Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

መርካቶ በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ወድቃለች

$
0
0

ህልማቸው በሜዲትራንያን ባህር የተዋጠው 7ቱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች
ከኤልሳቤት እቁባይና አለማየሁ አንበሴ

በቅርቡ በሜዲትራኒያን ባህር ከዘጠኝ መቶ በላይ ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ ሰጥማ 28 ተጓዦች ብቻ በህይወት በተረፉባት ጀልባ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት መካከል በአደጋው የሞቱት የሰባት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አሳዛኝ መርዶ የተሰማው ከትላንት በስቲያ ነበር፡፡ የሰባቱም ሟቾች የትውልድ ሰፈር ደግሞ በአዲስ አበባ መርካቶ በሚገኘው የአባኮራን ሰፈር ውስጥ ነው፡፡ በትላንትናው ዕለት የሟቾች ቤተሰቦችን ለማነጋገር ወደ አካባቢው ስንሄድ ሰባት ድንኳኖች ተርታውን ተተክለው ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድና ጓደኞች ለቅሶ ተቀምጠው ነበር፡፡
merkato
ከሊቢያ ባህር ዳርቻ ተነስታ ጣሊያን ልትደርስ ስትል በሰጠመችው ጀልባ ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩት የአባኮራን ሰፈር ልጆች መካከል ዘመን ኢብራሂም የተባለው ወጣት በአስገራሚ ሁኔታ ህይወቱ ሊተርፍ ችሏል፡፡ የጀልባዋን መስጠም አስመልክቶ በአልጀዚራ በተሰራጨ ዘገባ፣ ልጁ ከአደጋው ተርፎ በእርዳታ ሰራተኞች ድጋፍ ሲደረግለት ታይቶ ነበር። ይሄኔ ነው አብረውት የሄዱት የሰፈሩ ልጆች የት ገቡ የሚለው ጥያቄ በቤተሰብና በጓደኞች ዘንድ የተነሳው፡፡ ቀደም ሲል በተመሳሳይ መንገድ በባህር ተጉዘው ጣሊያን የገቡ የሰፈር ልጆች ባደረጉት ማጣራት ግን ከዘመን ኢብራሂም በስተቀር ሁሉም ባህር ውስጥ ሰጥመው እንደሞቱ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡ ወጣቱ ዘመን ኢብራሂም ተዓምራዊ በሚመስል ሁኔታ ነው ህይወቱ የተረፈው፡፡ ወደ ባህሩ ሲወድቅ በአጋጣሚ ውሃው ላይ ስትንሳፈፍ ያገኛትን አንዲት ጀሪካን ይዞ ለ2 ሰዓታት ያህል ራሱን ለማዳን ጥረት ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ነው የነፍስ አድን ሰራተኞች የደረሱለት፡፡ እስከዚያው ግን ብዙ በመሰቃየቱ አሁንም በሙሉ ጤንነት ላይ እንደማይገኝ ጓደኞቹ ነግረውናል፡፡ ዘመን ኢብራሂም አሁን የሚገኘው በጣሊያን ነው ተብሏል፡፡መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ለማሻሻል አውሮፓን አልመው ከሰፈራቸው የወጡት 9 ወጣቶች ሲሆኑ ስምንቱ በአደጋው እንደሞቱ ቢነገርም የአንደኛው ወጣት ወላጆች ግን “ልጃችንን በቲቪ አይተነዋል፤ አልሞተም” በማለት መርዶውን አልተቀበሉትም፡፡

አብዱል ጅላል ወጉ ወይም በሰፈር ስሙ ሙራድ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን በቀን ስራና በሱቅ በደረቴ ይተዳደር ነበር፡፡ ኑሩ መሀመድ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ የትምህርት ክፍል አንድ አመት ተምሮ ቤተሰብ ለመርዳት ትምህርቱን አቋርጦ ነው የተሰደደው፡፡ አብዱልከሪም ዘይኒ ደግሞ የ20 ዓመት ወጣት ሲሆን በቀለመወርቅ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነበረ፡፡ ሰይድ ይመር የ22 ዓመት ወጣት ሲሆን በተለያዩ የጉልበት ስራዎች ራሱንና ቤተሰቦቹን ያስተዳድር ነበር ተብሏል፡፡ አሊ መሀመድ የ26 ዓመት ወጣት ነበር፡፡ የሚሰራበት ሱቁ እንዲፈርስ በመወሰኑ ነው እቃዎቹን ሸጦና ገንዘብ ተበድሮ ለስደት የወጣው፡፡ ነጃ ሳቢር አወል የ24 ዓመት ወጣት ሲሆን የተለያዩ ተባራሪ አነስተኛ የንግድ ስራዎችን በመስራት ይተዳደር ነበር፡፡ እንድሪስ አደም ደግሞ የ18 ዓመት ወጣት ሲሆን ከኢንፎኔት ኮሌጅ በቴክኒክና ሙያ ተመርቆ ስራ አጥ እንደነበር ከአካባቢው ያሰባሰብነው መረጃ ያመለክታል፡፡ የእነዚህ ወጣቶች መርዶ ሰሞኑን ቢነገርም ወላጆች፣ ቤተሰቦችና ጓደኞች መሸበር የጀመሩት ግን በሊቢያ በአይኤስ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን መርዶ ከተሰማ ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ በየጊዜው ወጣቶቹ በአይኤስ እጅ ወድቀዋል የሚል መረጃን ጨምሮ ብዙ ያልተጣሩ ወሬዎች ይመጡ ስለነበር፣ ቤተሰብና ጓደኞች በስጋት ውስጥ ነው የከረሙት። አብዱ ሀሰን አሊ የተባለው የሟቾቹ አብሮ አደግ መርዶውን እንዲያረዳ ከጣሊያን ሲደወልለት ሊሸከመው የማይችል ዱብ እዳ እንደወረደበት ነበር የቆጠረው፡፡ “ ማን ማንን ሊያፅናና ነው?” የሚል ከፍተኛ ጭንቀትና ፍርሀት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡

ሆኖም መርዶው በድንገት ደርሶ ቤተሰብ ከሚጎዳ በሚል የአካባቢውን ሽማግሌዎች ሰብስቦ መርዶው ከትላንት በስቲያ እንዲነገር ማድረጉን ገልጿል፡፡ በመርካቶ አባኮራን ሰፈር መርዶው ለቤተሰብ ከተነገረበት ሰአት ጀምሮ በከፍተኛ ሀዘን የተዋጠ ሲሆን ሰባቱም ሟቾች ጎረቤታሞች በመሆናቸው በመደዳ በተጣለው ሰባት ድንኳን ሰዎች ሀዘን እየደረሱ ነው፡፡ ይሄ አሳዛኝ ክስተት ለመላው ኢትዮጵያውያን መሪር ነው – በተለይ ደግሞ ለወላጆችና ቤተሰቦች፡፡ ህልማቸው በሜዲትራኒያን ባህር የተዋጠው ወጣቶች ወላጆች እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ብዙዎቹ ልጆቻቸው የሚጦሯቸው ናቸው፡፡ መተዳደሪያ ያላቸው ደግሞ ከእጅ ወደ አፍ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ በጥበቃ፣ በፅዳት፣ ልብስ በማጠብ፣ ጉሊት በመቸርቸርና እንጀራ በመጋገር ነው የሚተዳደሩት፡፡ ልጆቻቸው ሊቢያ፣ ቤንጋዚ ሲደርሱ ወደ አውሮፓ ለመሻገር በመቃረባቸው ገንዘብ እንዲልኩላቸው ጠይቀው፣ ከሰፈር ሰዎች ተዋጥቶና አንዳንድ ወላጆች በዋስ ተበድረው እንደላኩላቸው ለማወቅ ችለናል፡፡ ወጣቶቹ ሊቢያ ለመድረስ እያንዳንዳቸው ወደ 80ሺ ብር የሚጠጋ ገንዘብ እንደፈጀባቸው ታውቋል፡፡ በህይወት የተረፈው የዘመን ኢብራሂምን ወላጆች ለማግኘት ብንሞክርም ልጁ ወላጆቹን ያጣው በለጋ እድሜው እንደነበርና ጎረቤቶች እንዳሳደጉት ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ በጓደኞቻቸው ላይ ያጋጠመው አደጋ ያስደነገጣቸው አብሮ አደጎቻቸው በግራ መጋባት መንፈስና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ያሉ ሲሆን አሁንም ጣሊያን መግባት የቻሉ ሁለት የሰፈሩ ልጆች ወደ ሌላ ከተማ ለመሻገር ሁሉም የቻለውን አዋጥቶ እንዲልክላቸው በመማፀናቸው የአካባቢው
ነዋሪዎች የሚችሉትን እያደረጉ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡

ምንጭ – በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ

The post መርካቶ በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ወድቃለች appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>