩ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካም የመጀመሪያው የሆነ «ጆይ የኦውቲስቲክ ልጆች ማዕከል» የተባለ ተቋምም አቋቋሙ። የአያሌ ኦውቲስቲክ ልጆችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚለውጥ፤ የእርሳቸው ቢጤ እናቶችን የሕይወት ዘመን ሰቀቀንና ሐዘን የሚቀርፍ ማዕከል በማቋቋም «አበጀሽ» ተባሉ።

እነሆ ማዕከሉ እ..አ በ2002 ከተመሠረተ በኋላ ሥራውን የጀመረው የወይዘሮ ዘሚን ልጅ ጨምሮ በሌሎች ሦስት የኦውቲስቲክ ልጆች ነው። « …የእኔ አስተማሪዎች ልጄና በማዕከሉ የተቀበልኳቸው ሌሎች ሕፃናት ናቸው…» የሚሉት ወይዘሮ ዘሚ የአላቸውን የንባብ ባህል በመጠቀም፤ ጥናትና ምርምርም በማድረግ የማዕከሉን ተቋማዊ አደረጃጀት አሳድገውታል። እነሆ ዛሬ በማዕከሉ የሚገለገሉ የኦውቲስቲክ ልጆች ቁጥር ሰማንያ ደርሷል። «…ኦቲዝም እንከን እንጂ በሽታ ወይም ሕመም አይደለም…» የሚሉት የማዕከሉ መሥራች፤ ለእንከኑ ፈውስ የሚገኘውም የሕክምና መድኃኒት በመውሰድ ሳይሆን ይልቁንም ለልጆቹ ልዩ የትምህርት ዘዴ በመዘርጋትና ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም የተለየ እንክብካቤ በመስጠት እንደሆነ በአፅንኦት ይናገራሉ። ማዕከሉ ልዩ የማስተማር ዘዴና ጨዋታ፣ ከስሜት ሕዋሳት ጋር የሚገናኝ ፊዚዮ ቴራፒ በመጠቀም መፃፍ እንዲለማመዱ የሚያስችሉ ስዕሎችና ቀለማት እንዲለዩ እንዲሁም ዓይን፣ እጅና አዕምሯቸውን አቀናጅተው ስዕል እንዲሰሩ፣ እንዲነጋገሩና እንዲግባቡ መጠነ ሰፊ ጥረት ያደርጋል። ለኦውቲስቲክ ልጆች በሚመች መንገድ በቀላሉ ማንበብና መፃፍ እንዲችሉ የሚያደርግ በአማርኛና በእንግሊዘኛ የሚሰራ አቡጊዳ ፎኔቲክስ በመፍጠር የባለቤትነት ማረጋገጫ በመጠባበቅ ላይም ይገኛሉ። በማዕከሉ ተጠቃሚ የሆኑት የኦውቲስቲክ ልጆች በዚህ ቴክኖሎጂ ማንበብና መፃፍን ፣አንብበው መረዳትና መግባባትን ችለዋል። እየቻሉም ነው።

የወይዘሮ ዘሚ ጥረትና ውጤት በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። መንግሥትም የጀመሩትን ጥረት በአገሪቱ ተደራሽ እንዲሆን ድጋፉን አልነፈጋቸውም። እሳቸውም የኦውቲዝም ልጆች መምህራንን ከማሰልጠን ባለፈ በአዲስ አበባ አስር የመንግሥት ትምህርት ቤቶች አንድ አንድ ክፍል በማዘጋጀት የኦውቲስቲክ ልጆች በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ አስችለዋል። በኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶችም የኦውቲዝም እክል ያለባቸው ሕፃናት ቀን ወጥቶላቸው የተማሪነትን ወግ አግኝተዋል።

ወይዘሮ ዘሚ ለኦውቲስቲክ ልጆች ብቻ ሳይሆን እንደእርሳቸው ልባቸው ለሚደማ እናቶችም አለኝታ ሆነዋል። በእርግጥ የኦውቲስቲክ ልጆች ማዕከል ተቋቁሞ እክል ያለባቸውን ልጆች ለመንከባከብና ለማስተማር በመብቃታቸው እርካታቸው ወሰን የለውም። ትልቁን ደስታቸው የሚያገኙት ግን የአዲስ አበባ አስተዳደር የሰጣቸውን መሬት ከቦሌ ክፍለ ከተማ ከወረዳ አስር ተቀብለው ዋናውን «የኦውቲዝምና ልዩ የዕድገት ፍላጐት ያላቸው ልጆች ማዕከል» ተገንብቶ የኦውቲስቲክ ልጆች ከአሁኑ የበለጠ ልዩ እንክብካቤና ልዩ የትምህርት ዘዴ ተጠቃሚ ሲሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ።

የሕይወት ስንቅ

«…የምችለውን በጐ ነገር ሁሉ ማድረግ ያስደስተኛል» የሚሉት የዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ ዘሚ የኑስ ዛሬ ደግሞ «ጋዜጠኛ» ሆነው «ያገባኛል» የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም በፋና ብሮድካሲንግ ኮርፖሬት ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም ጀምረዋል። በዚህ ፕሮግራም በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረክ ከፍተው ሰናይ ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

በሌላም በኩል ለኦቲዝም ጉዳይ የተለየ ትኩረት ሰጥተው የመንቀሳቀሳቸውን ያህል ለኦውቲስቲክ ልጆች እናቶችም በአለኝታነት በመቆም በሥራ ፈጣሪነት ቆመዋል። ለዚህም ልጆቻቸው ጆይ የኦውቲስቲክ የልጆች ማዕከል ቢገቡም ባይገቡም በተናጠልም ሆነ በማደራጀት የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችለዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ መካኒሳ አካባቢ «ስንቅ ቤት» የሚል ፕሮጀክት ነድፈው እውን በማድረግ በተለይ ዕድሜያቸው እስከ ሃያ አራት ዓመት ያሉ ወጣት ሴቶች መጠጊያና የሕይወት ክህሎት ዕውቀት ደሀ ሆነው ወደ ሴተኛ አዳሪነት እንዳይገቡ አርአያነት ያለው ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

ፕሮጀክቱ በተለይ በተለያየ ምክንያት «ወደ አረብ አገር እንሄዳለን» በማለት ትዳራቸውን ትተው ከወላጆቻቸው ተነጥለው እየጠፉ የሚመጡ ወጣት ሴቶች ሥልጠና ከመውሰዳቸው በፊት ወደ ትዳራቸው እና ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ካልሆኑ በዝንባሌያቸው መሠረት በቤት አያያዝ፣ በምግብ አዘገጃጀት፣ በፅዳት አጠባበቅ፣ በልብስ ንጽህናና በሌሎችም ተያያዥ ሙያዎች ላይ ስልጠና በመስጠት የሕይወት ዘመን ስንቅ እንዲቀስሙ ያደርጋል። እስከ አሁን አንድ መቶ ወጣት ሴቶችን ያሰለጠኑ ሲሆን፤ ወደፊትም አምስት መቶ ወጣት ሴቶችን በማሰልጠን የትም ቦታ የሚጠቅም ትምህርት እንደሚሰጧቸው ይናገራሉ። 

እንደማጠቃለያ

በነባራዊው ዓለም ውስጥ እውን የሆነውን የሕይወት ውጣ ውረድ በፅኑ መንፈሳዊ ጥንካሬ፤ ወሰን በሌለው የሥራ ትጋት፤ ለዝንባሌያቸው ተገዝተው የሥነውበት ምሁር በመሆን ለአያሌ ወገኖቻችን ሙያቸውንና ዕውቀታቸውን ለማካፈል በቅተዋል። በሥራ ፈጣሪነትና በችግር ፈቺነትም ተሰልፈው ስኬታማ ሆነዋል። 

ወይዘሮ ዘሚ የኑስ ዛሬም ሮጠው አልደከሙም፤ ሰርተውም አልታከቱም። የበለጠ ሰብአዊና ሕዝባዊ አገልግሎት ለመስጠት ዛሬም ፅናት ባለው መንፈስ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። እየሰጡት ያለው አገልግሎት ወገን ተኮር በመሆኑ «ጋን በጠጠር ይደገፋል» እንዲሉ ማንኛውም አቅም ያለው ሰው የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ «አለሁልሽ» ሊላቸው ይገባል። ምክንያቱም የበጐ ተግባር ምሳሌ የሆኑት ወይዘሮ ዘሚ የኑስ እየተገበሩት ያለው ሕያው ተግባር የጋራ አገራዊ ጉዳይ ነውና።

The post ዘሚ የኑስ – የኦቲዝሟ «አምባሳደር» appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>