Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የመሬት –መስኮት፤ የሰማይም –በር ነው ተስፋ፤ –ሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

ተስፋ በሞግዚት አይገኝም ወይንም በሞግዚት አይተዳደርም የድርሻን በመወጣት – እንጂ። እኔ ተስፋ ፈላጊዋ ተስፋዬን ለማግኘት ተስፋዬን ለማስጣት ከሚተጉት ማናቸውም ጉዳዮች ጋር መፋለም ግድ ይለኛል።

ከሥርጉተ ሥላሴ 17.05.2015 / ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ /

„መዳህኒቴ፡ እና፡ ክብሬ፡ በእግዚአብሄር፡ ነው፤ የረድኤቴ፡ አምላክ፡ ተስፋዬም፡ እግዜአብሄር፡ ነው።“/ መዝመር 61 ቁጥር 7/

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 02.023.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

ወራቱን አላስታውሰውም „ግንቦት ሆይ“ የሚል ጹሑፍ ከዚኽው ከዘሃበሻ አግኝቼ አንብቤ ነበር። በወቅቱም መልሱን ጽፌ ነበር። የከተማ ሽምቅ ውግያም ሆነ ተናጠላዊ የበቀል ወርክሾፕ ለእኔ የማይመቸኝ ስለነበር። ነገር ግን ቀደም ብሎ የእኔ ሌላ ጹሑፍ በወጣልኝ ባላተራራቀ ጊዜ ስለነበር ወረፋ የሚጠብቁትን ስለተጋፋ – አልወጣም። ስለዚህም ዘሃበሻንም ተወቃሽ አያደርገውም። ነገር ግን በራዲዮ ፕሮግራሜ – ሰርቸዋለሁ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ወጣት ጃዋርን ይቅርታ የጠዬቀ ጹሑፍ ከረንት ላይ አነበብኩኝ። እርእሱን አላስተውሰውም። በህይወቴ አንብቤ ያልገባኝ የመጀመሪያው ጹሑፍ ነበር። ስለሆነም ከሥር ያሉትን አስተያዬቶችን ማንበብ ግድ ስለነበር እንደ እኔ ያልገባቸው ሰዎች መኖራቸውን ሳገኝ ብቻዬን አለመሆኔን አረጋገጥኩኝና – ተጽናናሁ።

የገጣሚ ወጣት ሄኖክ የሺጥላ ሥነ ግጥም መጸሐፉን ወዳጄ በገንዘቧ ገዝታ ልካልኝ በውስጡ መደዴ ያልሆኑ ረቂቅ ግጥሞችን – አንብቤያለሁ፤ መግቢያው እጅግ ጥልቅ ትንተና ኖሮት የመጸሐፉ እርእሱ ግን በፍጹም ሁኔታ ያልተመቸኝ ነበር። እስካሁን ድረስ – አልገባኝም። ገዝታ ለላከችልኝ እህቴም ነግሬያት ነበር። በወቅቱ አድናቆታቸውን የገለጹለት ታዋቂና ተደማጭ ወገኖቼን ሳስብ ከእኔ የተሻለ ግንዛቤ እንዳላቸው ተረዳሁ። የሆነ ሆኖ አሁንም የሥነ ግጥሙ መጸሐፍ እርእስ አልገባኝም ብቻ ሳይሆን አልተመቸኝም።

ባለፈው ሳምንት ታናሼ በዕድሜ እንጂ በፖለቲካ ደረጃ ወይንም በሥነ ግጥም መክሊት ማለቴ አይደለም ደረጃዬ ከእሱ ጋር ለመመጠን ብዙ መሥራት እንደ አለብኝ  በሚገባ አውቃለሁኝ። ወንድም ገጣሚ ሄኖክ የሽጥላ ፌስ ቡኩ ላይ የለጠፈውን ዘሃበሻ ላይ አነበብኩኝ። ገብቶኛል። ስለዚህም መልስ ልሰጥበት ወደድኩኝ። ተስፋ ሳይኖር ተስፋ መቁረጥ: የተስፋ ቢሶች ተስፋ ( ሄኖክ የሺጥላ )“ http://www.zehabesha.com/amharic/archives/41302

ወጣትነት በራሱ ተስፋ ነው አባቱ! አንተ በራስህ ለትውልዱ የተስፋ ቤተኛ ብቻ ሳትሆን የተስፋ መሪም ነህ – እኔን ሲገባኝ። አንተ አኮ ደረጃህ ከፍ ያለ ብቻ ሳይሆን የተደማጭነትህ ዕሴትም ከእርከኑ በላይ። ስለምን? ተስፋ ስለሆንክ። ስለዚህም ክብር ስጠው። እግዚአብሄር አምላክ ዬሥነ ጥበብ ማዕደኛ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ያንተን ያህል ግርማና ሞገስ ያላገኙ ብቁዎችም እንዳሉ ማሰብም ያለብህ ይመስለኛ። እንዲሁም አንተ በምትገኝባቸው የህዝብ አደባባዮች በዕድሜ፣ በዕውቀት – ደረጃ፤ በተምክሮ ልቅና የሚበልጡህ ከመቃጫቸው ብድግ ብለው አቀባባል ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሁለመናቸውን ለአንተ ለግሰው መንፈሳቸውን ይሸልሙኃል። አድማጭ ማግኘት ነው የሥነ ጥበብ ሰው ሃብቱ በለው ህልሙ፤ ህልሙ በለው ድሉ። „ፍቅር“ ለዛውም የህዝብ ሲታደሉት ብቻ የሚገኝ ዕንቁ ነው – ለመንፈስ። ሥነ ጥበብ ከነታዳሚዋ በሯን በዚህ ቀንበጥ ዕድሜው የከፈተችለት ዕድለኛ ወጣት እኮ ነህ። ልዑል እኮ ነህ አንተ – ለዘመኑ። ሥጦታውን፤ አጋጣሚውን ሆነ ተደማጭነቱን አታቅልለው። በዕድሜያቸው የአንድ ስንኝ ዘለላ ትንፋሽ አንደበት መስኮት አጥተው የቀሩ ሊቃናት ዓለማችን ነበራት – አላትም። በህይወት እያሉ ባሊህ ባይ አጥተው ግን ካለፉ በኋላ ዓለም የምትዳደርበት ሥነ ፈለግ ሰርተው ሸልመውን – ሄደዋል።

ከዚህ አንፃር ሲታይ አንተና መክሊትህ ወፍ ያወጣችሁ የሥነ ጥበብ ዕድላም ናችሁ። ከእኛ አንድ ምሳሌ ላንሳልህ ሊቀ ሊቃውንቱ ጎመራው ኃይሉ ሥነ ግጥምን ጻፈው ከምልህ ፈጠረው ብልህ ይቀለኛል – ወንድምአለም። ጠረኑ ፈውስ ነበር። መንፈሱም ድህነት፤ ግን ምን አደረግንለት …. ትውልድን ገንብቶ አለፈ – ክልትምትም እንዳለ – በስደት። …. አንዲት ካሌንደር በስሙ አሳተምንለትን? ስንት ሰው ከመቀመጫው ተነሳለት? ለመሆኑ የዛን ሊቀ ሊቃውንት አራትዓይናማ ታሪክና ሥራውን ትውልዱ ያውቀዋልን? የሚመጥን ዕውቅና ሰጥተነው ነበርን? /ሲዊዲኖችንና ፍራንክፈርቶችን አይመለከትም/ እነሱ የሚችሉትን ክብርና ሞገስ ሰጥተውታልና። እውነቱን ልንገርህ እኔ ግልጽና ቀጥተኛ ሴት ነኝ። የሚሰማኝን ገቨር ሳልሻ ነው የምጽፈው። እሱና አንተን ስመዝነው ያንተው የገነት ያህል ነው፤ እሩቅ – ፈጣን ክብርህ እውቅናህና ደረጃህ። ሊቁን በአካልም አውቀዋለሁ። በብቃት ደግሞ አንተና ሊቀ ሊቃውነቱ የሥነ ግጥም አባት ከቁራጩም – አትደረስም። ተተኪ ቀርቶ አምሳያ የለውም። የሥነ ጥበብ ቅኔ ቁርባን ነበር። እሱ እንደ አንተ ዕድሉ አልገጠመችም ነበር። የተዘጋ ዕንቁ!

አሁን ወደ ነጥቤ ልመልስህ እናትዬ – እኔ እንደሚገባኝ ሥነ ጥበብ ህዋሷ ተስፋ ነው። ተስፋ ቢስ የጥበብ ሰው ምድር አፍርታ አታውቅም። የሥነ ጥበብ ቤተኛ ተስፋው ለራሱ ብቻ አይደለም – እእ። ለዕልፍ ተስፋ ነው የሚሆነው። ተስፋውን ማብቀል የሚችለው ደግሞ ሞግዚት ሳያሻው እራሱ ተግቶ በተሰጠው ጸጋ ለተስፋው ሲማስን ብቻ ነው። ሥነ ጥበብ ትንፋሹ ርትህ ነው። የርትህ ሚዛን ሲወላገድ ገብቶ ይማገዳል – መቆስቆሻ አይሻምና።

እናትዬ – ተስፋ ያለው ተስፋውን ያገኛል፤ ተስፋውን ያሾለከ ደግሞ ተስፋው ቀርቦ ፈቃድ ቢሰጠውም – ይሰወርበታል። እኔ እራሴ  ለእኔ ተስፋ ነኝ። በሌላ በኩል ተስፋን ለማግኘት ተስፋ መሆን መቻልም ይቻላል። ሌላ ማገዶ ሳይፈልጉ። የግድ የፖለቲካ ድርጀት አባልነት ወይንም የማህበር አባልነት አይጠይቅም። ብዙ መንገዶች አሉ ተስፋን ለማግኘት ስልተ – ገብ፤ የተመቸውን መርጦ መሞከር፣ አልሳካ ሲል ደግሞ ሌላ መተለም። እሱም አልሆን ካለ አዲስ ሃሳብ አፍልቆ ወይንም ፈጥሮ በአዲሱ …. መጪ ማለት የነፃት እልፍኝ ነው። „ተስፋ የለም መቼስ ኑሮ ያውቃል የሚለው የጹሑፉ አናት አምክንዮ“ ለተስፋ ሲሉ የተሰዉ፣ የታሰሩ፣ የተንገላቱ፣ የሚፋለሙም፣ የሚማገዱትን መስዋዕትነታቸውን ዕሴታዊ ግምገማ ያጎሳቁለዋል – በግፍም ይጨፈጭፈዋል፤ ሥቃያቸውም – ይወቅሰናል። ለእኔስ ተስፋዎቼ ትናንትም ነበሩ ዛሬም አሉ፤ ሚሊዮኖች የተማገዱበትም ዛሬም እዬተማገዱ ያሉበት ….. ሃቅ ነውና። ሀገሬ ልዕልት ኢትዮጵያም ተስፋዬ ናት። „ኢትጵያዊ“ ብዬ ነው ጥግ አግኝቼ በልቼ ጠጥቼ፣ መጠለያ አግኝቼ አንገቴን ቀና አድርጌ እምኖረው።

ተስፋን ማግኘት የድርሻን የመወጣት ጥያቄ ነው። በነፃነት ተስፋ ጉዞ የሞድ ሱቅ ዕቃ ባለመሆኑ ትግሉ ከሞት፣ ከስደት፣ ከመካራ፤ ከመገለል፤ ከፈተና ጋር ነው። መንገዱም የጠቆረ፣ አድካሚና አሰልቺ ነው። የተስፋን ውጤት ለማግኘት አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ሊሆን አይችልም። ጥረት ብቻ ተስፋን ይወልዳል። እራሱ የጥረቱ ፈተና ታላቅ ተቋም ነው። በሂደቱ ብዙ ትርፍ ይገኛል።

ተስፋን ምራኝ ማለት ወይንም መወጠን – አንደኛ ተስፋ ጋር አለመፋታትን፤ ሁለተኛ አዲስ ፕሮጀክት ተስፋን አልሞ በጀመሩ ቁጥር አዲስ ሃይልና አቅም ያለው አዎንታዊ ነገ ይገኛል። ላይገኘም ይችላል። ግን ነገር ግን እኔ „ከእኔ“ የሚለውን መልስ ማግኘት ከተቻለ ህሊና ለህሊና የተስፋ ስንቅና ትጥቅ ይኖረዋል። ተስፋ ማደረግ በሰው ወይንም በቁስ ወይንም በዕድል አይደለም። ቅድመ – ማዕከለና – ድህረ ዓለምን የፈጠረ፤ የሚመራና የሚያስተዳድረው የሰማይና የምድር ንጉሥ የልዑል እግዚአብሄር ስለሆነ እሱን ኃይልን መከታ፤ መጠጊያ መጠለያ ማደረግ ነው።

በሌላ በኩል „ተስፋ የለም፤ ተስፋ መቼ ኑሮ ያውቃል“ ማለትም የሚቻል አይመስለኝም። ተስፋ አለ። ተስፋ እምነት ነው። እምነት ከሌላ ሰው የመሆን ትርጉሙም የለም ማለት ነው። ይሄ የአምክንዮ ወይንም የዕድምታ ድርድር አይደለም። ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የተፈጠረ አካልና አምሳል ነው ሥጋና ደም ነው ተስፋ – ቃል። የኖኽ መርከብ የፍጥረት ተስፋ ….. የተፈጥሮ ጌጥ፤

ተስፋ ፈላጊው ተስፋ መኖሩን በቂ ዕውቅና ካልሰጠው ተስፋ እራሱ ሊያስተናግደው አይችልም። የተስፋ ሚዛን በሚታዩ ነገሮች ብቻም አይለካም። ተስፋ የመንፈስ ልማት መደርጀትን ብቃትን ሁሉ ያካታል። ተስፋ መንፈስ ነው። ተስፋ ጥልቀቱን ማዬት የሚቻለው ጥልቀት ባለው ትእግስት ብቻ ነው። የተስፋን አሸናፊነት ማረጋገጥ የሚቻለውም ጠንክሮ በተከታታይነትና በታታሪነት ተግተው ሲማስኑ ብቻ ነው። ተስፋ አሳላፊ አይሻም። ባዶ ብርጭቆ ይዞም ማንቆርቆሪያ አይጠበቅም፤ ወይንም በውክልና ተስፋ አይተዳደርም። ተስፋ የሚወለደው በራስ መዳፍ ብቻ ነው።

ወንድም ዓለም – ነገ ማለት ተስፋ ነው። ከሰዓት በኋላ ማለትም ተስፋ ነው፤ የዛሬ ወር ማለት ተስፋ ነው፤ ወላጆች ልጆቻቸውን ተስፋዬ፣ ተስፋዓለም፤ ተስፋሁን፤ ተስፋነሽ፤ ተስፉ፤ ተስፋ ትሁን፤ እያሉ የሚጠሩት በተለምዶ ወይንም የፊደላቱ ጥምረት እንደ ብርንዶ ሽው ብሏቸው አይደለም። ረቂቅ አምክኖዊ ሙቀት ለነገ በማለም ነው። ተስፋ እኮ የነገ ማለትም የማግሥት የሚነጋ የኑሮ መርህ ነው። መርኃ ግብርም ንድፍም ነው። ተስፋ ዬግል፣ የድርጅት፣ የመንግሥታት፣ የአጭር – የመካከለኛና የረጅም ጊዜ  ዕቅድ ነው። ተስፋን ብራናውም ቀለሙም ቢሰለፉ ውቅያኖሳዊ አውንታዊነቱን ሆነ ህያውነቱን ዘርዝረው አይዘልቁትም። ተስፋ ፍቅር ነው። ተስፋ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ተስፋ ደስታ ነው፤ ተስፋ ራዕይ ነው፤ ተስፋ ትልም ነው፤ ተስፋ ምህረት ነው፤ ተስፋ ጽናት ነው፤ ተስፋ ቋሚ ነው። ተስፋ ልጆች ናቸው፤ ተስፋ ኑሮና መኖር ነው፤ ተስፋ ትንፋሽ ነው፤ ተስፋ እናንተ ወጣቶች ናችሁ፤ ተስፋ የህሊና ዕሴት ነው፤ ተስፋ የህይወት አናባቢ ነው፤ ተስፋ ዳሳሽ ነው፤ ተስፋ አጽናኝ፤ ተስፋ ተፈጥሮን እና ሥጦታዎችን በአግባቡ በማክበር መተርጎምና ከተፈጥሮ ጸጋዎች ጋር መግባበት ይቻል ዘንድም መቻቻል ነው ወዘተ …..

በተስፋ ተፈጥሮ ውስጥ አሉታዊ ነገሮች የሉበትም፤ ስለምን? ተስፋ የብሩህ መንፈስ ጭማቂና ብርሃን ስለሆነ። ተስፋ ሁልጊዜ ብሥራት ነው። የምስራች ዜና አብሳሪ ነው። የውጤት ስኬት ነው። ተስፋ ቅድስቷን እርግብ ይመስላል። ተስፋ ጭልምተኛ አይደለም። በተስፋ ውስጥ ጭጋግ የለም፤ በተስፋ አውሎ የለም። ይህ ማለት ጉዞውን የሚያደናቅፉ ጨላማዊ፣ ጭጋጋዊ፣ አውሏዊ ገጠመኞች ወይንም ጸላዬ ሰናዮች የሉም ለማለት አይደለም። እነሱ እሱን እንዳናገኝ መንገድ ዘግተው ወይንም መተላለፊያውን አግደው ለመያዝ የተፈጠሩ አሜኬላዎች ናቸው። ተስፋ በነፍሱ ግን የመልካም ነገሮች ሁሉ መናኽሪያ መዲና ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ከዚህ ማዕቀፍ ከወጣ በጤናውም ሆነ በኑሮው ላይ ሰፊ የሆኑ ሊፈቱ የማይችሉ ትብትቦች ይገጥሙታል። የጭንቀት በሽተኛ ቁራኛ መሆንም አለ፤ ዓለምን አጨልሞ የማዬት፤ ነገን የመፍራት ወዘተ …. ገዳዳ ዕጣዎች ይጠብቃሉ ….

አባቱ – ወጣትነት ውብ የዕድሜ ዘመን ነው። ወጣት አትሁን ማለት ከተፈጥሮ ጋር መጣላት ነው። ነገር ግን ወጣት ከተስፋ ጋር ከተጣላ የተሳሳተ ጊዜና ቦታ ላይ ስላለ ሃግ ሊባል ይገባዋል ባይ ነኝ። ምክንያቱም የነገ ትጉኃን ላይ ጠባሳ ስለሚሆን። ዛሬንም ቢሆን አቅሙን ይበላል። አንድን ህዝብ በተስፋ ዙሪያ ማሰባሰብ የፕሮፖጋንዳ ተግባር አይደለም። የነፃነት ትግል የፕሮፖጋንዳ ምርት ውጤት አይደለም። የዕውነት ፍሬ ዘር እንጂ። እንደዚህ መሰል ዕይታዎች ደግሞ ብዙ የተያያዙ ኔቶችን ያረግባሉ። ወይ ይወጥራሉ። ከረገቡ – የዛለ መንፈስ፤ ከተወጣረ ደግሞ መበጠስ ይኖራል። ስለዚህ በተመሳሳይ ሙቀትና ሂደት ፍላጎት ይመራ ዘንድ የመንፈስ ሥራዎችን ከሚንዱ ግላዊ ስሜቶች እራስን መግታት የተገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም ለዚህ ተግባር ብቻ የተሰለፈ ወይንም የሚሠራ ዕውቅና ያለው ኃይል የለንምና። … ትውልድን በተስፋ ገንብቶ ብልጹግ ማድረግ የምሽት የቅልቅል ግብዣ አይደለም። ኃላፊነቱን ወስዶ፣ በሙሉ ጊዜና ኃይል የሚከውን መዋቅር፤ የተደራጀ ያስፈልገዋል። በልመና ገንዘብ ይህ ተግባር አይታሰብም። በቋሚ በጀት የሚመራ እጅግ ረቂቅ የሆኑ የመንፈስ መስመሮች ለመዘርጋት ብቁዎችንም – ይጠይቃል። ይህም ሆኖ  በእጅ ባለው ነገር ሁሉ በፈቃዳቸው በሚተጉ፤ ጠለቅ ያለ ትንተና እያቀረቡ ትውልዱን ለመገንባት በሚጥሩ ወገኖች ላይም ንደት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ የቤት ሥራም ይመስለኛል። በሌላ በኩል የጊዜም ሆነ የአቅም ብከነትም ነው – ተስፋን ማራቅም፤

ከዚህ ጋር አብሮ ሊታይ የሚገባው ቀለል ያሉ ህይወት ነክ ጉዳዮች ባነሳ ዓለም በተስፋዋ ዙሪያ የደረሰችበት ደረጃ እኛም ተጠቃሚ አድርጎናል። ወንድሜ ጦር ግንባር እያለ እናቴ በስልክ ደጃፍ ፊቱን እያዬሁ የማወራበት መላ ቢኖር ትል ነበር። እንሆ ዛሬ ዓለም ካለወጪ በነፃ እዬተያዬ በስካይፕ፤ በፓልቶክ፤ በባይበር እዬተያዩም ሆነ በድምጽ መገናኘት ይቻላል። አንዲት የታይፕ ጸሐፊ ሲበላሽባት መቅደድ ወይን በኡሑ ማጥፋት ነበረባት፤ ወይንመ አዲስ መጀመር ዛሬ ያ ሁሉ የለም፤ ቀደም ባለው ጊዜ ልብስ በእጅ ይታጠብ ነበር፤ እዚህ ሲዊዝ የ89 ዓመት እናት አለችኝ እማማ ስትነግረኝ ት/ቤት ሲሄዱ ሽርጥ ታጥቀው ነበር – ተማሪዎች። ስለምን? ከቆሻሻ እንዲታደግላቸው። ዛሬ በሰለጠነው ዓለም የለም። ስለምን? ተስፋ ያደረጉ ፍጥረታት ተግተው መዳፋቸውንና ህሊናቸውን ስላሰሩ አይደለም ለእነሱ ለእኛም ተርፈውናል። እኔ እላለሁ። ተስፋ ተፈጥሮ ነው። ስለሆነም ተስፋ ነበረ አለ ወደፊትም ይኖራል። ተስፋን ኮርኩሞ ከግንባር ሥር ወሽቆ „ተስፋ የለህም አልተፈጠርክም“ ማለት ግን ግሎባል የሆኑ ትስስሮችን፤ ተጠቃሚነት ሁሉ የሚያደቅ ዕይታ በመሆኑ የተሳሳተ መስመር ነው።

ሌላው የተነሳው የወሬ ወፍጮ፤ አፈር ፈጭተው ሰው ያደረጉን እኛ የነሱ ልጆች ወሬ ፈጭተን ሰው ልናደርጋቸው አሰብን” ሰቀቀኑ ከመከረኛው የተነሳ፤ ተሎ ልንደርስለት አልቻልንም ለህዝባችን ነው። ይህም በራሱ ተስፈኝነት ሲሆን አዎንታዊ ቢሆንም፤ ዓለም እራሷ የምን መቀነት ነው ያላት፤ ስልጣኔ – ቴክኖሎጂ ሁሉም እኮ የወሬ ፍሬዎች ናቸው። አግልጋይነታቸውም ለወሬ ነው። ወሬ ሲባል የመረጃ ልውውጥ ማለት ነው። ዓለም ካለ መረጃ መኖር አትችልም። በመረጃ ልውውጥና ሽርሽር ነው ልትጠፋ ተነገዳግዳ የነበረቸው ዓለም ኃይልና በርታት አግኝታ በህብረት ህልውናዋ የተረጋገጠው። ዛሬም ለሰው ልጆች ሰቆቃ ሰበነክ ድርጅቶች መድረስ ችለው „ሰውን“ ያህል ክቡር ነገር የሚያተርፉት።

በሌላ በኩል ሀገሮች የሚተዳደሩት በወሬ ነው። በስብሰባ ነው የሚመረጡት፤ ከተመረጡ በኋላም የሚያስተዳድሩት – በወሬ። አፍ ተከርችሙ መሪነት የለም። „ምረጡኝ“ ለማለት ማውራት ያስፈልጋል፤ „ሥሩ“ ለማለትም አንደበትን መክፈት ይሻል፤ ልሳን አንደበት የተፈጠረውም ለዚኸው ተግባር ነው። አፍና ሠራዊቶቹ ከተፈጥሮቸው ይታቀቡ ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ ፊደላትን ማሰለፍ ፈጣሪያቸውን አሻቅቦ መክሰስ ይመስለኛል።

በሌላ በኩል ንግግር ሙያ ነው። ንግግር ጥበብ ነው። በሀገራችን በኢትዮጵያም የንግግር ጥበብ በትምህርት ደረጃ ይሰጥ ነበር። እኔ እራሴ የዕድሉ ተጠቃሚ ነኝ። ንግግር በተሰጦ የሚገኝ ቢሆንም ክህሎቱን በሥልጠና ማጎልበት ይቻላል። ውይይቶች፤ ስብሰባዎች፤ ወርክሾፖች ሆኑ ፓናል ዲስክሽኖች ግባቸውን የሚመቱት በንግግር ተስጥዖ ልቅና ባለው ሰዎች ነው። የሰላም ድርድሮች፤  የኢኮኖሚ መግባባቶች፤ የፓለቲካ ስምምነቶች፤ የባህል ልውውጦች፤ የጋራ ውሳኔዌች፤ የወል ምክክሮች ሁሉ ፊደላቸው ንግግር ነው። አስተርጓሚዎችም ለዚህ ተግባር ተብለው ይሰለጥናሉ። ትልቁ የአንደበት መክፈቻ ቁልፍም ንጉሡ ቋንቋ አለ። ቋንቋና መክሊቱም ሌላው የተስፋ በር ናቸው። ውቅያኖስ ጸጋው ጋር ቋንቋ 13ኛው ፕላኔት ነው።

ሚዲያ ገንዘብ ነው። ሚዲያ ህይወት ነው። ሚዲያ ተስፋ ነው። ሚዲያ የዘመናችን የግብይት መናኽሪያ ነው። ገቢውም ሆነ ዲታነቱም እንዲሁም ተፈላጊነቱና ተደማጭነቱም የዚያን ያህል ውድ ነው። በምን ዕያታ በምን ምንዛሬ ከዚህ አጠቃላይ ግንዛቤ እንደተደረሰ ባላውቅም ዓለምና የመረጃ ምንጮችን ሆነ፤ የመረጃ መስመሮቻን እንዲሁም የመረጃ ተገልጋዮቿን ከነሥልጣኔያዊ ገፃቸው አፈርድሜ ያስጋጣ አገላለጽ ነው። አዝናለሁ – ከልብ።

በዚህ ሙያ በቴክኒኩ፤ በሎጅስቲክስ፤ በአድራጊና በተደራጊ የሚሊዮኖች ተወዳጅ የሙያ ዘርፍ ነው። ሙያው ዓለምን በር፣ መስኳት፣ መግቢያና መተንፈሻ ቧንቧ እንዲኖራት አድርጓታል። እኛም ቤተኛ በመሆናችን በራችን ዘግተን አለመቀመጣችን ከጥንቱ ከብራናው ዘመን ጀምሮ እስከ አሁኑ ኮንፒተራይዝድ ድረስ ሙሉ ድርሻችን በሙሉ ብቃት ደስ ብሎን ዕድሉን አክብረነው እንሳተፋለን። ይህ ደግሞ እንደነውር ተቆጥሮ የሚያስወቅስ መሆኑ ሌላው እልባት ሊያገኝ የሚገባው ጉዳይ ይመስለኛል።

ሆምፔጆች ይዘጉን? የኮሚኒቲ ራዲዮ ፕሮግራሞች ይከርቸሙን? የቴሊቪዢን ዝግጅቶች ይቋረጡን? ብዕርና ብራና ዬት ይደበቁ? የተፈጥሮ ድምጽስ ታፍኖ ይቀመጥና – ይሻግት? ሽሁራር እንስበላው – መንፈሳችነን? ልጅ ሄኖክ ለአንተ አላውቅም፤ ለእኔ ኢትዮጵያዊ ሚዲያዎች ሆኑ የነፃነት ትግል መንፈሶች እንዲሁም የባህል ዓውዶች ሁሉ „የመረጃ“ ምንጮች ብቻ ሳይሆኑ የትምህርት፤ የመወያያ፤ የመገናኛ፤ የመግባቢያ መድረኮች ናቸው። ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው ከጓደኛው ጋር ተገናኝቶ ሲነጋገር አንደበቱን ሲከፍት የአፍ ጡንቻዎች ይፍታታሉ፤ ሲስቅ ጤናው ይጎለምሳል፤ የጨነቀውን ነገር ሲጫወተው ይቀለዋል፤ እንደተጠቀልልክ – ተጠቅልለህ ተስናበት ዓይነት ከሆነ ከሁሉም መልካም ነገሮች ጋር ግጭት ብቻ ሳይሆን ሌላ የመንፈስ ለውጥ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

ከዚህ ጋር በኮሚዲ ሙያ የሚሰሩ፤ በትዕይነት ላይ የተሰማሩት የቲያትር ሆነ የፊልም ተዋናዮች ሙያቸው ተገላጭነቱ በባላንባራስ ወሬ ነው። የፍትህ ውሎ ችሎትም በወሬ ነው። ተከሳሽ – ዳኛ – አቀቢ – ህግ – ጠበቃ – ምስክር በጥቅሻ ይሁን ወይ ተግባራቸውን የሚከውኑት? ፍሬ ያለው ነገር ማዬት ካልቻልክ አንተ ፍሬ ሁነህ አፍራ!

ይህ የምንጠቀምበት ፌስቡክ ቢሆን የተስፋ ባለሟል ነው። ተስፋ ያለው ወጣት የፈጠረው። ተስፋውን አሳክቶ ሚሊዮኖችን ያገናኘ፤ የት ላይ እንደቆምክ፤ እንዳለህም ግር እስኪለኝ ድረስ ደጋግሜ ጹሑፉን ሳነበው ደረጃህን – መክሊትህን – ዕውቅናህን – ተደማጭነትህን ለመቼ ቀጠሮ እንደሰጠኃቸው አልገባኝም። አንተን የሚወዱ፣ ያከበሩ፣ ተስፋ ያደረጉ፣ በመንፈሳቸው መስጠረው ያስቀመጡህ ወገኖችህ ሁሉ ቦታ አጥተው፤ ጥግ አጥተው ጥርኝ ልመና ላይ እንዳሉ ይሰማኛል። አንድ ዬጥበብ ቤተኛ ከሚያውቃቸው ደጋፊዎቹ ይልቅ የማያውቃቸው እጅግ በርካታ ስለሚሆኑ ለእነሱም በእንቡጢጣ  እሰብላቸው። ለመሰከሩልህም፤ ለምን? የወደዱህ – ያከበሩህ፤ ያፈቀሩህ እኮ ተስፋቸው ስለሆንክ ነበር። ታዲያ ስለምን ተስፋ ቢስ ታደርጋቸዋለህ? ተኝተህ እሰበው – ግን ከመንፈስህ ሆነህ። ሌሎች ስላነሳሱህ ወይንም ስለኮለኮልህ ሳይሆን ለአንተ ብቁ መሪው አንተው ብቻ ነህ። ምክንያትም ከውጪ እውቅና ይልቅ እራስን ማወቅ ብልጫ ስላለው።

እንደ ተተኪ ትውልድነትህም የነገ አደራ ተረካቢ ሆነህ ሳለ፤ ለአደራህ አንጋጠህ መጠበቅህ ከወጣትነት ሥነ ደንብ ጋር የሚያጣላህ ይመስለኛል። ወጣቶች ሁልጊዜ ወደፊት ናቸው፤ ወጣቶች ፍጥነታቸውን የሚያሳርፉት በተስፋቸው ላይ ነው። ተስፋቸውን ለማፍጠን የተስፋቸው ወታደሮች እነሱ እንጂ ሌላ አለመሆኑን ስለሚውቁ አውሎ አይነቀንቃቸውም፤ ወይንም በአማላጅ ወደ ተስፋ ጉዙ እንዲያዘንብሉ የግብዣ ወረቀት ከዬትኛውም ወገን አይጠብቁም።

እግዚአብሄር ይመስገን እኔ ሥርጉተ ወጣትም ነበርኩኝ፣ ወጣት አደራጅም ነበርኩኝ፤ እኔ የማውቃቸውና እመራቸው የነበሩት ወጣቶቼ የግንባር ሥጋነታቸውን በተግባር ያቀለሙ ነበሩ። ውጪ ሀገር እንኳን ያደራጀኋቸው ወጣቶች ስንት ተግባር አንደከወኑ ታሪክ አንድ ቀን ይዘክረዋል። ስለምን? ከወጣት ጋር መሥራት የድርብ ውጤት ባለሟልነት ገጸ በረከት ስለሆነ፤ ድፍረታቸው ትጋታቸው፤ ጽናታቸው፤ ሀገር ወዳድነታቸው፤ ፍትህ ራህብተኝነታቸው ሁለመናቸው የወጣትነትን ሥነ ደንብ ያሟሉ ብክነትም የማይጎበኘው ስለሆነ ለዛሬም ለነገም ለተነገ ወዲያም ወጣቶች ተስፋችን ናችሁ። ከቤቴ – ከተፈጥሮዬ – ከተሰጠኝ ጸጋ እውጣለሁ ካልክ ምርጫው የአንተ ሲሆን መቅኖ ከማፍሰሱ ላይ ግን ተግ ብትል መልካም ይሆናል። የተሰበሰበን መበትን /// እእ! እኔ ከአንተ ይህን አልጠብቅም። ተስፋ ነህ፤ ተስፋነትህን – ዋጠው። ትእዛዝ ግን አይደለም። ….  የትውልዱና የዘመኑ ታዳሚነትህ ግድ ስለሚል ብቻ።

ብክነት የመንፈስ ማለቴ ነው። መንፈሱ የሚባክን ወጣት የተላለፈው መሰመር አለ። ወጣት ከችኩልነቱ በስተቀር መንፈሱ ድርጁና ቋሚ ነው። አቅሙም ከብረት ቁርጥራጭ የተሠራ ተከታታይነት ያለው ነው። የትም ሀገር የሚቀሰቀሱ የፍትህ ጥያቄዎች አቀጣጣዮች፤ ሳይታክቱ ተግተው የሚሠሩ ወጣቶች ናቸው። ወጣትነት ክብርና ዝና ምኑም አይደለም። የህዝብ መበደል ነው ማዕከላዊ አጀንዳው። ስለዚህም ይማስናል – ለፍትህ፤ ለሰው ልጆች እኩልነት፤ ለሰው ልጆች ሙሉዑ ነፃነት ቀድሞ – ይማገዳል።

ተስፋዬ! ዛሬ ላልንበት ደረጃ ያደረሱን ወጣቶች ነገንም አሳምረው አደራጅተው የመምራት አቅምና ቁርጥኝነት አላቸው። ዛሬን የሰጡን ወጣቶችን ውለታው ቀርቶባቸው ስንሰርዛቸው ዘመን – ይታዘበናል። ትናንትም ወደፊትም ወጣት አዋቂ ፆታ ዕድሜ ዕምነት ብሄረሰብ ደንበር ሳይገድባቸው ለወል ተስፋችን የሚባክኑ – የሚደሙ – የሚቆስሉ – የታሰሩ – የተንገላቱ – የተደበደቡ – የተደፈሩ የተሰው ወገኖቼን ከልብ አምስግኜ ተስፋዎቼን ያኑርልኝ – እላለሁኝ። ግልጽነትህን ውስጥህን ማስጎብኘት መቻልህ ልዩ ነውና አመስግናለሁ። አይዞህ ታናሽ – ጤናማ ሳቂተኛ ንፋስ ይመጣል – ለተስፋ ማደር ከተቻለ- በህግጋታቱ መተዳደር ከተፈቀደ —-

ውዶቼ መሸቢያ ሰሞናት፤ ደህና ሰንብቱልኝ።

ተስፋችን የፈጠረ፣ ለተስፋችን አቅም የሰጠ፣ ተስፋችን መርቆ የሸለመን አምላካችን የተመሰገነ ይሁን። አሜን!

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ – ይበቃኛል።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 

 

The post የመሬት – መስኮት፤ የሰማይም – በር ነው ተስፋ፤ – ሥርጉተ ሥላሴ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>