(በአዲስ አበባ የሚታተመው ወርልድ ስፖርት ጋዜጣ እንደጻፈው)
ባለፉት 25 እና 26 አመታት በአለም የአትሌቲክ መድረክ ታላላቅ ውጤቶችን በማስመዝገብ አለምን ያስደመመውና ለወጣት አትሌቶች ተምሳሌት መሆን የቻለው ኃይሌ ገ/ስላሴ ፊቱን ወደ ፖለቲካው አለም ሊያዞር ነው፡፡ ኢትዮጵያን በፕሬዝዳንትነት መምራት እንደሚፈልግና የፓርላማ አባል ለመሆን እቅድ እንዳለው ዘ ኦብዘርቨር ከተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ሰፊ ቃለ ምልልስ ገለፀ፡፡ የ40 አመቱ ጐልማሣ ኃይሌ ገ/ስላሴ በስፖርቱና በቢዝነሱ ተሣክቶለታል በቅርቡም ከፍተኛ የቡና እርሻ ጀምሯል፡፡ ከሁለቱ አመት በኋላ ደግሞ ፊቱን ወደ ፖለቲካው አለም በማዞር በ2007ቱ ሀገራዊ ምርጫ የግል ተወዳዳሪ ሆኖ እንደሚቀርብ ከጋዜጣው ጋር ባደረገው የስልክ ቃለ ምልልስ ጠቁሟል፡፡ ፕሬዝዳንት ለመሆን ትፈልጋለህ ወይ ተብሎ ጥያቄ የቀረበለት ኃይሌ ገ/ስላሴ ያንን ማን የማይፈልግ አለ ሲል ሀገሩን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ተናግሯል፡፡ 547 መቀመጫ ያለውን የኢትዮጵያ ፓርላማ ለመቀላቀል በግሉ የሚወዳደረው ኃይሌ ገ/ስላሴ እድሉን ሊያገኝ እንደሚችልም ተንታኞች ከወዲሁ ይጠቁማሉ፡፡ በአሁን ወቅት በፓርላማው አንድ ግለሰብ በግል አባል ለመሆን መቻላቸው አይዘነጋም፡፡ እኚህ ግለሰብ የቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕ/ት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ኃይሌ በ2007ቱ ምርጫ ፓርላማ የሚገባ ከሆነ ሁለተኛው የስፖርት ሰው ይሆናል ማለት ነው፡፡