Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Art: ሁለገቧ አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤል

$
0
0

በማስረሻ መሀመድ

አርቲስት አዳነች ከአባቷ ወ/ገብርኤል ገብረ ማርያም እና ከእናቷ ፋና አምባው በ1952 ዓ.ም ይህችን አለም ‹‹ሀ›› በማለት ይፋትና ጠሞ በሚባል አውራጃ ካራቆሬ በተባለ ትንሽ ከተማ ውስጥ ተወለደች፡፡ እንደማንኛውም ልጅ እናትና አባቷን በቤት ውስጥ በማገልገል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በዚችው ካራቆሬ በተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ ተከታተለች፡፡ ከዛም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደብረሲና ከተማ ውስጥ ከተከታተለች በኋላ 9ኛ ክፍል ሠንዳፋ ጅማ ሰንበቴ ትምህርት ቤት ከታላቅ እህቷ ኮማንደር ብርቄ ወ/ገብርኤል ጋር በመሆን እዛው ትምህርቷን እንድትከታተል ሆነ፡፡ ይሁንና የነበሩበት ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች ስላልተስማማቸው አዳነችና እህቷ ብርቄ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ተገደዱ፡፡
Adanech
አዲስ አበባም አጎቷ ሻንበል ባሻ ተረፈ አንባ ጋር በመሆን ያቋረጠችውን ትምህርቷን ማለትም ከ9ኛ ክፍል በግዜው የፈጥኖ ደራሽ ካንፕ (ሙዚቃ ክፍል) አጠገብ ከነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መማር ቀጠለች፡፡ ‹‹እንዴት ነበር ለትምህርት የነበረሽ ፍላጎት››? የሚል ጥያቄ አቀረብኩላት ‹‹ኦ ይሄ ነው ልልሽ አልችልም ብቻ ተመጣጣኝ ነው ማለቱ ይቀለኛል፡፡ እኔ በተለይ በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ቤት ስማር በግዜው በጣም ወጣት ነኝ ፍላጎቴ በሙሉ የነበረው ስፖርት ላይ ነው፡፡ እንዲሁም
ከዚሁ ትምህርት ቤት በፊት በተማርኩባቸው ት/ቤቶች በጠቅላላ ስፖርት ከመስራቴ ባሻገር ውድድር ውስጥ ሁሉ እገባ ነበር፡፡ እንደውም ጅማ ሰንበቴ ትምህርት ቤት ስማር ለስፖርት ተመርጬ ለውድድር ወደ አዲስ አበባ ስቴድየም የመጣሁበት ግዜ ሁሉ አለ፡፡ የምድር ዝላይ፣ ሪሌይ፣ 100 ሜትር ሩጫ እና ሌሎችንም ተወዳድሬ ወደ አራት ሜዳሊያዎችን ለትምህርት ቤቴ ያስገኘሁበትን ግዜ አልረሣም›› የሚል መልሷን ሠጠችኝ፡፡
ከዚህ በኋላ አዳነች በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርቷን እየተከታተለች ቢሆንም ከፈጥኖ ደራሽ ካንፕ ሙዚቃ ክፍል የሚንቆረቆረው የባንድ ዜማ እና ከፍተኛ ድምቀት የነበረው የማርሽ ቡድኑ ጣዕመ ዜማ ከግዜ ወደ ግዜ ቀልቧን እየገዛ መጣ፡፡ ታዲያ በዚህ መሀል ፈጥኖ ደራሽ የሥራ ማስታወቂያ ለጠፈ፡፡
ይህን በመከተል ታዲያ 1968 ዓ.ም አዳነች በ16 አመቷ ትምህርቷን በማቋረጥ ፈጥኖ ደራሽ ያወጣውን መስፈርት በብቁነት በማለፍ ወደ ውትድርናው አለም ‹‹በእድሜ ትንሽ ብትሆንም እዚሁ ታድጋለች›› በማለት የሙዚቃ ክፍሉ ሀላፊ ኮረኔል አያሌው አበበ፣ ተስፋዬ አበበ እና ኮረኔል ግርማ በተወዛወዥነት እንድትቀላቀል አደረጓት፡፡ በዚህም ግዜ ፒያኖ፣ የማርሽ ሙዚቃና የተለያዩ በካንፑ ይሰጡ የነበሩ ትምህርቶችን በፖሊስነት ተምራና ሠልጥና ብቁ ሆና ተመረቀች፡፡ የፖሊስ ተወዛዋዥ ሆና ለስድስት ወር ሠልጥና ከተመረቀች በኋላ በህጉ መሠረት በግዜው የሚሞላ ቃል የመግቢያ ፎርም ነበረና በፎርሙ መሠረት ለሠባት አመት ላታገባ፣ ላትወልድና፣ የሰውነት አቋሟ ላይለወጥ ቃል ገባች፡፡ በህይወት ላይ መቼም አንዳች አይጠፋምና አዳነች ስራዋን ለተወሠኑ ግዜያት ከሠራች በኋላ በውዝዋዜው በግዜው ያሠለጥናት የነበረው ሻንበል ባሻ ጌታቸው አንዳርጌ በፍቅሯ በመውደቁ ጠልፏት እቤቱ ይዟት ገባ፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ በካንፕም በመሠማቱ ከፍተኛ ቁጣን አስነሣ፡፡ ይህን ተከትሎም የህግ ጥሠት ተካሄዷል ተብሎ አዳነችና ጌታቸው ቻርጅ እንዲሞሉ ተደረገ፡፡ ቅጣትም ተላለፈባቸው፡፡ ቅጣቱ በግዜው ጦርነት ወደነበረበት አስመራ ክፍለ ሀገር ጌታቸው ባሰልጣኝነት አዳነች ደግሞ በረዳት አሠልጣኝ ሆነው ወደ አስመራ ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል እንዲዘዋወሩ ተደረገ፡፡
‹‹ለግዜው ቅጣቱ ሲወሰንብሽ ምን አይነት ስሜት ተሠማሽ›› የሚል ጥያቄ አነሣሁላት ‹‹እንደማንኛው ሰራዊት ህጉን በመጣሴ ቅጣት ተላልፎብኛል፡፡ ለምን ቅጣቱ ተላለፈብኝ ብዬ አላዛንኩም፣ ቅሬታም አላሠማሁም፣ ጥፋቴንም አምኛለሁ፣ ለመቀጣትም ዝግጁ ነበርኩ›› በማለት በራስ የመተማመን ስሜቷ ፊቷ ላይ በግልፅ እያሣየችኝ ለጠየኳት ጥያቄ መልሷን ለገሠችኝ፡፡
አዳነች በአዲስ አበባ ፈጥኖ ደራሽ ሙዚቃ ክፍል የተወሠኑ ጊዜያት ብቻ የቆየች ቢሆንም ኤርትራ ክፍለ ሀገር አስመራ ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ግን ብዙ ግዜያትን አሣልፋለች፡፡ ከዛም አልፎ ከሌሎች ለየት ባለ ብዙና አጥጋቢ እንቅስቃሴዎችን ታደርግ ነበር፡፡ ይህን የምታደርገው ታዲያ አንደኛ በፖሊስነት ሌላም ደግሞ በሲቪልነት ነበር፡ ፡ ታዲያ ከምታደርገው ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ የተነሣ የአራት ሲኒማ ቤቶች ማለትም ሲኒማ ካፒቶል፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሲኒማ ሮማ እና ሲኒማ አባ አሉላ አባ ነጋ አዳራሽ የተባሉ ሲኒማ ቤቶችን አስተዳድራለች፡፡
በዚህ ግዜ ታዋቂ አርቲስቶች የተባሉ አርቲስት አማኒ ኢብራሂም፣ ይገዙ ደስታ እና ሌሎች ሌሎችም ከአዲስ አበባ ራስ ቲያትር እየመጡ እሷ የምታስተዳድራቸው ሲኒማ ቤቶች ዝግጅታቸውን በሚያቀርቡ ሠዓት የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች የምታቀርብላቸው እሷ ስለነበረች ከነሱ ጋር የመተዋወቅ እድሉ ተከፍቶላታል፡፡
አዳነች ከ1969 እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ በኤርትራ ከላይ የጠቀስኳቸው ሲኒማ ቤቶችን ስታስተዳድር አያሌ የሚባሉ አስደማሚ ግዚያቶችን ማሳለፏን ትናገራለች፡፡
አዳነች ሲኒማ ካፒቶል እያለች ‹‹ጭቁኗ ሴት ተነሽ›› የሚል ድርሠት በመፃፍ ለእይታ አብቅታለች፡፡ በሠዐቱ አስመራ ውስጥ 107 ቀበሌዎች የነበሩ ሲሆን በነበራት ጠንከር ያለ እንቅስቃሴዎች ከሚሊተሪ ውጪ የሴቶች ሊቀመንበር በመሆን አገልግላለች፡፡ ታዲያ በወቅቱ ስለነበረው የሻዕብያ ጦርነት ቤት ለቤት በመዞር ሴቶችን በማነሣሣትና የተለያዩ ኪነ ጥበብ ነክ ስራዎች በመስራት የማነቃቃት ስራዎችን ሠርታለች፡፡ ይህ ታዲያ ታይቶ ከተራ ወታደርነት የ50 አለቃ ማዕረግን ለማግኘት በቅታለች፡፡ በግዜው ጀነራል ግርማ አየለ የማዕረግ ሽልማቱን (አበርክተውለታል፡፡)
ከዚህ በኋላ አዳነች አስመራ የነበራትን እንቅስቃሴ ወደአዲስ አበባ ለመቀየር በማሰብ ለአራቱም ሲኒማ ቤቶች ባለቤት አቶ ሀይሉ የስራ መልቀቂያ በማስገባት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሲኒማ ራስ ተቀጥራ ማገልገል ጀመረች፡፡ ከ1974 በኋላ ወሩን በትክክል ባታስታውሰውም ከላይ እንደጠቀስነው በአሁኑ ራስ ቲያትር ቤት በቀድሞው ስሙ ራስ ሲኒማ ማገልገል ጀመረች፡፡ ወደዚህ የመጣችበትን ዋና ምክንያት ብላ እንደገለፀችው አዲስ አበባ ያለው ሲኒማ ኢትዮጵያና ራስ ቲያትር ከተስፋዬ አበበ ጋር ግንኙነት ስለነበራቸውና ደሞዟም ሞዴል እየተባለ ከአስመራ እየተላከ ይከፈላት ስለነበር ነው፡፡
‹‹በዚያን ግዜ ደሞዝ ስንት ይከፈልሽ ነበር?›› የሚል ጥያቄ አነሣሁላት እሷም እየሳቀችና የአግራሞት ስሜትን እያንፀባረቀች ‹‹የያኔ ብር እንዳሁን ግዜ አልነበረም፤ እኔ እንዳውም ትልቅ ደሞዝ ይከፈላቸው ከነበሩት ውስጥ አንዷ ነበርኩኝ፤ 375 ብር ይከፍሉኝ ነበር›› የሚል መልስ ሠጠችኝ፡፡
ከዚህ በኋላ አስቴርዬ ክለብ ማገልገል ጀመረች፡፡ ክለቡ በሲሊንደር ፍንዳታ ምክንያት በመቃጠሉ በራስ ቲያትር የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ በመሆን ተቀጥራ በዚሁ ቦታ ላይ ለ15 ዓመታት ያህል አገለገለች፡፡ ከዚያም ወደ ሀገር ፍቅር ቲያትር በመዘዋወር ከ1994 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ በዚሁ ሞያዋ አገለገለች፡፡
ከ1996 ዓ.ም በኋላ በኢትዮጵያ መገናኛ ኤጀንሲ ውስጥ ተቀጥራ የፕሮሞሽን ስራዎችን ፣ መፅሔቶችንና የተለያዩ ኪነ ጥበብ ነክ ስራዎችን በመስራት ለተወሰኑ አመታት ካገለገለች በኋላ ከመስሪያቤቱ በግሏ ስራ የመልቀቅ ፍላጎቷን በመግለፅ ከስራዋ ለቀቀች፡፡
ከዚህ በኋላ እንግዲህ አዳነች ስራዎቿን ሁሉ ከተቀጣሪነት ይልቅ በግሏ ለመስራት በመወሠን ‹‹ጀአዲ አርት ፕሮሞሽን›› የሚል ድርጅት መሠረተች፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ ታዋቂ የነበረውንና የመዝናኛና የኪነጥበብ ስራዎች ይቀርብት የነበረውን ‹‹ጠብታ›› የተሠኘውን መፅሔት በ2000 ዓ.ም መሠረተች፡፡ ይህ መፅሔት በአዲስ አበባ ውስጥ ጎልተው ከወጡ መፅሔቶች ውስጥ አንዱ የነበረ ሲሆን በውስጡም እነ ፕሮፌሠር አብይ ፎርድር ፣ሀይሌ ገሪማ፣ የሼክ አላሙዲን ባዬግራፊና ሌሎች ታዋቂ ሠዎችን
ይዞ የሚወጣ መፅሔት ነበር፡፡ መፅሔቱን አዳነች ለሁለት አመታት አሣትማ ለህዝብ ያቀረበች ቢሆንም በወቅቱ የነበረውን የህትመት ዋጋ መቋቋም ባለመቻሏ በ2002 ዓ.ም መፅሔቷን ከመታተም እንዲቆም አደረገች፡፡ ከ2002 ዓ.ም ላይም ‹‹ሳሎን ኢትዮጵያ›› የተባለ ጋዜጣ በበአሜሪካ ሲያትል ከተማ ውስጥ በየ15 ቀኑ አሳትማ ለኢትዮጵያውያን ታቀርብ የነበረ ቢሆንም ከአሳታሚዎች ጋር በነበራት አለመስማማት ጋዜጣዋን ልታቆም ችላለች፡፡
‹‹በነገራችን ላይ እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ፣ መሠረት እንድጥልና በራሴ እንድተማመን ያደረገኝ የፖሊስ ሠራዊት ቤት ነው፡፡ ትልቁን በስነ ምግባር እንድታነፅና ህይወቴን እንድመራ ያደረገኝ ይሄው የፖሊስ ቤት ስርዓት ነው፡፡›› የምትለው አዳነች እሷ የነበረችበት ግዜ የነበረው የፖሊስ ሥነ ስርዓት እንዲህ በቃላት ልትገልፀው እንደማትችል ታስረዳለች፡፡ በሚሊተሪ ውስጥ የማትረሣው ነገር አዳነች ሙዚቃ ክፍል እያለች የነበረው መተሣሠብ፣ መፈቃቀርን፣ መከባበሩንና ሰርዓቱን ነው፡፡ ‹‹እስከ ዛሬም ድረስ በፈጥኖ ደራሽ ነባር የነበሩትን መኮንን መርሻን፣ እና ዳንኤልን ሣይ እንባዬ ይመጣል›› ትላለች፡፡
አዳነች በአሁኑ ሠዓት በራሷ ድርጅት ‹‹ጀአዲ አርት ፕሮሞሽን›› ላይ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ በቅርቡም የልጇ ባለቤት የሆነው አርቲስት አለማየሁ ታደሠ የደረሠው ድርሰት ላይ አብራ ለመስራት እንቅስቃሴ እያደረገችም ትገኛለች፡፡ ‹‹በቅርቡ የሠው ለሠው ድራማ ላይ እየተወንሽ ትገኛለሽ እንዴት ነው እንቅስቃሴው?›› አልኳት ‹‹ኦው! የሰው ለሰው ቤተሠቦች እጅግ ጎበዝና የቀልጣፋ ተዋናዬች ስብጥር ሲሆን አንጋፋና ወጣት ተዋንያን የተሣተፉበትም ጭምር ነው፡፡ እንዳውም ‹የአስናቀ ሚስት› እያሉ መንገድ ላይ ስሜን ቀይረውት ይጠሩኛል፡፡
በይበልጥ በድራማው ታዋቂነትን አትርፌያለው ብዬ አስባለሁ›› የሚል መልስ ሰጠችኝ፡፡ አዳነች ከባለቤቷ ጋር የነበራት ኑሮ እጅግ መራራ እንደነበረ ትገልፃለች፡፡ እሷ ወጣት በመሆኗና ባለቤቷ ሻንበል ባሻ ጌታቸው በእድሜ ስለሚበልጣት እንደ ልጅ በየግዜው ይደበድባት እንደነበር ትገልፃለች ይህ ያማረራት አዳነች፤ ቢኒያም ጌታቸው እና ማርታ ጌታቸው የተሠኙ ልጆቿን ከወለደች ከተወሰኑ አመታት በኋላ ከባለቤቷ ጋር ልትለያይ ችላለች፡፡ ባለቤቷም ሌላ ቤተሰቦችን መስርቶ ልጆችን ያፈራ ቢሆንም ከዚህ አለም በሞት የተለየ መሆኑና ልጆቹንም እንደ ልጆቿ እያየች እንዳሳደገች ታስረዳለች፡፡ ሻይና ዳቦ ከማንኛውም የምግብ አይነቶች የምታስበልጥ ሲሆን እስፓርታዊ እንቅስቃሴንም አሁንም ድረስ አላቋረጠችም፡፡
አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤል በቲቪ ድራማዎች ላይ ያልተሄደበት መንገድ፣ ቅብብል እንዲሁም አሁን በሚታየው የሠው ለሰው ድራማ ላይ የተሣተፈች ሲሆን የራሷ ድርሰት በሆነው የሳት ዕራት፣ ክብረነክ፣ ኮሞሮስ፣ አልደወለም፣ አልነግራትም እንዲሁም ፊደል አዳኝ የተሠኙ ፊልሞችን ሠርታለች፡፡ አማጭ፣ ዲያስፖራ፣ ሩብ ጉዳይ እንዲሁም የብዕር ስም የተባሉ ቲያትሮች ላይም ተውናለች፡፡ ከዚህ በተረፈ የሸዋንዳኝ ሀይሉን፣ የሄኖክ አበበን፣ የሄሎ አፍሪካ ጄሪን፣ የነዋይ ደበበን (አሜን)፣ የፀሐዬ ዩሀንስን (ሳቂልኝ) አልበሞችን ፕሮሞት ያደረገች ሲሆን የቴዲ አፍሮን እና የሸዋንዳኝን፣ ኮፒ ራይት ማህበር ያዘጋጀውን፣ የከተሞች ቀን የተከበረበትን፣ ስፖርት ለሠላም የተሠኙ ኮንሰርቶችን ፕሮሞት አድርጋለች፡፡ ቻቺ ታደሰ እንዲሁም የሌሎች ታዋቂ አርቲስቶች ፕሮሞተር በመሆን ሠርታለች፡፡ ‹‹ሥራዬን መቼም አላቆምም ወደፊትም ለህዝብ የማቀርበው ሥራዎች አሉኝ›› በማለት የወደፊት ዕቅዷን ነግራኛለች፡፡ እነሆ አዳነች 53ኛ ዓመት ዕድሜዋን በደመቀ ሁኔታ አክብራለች፡፡ በእርግጥም የብዙ ሙያዎች ባለቤት መሆኗን አስመስክራለች፡፡
ቸር እንሠብት፡፡S


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>