Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

አሁን ገና ‹‹ፕሮፌሰሮቹ›› ሞቱ

$
0
0

ከዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

ባለፈው ወርኃ መጋቢት 19፣ ቅዳሜ ቀትር ላይ ከወዳጆቼ አንዱ ይደውልልኛል፡፡ ለጥሪው ምላሽ ስሰጥ፣ በዚያው ሰዓት ከሸገር ኤፍ. ኤም 102.1 እየተላለፈ የነበረውን የቀትር ወሬዎች እንዳዳምጥ ይጠቁመኛል፡፡ የስርጭት መሥመሩን አስተካክዬ ሳዳምጥ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ ከምክትል ፕሬዝዳንቶቹ ጋር ስለ ሰጡት መግለጫ የሚተላለፍ ዘገባ ነበር፡፡ ከመግለጫ አርእስተ ጉዳዮች ውስጥ ዩኒቨርስቲው እኔን እና ዶ/ር መረራ ጉዲናን ስለማባረሩ የተመለከተ ማብራሪያ ይገኝበታል፡፡
Dr Dagnachew
ዘገባውን በማዳመጥ ላይ እንዳለኹ በአእምሮዬ የመጣችው ዕውቋ ድምፃዊት አስቴር ዐወቀ ነበረች፡፡ የፕሬዝዳንቱን እና በተለይም የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ጄይሉ ዑመርን ከእውነት የማፍግፈግ እና ሐቅን የመሸፋፈን ድርጊት በተመለከተ ‹‹እስኪ ይሰማለት ምን አለችኝ ይላል›› እና ‹‹ራሱ በድሎ ራሱ አለቀሰ፤ በአሉባልታ ፈረስ አገር አዳረሰ›› የሚሉት የድምፃዊቷ ዜማዎች እና የዜማ ስንኞች በአዕምሮዬ ላይ ተመላለሱ፡፡

ለአንባቢያን ግልጽ ይኾን ዘንድ ኹለቱ የዩኒቨርስቲው ሹማምንት፣ ከሪፖርተሩ ጋዜጠኛ ነአምን አሸናፊ ሲቀርብላቸው የሰማኹት ጥያቄ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፡-

“ከሠራተኛ ምደባ ጋራ በተያያዘ ከመድረኩ የተብራራ ነገር ነበር፡፡ ምደባው የተከናወነው በሕጉ መሠረት አድርጎ ግልጽነት በተሞላበት አኳኋን ነው ተብሏል፡፡ በሚዲያዎች እንደምንሰማው ደግሞ ከኹለት ወይም ከሦስት መምህራን የቅጥር ውል እድሳት ጋራ በተያያዘ የተለያዩ ዘገባዎችን እያዳመጥን ነው፡፡ በተለይም ዶ/ር ዳኛቸውን እና ዶ/ር መረራን ይመለከታል፡፡ ከዶ/ር መረራ ጉዳይ ጋራ በተገናኘ የፖሊቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሊቀ መንበር ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ ከሓላፊነታቸው መልቀቃቸውን ሰምተናል፡፡ በነዚኽ ጉዳዮች ላይ የዩኒቨርስቲው አያያዝ እና ምላሽ ምንድን ነው? የሰዎቹ የኮንትራት ውልስ ያልታደሰው ለምንድን ነው? ”

ለዚኽ ጥያቄ ፕሬዝዳንቱ እና ምክትላቸው የሰጧቸው መልሶች፣ የመጀመሪያው የአሠራር ሒደትን የሚመለከት ሲኾን፣ ኹለተኛው ደግሞ የአካዳሚክ ስታፍን የሥራ አፈጻጸም የሚጠቅስ ነው፡፡ ሹማምንቱ በእኒኽ ኹለት ነጥቦች ላይ በማተኮር ከሰጧቸው ምላሾች የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው፤
አንደኛ ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ ከተናገሩት፡-

“የኹለቱ መምህራን ጥያቄ ከጡረታ ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ ይኼ እንግዲኽ መንግሥት ያወጣው መመሪያ አለ፤ ደንብ አለ፤ አንድ የአካዳሚክ ሠራተኛ የጡረታ ዕድሜው ከደረሰና የሚተካው ሰው ከሌለና ከጠፋ፣ የጡረታ ዕድሜው ሊራዘምለት ይችላል፤ ይኼም ፕሮሰስ አለው፤ ከሦስት እና ከአራት ወራት በፊት ቀደም ብሎ መጀመር አለበት፤ በትምህርት ክፍሉ ይታያል፤ ማስታወቂያ ይወጣል፤ በዚያ ሞያ በገበያ ላይ ሰው ማግኘት የማይቻል መኾኑ ማስታወቂያ ይወጣና ትምህርት ክፍሉ ካየው በኋላ ለኮሌጁ ይላካል፤ ኮሌጁ ለአካዳሚክ ይልከዋል፤ ከዚያ ሒደቱን ተከትሎ ወደ ፕሬዝዳንቱ ይመጣና ለሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ይላካል፤ ጡረታ የማራዘሙ ኹኔታ፤ በዚኽ መሠረት የመጣ ጡረታን የማራዘም ጥያቄ የታገደበት ኹኔታ የለም፥ እውነቱን ለመናገር፡፡

… ለማራዘም ደግሞ ወቅቱን ጠብቆ በትክክለኛው መንገድ ማስታወቂያ ወጥቶ ገበያ ላይ ሰው ሳይኖር ሲቀር ያ በደንብ ተጠናቅሮ ለዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ይላካል፤ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ደግሞ ወደ ሲቪል ሰርቪስ የሚጠይቅበት ኹኔታ አለ፤ በነገራችን ላይ የአንድን ሠራተኛ የጡረታ ዕድሜ ለማራዘም መሥሪያ ቤቱ ፍላጎት ማሳየት አለበት፤ ሠራተኛው ይጠቅመኛል፤ የሚሠራው ሥራ አለ፤ ብሎ በደንብ አድርጎ ማስታወቂያ ማውጣት አለበት፡፡ ይህ ሒደት አለው፤ ይኼ ሕጋዊ ፕሮሰስ አለው፤ ይኼ ሕጋዊ ፕሮሰስ ተግባራዊ ባልኾነበት ኹኔታ የአንድን መምህር የጡረታ ጊዜ ማራዘም አንችልም፡፡”
ኹለተኛ ዶ/ር ጄይሉ ዑመር በበኩላቸው፡-

“ምናልባት በጡረታው ላይ አንድ ነጥብ ብጨምር ደስ ይለኛል፡፡ በመሠረቱ እንደ ሌላው ሲቪል ሰርቫንት አይደለም ሃየር ለርኒንግ አካዳሚክ ኢንስቲቱሽንስ አካዳሚክ ስታፉን የሚያስተዳድሩበት፡፡ እያንዳንዱ አካዳሚክ ስታፍ በየኹለት ዓመቱ ኮንትራት ይታደስለታል፡፡ ኮንትራት ነው የሚፈርመው፡፡ ስለዚኽ በየኹለት ዓመቱ ውስጥ የአካዳሚክ ስታፉ ፐርፎርማንስ በሚፈለገው ደረጃ ካልኾነ ተቋሙ የፈረመውን ኮንትራት ያለማደስ መብት አለው፡፡ ከጡረታ በኋላ ደግሞ የሚነሡ ጥያቄዎች፣ የሥራው ተፈላጊነት እና በቦታው የሚተካ ብቁ ሰው ያለማግኘት ኹኔታ ነው ከጡረታ በኋላ ‘further extension’ የሚጠየቅበት፡፡ በተቋሙ ጡረታን ማስረዘም እንደ ግዴታ ወይም እንደ መብት ሊነሣም አይችልም፤ በዩኒቨርስቲው የሴኔት ሕግ መሠረት፡፡”

ሹማምንቱ የዩኒቨርስቲውን የአሠራር ሒደት እና የአፈጻጸም ምዘና ሕግ ጠቅሰው የሰጡት መግለጫ የተዛባ እና ዕብለት የተመላበት ነው፤ ለዚኽም ሩቅ ሳንሔድ አልያም የእኔን ማብራሪያ ሳይሻ ወሳኝ ምላሽ አድርጌ የማቅርበው በመጀመሪያ ላለፉት አራት ዓመታት የፍልስፍና ትምህርት ክፍልን በሊቀ መንበርነት የመሩት ዶ/ር ጠና ዳዎ የእኔን የጡረታ ጊዜ ስለማራዘም እና ሳባቲካል ፈቃድ በተመለከተ በወቅቱ የሶሻል ሳይንስ ዲን ለነበሩት ለዶ/ር ገብሬ ይንቲሶ የጻፉትን ደብዳቤ ሲሆን በተጨማሪ ዶ/ር ጠናን ተክተለው እስከ አለፈው ወር መጨረሻ ድረስ የትምህርት ክፍሉ ዋና ሓላፊ የነበሩት ዶ/ር ዐቢይ ጸጋዬ፣ ለማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲኑ ፕሮፌሰር ወልደ አምላክ በዕውቀት፣ በቅርቡ በፍልስፍና ትምህርት መስክ ለሚከፈተው የሦስተኛ ዲግሪ (ዶክትሬት) መርሐ ግብር የሥራ ጊዜዬን፣ የሞያ አስተዋፅኦዬን እና ደረጃዬን አስመልክቶ የሰጡትን የማያሻማ ምስክርነት ነው፡፡

የቀድሞው የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ሊቀ መንበሩ ዶ/ር ጠና ዳዎ ባለፈው ዓመት ግንቦት 2 ቀን 2006 ዓ.ም. በጻፉት ሦስት ገጽ ደብዳቤአቸው፣ የጡረታዬ ጊዜዬ እንዲራዘም እና የሳባቲካል ፈቃድ እንዲሰጠኝ ትምህርት ክፍሉ መክሮ በወሰነው መሠረት የሚከተለውን ምስክርነት በመስጠት ጥያቄ አቅርበው ነበር፤

“…ትምህርት ክፍሉ አገልግሎታቸውን አጥብቆ የሚፈልግ በመኾኑ ደብዳቤአቸውን መነሻ በማድረግ የጡረታ ጊዜ እንዲራዘምላቸው መጠየቅ ወይም እርሳቸውን የሚተካ ባለሞያ ማዘጋጀት ነበረበት፡፡ በዚኽ መሠረት በዕድገትም ኾነ በድልድል እርሳቸውን ሊተካ የሚችል ከክፍሉ መምህራን መካከል ማግኘት አልተቻለም፡፡ ስለዚኽ በእርሳቸው ቦታ መቀጠር የሚችል መምህር ለመፈለግ በእርሳቸው ጠያቂነት ዩኒቨርስቲው በጋዜጣ ማስታወቂያ እንዲያወጣ ተደረገ፡፡ ይኹን እንጂ በተጠቀሰው ጊዜ ገደብ ውስጥ ቀርቦ ያመለከተ ሰው ባለመኖሩ ትምህርት ክፍሉ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በአመለከቱት መሠረት የአገልግሎት ጊዜአቸው እንዲራዘም ጠየቀ፡፡

…. የትምህርት ክፍሉ ባለበት የመምህራን እጥረት ምክንያት የእርሳቸውን አገልግሎት በእጅጉ ይፈልጋል፡፡ በመኾኑም የተጠቀሰው የጡረታ ጊዜ እንዲራዘምላቸውና የሳባቲካል ፈቃዳቸው የሚራዘምበት ኹኔታ እንዲመቻችላቸው የትምህርት ክፍሉ ይጠይቃል፡፡”
ዶ/ር ዐቢይ ጸጋዬ በበኩላቸው የኮንትራት ዉሌ እንዲራዘም ካቀረቡት ምክንያቶቸ ውስጥ በዋናነት የሚከተለውን እናገኛል፡-
‘Launching of the PhD program:
The department is ready to launch the PhD program during the second semester of the current academic year. The program contains two streams of the studies: Africans and Western philosophy. Even though we have excellent instructors in our department in African and Asian philosophy, Dr. Dagnachew is the only Ethiopian staff who has done his PhD in Western philosophy, as a result his services are indispensable in covering the Western stream.
In view of his diligence as a teacher and strong commitment to the world of academia, and also in lieu of his much needed services by the department, the Department is strongly looking forward for your good office to extend his services by three years.’
ይህም የእንግሊዘኛ ጽሑፍ ወደ አማርኛ ሲተረጎም፡-

“የዶክትሬት ዲግሪ መርሐ ግብር ስለ መጀመር፤
የፍልስፍና ዲፓርትመንት በተያዘው የትምህርት ዘመን ኹለተኛ አጋማሽ ላይ የዶክትሬት ዲግሪ መርሐ ግብር ይጀምራል፡፡ መርሐ ግብሩ የአፍሪቃ ፍልስፍና እና የምዕራብ ፍልስፍና የተሰኙ ኹለት የጥናት ዘርፎችን የያዘ ነው፡፡ የትምህርት ክፍላችን በአፍሪቃ እና ኤዥያ ፍልስፍና ጥናት ላቂያ ያላቸው መምህራን ቢኖሩትም በምዕራብ ፍልስፍና አስተምህሮ የዶክትሬት ጥናታቸውን የሠሩ የዲፓርትመንቱ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ባልደረባ፣ ዶ/ር ዳኛቸው በመኾናቸው በዘርፉ ያላቸው አስተዋፅኦ በእጅጉ አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው፡፡

ዶ/ር ዳኛቸው ለመምህርነት ሞያ ያላቸው አቅም እና ተነሣሽነት እንዲኹም በአካዳሚው መድረክ (በዩኒቨርስቲው) የሚያሳዩት ትጋት ለትምህርት ክፍላችን ከሚኖረው ጠቀሜታ በመነሣት የአገልግሎት ዘመናቸው መራዘም አስፈላጊ መኾኑ ታምኖበታል፡፡ ስለዚኽም የትምህርት ክፍሉ የዶ/ር ዳኛቸው የሥራ ጊዜ በሦስት ተጨማሪ ዓመታት እንዲራዘም ይደረግ ዘንድ የቢሮውን መልካም ትብብር ይጠይቃል፡፡”

ፕሬዝዳንቱ እና ምክትላቸው ከተናገሩት በተፃራሪ ከዚኽ በላይ በአስረጅነት የቀረቡት ሰነዶች ለአንባቢያን እውነታውን በሚገባ ያሳያሉ ብዬ አምናለኹ፡፡ በፍልስፍና የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች የቀረበው ገለፃ፣ የሁለቱን ሹማምንት እበላ እና ሃሰተኛ አቀራረብ ፍንትው አድርጎ እንደሚያሳይ ብዙም ክርክር አያስፈልገውም፡፡

ምናልባት እነኚህ በትልቅ ተቋም ውስጥ በኃላፊነት የተቀመጡ ግለሰቦች፣ እንዴት ከእውነት ጋር የተጣላ ግንኙነት ሊኖራቸው ቻለ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ይኖራል፡፡ እኔ እስከምረዳው ድረስ ሁለቱ ግለሰቦች የሚከተሉት ፈለግ ከእምሯዊ ግድፈት የመነጨ ችግር ብቻ ሳይሆን፣ የተደላደለ ኑሮን ለመጎናጸፍ እውነት መሽቀንጠር ካለባት ያለ ምንም ማቅማማት ገፍትረው ለመጣል ምን ግዜም ዝግጁ በመሆናቸው ነው፡፡

የድሎትንና የውሸትን ግንኙነት እና መስተጋብር ለመረዳት፣ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ‹‹ውይይት›› (Dailogue) በሚል ርዕስ በዩኒቨርስቲ መምህራን ማህበር የሚታተም መጽሔት ላይ የዛሬ አርባ አምስት ዓመት የደጃዝማች ከበደ ተሰማን ‹‹የታሪክ ማስታወሻ›› የሚባለውን አስደናቂ መጽሐፍ ሲገመግሙ፣ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚከተለውን ብለዋል፡-

‹‹… ለምን እንዲህ እንደሚሆኑ መጠይቅ አይሻም፤ በአንድ በኩል እንጀራቸው ውሸት መሆኑን፣ በአንድ በኩል ደግሞ የእውነትን ግርማና ሥቃይ ያውቁታል፡፡›› ፕ/ሩ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ሁለት አበይት የሆኑ ጉዳዮችን አቅርበዋል፡፡ አንደኛ፣ አንዳንድ ሰዎች ውሸትን የሚኖሩት ብቻ ሳይሆን፣ እንጀራቸው ውሸት ላይ የተመሰረተ መሆኑን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ‹‹እውነት ማለት የኔ ልጅ›› ብሎ እውነትን መጨበጥና አብሮ መራመድ አልፎ-አልፎ አደጋ እና ችግር እንደሚያስከትል በተዋበ ስንኝ የነገረንን፣ ከላይ እንዳየነው ቀደም ሲል ፕ/ር መስፍን የእውነትን “ግርማና” ችግር መሸከም አስቸጋሪ ስለሚሆንባቸው አንዳንድ ሰዎች ወደ ውሸት ማዘንበሉን ይመርጣሉ ሲሉ በሚያምር ገለፃ አቅርበውታል፡፡

በሌላ በኩል ኹለቱ ሹማምንት ስለ ጡረታ ጊዜ ማራዘም ከሰጧቸው ማብራሪያዎች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ነገሮችን መመልከቱ አስቸጋሪ አይኾንም፡፡ ከኹሉ በፊት፣ ፕሬዝዳንቱ የጡረታ ጊዜን ለማራዘም ዩኒቨርስቲው ጥያቄ ያቀርባል እንጂ፣ ሥልጣኑ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ ደግሞ የጡረታ ጊዜውን ለማራዘም ወሳኝ የኾነው ሒደት በዩኒቨርስቲው ተቋማዊ ሥርዐት እና ደንብ ውስጥ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ይኸው በራሳቸው ቃል በወሳኝነት የተገለጸውና ዲፓርትመንቱ እንዲኹም ኮሌጁ ሕጋዊ አካሔዱን ተከትለው ያቀረቡትን የማራዘም ጥያቄ ተቀብለው ተገቢውን ምላሽ መስጠት ተስኗቸዋል፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴርም ቢኾን በዩኒቨርስቲው የተጠየቀውን የጡረታ ማራዘም ጥያቄ ያለአንዳች ማንገራገር ተቀብሎ ያስተናግዳል እንጂ፣ ፕሬዝዳንቱ ከተጠያቂነት ለመሸሽ እንዳደረጉት፣ ‹‹ሞያዊ አስተዋፅኦው ተፈላጊ ነው›› የተባለን መምህር የማባረሪያ ምክንያት ሊኾን አይችልም፡

ሳባቲካል ፈቃድን በተመለከተ፣ አሠራሩ አንድ መምህር ለስድስት ተከታታይ ዓመት ካስተማረ፣ አንድ ዓመት የጥናት እና ምርምር ፈቃድ ዕረፍት እንደሚያገኝ በሴኔት ሕጉም ኾነ በሥራ ውሉ ላይ በግልጽ የተቀመጠ ነው፡፡ ኾኖም ፕሬዝዳንቱ አንድ መምህር በማመልከቻ ቅጹ መሠረት ፈቃዱን ሲጠይቅ ጠቅሶ እና አካትቶ የሚያቀርባቸውን የተለመዱ ነጥቦች የማይታወቁ ያኽል፣ ከሳባቲካል ፈቃድ መልስ ‹‹ብቁ አስተማሪ ይኾናል፤ ምርምር እየሠራ አስተዋፅኦ ያደርጋል›› በማለት መናገራቸው ነገሮችን ለማወሳሰብ ካልኾነ በቀር፣ ለተያዘው ጉዳይ ምንም ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በእኔ ሳባቲካል ፈቃድ ጉዳይ ወደሚመለከተው ፍርድ ቤት የሚያመራ ቢኾንም ፕሬዝዳንቱ እና ምክትላቸው ከተናገሩት በተቃራኒ ከጡረታ ዘመኔ በፊት ማቅረቤን የሚያሳይ ማስረጃ በእጄ ይገኛል፡፡

ነፃነትና ዩኒቨርስቲ

ከግል ጉዳዬ ትንሽ ፎቀቅ ብዬ ስለሰው ልጅ የነፃነት ሕሊና እና ስለ ዩኒቨርስቲ ባህርያት የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡
Beings who have received the gift of freedom are not content with enjoyment of
comfort granted by others.
[ Immanuel Kant, The Quarrel Between the Faculties (1798) ]
ትርጉም፡- የነፃነትን ጸጋ የተሰጡ ህልዋን (ሰዎች) ከሌሎች በሚናኝ ተድላ እና ምቾት፣ ደስታ እና እርካታ
አያገኙም፡፡ (ኢማኑኤል ካንት)
ነፃነት ለሰው ልጅ ተፈጥሮ ባሕርያዊ ቢኾንም፣ አልፎ አልፎ ሰው ለቁሳዊ እና ጊዜያዊ ፍላጎቱ ሲል፣ ባሕርያዊ ነፃነቱን አሳልፎ ይሰጣል፤ መጽሐፉም፣ ብኵርናውን በምስር ወጥ ስለለወጠው ዔሳው ያስተምረናል፡፡ በዩኒቨርስቲው ላዕላዊ አመራር ውስጥ ያለው ሰብአዊ እና አእምሯዊ ነፃነትን ከሚፈታተኑ ቁልፍ ችግሮች አንዱ ይኼ ነው፡፡

በሌላ በኩል፣ ከመልካም አስተዳደር የተጣላ ሥርዐት እንዲያብብ ያደረገው በዩኒቨርስቲው አሠራር ውስጥ የሰረገው ጥቅምን መሠረት ያደረገ ሽርክናዊነት (Patrimonialism) ነው፡፡ እንደ ዕውቁ የኻኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሥነ ማኅበረሰብ ተመራማሪ ማክስ ቬበር (Max Weber)፣ ጥቅምን መሠረት ያደረገ ዝምድና በመደበኛ እና በግላዊ የሥራ ድባብ መካከል ልዩነት አያደርግም፡፡ አንድን ተቋም የሚመለከት ጉዳይ በሙሉ ከተቋሙ ዋነኞች የግል ስንክሳር ጋራ በማቆራኘት ነው የሚወስደው፤ ሲከፋም ተቋሙን ሳይቀር እንደ ግል ንብረት ይቆጥራል፡፡

ለዚኽም ነው፣ ዶ/ር አድማሱ በድርጊቶቻቸው እና በመግለጫዎቻቸው ደጋግመው እንዳረጋገጡት፣ ዩኒቨርስቲው ሲተች እርሳቸው በግል እንደተተቹ፣ የእርሳቸውም የአመራር አቅም ሲጠየቅ፣ የዩኒቨርስቲው ስም እንደ ጎደፈ እና እንደጠፋ የሚመስላቸው፡፡

በዚኽ ጽሑፌ ዋናው መልእክቴ፣ የፕሬዝዳንቱ እና የምክትላቸው ማብራሪያዎች እኔን በትክክል እና በአግባቡ ከሚገልጹ የዩኒቨርስቲው ሰነዶች ጋራ የቱን ያኽል እንደሚራራቁ ማስረዳት ነው፡፡ስለ ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ፣ ‹‹የካውንት ሊዮ ቶልስቶይ ጀነራል እና የኢሕአዴጉ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት›› በሚል ርእስ ሰፋ ያለ ሐተታ በቅርብ አቀርባለኹ፡፡ የጥቅቅም ሽርክናው (Patrimonialism) በተመለከተ ግን ለጊዜው፣ ምክትላቸው ዶ/ር ጄይሉ ዑመር ያሉበትን ኹኔታ በአብነት አቀርቤ ጽሑፌን እቋጫለኹ፡፡

ከላይ እንዳወሳነው፣ ሰብአዊ እና አእምሯዊ ነፃነትን በሚፈታተነው የዩኒቨርስቲው የጥቅቅም ሽርክና የተመላበት የሥራ ዝምድና፣ ለሓላፊነት እና ለሹመት ለመታጨት ቀዳሚ መለኪያው አካዳሚያዊ እና አስተዳደራዊ ብቃት ሳይኾን፣ በአገሪቱ የፖሊቲካ ክፍል በጠንካራ ዐቃቤ (Patron) መደገፍ ወሳኝ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲው ላዕላዊ አመራር ጠገግ ጠንካራ ዐቃቤ እና የፓርቲ ድጋፍ የሌለው ከፍተኛ ሹም ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ይህን የተደገፉበትን ጠንካራ አጋር ሲያጡ በራስ መተማመናቸው ከድቷቸው በሌሎች መገፍተሩ እና መናቁ የሚጠበቅ ነው፡፡ ጥቂት በማይባሉ የዩኒቨርስቲ መምህራን ዘንድ እንደሚነገረውም፣ የዶ/ር ጄይሉ ዑመር ችግር ከዚኽ ያልተለየ ነው፡፡

አንድ አረጋዊ ከዐፄ ቴዎድሮስ ጋራ በተያያዘ ያጫወቱኝ ነገር ዶ/ር ጂይሉ ዑመር ያሉበትን ኹኔታ በትክክል ሊያስረዳልኝ ይችላል፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ የሚወዱት ‘ቀንዲል’ የሚባል በሬ ነበራቸው፡፡ በሬው ባሻው ማሳ እየገባ ይበላል፤ በመሸበት ያድራል፤ ገበሬው ይቅርና ሹመኞቹ እንዲሁም ጅብ እንኳን ሳይቀር ዐፄውን ስለሚፈሩ ‹‹ማንም አይነካውም›› ይባል ነበር፡፡

የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ፍጻሜ ሲቃረብ ግን፣ በሬው ይጠፋል፡፡ ብዙ ቢታሰስም መገኛው ባለመታወቁ በጅብ ሳይኾን በገበሬዎች ታርዶ እንደተበላ ለንጉሡ ጭምጭምታ ይደርሳቸዋል፡፡ ከበሬው መጥፋት በኋላ በአጀብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ሲሔዱ በአንዳንድ ቦታ ባላገሩ ፍርድ እንዲያገኝ፣ ‹‹ንጉሥ ሆይ፣ ጃንሆይ›› እያለ አቤት ሲል፣ በፈረሳቸው እንዳሉ ወደ አጃቢዎቻቸው ዘወር እያሉ ‹‹አኹን እኮ የእውነት ‹ንጉሥ› እየመሰልኋቸው ነው›› ሲሉ አጃቢዎቻቸው ‹‹በሚገባ እንጂ፣ ንጉሥ ነዎት እኮ›› ሲሏቸው፤ እሳቸውም ‹‹የእውነት ንጉሥ ብኾን ኖሮ ‘ቀንዲልን’ አርደው ይበሉት ነበር ወይ?›› ብለው በመደመም ሳይፈርዱ አልፈው ይሔዱ ነበር፡፡

ዶ/ር ጄይሉ ዑመርም በሥልጣናቸው ክልል ሊታይና ሊወሰንበት የሚችልን ጉዳይ እና አቤቱታ ሲቀርብላቸው፣ በአንድ በኩል መልስ ባለመስጠት (በእኔ ላይ እንዳደረጉት) በሌላ በኩል ወደ ፕሬዝዳንቱ በመግፋት ድርሻቸውን አይወጡም፤ ከሓላፊነትም ይሸሻሉ፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ፍጻሜ መንግሥታቸው የተዳረሰባቸው ንጉሠ ነገሥቱ ‹‹አኹን እኮ ንጉሥ መስዬአቸው ነው›› እንዳሉት ዐቃቤአቸውን ማጣታቸውን ተከትሎ ‹‹አኹን እኮ የእውነት ምክትል አካዳሚክ ፕሬዝዳንት እየመሰልኋቸው ነው›› ሳይሉ ቀርተው ነው ብላችኹ ነው!?

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው፣ ዶ/ር ጄሉ ዑመር ያለ አጋር እና ድጋፍ (Patron) መሆናቸውን ቀድመው የተረዱት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ ናቸው፡፡ ምክትላቸው የበላይ ጠባቂያቸው እንደሌለ ሲያውቁ፣ በመጀመሪያ ያደረጉት ነገር በዩኒቨርስቲው ታሪክ የመምህራኑን የውል ዘመን የማራዘም ሥልጣን የምክትል ፕሬዝዳንቱ ሆኖ ሳለ፣ ፕሬዝዳንቱ የሆነ የሲቭል ሰርቪስ አንቀጽ ጠቅሰው ይሄንን ሥልጣናቸውን ወደ ራሳቸው ጠቅልለዋል፡፡ የም/ል ፕሬዝዳንቱን ሥልጣን የመጠቅለል ድርጊት በተለያየ ኹኔታ ስለተከሰተ ማስረጃ ማቅረቡ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ለዚህም ነው ዶ/ር ጄሉ ዑመር የውሳኔ ጉዳይ ሲቀርብላቸው አንገታቸውን ደፍተው ወደ ፕሬዝዳንቱ ቢሮ የሚያስተላልፉት፡፡
ጉዳያችንን ከመቋጨታችን በፊት፣ ስለ ዩኒቨርስቲ ምንነት ጥቂት ነጥቦች ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ይሄም የሚሆንበት ምክንያት፣ ዩኒቨርስቲ መሆን የሚገባውን አጠቃላይ ገጽታ በጥቂቱም ቢሆን እያቀረብን፣ በአንፃሩ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አሁን ያለበትን ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ለመቃኘት ይረዳናልና፡፡
ይሄንንም ለመተግበር በቅርቡ በፕሮፌሰር አለን ብሉም (Allan Bloom) The Closing of the American Mind በሚል ርዕስ ስለ ዩኒቨርስቲ በፃፉት ሃሳብ ላይ በመመርኮዝ ይሆናል፡፡ እንደ እርሳቸው አቀራረብ ዩኒቨርስቲ ቢያንስ- ቢያንስ የሚከተሉትን አራት ባህሪያትን ይይዛል፡፡
አንደኛ- ዩኒቨርስቲ ‹‹ከብርሃነ-ህሊና›› ጋር የተያያዘ ገጽታ አለው፡፡ ይሄም ማለት፣ ዩኒቨርስቲ ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚደረግ አዕምሯዊ ወይንም የአመለካከት ሽግግር የሚካሄድበት መድረክ ነው፡፡ ከጨለማ ወደ ብርሃን ጉዞ ማለት ደግሞ ከአስተያየት፣ ከመላምት፣ ከዘልማድ፣ ከደመነፍስ ወዘተርፈ የምንቀበላቸውን ኹነቶች በአግባቡ ፈትሸን ከአለማወቅ ወደ ማወቅ የምንሸጋገርበት ሂደት ነው፡፡ ጥንታዊ ግሪካዊያን እንደሚሉት ሽግግሩ በአጠቃላይ ከአስተያየት (Doxa) ወደ ሳይንስ (Episteme) ይሆናል ማለት ነው፡፡

ኹለተኛ- ዩኒቨርስቲ የሚል ስያሜ የተሰጠው ማንኛውም ተቋም በሙሉ፣ ሁለት ቁም ነገሮችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡ 1. ዩኒቨርስቲ ማለት የአዕምሮ ህይወት ተዘርቶ የሚኮተኮትበት መስክ ነው፡፡
2. ዩኒቨርስቲ በማያጠራጥር መልኩ ‹ምክንያታዊነትን› በበላይነት አንግቦ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው፡፡
ሦስተኛ- ዩኒቨርስቲ ከዚህ ቀደም በሰው ልጅ ታሪክ የተነሱትን ጥያቄዎች እንዳይረሱና እንደገና እንዲፈተሹ የሚያደርግ ሲሆን፣ አሁን ባለንበት ጊዜም ቢሆን አዳዲስ ጥያቄዎችን አንስቶ የሚወያዩበት እና ከግለሰብ ሆነም ከአገር አስተዳዳሪዎች የሚመጣን ሃሳብ በወል የሚመረመርበት ሥፍራ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲ በአንድ በኩል ‹‹ጥቅም አቅራቢ›› በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ችግር ፈቺ›› መሆን አለበት በሚል ፈሊጥ የተነሳበትን ዓበይት ርዕይ እና ዓላማ መሳት የለበትም፡፡

አራተኛ- ብዙ ጊዜ ሀገር የሚያስተዳድሩ ባለሥልጣናት አንድ ፖሊሲ ወይንም መመሪያ ከቀረጹ በኋላ፣ ለህዝቡ ይህ ከመሆን በቀር ‹‹ሌላ አማራጭ የለም›› በማለት ሃሳባቸውን ያለ ምንም ተገዳዳሪ ሃሳብ ለመተግበር ይፈልጋሉ፤ በአንፃሩ ዩኒቨርስቲ ይበጃል ተብሎ በብቸኝነት የቀረበን ሃሳብ አሻሽሎ ወይንም ሽሮ አሊያም በርካታ የሆኑ አማራጭ ሃሳቦችን ማቅረብ የሚችል ተቋም ነው፡፡

ስለዩኒቨርስቲ ባህሪያት ይሄንን ካልን ዘንዳ፣ ስለ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጥቂት ነገሮችን ብለን ብዬ ጽሑፌን አጠናቅቃለሁ፡፡ የዩኒቨርስቲ ልዕልና ወይም የአካዳሚክ ነፃነት፣ ከሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ጋራ በእጅጉ የተሳሰረ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሊብራል ዴሞክራሲ በሰፈነበት ቦታ የአንድ ዩኒቨርስቲ ልዕልና የተከበረ ይሆናል፡፡
ወደ እኛ ሀገር በምንመጣበት ጊዜ ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው ፓርቲ የምከተለው ሥርዓት ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ነው ብሎ ያምናል፤ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት እንደተመለከትነው ደግሞ ሥርዓቱ ለማንም ተቋም ልዕልና እና በራስ የመወሰንን መብት የማይሰጥ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ገዢው ፓርቲ አንድን ነፃ ተቋም መቆጣጠር ሲፈልግ አስቀድሞ የእርሱን ፍልስፍና እና ፈለግ የማይከተሉትን አስተዳዳሪዎች ይሽርና የራሱን ሰዎችና ካድሬዎች በቦታው ላይ ይሾማል፡፡ በቅርብ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ውስጥ የተካሄደው ይሄው ነው፡፡
ወደ ፕሮፌሰር ብሉም መጽሐፍ ልመለስና አንድ ያስደመመኝን ነገር ላቅርብ፤ በጀርመን አገር ‹‹ናሽናል ሶሻሊስት ፓርቲ›› (የሂትለር ፓርቲ) ሥልጣን ሲይዝ በአገር ውስጥ ያሉትን ዩኒቨርስቲዎች በሙሉ በቁጥጥር ሥር ያውልና የፓርቲውን ተቀዳሚ ካድሬዎች በአስተዳዳሪነት ይሾማል፡፡ ይሄንን የታዘበ አንድ የሕገ-መንግሥት ኅልዮት ባለሟል፣ ምንም እንኳን እርሱ ራሱ የፋሽስት ፓርቲ አቀንቃኝ ቢሆንም ነገሩ አንገሽግሾት ‹‹አሁን ገና ሄግል በጀርመን ሞተ›› ብሎ ትዝብቱን ተናገረ፡፡ይህንንም በዋነኛነት ያለበት ምክንያት ሄግል ለብዙ ዓመታት በዩኒቨርስቲ ውስጥ ያገለገለ ስለሆነ ነው፡፡
እኔም አሁን በከፍተኛ አመራር ላይ ያለውን የዩኒቨርስቲ የካድሬ ስብስብ በምመለከትበት ጊዜ የተሰማኝ ልክ ‹‹ሄግል አሁን ገና በጀርመን ሞተ›› እንደተባለው፣ በኢትዮጵያም እነ ታደሰ ታምራት፣ ሠርገወ ሀብለሥላሴ፣ መርዕድ ወልደ አረጋይ፣ ካሳ ወልደማርያም፣ ዮናስ አድማሱ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ደበበ ሠይፉ እና ሌሎችም በህይወት የሌሉ በዩኒቨርስቲ ያስተማሩ አሁን ገና እንደሞቱ ተሰማኝ፡፡

The post አሁን ገና ‹‹ፕሮፌሰሮቹ›› ሞቱ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>