አንድ ለ3 ዓመት አብራኝ ለዘለቀች ፍቅረኛ አለችኝ፡፡ ይህቺ ልጅ አፈር ስላት ውሃ ውሃ ስላት ደግሞ አፈር እየሆነች መከራዬን አበላችኝ፡፡ እወድሃለሁ ትላለች፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ በስልኬ እንዳትደውል ትላለች፡፡ እሺ ብዬ ዝም ስል ቤቴ ድረስ መጥታ ‹‹አንተ ጨካኝ በእኔ አስችሎህ እኔኮ ያላንተ አይሆንልኝም›› ትላለች፡፡ የመለየት ሐሳብ ሳነሳ ከእኔ ተለይታ መኖር እንደማትችል፣ ከተለየኋት ሥራዋን ጥላ ከሀገር እንደምትጠፋ ትናገራለች፡፡ አብሮ ስለመኖር ሐሳብ ሳቀርብ ‹‹ዕድሜ ልኬን ከአንተ ጋር ስጨቃጨቅ ልኖር…›› እስከማለት ደርሳ ታውቃለች፡፡ የእኔ ፍቅር ደግሞ ከዕለት ዕለት እየጨመረ መጣ፡፡ ሳትደውል ወይም ሳትመጣ ከቀረች ጭንቁን ስለማልችለው፣ በምትሰራበት የቤተሰቧ ሱቅ ዞር ዞር ብዬ ደህንነቷን አረጋግጣለሁ፡፡ እንዲያው አንዳንዴ መስተፋቅር ምናምን የሚሉትን አድርጋብኝ ይሆን እያልኩ አስባለሁ፡፡ ጓደኞቻችን እንኳ ሁኔታችንን አውቀው ‹‹ዛሬ ሰላማዊ ነው››፣ ‹‹ዛሬ የጦር ውሎ ነው›› ምናምን የሚሉት ፈሊጥ አላቸው፡፡ አንዳንዴ ድህነቴን ጠልታ ይሆን ብዬ አስብና በዚህ 3 ዓመት እንኳ ያመጣሁትን ለውጥ አይታ በቅርቡ ትልቅ ደረጃ እንደምደርስ ታስባለች ብዬ ራሴን አፅናናለሁ፡፡ የእኛ ነገር በአጠቃላይ ግራ ያጋባኛል፡፡ እኔ የምላችሁ ይህቺ ልጅ ታፈቅረኛለች ብዬ እርግጠኛ ለመሆን ወይም አታፈቅረኝም ብዬ ራሴን ለመለያየት ምን አድርግ ትሉኛላችሁ? ውሳኔ ሰጥቼ መንገዴን ማስተካከል የሚያስችል ምላሽ ስጡኝ እባካች፡፡
ቲ ነኝ
ጠያቂያችን ቲ ለሰላምታህ አፀፋዊ ምላሻችንን እየሰጠን በቀጥታ ወደ ምላሻችን እናምራ፡፡
ከጽሑፍህ መረዳት እንደቻልነው፣ ፍቅረኛህ አንዳንዴ እንደምትወድህ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደማትወድህ ትነግርሃለች፣ ይሄም የእሷን እውነተኛ የፍቅር ስሜት እንዳትረዳ አድርጎሃል፡፡ ስለ እውነተኛ አፍቃሪ መለያ መንገዶች ጥቆማና ማድረግ ስላሉብህ ነገሮች ገለፃ ከማለፋችን በፊት ስለ ፍቅር አንዳንድ ስነ ልቦናዊ ትንተናዎችን እናቀርብልሃለን፡፡
አዕምሮአችን እያንዳንዱን ነገር የሚረዳው በምስሎች ነው፡፡ ለምሳሌ አዕምሮህ ውስጥ አበባን የሚወክል ምስል አለ፡፡ ስለሆነም አበባ ስታይ የተመለከትከው ነገር በአዕምሮህ ካለው ምስል ጋር የሚመሳሰል ሲሆን ያ ነገር አበባ እንደሆነ ትረዳዋለህ፡፡ ይህ የሚሆነው ለቁሳዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን ሐሳቦችም ነው፡፡ አዕምሮአችን እያንዳንዱን ሐሳብ ለመገንዘብ ምስሎችን ይጠቀማል፡፡ ለምሳሌ ሰላም የሚለውን ሐሳብ የምንረዳው ለሐሳብ ባስቀመጠው ምስል መሰረት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰዎች በሐሳብ የማይስማሙት- የአንዱ ሐሳብ አንዱ የሳለበት መንገድና ሌላው የሳለበት መንገድ ስለሚለያይ፡፡ ይህን ጉዳይ ወደ ፍቅር ስናመጣው ደግሞ፣ አዕምሮአችን ፍቅር የሚለውን ሐሳብ የሚረዳው ምስልን በመጠቀም ነው፡፡ በስተመጀመሪያ ፍቅር የሚለው ሐሳብ በሆነ ምስል ይወከላል፡፡ ከቆይታ በኋላ አንዲትን ሴት በተደጋጋሚ ስታያት ወይም መቀራረባችሁ ሲጨምር፣ ፍቅር የሚባለው ሐሳብ በልጅቱ ምስል እየተተካ ይሄዳል፡፡ ያኔ ነው እንግዲህ ፍቅር ያዘን የሚባለው፡፡ ስለፍቅር ባሰብን ቁጥር የልጅቱ ምስል እየመጣ ድቅን ይልብናል፡፡ ስለልጀቱ በተደጋጋሚ ባሰብን ቁጥር፣ አዕምሮአችን ያለውን ፍቅርን የሚወክለው የልጅቱ ምስል እየጎላና እየደመቀ ይመጣል፡፡ የፍቅራችን መጠንምእየጨመረ ይመጣል፡፡ እንደ ምሳሌ ያንተን ብንወስድ፣ በደብዳቤህ እንደነገርከን ከልጅቱ ጋር ሶስት ዓመት ቆይታችኋለ፡፡ ይህ የሚነግረን ደግሞ በአንተ አዕምሮ ውስጥ ፍቅር የሚባለው ሐሳብ በልጅቱ ምስል ተወክሏል ማለት ነው፡፡ እየቆያችሁ ስትመጡና ስለሷ ብዙ ስታስብ ደግሞ ፍቅርህ እየጨመረ ሄዷል፡፡
ይህንን ትንተና ወደ አንተ ሁኔታ ስናወርደው ያንተዋ አፍቃሪ እወድሃለሁ ብላህ ትወደኛለች ብለህ በተረጋጋህበት ሰዓት አልወድህም ትልሃለች፡፡ ይህ ደግሞ ስለ ልጅቱ ብዙ እንድታስብ ያደርግሃል፡፡ ስለልጅቱ በተደጋጋሚ አሰብክ ማለት ደግሞ አዕምሮህ ውስጥ ያለው የልጅቱ ምስል እየጎላና እየደመቀ ይመጣል ማለት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አትወደኝም የሚል ድምዳሜ ልትደርስ ስትል እንደምትወድህ ትነግርሃለች፡፡ ይህ ሁኔታ ደግ አሁንም ስለ ልጅቱ የማሰብ ነገር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያደርገዋል፤ ማሰብህ በተራው አዕምሮህ ውስጥ ያለውን እና ፍቅር የሚወክለውን የልጅቱን ምስል እንዲጎላ ብሎም ፍቅርህ እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡ በአጠቃላይም የልጅቱ የዛሬ እወድሃለሁ፣ የነገ አልወድህም፣ የከነገ ወዲያ እንደገና እወድሃለሁ ወዘተ… ተግባር አንተን ስልልጅቱ በብዛትና በተከታታይ እንድታስብ አድርጎሃል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ አዕምሮህ ፍቅርን የሚወክልበት ምስል በጣም በማጉላቱ ያንተን ፍቅር በእጅጉ ጨምሮታል፡፡ በዚህም አለ በዚያ፣ ልጅቱ አውቃም ይሁን ሳታውቅ አንተን እንድታፈቅራት የሚያደርጉ ተግባራት ከውናለች፣ አንተም በጣም አፍቅረሃታል እንጂ መስተፋቅር ማድረጓን የሚያሳይ ምንም መረጃም ሆነ ማስረጃ የለም፡፡ በመሰረቱ አብሮ ለመኖርም ሆነ በፈቅር ለመዝለቅ ያንተ ፍቅር ብቻ ሳይሆን የእሷም ፍቅር ያስፈልጋልና ቀጥሎ ደግሞ እርሷ ታፈቅረኛለች ወይ የሚለውን ጥያቄ እንዴት መመለስ እንደምትችል አቅጣጫ ልጠቁምህ፡፡
የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚያብራሩት ፍቅር ሶት መዋቅሮች አሉትት፡ አንደኛው ቅርብ ግንኙነት የሚባለው ሲሆን ይህም የመቀራረብ፣ አብሮ የመሆን፣በጋራ ነገራትን የመከወን፣ የመገናኘት፣ የመተያየት እና የመሳሰሉ ፍላጎቶችንና ክንዋኔዎችን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጥልቅ ስሜት ሲሆን የመፈላለግ፣ የመሳሳም፣ በተፈቃሪው ሁኔታ የመሳብ፣ የወሲህ እና ወዘተ ስሜቶችን የሚያካትት ነው፡፡ ሶስተኛው መስዋዕትነት ሲሆን አንዱ ለሌላው የማሰብ፣ የመጨነቅ፣ በችግር ጊዜ የመድረስ፣ ከራስ ፍላጎት ይልቅ ለሌላኛው ፍላጎት ቅድሚያ የመስጠት፣ ፍቅርን ዘላቂ ለማድረግ አስፈላጊውን ማድረግ/ ለማድረግ መፈለግ፣ ወዘተ የሚይዝ ነው፡፡
ሙሉ ፈቅር የሚባለው ደግሞ እነዚህን መዋቅሮች የሚያሟላ ሲሆንነው፡፡ ስለሆነም ቲ የምታፈቅራት ልጅ ታፈቅረኛለች ወይ የሚለውን ለመመለስ፤ መከወን ያለብህ ተግባር በልጅቱ ውስጥ እነዚህ ሶስት የፍቅር መዋቅሮች መኖቸውን/መታየታቸውን ማረጋጥ ነው፡፡ አንተ ከእሷ ጋር ለመሆን ጥረት ታደርጋለህ፣ እሷስ አካንተ ጋር ለመሆን የመጣር ሁኔታዋ እንዴት ነው? አንተን የመፈለግና አንተ ጋር የመሆን ስሜቷስ ፍቅረኛህ ስትጠፋብህ ሱቋ ድረስ ትሄዳለህ? እሷስ ስትጠፋባት አንተን ለማግኘት ምን አይነት መስዋዕትነት ትከፍላለች? አንተን ለመደገፍ ምን ያህል ትጥራለች? በችግር ጊዜህ የመድረስ ሁኔታዋና ፍጥነቷ የት ድረስ ነው? እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ለራስህ በመጠየቅና ተግባራቶቿን በመመዘን ልጅቱ ታፈቅረኛለች አታፈቅረኝም የሚለውን መለየት ትችላለህ፡፡ ነገሩ እንዲህ እደምፅፍልህና እንደምታነበውም ቀላል አይደለም፡፡ ይልቁንም ትልቅ ሥራንና አስተዋይነትን የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ ጊዜ ወስደህ ቁጭ በልና ሶስቱን መዋቅሮች ወረቀት ላይ ፃፍ፡፡ እያንዳንዱን መዋቅር እንዴት መለካት እንደምትችል በጥልቀት አስብና በመዋቅሩ ስር መለኪያ ጥያቄዎችን ወረቀቱ ላይ አስፍር፡፡ በመቀጠል በአፍ የምትነግርህን ሳይሆን ተግባራቷን አጥና፡፡ ከጥናትህ በመነሳት በእያንዳንዱ መዋቅር ስር ያለፈችባቸው ላይ / ምልክት፣ ያላለፈችበት ላይ የX ምልክት አስቀምጥ፡፡ ምሳሌ ሰጥቼ ላስረዳህ፡፡ የፍቅረኛህን የመስዋዕት መዋቅር ለመመዘን ‹‹በችግሬ የመድረስ ሁኔታዋ እንዴት ነው?›› የሚል ጥያቄ አዘጋጅ፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ስልክ ደውልና አሞኝ ቤቴ ተኝቻለሁ ብለህ ንገራትና በቀጣይ የምታደርገውን ተግባር ተመልከት፡፡ ወደ ቤትህ መጥታ መንከባከብ፣ ያን ካልቻለች ደግሞ ስልክ እይደወለች ታከምክ? መድሃኒትህን ወሰድክ? ምግብ በላህ? ወዘተ አይነት ክትትል ካደረገች ይህንን ካልቻለች ደግሞ ሰዎችን በመላክ ስላንተ ሁኔታ ክትትል ካደረገች፣ ወዘተ በጥያቄው ትይዩ የ/ ምልክት ታደርጋለህ፡፡ የማታደርግ ከሆነ ደግሞ X ምልክት ታደርጋለህ ወይም ሌላ መመዘኛ (ለምሳሌ ስራህ ላይ ያጋጠመህን ችግር መንገር) በመጠቀም ለጥያቄህ ምላሽ ለማግኘት ትሞክራለህ፡፡ በተመሳሳይም እያንዳንዱን ጥያቄ በዚህ መልኩ ትመስንና በስተመጨረሻ አጠቃላይ ምዘነሃን በማስቀመጥ ትወደኛለች ወይም አትወደኝም ወደሚል ድምዳሜ መድረስ ትችላለህ፡፡
እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ልጠቁምህ፡፡ አንደኛ ለአዘጋጀኸው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት እሷን አትጠይቅ፡፡ ይልቁንም ከምታወራውና ከምትሰራው የራስህን ፍርድ/ግምት ውሰድ፡፡ ሁለተኛው ነገር የእሷን ሁኔታ ስትገመግም/ስትመዝን ነገራትን ሁሉ ልክ እንዳንተ ካደረገች መመዘኛውን እንዳላለፈች ከመቁጥር ተቆጠብ፡፡ ምክንያቱም የአንተ እና የእሷ ፍቅር አንድ ላይሆን ይችላል፡፡ ወይም እሷ የፍቅር መግለጫ የምትለው ተግባርና አንተ የፍቅር መግለጫ የምትለው ተግባር የተለያየ ሊሆን ይችላልና፡፡ ለምሳሌ አንተ ፍቅረኛህ ስትጠፋብህ ስራ በቦታዋ በመሄድ እሷን ለማየት መስዋዕት ትከፍላለህ፡፡ በተመሳሳይ አንተ ስትጠፋ እሷ ያንተ የሥራ ቦታ ስላልመጣችና ስላላየችህ መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ አይደለችም አትበል፡፡ ይልቁንም መስዋዕት መክፈሏን የሚያሳዩ ሌሎች ተግባራትን ተመልከት፡፡
ውድ ጠያቂያችን ለሰጠኸን ጥያቄ በቂ ምላሽ እንደሰንህ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን አንድ አብይ ነገር እናንሳ፡፡ በፅሑፍህ እንደገለፅከው የልጅቱ ባህሪ ይለዋወጣለ፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ አንድን ሁኔታ ለማረጋገጥ ስትሞክር በአንድ ጊዜ ባህሪዋ ብቻ መመዘን ወደተሳሳተ ድምዳሜ ሊወስድህ ይችላል፡፡ ስለሆነም ለአንድ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ምዘናህን በሁለትና ከዛ በላይ በሆኑ መለኪያዎች ለካ ባይ ነኝ፡፡ በስተመጨረሻ መልካም የለውጥ እና የፍቅር ጊዜ እየተመኘኹልህ እሰናበትሃለሁ፡፡ ቻው!
The post Health: ግራ የተጋባ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ነኝ፤ እንደምታፈቅረኝ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንደምችል ጠቁሙኝና ልወስን! appeared first on Zehabesha Amharic.