የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የግንቦት 7 ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በከፍተኛ ህመም በመሰቃየት ላይ ሲሆኑ እስካሁን በዶክተሮች ለመጎብኘት አልቻሉም።
አያያያዛቸው የከፋ መሆኑን በማስመልከት የእንግሊዝ መንግስት አስቸኳይ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መጻፉንም ምንጮቻችን ገልጸዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ያለፉትን ተከታታይ ወራት ጸሃይ የሚባል ነገር ሳያዩ ጨለማ ቤት ተዘግቶባቸው አሳልፈዋል; ከህመማቸው ጋር በተያያዘም ምግብ መመገብ በእጅጉ ቀንሰዋል።
በከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ውስጥ የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው፣ አያያዛቸው አስከፊ እንደሆነ በቅርቡ ለጎበኙዋቸው የእንግሊዝ አምባሳደር መናገራቸውን ምንጮች ገልጸዋል። ይህንን ተከትሎም የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ጠንከር ያለ ደብዳቤ መጻፉን የአዲስ አበባ ምንጮች ገልጸዋል። የአቶ አንዳርጋቸው አያያዝ በአፋጣኝ የማይለወጥ ከሆነ፣ በህይወታቸው ላይ ያልተጠበቀ አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል ያስጠነቀቁት የእንግሊዝ ባለስልጣናት፣ አቶ አንዳርጋቸው የኮንሱላር ድጋፍ እንዲያገኙ፣
በመደበኛ እስር ቤት ውስጥ እንዲታሰሩና በጠያቂዎች እንዲጎበኙ ፣ ሃኪሞች እንዲያዩዋቸውና ሰብአዊ መብታቸው እንዲከበር ደብዳቤ መጻፋቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ገዢው ፓርቲ ከአቶ አንዳርጋቸው የረባ መረጃ ለማግኘት ባለመቻሉ_የስነ ልቦና ጫና በማሳረፍና ህክምና በመከልከል ለመጉዳት ማሳቡን ምንጮች ገልጸዋል።
የእንግሊዝ ባለስልጣናት በሂደት ስለሚወስዱት እርምጃ ግልጽ ባያደርጉም፣ ጉዳዩን በቀላሉ እንደማያዩት ለኢህአዴግ ሹሞች እንደገለጹላቸው ታውቋል።
አቶ አንዳርጋቸው በየመን የጸጥታ ሃይሎች ተይዘው ለኢህአዴግ የጸጥታ ሃይሎች ተላልፈው ከተሰጡ በሁዋላ፣ ገዢው ፓርቲ ሁለት ጊዜ በቴሌቪዥን አቅርቧቸዋል። ተቆራርጦ የተላለፈውን ቪዲዮ ተከትሎ ገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ትችት ሲቀርብብት ቆይቷል።
ኢህአዴግ አቶ አንዳርጋቸውን ህዝብ ሊጎበኛቸው በሚችል እስር ቤት አለማሰሩና ሰብአዊ መብታቸውን ሁሉ መግፈፉ የገዢውን ፓርቲ የፍርሃትና የበቀል ደረጃ፣ እንዲሁም ራሱ ላወጣው ህግ እንኳን የማይገዛ መሆኑን የሚያሳይ ነው ተብሏል።
The post አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የተያዙበት ሁኔታ ለህይወታቸው አስጊ ነው ተባለ appeared first on Zehabesha Amharic.