የዓይን ፍቅር /Sight love/ የምንለው አንድን ግለሰብ በተደጋጋሚ በመመልከትና አዕምሮአዊ ስዕል በመሳል የፍቅር ስሜትን ውስጣችን ውስጥ ማዳበር ማለት ነው፡፡ ንቁ የሆነው የአዕምሯችን ክፍል በአካባቢው ያሉ መረጃዎችን የማሰባሰብ ኃይል ያለው ክፍል ነው፡፡ ይህ የአዕምሯችን ክፍል ከአካባቢው ያገኘውን መረጃ የማጠራቀሚያ ቦታ ስለሌለው ወደ ሌላኛውና ንቁ ወዳልሆነው የአዕምሮ ክፍል /the unconscious mind/ መረጃዎችን በሙሉ ያስተላልፋሉ፡፡ ንቁ ያልሆነው የአዕምሯችን ክፍል የተሰጠውን መረጃ እውነት አድርጎ የሚቀበልና ኢ-ምክንያታዊ ስለሆነ ንቁ ከሆነው የአዕምሯችን ክፍል የመጣውን መረጃ በሙሉ ያጠራቅማል፡፡
ከአካባቢያችን ጋር መስተጋብር የሚፈጥረው ንቁ የሆነው የአዕምሯችን ክፍል ስለሆነና በአካባቢያችንም ብዙ ነገሮች ስላሉ ይህ የአዕምሯችን ክፍል የተወሰኑት ላይ ትኩረት በማድረግ ወደ ውስጠኛውና ንቁ ወዳልሆነው የአዕምሯችን ክፍል ይልከዋል፡፡
ወደ ዓይን ፍቅር ስንመጣ አንድ ግለሰብ አንድ የሆነ ሰውን በሚያይበትና ልዩ ሆኖ/ና በሚታይበት ወይም በምትታይበት ጊዜ ንቁ የሆነው የአዕምሯችን ክፍል ትኩረት ሰጥቶ መከታተል ይጀምራል፡፡ ልዩነቱንም ያደንቃል /በተደጋጋሚ መረጃውን ያውጠነጥናል/፡፡ ይህ በሚሆንበት ሰዓት አንድን መረጃ ንቁ ወደሆነው የአዕምሯችን ክፍል በተደጋጋሚ ይልካል፡፡ በዚህ ጊዜ ንቁ ያልሆነው የአዕምሯችን ክፍል በተደጋጋሚ የተሰጠውን መረጃ በመቀበል የታየውን /የታየችውን/ ሰው ምስል ቀርፆ ይይዛል፡፡ በማስታወሻ የአዕምሯችን ማዕከልም ውስጥ ይህ ስዕል በሚገባ ይሳላል፡፡ በተጨማሪም ንቁ የሆነው የአዕምሮ ክፍል ስለፍቅር ወይም ስለወሲብ ወይም በጠቅላላው ስለተቃራኒ ፆታ በሚያስብበት ሰዓት የሚያስበው/የሚያገኘው መረጃ ያን ስዕል ይሆናል፡፡ በመሆኑም ፍቅርን ሲያስብ የሚያስበው በአዕምሮው የሳላትን/የሳለውን ሰው ብቻ ይሆናል፡፡ ታዲያማ ይህ ሰው የዓይን ፍቅር ያዘው ማለት ነው፡፡
ይህንን ሃሳብ በደንብ ለማስረዳት የጠያቂያችንን ገጠመኝ መመልከቱ በቂ ነው፡፡ በአካባቢው ብዙ ሴቶች ያሉ ቢሆንም ከእነዚህ ውስጥ አንዷ ግን የተለየች ናት ማለትም ረጋ ያለችና ደብተሯን ደረቷ ላይ ለጥፋ የምትሄድ አይነት ነች፡፡ በመሆኑም ንቁ የሆነው የአዕምሮው ክፍል ትኩረት ሰጣትና በተደጋጋሚ ስለእሷ አውጠነጠነ፡፡
ይህም ሲሆን ንቁ ያልሆነው የአዕምሮው ክፍል የልጅቱን ስዕል መሳል ጀመረ፡፡ በተጨማሪም ከልጅቱ ጋር አብረዋት የተማሩ ልጆችና እርሷን በቅርበት የሚያውቋት ሰዎች ስለ እሷ ያወሩ ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ ንቁ የሆነው የአዕምሮ ክፍል ይህንን መረጃ ንቁ ወዳልሆነው የአዕምሮው ክፍል የልጅነቱን ስዕል በሚገባ ሳለው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ኤ.ኤም ፍቅርን ባሰበ ቁጥር የልጅቱን ስዕል እንዲያመላልስ አስገድዶታል፡፡ ይህንንም በጽሑፉ ላይ እንዲህ ብሎ ገልፆታል፡፡ ‹‹እኔም ሳላስበው ስለእሷ ሌት ተቀን ማሰብ ጀመርኩ›› በማለት እዚህ ላይ አንድ ነገር አስተውሉልኝ፡፡ ስለ እሷ የሚነገረው ኔጌቲቭ ነገር ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን አንተ እንደሚወራለት አታስባትም፡፡ ይህ የሚያሳየው ንቁ ያልሆነው አዕምሯችን ነገሮችን ጥሩ ወይም መጥፎ ብሎ እንደማይመዝን ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ ንቁ የሆነው አዕምሯችን የሚያስተላልፍለት መረጃ ዝም ብሎ የሚቀበል መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም ኤ.ኤም ንቁ የሆነው የአዕምሮ ክፍል ስለ ልጅቱ የሚሰበስበው መረጃ ወደ ንቁ ወዳልሆነው የአዕምሮ ክፍል በተደጋጋሚ ስለላከ ንቁ ያልሆነው የአዕምሮው ክፍልም አምኖ ተቀብሎ የልጅቱን ስዕል በሚገባ ስለሳልከው ኤ.ኤም ወደ አይን ፍቅር ገባህ ማለት ነው፡፡
ከዓይን ፍቅር እንዴት መውጣት እንችላለን?
ከዓይን ፍቅር መውጫ መንገዶችን ወደ መጠቆሜ ከመግባቴ በፊት አንድ አብይ ቁም ነገር ላካፍላችሁ፡፡ የዓይን ፍቅር በሚይዘን ሰዓት የምናፈቅረው ተፈቃሪውን ሳይሆን የተፈቃሪውን ስዕል ነው፡፡ አንድ ሰው እውነተኛ ፍቅር የሚይዘው የተፈቀረውን ግለሰብ ሰብዕና ጠንቅቄ አውቀዋለሁ በሚልበት ሰዓት ነው፡፡ ይህም ሲሆን የግለሰቡን ጥሩና መጥፎ ጎኑን ያጠናና ጥሩውን አድንቆ፣ መጥፎውን ደግሞ አንድ ቀን ይለወጣል ብሎ አምኖ ወይምንም የሆነው ቢሆን ተቀብዬው እኖራለሁ ብሎ ሲቀበል ነው፡፡ የዓይን ፍቅር በሚሆንበት ሰዓት ግን የግለሰቡን ሰብዕና ሳናውቅ ነገር ግን ስለ ግለሰቡ በሃሳብ የሳልነውን ስዕል በሚገባ ስላወቅነው ስዕሉን እንወደዋለን፡፡
ስለሆነም ከዓይን ፍቅር ለመውጣት የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት የግለሰቡን ትክክለኛ ስዕል ለመረዳት መሞከር ነው፡፡ የግለሰቡን ትክክለኛ ስዕል በሚገባ ለማወቅ ደግሞ የግለሰቡን ሰብዕና ወይም ማንነት በቅርበት መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ጠያቂያችን ኤ.ኤም ሁሌ የምታስባትን ልጅ በጥልቀት ቀርበህ ትክክለኛ ማንነቷን ካወቅክ በኋላ ስለ እሷ ያለህን ሃሳባዊ ስዕል በትክክለኛው የእሷ ስዕል መቀየር አለብህ፡፡
በተግባር በምናይበት ሰዓት ግን በዓይን ፍቅር የወደቅንለትን ሰው በአካል ቀርቦ ለማነጋገር ብሎም ለማጥናት አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምን አስቸጋሪ እንደሚሆንና ጠያቂያችንም ለምን የገዛላትን ስጦታ ለመስጠት እንደከበደህ ላብራራልህና የመፍትሄ አቅጣጫ ልጠቁምህ፡፡
ስለ አንድ ግለሰብ በተደጋጋሚ ይነገረንና ስለ ግለሰቡ የራሳችን የሆነ ሃሳባዊ ስዕል በአዕምሯችን እንስላለን፡፡ ያንን ግለሰብ በተግባር ስናገኘው ደግሞ አዕምሯችን የሰውዬውን ትክክለኛ ስዕል ይስላል፡፡ በአብዛኛው እነዚህ ሁለት ስዕሎች ይጋጩብናል፡፡ በዚህ ጊዜ አዕምሯችን የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ ግጭት ደግሞ አዕምሯችንን ሰላም ያሳጣዋል፡፡ የሰው ልጅ በባህሪው ደግሞ ሰላን የሚያሳጣውን ነገር ይፈራል፡፡ ስለሆነም መሸሽን ይመርጣል፡፡ ስለዚህም በአይን ፍቅር የወደቅንለትን ሰው በአካል ብንቀርበው ሊፈጠር የሚችለው አዕምሯዊ ግጭት ስለማንፈልገው እንፈራዋለን፡፡
በዓይን ፍቅር የወደቅንለትን ሰው ከተቀራረብነው በኋላ የሚከሰት አንድ አብይ ችግር አለ፡፡ የዓይን ፍቅር ሲይዘን ስለ ግለሰቡ የሳልነውን ሃሳባዊ ስዕል ይዘን ግለሰቡን ስንቀርበውና የግለሰቡን ማንነት እያወቅነው ስንመጣ ግለግለሰቡ ትክክለኛ ስዕል እየሳልን እንመጣለን፡፡ ነገር ግን አዕምሯችን የአንድን ግለሰብ ስዕል በሌላ ለመተካት ጊዜ ይወስድበታል፡፡
በተጨማሪም የቀድሞውን ስዕል በአዲስ መተካቱ ውስጣዊ ሰላሙን ያዛባዋል፡፡ ይህ ስለሆነም በዓይን ፍቅር ወድቀን ተፈቃሪውን እየቀረብነውና እያወቅነው እየመጣን እንኳ አዕምሯችን የሳለውን ስዕል በእውነተኛው ስዕል ሳይተካው ይቀርና ያፈቀርነውን ሰው በውል ሳንረዳው ወደ ትዳር ዓለም ዘልቀን ለመግባት እንሯሯጣለን፡፡
ይህ ደግሞ በትዳር ዓለማችን ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግርና በአፍቃሪው ላይ ከፍተኛ አዕምሯዊ ፀፀት ብሎም የአዕምሮ ጤና ችግር ያስከትልበታል፡፡ ምክንያቱም ሃሳባዊ ስዕሉ የሰውዬውን ማንነት በደንብ እንድንረዳ አድርጎን እውነተኛውን የግለሰቡን ሰብዕና ሳንረዳ ወደ ትዳሩ ዓለም እንዘልቅና በኋላ ላይ በትዳር ዓለም ስንሆንና የግለሰቡን እውነተኛ ማንነትና ትክክለኛ ነው ብለን የተቀበልነው ማንነቱ ሲጋጭብን ትዳራችንን ለግጭት አዕምሯችንን ደግሞ ለፀፀት ያጋልጠዋል፡፡ በመሆኑም አንተም ተፈቃሪዋን ቀስ በቀስ ቅረባት፡፡
ለምሳሌ መጀመሪያ በስልክ እየደወልክ ወሬዎችን ለረዥም ጊዜያት ማውራትን ተለማመድ፣ ስለራስህ በመግለፅ ስለ እሷ እንድትገልጽልህ በማድረግ፣ እራስህን ገልፀህላት የሆነ ቦታ እንድታይህ በማድረግ፣ አካባቢያችሁ በሚገኝ ቦታ እንድታይህ በማድረግ፣ አካባቢያችሁ በሚገኝ ቦታ ሁለታችሁንም የሚያውቁ ሰዎች ባሉበት ቦታ በመገናኘት፣ ቀስ እያላችሁም ብቻችሁን በመገናኘት ወዘተ… የመቀራረብ ሁኔታችሁን ማዳበር፡፡ በአዕምሮህ ሃሳባዊ ስዕል ከሳልከው በኋላ በአካል ያገኘኸውን ሰው ለማነጋገር፣ ለመቅረብ ቀስ በቀስ ግን እያወቅከው ትመጣና በስተመጨረሻ ለምደኸው ልክ እንደሌሎች ሰዎች አይነት እንደሆነና የተለየ እንዳልሆነ ትረዳዋለህ፡፡ ይህ ጊዜ ይወስዳል እንጂ መሆኑ አይቀርም፡፡ እዚህ ላይ ግን ላስጠነቀቅህ የምፈልገው ነገር ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልህ ከዚህ ቀደም ስለ እሷ የሳልከው ስዕል የአሁን ማንነቷን/እውነተኛ ማንነቷን እንዳታውቅ ሊያደርግህ ስለሚችል ሌላ በህይወት ወሳኝ የሆነ ውሳኔን ከመወሰንህ በፊት የእርሷን እውነተኛ ማንነት ከሞላ ጎደል በሚገባ ልታውቅ ይገባሃል፡፡
ያን ካላረግክ ግን በወደፊቱ ህይወትህ ለሚመጣው መመሰቃቀል ኃላፊነቱን በፍቃደኝነት ወስደሃል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ ቅረባት፣ ማንነቷን በሚገባ እወቀው፡፡ በስተመጨረሻም አስፈላጊውን ውሳኔ ወስን፡፡ አጠቃላይ ምክሬ ነው፡፡ አበቃሁ፡፡ መልካም የፍቅር ጊዜ ይሁንልህ፡፡
The post Health: ከዓይን ፍቅር እንዴት መውጣት እንችላለን? appeared first on Zehabesha Amharic.