አንሄልዲ ማሪያ ወደ እግርኳስ የመጣው በአጋጣሚ ነው፡፡ ተጨዋቹ በልጅነቱ ቅዥቅዝ ያለ ነበር፡፡ ይህ ያሳሰባቸው ቤተሰቦቹ ወደ ሐኪም ቤት ወሰዱት፡፡ ዶክተሮቹ ልጃቸው ላለበት ችግር መፍትሄው እንቅስቃሴ የሚያደርግበትን መፍጠር መሆኑን ለቤተሰቦቹ አስረዷቸው፡፡ አል ቶሪቶን የተቀላቀለው ያን ጊዜ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚናገሩት ሮሳሪዮ ሴንትራል የስድስት ዓመቱን ተጨዋች በመውሰድ ጥያቄ ሲያቀርብ ኤል ቶሪቶ ለዝውውሩ እውን መሆን በምላሹ የጠየቀው 26 ኳሶችን ብቻ ነበር፡፡ የሚያስገርመው በ1974 የዓለም ዋንጫ ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገውን የሆላንድ ብሔራዊ ቡድን ለመዘከር ብርትኳናማ ማሊያ የሚለብሰው ኤል ቶሪቶ የጠየቃቸውን ኳሶች እንኳን ያልተቀበለ መሆኑ ነው፡፡
ለዲ ማሪያ ዝውውር የወጣው ገንዘብ ጉዳይ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ዝውውሮች በአርጀንቲና እግርኳስ በየትኛውም እርከን ላሉ ቡድኖች የህልውና መሰረት ናቸው፡፡ ዲ ማሪያ ከቤንፊካ ወደ ሪያል ማድሪድ እንደዚሁም የብሪታኒያ ሪከርድ በሆነ ዋጋ ከማድሪድ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ያደረገው ዝውወር ለሮሳሪዮ ሴንትራል ጥሩ የገቢ ምንጭ ሆኖለታል፡፡ በስምምነታቸው መሰረት ዲ ማሪያ ከሚያደርጋቸው ዝውውሮች 2% የሚሆነውን ገንዘብ ለአርጀንቲናዊው ክለብ ገቢ ይሆናል፡፡ በ1978 የዓለም ዋንጫን ወዳስተናገደው ስታዲየም የሚገባው ገንዘብ ከዚህም በላይ ሊሆን የሚችልበትን አጋጣሚ ያልተጠቀመበት ክለብ ራሱ ነው፡፡ ተጫዋቹ ወደ ቤንፊካ ሲያመራ ሴንትራል 20% የዝውውር መብት ነበረው፡፡ በኋላ ላይ ግን ቤንፊካ የተወሰነ ገንዘብ ከፍሎ የዝውውር መብቱ እንዲያንስ አደረገ፡፡
‹‹ለሁሉም ተጨዋቾች ወደ አውሮፓ መጓዝ ህልም እንደሆነው ሁሉ እኔም ወደ ሴንትራ የመመለስ ህልም አለኝ›› ሲል ዲ ማሪያ ሴፕቴምበር ላይ ተናግሯል፡፡ አብዛኞቹ አርጀንቲናውያን ተጨዋቾች መነሻቸውን አይዘነጉም፡፡ በአውሮፓ መድረክ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እንዲችሉ መንደርደሪያ የሆነችውን ክለብ ተመልሰው የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ ዲ ማሪያ በአንድ ወቅት ከሜሲ ጋር እንዲቀራረቡ ያደረጋቸው በአንድ ከተማ ማደጋቸው እንደሆነ ሲጠየቅ ‹‹እንደዚያ ለማለት እንኳን አልችልም፡፡ ሜሲ ኔዋልስ እኔ ደግሞ ሴንትራል ነኝ›› በማለት ሮሳሪዮን ለሁለት የከፈላትን የእግርኳስ ባላንጣነት ያስታውሳል፡፡
ዲ ማሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለሮሳሪዮ ሴንትራል ያከናወነው በ17 ዓመቱ ነው፡፡ በወቅቱ የክለቡ አሰልጣኝ የነበሩት በክለቡ ጋር ሶስት ዋንጫዎችን ያነሱት እና በኖቬምበር 2014 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አንሄል ዞፍ ነበሩ፡፡ ዲ ማሪያ ለሴንትራል ዋናው ቡድን የተጫወተው ለሁለት ዓታት ብቻ ነው፡፡ ያ የሆነው ክለቡ ታዳጊን በጥሩ የዝውውር ዋጋ ለመሸጥ በመፈለጉ ነው፡፡ በዚያ ጊዜ ውስጥ ከ40 ያነሱ ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈ ሲሆን ከስድስትየተለያዩ አሰልጣኞች ጋር ሰርቷል፡፡ በሮሳሪዮ ሳለ የተወሰኑ የአካባቢው ጋዜጣዎች ፕሴይሜከር ብለው ገልፀውት ነበር፡፡ ነገር ግን ቀጥተኛ አጨዋወቱ እና ፍጥነቱ በመስመር ለማጥቃት የተመቸ ነበር፡፡ ቤንፊካም ክለቡን ለቅቆ የሄደው ሺማኦ ምትክ አደረገው፡፡
ዲ ማሪያ ቤንፊክ የደረሰው የሊዝበኑ ክለብ አለመረጋጋት ውስጥ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ በ2007 የፖርቹጋሉን ቡድን ሲቀላቀል ዝውውሩ ወደ አውሮፓ ታላላቅ ክለቦች በሚያደርገው ጉዞ መሸጋገሪያ መሆኑን ገልጿል፡፡ በአስተያየቱ የቤንፊካ ታማኝ ደጋፊዎች መጠነኛ ቅሬታ ተሰምቷቸዋል፡፡ ነገር ግን ንግግሩ የታዳጊውን ወሳኝ ሰብዕና የሚገልጽ ነበር፡፡ በተሰጥኦው እንደሚተማመን ጠቋሚ ነበር፡፡ መጀመሪያ አካባቢ አጨዋወቱን ለመግለፅ ተቸግሮ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ የድንቅ ብቃት ባለቤት መሆኑን የሚጠቁሙ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ የዘለለ ተፅዕኖ አልነበረውም፡፡ ነገር ግን ሆርጌ ጂለስ የቤንፊካ አሰልጣኝ ሆነው ሲሾሙ ሁሉም ነገር ተለዋወጠ፡፡ ‹‹በእኔ ላይ ከልቡ እምነት የጣለ የመጀመሪያው አሰልጣኝ ጃሰስ ነበር›› በማለት ዲ ማሪያ በኋላ ላይ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ አሰልጣኙም ቢሆኑ በአርጀንቲናዊው ላይ ያሳዩት አቋም ተገቢውን ዋጋ አስገኝቶላቸዋል፡፡
በ2010 ቤንፊካ በሚያስደንቅ ብቃት ወደ ዋንጫ ሲገሰግስ አርጀንቲናዊው እጅን በአፍ የሚያስጭን እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ አበርክቷል፡፡ ጄሰስ ተግባራዊ ያደረጉት ከፍተኛ ፍጥነት ያለው አጨዋወት እና በግራ መስመር ከፊቢዮ ኮኤንትራኦ ጋር የፈጠሩት ጥምረት አጨዋወታቸውን ለማቆም የሚያስቸግር አድርጎት ነበር፡፡ ንሰሮቹ በርካታ ጥሩ እንቅስቃሴ ባደረጉበት በዚያ የውድድር ዘመን ዲ ማሪያ የማይዘነጉ አጋጣሚዎች ነበሩት፡፡ በዩሮፓ ሊግ ኤቨርተንን ሲገጥሙ እና በፕሪሜራ ሊጋው ሊይክሰስን ሲገጥሙ ድንቅ ነበር፡፡ አርጀንቲናዊው ብቻውን ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ተጋጣሚዎቻቸውን ከጥቅም ውጪ አደረጋቸው፡፡ በዚያ የውድድር ዘመን ዲ ማሪያ ምር ብቃቱን በማሳየቱ ቤንፊካ ሊያቆየው አልቻለም፡፡ በ2007 ለክለቡ ሲፈርም የተነገረው ነገር እውነት ነበር፡፡ አሁን ያንን በማለቱ የሚኮንነው የለም፡፡
ከኢንተር ሚላን ጋር የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግን ካሸነፉ በኋላ የስፔኑን ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ የተረከቡት ጆዜ ሞውሪንሆ 30 ሚሊዮን ዩሮ ከፍለው ወደ ቤርናቢዮ ያመጡት የመጀመሪያው ተጨዋች እርሱ ነበር፡፡ ዲ ማሪያ በቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች ለመሆን ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ በካርሎ አንቼሎቲ ዘመንም ወሳኝ ተጨዋች መሆኑን አስመሰከረ፡፡ ባለፈው ግንቦት ሪያል ማድሪድ ለአስረኛ ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ሲያነሳ በፍጻሜው ጨዋታ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው እርሱ ነው፡፡
በላሊጋ በቆየባቸው አራት የውድድር ዘመናት ዲ ማሪያ 49 ጎል የሆኑ ኳሶችን አቀብሏል፡፡ ለጎል አመቻችቶ በማቀበል የሚበልጠው በሊዮኔል ሜሲ ብቻ ነበር፡፡ በሁሉም ውድድሮች ላይ ባደረጋቸው 190 ጨዋታዎች 36 ጎሎችን ሲያስቆጥር 72 ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡ እነዚህ ቁጥሮች ለምን ካርሎ አንቼሎቲ ለተጨዋቹ ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጡ ይጠቁማሉ፡፡ ነገር ግን አሃዛዊ መረጃዎቹ ብቻቸውን ሙሉውን ታሪክ አይነግሩም፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን በ80 ሚሊዮን ፓውንድ የተገዛውን ጋሬት ቤል በአሰላለፍ ውስጥ ለማካተት ሲባል ወደ ግራ መስመር ቦታ እንዲለውጥ መደረጉን የተቀበለው በፍቃደኝነት አልነበረም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ዲ ማሪያ ያለመታከት ወሳኝ እንቅስቃሴዎችን ያደርግ ነበር፡፡ የተከላካይ መስመሩን ከአጥቂዎች ጋር በማገናኘት የታክቲክ ብስለቱንም አሳይቷል፡፡
አንቼሎቲ ዲ ማሪያን ማጣት አልፈለጉም ነበር፡፡ በተለይ በብራዚሉ የዓለም ዋጫ አርጀንቲናን ለፍፃሜ ለማብቃት የተወጣውን ሚና ከተመለከቱ በኋላ ለተጫዋቹ የነበራቸው ክብር ጨምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ዲ ማሪያ በማድሪድ የውስጥ ፖለቲካ እና ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ የኃይል ሚዛናቸውን አስጠብቀው ለመቆየት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተስፋ ቆረጠ፡፡
በዓለም ዋንጫ ድንቅ ብቃቱን ከማሳየቱ በፊት ኮሎምቢያዊው ሃሜስ ሮድሪጌዝ በማድሪድ የዝውውር ራዳር ውስጥ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ባላንጣቸው ባርሴሎና ልዊስ ሱአሬዝን በማስፈረሙ ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ትልቅ ስም ያለው ተጨዋች ወደ ቡድናቸው መቀላቀል ፈለጉ፡፡ የስፔኗ ዋና ከተማ ቡድን ቶን ክሩስን በማስፈረሙ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ወደ ቡድኑ ይቀላቀላል፡፡ የሮድሪጌዝ ቤርናቢዩ መድረስ ደግሞ ፔሬዝ በስልጣን ላይ በነበሩባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ እንደሚያደርጉት ትኩረት የሚሰጡ ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ መቀላቀላቸውን ይጠቁማሉ፡፡
ማድሪድ ለዲ ማሪያ አዲስ ኮንትራት አቅርቦለት ነበር፡፡ እንዲያውም ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ቀጥሎ ከፍተኛው ተከፋይ ተጨዋቾች ሊያደርጉት ተዘጋጅተው እንደነበር ፔሬዝ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ዲ ማሪያ በማድሪድ ቤት ተፈላጊነቱ እንደቀነሰ አሰበ፡፡ ከክለቡ ሌሎች ተጨዋቾች ያነሰ ትኩረት እንደሚሰጠውም አሰበ፡፡ በኋላ ላይ አስ የተባለው የማድሪድ ዕለታዊ ጋዜጣ ተጨዋቹ ክለቡን የለቀቀው ‹‹በበርካታ ማሊያዎችን ስለማይሸጥ›› በማለት ፅፏል፡፡ በዚህ ምክንያት ዲ ማሪያ ኦገስት ላይ የብሪታኒያ የዝውውር ሪከርድ በሆነ 59.7 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ አመራ፡፡ ‹‹ክለቡ እርሱን ለማቆየት የቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ነገር ግን የእርሱ ውሳኔ የተለየ ነበር፡፡ መልካሙን ሁሉ እንመኝለታለን›› በማለት አንቼሎቲ ያለውዴታቸው ያጡትን ተጨዋች ተሰናብተዋል፡፡
ኦልድ ትራፎርድ ሲደርስ ቀድሞ ጆርጅ ቤስት፣ ኤሪክ ካንቶና፣ ዴቪድ ቤካም እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ የለበሱት ሰባት ቁጥር ማሊያ ተበረከተለት፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ ልዊስ ቫን ሃል ማንቸስተርን በእንግሊዝ እግርኳስ ወደቀድሞ ክብሩ መመለስ እንዲችሉ ለመርዳት ክለቡ ከመደበው 150 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደው በብራዚል ድንቅ ጊዜን ያሳለፈው አርጀንቲናዊ መሆኑ አያስገርምም፡፡
ሪዮን በምልሰት
አርጀንቲናዊያን በጁላይ 12 ቀን 2014 በሪዮ ደ ጄኔይሮው ማሬካኛ ስታዲየም የተከናወነውን ጨዋታ እያስታወሱ እንዲህ ቢሆን ኖሮስ ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ጎንዛሎ ሂጉዌይን በጨዋታው መጀመሪያ አካባቢ ያገኘው አጋጣሚ የተጠቀመበት ቢሆን ኖሮስ? በኋላ ላይ ሮድሪጎ ፓሊሲዮ ኳስ እና መረብ አገናኝቶ ቢሆን ኖሮ? ሜሲ ወይም ሰርጂዮ አጉዌሮ በቶርናመንቱ ላይ በተሻለ አቋም ላይ ቢሆንስ ኖሮ? ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚደመጠው ደግሞ በዕለቱ ዲ ማሪያ ለጨዋታ ብቁ ሆኖ ቢሆንስ ኖሮ? የሚል ነው፡፡
በሪያል ማድሪድ ቁልፍ ተጨዋቾች መሆን ሲጀምር በአርጀንቲናውያን ብሔራዊ ቡድንም ተፅዕኖው መጉላት ጀምሮ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ሜሲ፣ አጉዬሮ እና ሂግዊይንን የያዘውን የፊት መስመር ከአማካይ ክፍሉ ጋር በማገናኘት በኩል ሚናው የጎላ ነበር፡፡ የአማካይ እና የተከላካይ ክፍሉን ያለመታከት ያግዝም ነበር፡፡
በዓም ዋንጫው አሌሃንድሮ ሳቤላ ቡድናቸው ቀጥተኛ የሆነውን እና ከቶርናመንቱ በፊት ውጤታማነቱ የተረጋገጠውን የመልሶ ማጥቃት እንዳይተገብር አደረጉ፡፡ ይህም አርጀንቲና በሚገባው መጠን አስፈሪ እንዳትሆን አደረገ፡፡ ቡድኑ የምድብ ማጣሪያውን ማለፍ የቻለው ሜሲ ባስቆጠራቸው አራት ጎሎች ታግዞ ነበር፡፡ ነገር ግን ሜሲ እራሱ በአንደበቱ እንደተናገረው ቶርናመንቱ እየገፋ ሲሄድ ድካም ተጫጭኖት ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሂግዌይንም ሆነ አጉዌሮ በምርጥ ብቃታቸው ላይ መገኘት አልቻሉም፡፡ ውድድሩ እየገፋ ሲሄድ የቡድኑ ዋነኛ ተስፋ ዲ ማሪያ ነበር፡፡ ወደ ሩብ ፍፃሜ የተደረገውን ጉዞ ያቃናው ስዊዘርላንድ ላይ ባለቀ ሰዓት ያስቆጠረው ጎል ነው፡፡ ምንም እንኳን ከቤልጅየም ጋር ሲጫወቱ ብቸኛውን ጎል ያስቆጠረው ሂግዌይን ቢሆንም በሙሉም የቶርናመንቱ መርሃ ግብሮች የማይዋዥቅ አቋም ያሳየው ዲ ማሪያ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው የፍፃሜ ጨዋታ አርጀንቲና ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ብትችልም እጅግ ወሳኝ ተጨዋች ሜዳ ላይ አልነበረም፡፡
ዲ ማሪያ ለአርጀንቲና ባደረገው የመጀመሪያ ቶርናመንት ላይም የፍፃሜው ጨዋታ አምልጦታል፡፡ በ2007 በካናዳ በተዘጋጀው እና በአርጀንቲና የአጉዌሮ ቶርናመንት በመባል በሚታወቀው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ አጋጣሚው ተከስቷል፡፡ ቶርናመንቱ በአርጀንቲና ያንን ስያሜ ያገኘው የሲቲው አጥቂ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ የወርቅ ጫማውን በመውሰዱ ነው፡፡ በዚያ ቡድን ውስጥ ከነበሩ እና በ2014 የብሔራዊ ቡድኑ አካል ከነበሩ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ግብ ጠባቂው ሰርጂዮ ሮሜሮ ነው፡፡ በፍፃሜው አርጀንቲና ቼክ ሪፐብሊክን 2-1 ስታሸንፍ ዳ ማሪያ ባጋጠመው የጡንቻ ህመም ምክንያት ሜዳ ውስጥ አልነበረም ሲሉ ቀልደዋል፡፡
ምንም እንኳን በወዳጅነት ጨዋታ ላይ ቢሆንም ባለፈው ሴፕቴምበር ዲ ማሪያ አርጀንቲናውያን ያጡትን ነገር አሳይቷቸዋል፡፡ ጥሩ እንቅስቃሴ ከማድረጉም በላይ አራት ኳሶችን ለጎል አመቻችቶ አቀብሏል፡፡ አጋጣሚው ልዩ የሚያደርገው ተጋጣሚያቸው ጀርመን መሆኑ ነው፡፡
ዲ ማሪያ እስካሁን በቤንፊካ እና ማድሪድ ያሳየውን አይነት አቋም በዩናይትድ አላበረከተም፡፡ ጥሩ አጀማመር ቢያደርግም ተደራራቢ ጉዳት እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ ቫንሃል ምቹ ፎርሜሽን ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ምክንያት የመሀል ሜዳ አማካይ ሚና እንዲወጣ እየተደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ገና 26 ዓመቱ በመሆኑ ብቃቱን የሚያስመሰክርበት በቂ ጊዜ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
The post ዲ ማሪያ – ከሮሳሪዮ እስከ ዩናይትድ appeared first on Zehabesha Amharic.