የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐት ጀምሮ ለአራት ቀናት ያካሔደውን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ኹለተኛ ዓመታዊ ቀኖናዊ ጉባኤ ሲያጠናቀቅ ባወጣው ባለዐሥራ አንድ ነጥቦች መግለጫው÷ በሊቢያ ራሱን እስላማዊ መንግሥት(ዳኢሽ) እያለ የሚጠራው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን ስለ ክርስቲያንነታቸው በግፍ እና በአሠቃቂ አኳኋን የገደላቸውን ኢትዮጵያውያን እና ግብጻውያን ኦርቶዶክሳውያን የሰማዕትነት ሥያሜ በመስጠት በሰማዕትነት ክብር ማክበሩን አስመልክቶ፣ ተከታዮቹን ኹለት ዐበይት ውሳኔዎች ማሳለፉን ዛሬ፣ ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. አስታውቋል፡-
-
ምንም ጥፋት እና በደል ሳይኖርባቸው ክርስቲያኖች በመኾናቸው ብቻ በሊቢያ ሀገር አይ ኤስ በተባለ የአሸባሪ ቡድን በግፍ እና በሚዘገንን ኹኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በሟቾቹ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ተወያይቶ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ያለውን ኹኔታ በጥልቀት ከተረዳ በኋላ ሟቾቹ የዘመኑ ሰማዕት እንዲባሉተስማምቶ ወስኗል፡፡
2. እንዲኹም እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ሚያዝያ ፲፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በሊቢያ የተሠዉት 30 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ልጆቻችን እና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት 15 ቀን 2015 በሊቢያ የተሠዉት 21 የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ክርስቲያኖችበኹለቱም አብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶስ የሰማዕትነት ክብር የተሰጣቸው ስለኾነ፣ የኹለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት የ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት ተብለው በአንድነት እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡
3. በልዩ ልዩ ምክንያት ከኢትዮጵያ ሀገራቸው ወጥተው በባዕድ ሀገር የሚገኙትንና ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል እና ለማቋቋም ቤተ ክርስቲያናችን መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ጋራ በመቀናጀት አስፈላጊውን ኹሉ እንድታደርግ፣ ይህን በተመለከተ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ፣ የቤተ ክርስቲያናችን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንም ርዳታ ሰጪዎችንም በማስተባበር ሓላፊነቱን ወስዶ በንቃት እና በትጋት እንዲሠራ ጉባኤው ወስኗል፡፡
The post ቅዱስ ሲኖዶስ: በሊቢያ ክርስቲያን በመኾናቸው የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ‹‹የዘመኑ ሰማዕት›› እንዲባሉ ወሰነ፤ ‹‹የ፳፩ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰማዕታት›› በመባል በአንድነት ይታሰባሉ!!! appeared first on Zehabesha Amharic.