Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

አላሙዲ በኦሮሚያ ክልል የተገኘው ከፍተኛ ክምችት ያለው የወርቅ ማዕድንን ሊያወጡ ነው

$
0
0

ቀጣዩ ዘገባ የተገኘው ዛሬ በኢትዮጵያ ታትሞ ከተሰራጨው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው

ብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ዳዋ ዲጋቲ ቀበሌ በሚገኘውና በልዩ መጠሪያው ኦኮቴ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ያገኘው ከፍተኛ ክምችት ያለው የወርቅ ማዕድን ላይ ሥራ ሊጀምር መሆኑን፣ የኮርፖሬሽኑ ባለቤትና ባለሀብት ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ ሚያዝያ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ገለጹ፡፡
al amudi and abadula gemeda
ሼክ አል አሙዲ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት መገኘቱን የገለጹት፣ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በማዕድንና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የስምንት ቢሊዮን ብር ማስፋፊያ ፕሮጀክት መጀመሩን አስመልክቶ በሸራተን አዲስ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ነው፡፡

ብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን ላለፉት 15 ዓመታት ባደረገው ጥናት የወርቅ ክምችቱ መገኘቱን የተናገሩት ባለሀብቱ፣ ‹‹የማዕድን ሥራችን እየሰፋ ነው፡፡ ቦታው ትልቅ የወርቅ ልማት ያለበት ነው፡፡ ትልቅ የወርቅ ክምችትም አግኝተናል፡፡ ለሚድሮክ ጎልድ ትልቅ ፕሮጀክት ከመሆኑም በተጨማሪ ኢትዮጵያን የሚያስጠራ ፕሮጀክት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የተገኘው የወርቅ ክምችት ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለአገሪቱ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን ጠቁመው፣ ሁሉም ዝርዝር ጥናት እየተጠናቀቀ በመሆኑ፣ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ሼክ አል አሙዲ ገልጸዋል፡፡ ሌላው በትግራይ ክልል ስለተገኘው የማዕድን ክምችት ገልጸው፣ ብዙ ወርቅ ባይኖርበትም የዚንክ፣ የሊድና የብር ክምችት መገኘቱንና ወደ ምርት ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሶዳ አሽ ፕሮጀክት እንዳላቸውና ማምረት መጀመራቸውንም አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በዶ/ር አረጋ ይርዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመራው ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ወደ ላቀ ስኬት የሚያሸጋግረውን አዲስ ፕላን መንደፉን ገልጾ፣ የወርቅ ማዕድንና አግሮ ፕሮሰሲንግ ማስፋፊያ የስምንት ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዶ/ር አረጋ እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ ቴክኖሎጂ ግሩፑ ተግባራዊ ማድረግ የሚጀምረው ዕቅድ ከ15 እስከ 20 ዓመታት የሚያገለግል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚስፋፉት ፕሮጀክቶች የወርቅ ማዕድን ልማት፣ የተቀናጀ ዘመናዊ የዶሮ ዕርባታ፣ በመስኖ የተደገፈ ዘመናዊ የከብት መኖ (አልፋ አልፋ) ልማትና የተቀናጀ የወተትና የሥጋ ልማትን እንደሚያካትቱ አስረድተዋል፡፡

የማስፋፊያ ፕሮጀክቶቹ በሦስት ክልሎች እንደሚከናወኑ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ 4.2 ቢሊዮን ብር (55 በመቶ የሚሆነው) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ሥራ፣ ቀሪው በአማራ ክልል ለሚካሄደው አግሮ ፕሮስሲንግ (የዶሮ እርባታ) እና በኦሮሚያ ክልል ለሚካሄደው አግሮ ፕሮሰሲንግ (የመኖ፣ የወተትና የሥጋ) ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የሚውል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት የሚወስድ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በማዕድንና በአግሮ ፕሮሰሲንግ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ሥራው ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራው ሲገባ፣ በየዓመቱ ከምርት ሽያጭ 3.5 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚገኝና በልማቱ ዕቅድ ዘመን 61. 90 ቢሊዮን ብር የሽያጭ ገቢ ሊገኝ እንደሚችል ዕምነታቸው መሆኑን ዶ/ር አረጋ ተናግረዋል፡፡ ከልማቱ በታክስ፣ በሮያሊቲና በሌሎች ክፍያዎች በየዓመቱ 880 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ እንደሚደረግ ገልጸው፣ በተወጠነው የኦፕሬሽን የዕቅድ ዘመን (ከ15 እስከ 20 ዓመታት) በጠቅላላው 14.85 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገቢ ሊሰበሰብ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ ቴክኖሎጂ ግሩፑ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የልማት ዘርፎች የወርቅ ማዕድንና አግሮ ፕሮስሲንግ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶ/ር አረጋ፣ ማዕድንን በሚመለከት ዋናው ተዋናይ ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ መሆኑንና አግሮ ፕሮስሲንጉን በሚመለከት ደግሞ ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሚድሮክ ወርቅ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት አሥር ዓመታት በመተከል አካባቢ ሰፊ የማዕድን ፍለጋ ሲያካሂድ ቆይቶ፣ በቂ የወርቅ ክምችት መኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ባህር ዶልቢር ሚኒራልስ ኢንዱስትሪ አድቫይዘርስ በተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ የአዋጭነት ጥናቱን ማስጠናቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ አሥር ዓመታት የፈጀውን የማዕድን ፍለጋ ግን ኢትዮጵያውያን የኩባንያው ሠራተኞች ማከናወናቸውን አክለዋል፡፡ ኩባንያው በለገደንቢ፣ በሳካሮ፣ በሻኪሶና በረጂ ከተሞች አካባቢ የወርቅ ማምረቻ እንዳሉት ይታወቃል፡፡ ለአሥር ዓመታት ባደረገው የማዕድን ፍለጋ 310 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም ዶ/ር አረጋ አክለዋል፡፡ ሚድሮክ ጎልድ በመተከል አካባቢ ያገኘውን የወርቅ ማዕድን ልማት በ200 ሚሊዮን ዶላር ወይም 4.2 ቢሊዮን ብር ወጪ እ.ኤ.አ. በ2015 እንደሚጀምርም ጠቁመዋል፡፡

The post አላሙዲ በኦሮሚያ ክልል የተገኘው ከፍተኛ ክምችት ያለው የወርቅ ማዕድንን ሊያወጡ ነው appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>