Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

‹‹ጋዜጠኞች ከእስር ቤት እንደወጡ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጥላ ስር ሲሰባሰቡ መመልከት ያሳዝናል›› ዳዊት ከበደ [ጋዜጠኛ]

$
0
0

“ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?” በተሰኘውና በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ታትሞ በገበያ ላይ በዋለው መፅሀፍ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ የሰጠው ቃለ – ምልልስ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ይህቺን ምድር መስከረም 1 ቀን 1972 ዓ.ም. በአድዋ ከተማ የተቀላቀለው ዳዊት ከበደ፣ ከምርጫ 97 ጋር በተፈጠረ ቀውስ በዋና አዘጋጅነት ይሠራበት በነበረው ሀዳር ጋዜጣ ላይ ‹‹አመፅ በማነሳሳት እና ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ ሙከራ በማድረግ›› ተከሰው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለ21 ወራት ከታሰሩ ጋዜጠኞች አንዱ ነው፡፡ በየካቲት 2000 ዓ.ም. ሰፊ ተነባቢነት የነበራትን አውራምባ ታይምስ ጋዜጣን መሥርቶ ለሦስት ዓመት ከዘጠኝ ወር ሲሠራ የሲ.ፒ.ጄ. የ2010 የፕሬስ ነፃነት አሸናፊ ነበር፡፡ ‹‹ይቅርታዬ ተነስቶ ድጋሚ እንደምታሰር ከፍትሕ ሚኒስትር ታማኝ ምንጮች መረጃ ደረሰኝ›› በማለት ኅዳር 7/2004 ዓ.ም. የስደትን መንገድ ተቀላቀለ፤ ወደ አሜሪካም በመኮብለል በጋዜጣዋ ስም ድረ-ገፅ ከፍቶ (awrambatimes.com) በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ኤልያስ ገብሩ የዳያስፖራ ጋዜጠኝነት እና ፖለቲካን መሠረት ያደረጉ ጥያቄዎች አቅርቦለት ከዳያስፖራ ፖለቲካ በተቃርኖ መቆሙን የሚያሳይ ምላሽ በጽሑፍ ሰጥቶታል፡፡ ዘ-ሐበሻም እንደወረደ ቃለምልልሱን አቅርባዋለች
dawit kebede
ከአገር ከመሰደድህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በፕሬስ ጋዜጠኝነት ስትሠራ ነበር። አሁን ደግሞ በድረ-ገጽ አዘጋጅነት እየሠራህ ነው። በሁለቱ መሀከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
ልዩነቱ ግልጽ ነው። የጋዜጣ ሥራ በሣምንት አንድ ጊዜ ለሚወጣ የኅትመት ውጤት በመሆኑ ሣምንት ሙሉ መዘጋጀትን ይጠይቃል። በሣምንት ውስጥ ብዙ ነገር ይፈጠራል። እነዚያ ክስተቶች ጠቅለል ብለው እና ዳብረው ለአንባቢያን ይቀርባሉ። ወደ ድረ-ገጽ ስትመጣ ግን ክስተቶችን ሣምንት ሙሉ የምትጠብቅበት ሁኔታ አይፈጠርም። ማንኛውንም ክስተት [ክስተቱ በትክክል መፈጸሙን ለማረጋገጥ ጊዜ ካልፈጀብህ በስተቀር] ወዲያውኑ በደቂቃዎች ውስጥ አንባቢ ጋር ማድረስ ትችላለህ። ልዩነቱ በፍጥነት አንባቢ ጋር መድረሱ ብቻ ሳይሆን የድረ ገጽ ጋዜጠኝነት ከኅትመት ይልቅ ብዙ ቦታ የመዳረስ ዕድሉም ሰፊ ስለሆነ ነው። ለምሳሌ፣ የአውራምባ ታይምስ ድረ-ገጽ ዕለታዊ ጎብኚ፣ ጋዜጣው በአገር ቤት ሲታተም ከነበረው ሣምንታዊ የአንባቢ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር፣ የድረ-ገጽ አንባቢው ብልጫ እንዳለው ጥያቄ የለውም። በእርካታ ደረጃ ግን የሚገናኝ አይደለም። የድረ-ገጽ አንባቢ አርቲፊሺያል የሚባል ዓይነት ነው። ጠላትህም ወዳጅህም ሊሆን ይችላል። አገር ቤት ያለው የጋዜጣ አንባቢ ግን አንደኛ፣ መረጃህን የሚገዛው ገንዘቡን አውጥቶ ነው። ሁለተኛ፣ ‹‹ጋዜጣህን የምገዛው ገንዘቤን አውጥቼ ነው?›› ብሎ እጅ ጥምዘዛ ውስጥ አይገባም። ልዩነቱ ድረ-ገጽ የሚቀርበው በሰለጠነ አገራት ውስጥ ለሚገኝ ያልሰለጠነ ሀበሻ ሲሆን፣ ጋዜጣው ደግሞ ባልበለጸገች አገር ለሚገኝ የሰለጠነ ማኅበረሰብ መሆኑ ነው።
ማንኛውም ዜና የመዘገብ ሥራ አቋራጭ መንገድ ባይኖረው ይመረጣል። ብዙ ጊዜ የተወሰደባቸው እና ከባድ ጥረት የተደረገባቸው ዘገባዎች ምንጊዜም ትልቅ ፋይዳ እና ጠቀሜታ አላቸው። ከዚህ አኳያ የአገር ውስጡን እና ከአገር ውጪ ያሉትን የጋዜጣ እና የድረ-ገጽ ሥራዎች [ያንተን ጭምር] እንዴት ትገልጻቸዋለህ? አንባቢን የሚመጥን ሥራ እየተሠራባቸው ነው?
ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነህ ከስደት ጋር እየታገልክ የምትሠራው ሥራ ሁሌም ሁለተኛ ደረጃ (Secondary) የምትሰጠው ስለሆነ እና ‹‹የበሰለ ሥራ ነው›› ብለህ በኩራት የምትናገረው አይደለም። ዞሮ ዞሮ አገር ቤት ያላችሁም እዚህም ያለን ሰዎች የምንሠራው ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነህ እና ከኢትዮጵያ ርቀህ እኩል ልትሠራ አትችልም። ስለ ሌሎች ድረ- ገጾች መናገር አልፈልግም። ‹‹ስለ አውራምባ ታይምስ ንገረኝ?›› ካልከኝ ግን ጋዜጣው የ20 ሰው ልፋት እና ድካም ውጤት ነበር። ድረ-ገጹን የማዘጋጀት ኃላፊነት ግን ያለው በአንድ ሰው ትከሻ ላይ ነው። ዋሺንግተን ዲ.ሲ. እያለሁ ሪፖርተር፣ ቪዲዮ ቀራጭ፣ ቃለ-ምልልስ አድራጊ፣ ዜና ጸሐፊ፣ ዲዛይነር፣ ፎቶግራፈር እኔ ብቻ የሆንኩበትን አጋጣሚ አልረሳውም። በዚህ ሁኔታ የበሰለ ሥራ ሊሠራ አይችልም። ያ ማለት ግን ድካም እና ልፋት የለም ማለት አይደለም። አብዛኛው ልፋት በአንድ ሰው ትከሻ ላይ ነው።
ድረ-ገጽን በአንድ ሰው ብቻ የምትሠራው ለምንድን ነው? ይኼ የአንባቢን ብዝሐ ሐሳብ የማግኘት ዕድሉን አይገድብም? የጋዜጣ እና የመጽሔት ገቢ በሽያጭ እና በማስታወቂያ እንደሆነ ይታወቃል። ከድረ-ገጽ የምታገኘው ገቢ ምንድን ነው? [ከቻልክ የሌሎቹን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ድረ-ገጾች ገቢ ምን እንደሆነ ብትነግርኝ መልካም ነው።]
በአንድ ሰው ይሠራል ሲባል በአንድ ሰው ትከሻ ላይ እየወደቀ ያለው የማዘጋጀቱ (የሥራው) ኃላፊነት ነው እንጂ የድረ ገጹ ይዘት የአንድ ሰው አቋም አይደለም። ለምሳሌ አገር ቤት እያለን እኔ ኖርኩ አልኖርኩ ጋዜጣው ይሠራ ነበር። በ2010 አሜሪካን አገር ለሽልማት መጥቼ ሁለት ወር ገደማ ስቆይ ጋዜጣው ቀኑን እና ይዘቱን ጠብቆ ይወጣ ነበር። ያ የሆነበት ምክንያት ዘጋቢ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አዘጋጆችም ስለነበሩት ነው። ድረ-ገጹ ግን ዘጋቢ ካልሆነ እኔን ተክቶ የሚሠራ አዘጋጅ የለውም። አገር ቤት እያለሁ የነበረኝ በቡድን ሥራ የማመን ጥብቅ አቋም አሁንም አልተለወጠም። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን በውጪ አገር አዘጋጆችን ልቅጠር ብትል የማይሆን ነገር ነው። በአገር ቤትም አዘጋጅ ልቅጠር ብትል ይህ አዘጋጅ እንዴት አድርጎ ነው የተዘጋን ዌብሳይት ከፍቶና የምስጢር ቁጥር አስገብቶ የአዘጋጅነት ሚናውን ሊወጣ የሚችለው? ነገሩ መታየት ያለበት ከነዚህ መሰናክሎች አንጻር ነው። ድረ-ገጹ በአገር ቤት እንደ መዘጋቱ እንኳን አዘጋጅ ይቅርና በሪፖርተርነት እንኳን ሰዎችን ለማሠራት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ፖለቲካውን ጠንቅቀህ ታውቀዋለህ። ፍርሃቱ ደግሞ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። እነ ውብሸትን ያየ በዚህ ቢደነግጥ አይገርምም። እኔም ደግሞ ለማንም መታሰር ምክንያት መሆን አልፈልግም። እንደዚያም ሆኖ ያንን ስጋት ተቋቁመው እየዘገቡ ያሉ የአገር ቤት ዘጋቢዎቼን ሳላመሰግን አላልፍም።
የድረ-ገጾችን ገቢ በተመለከተ ሙሉ ለሙሉ ማወቅ ባይቻልም በአብዛኛው ግን ድረ-ገጾቹ የሚደግፏቸው የፖለቲካ ድርጅቶች በሚያዘጋጇቸው የገቢ ማሰባሰቢያ ምሽቶች የሚገኝ ገቢ ነው። እዚህ ዋሽንግተን በሚገኝ አንድ የኢትዮጵያ ጎረቤት ኤምባሲም የሚደገፉ እንዳሉ አውቃለሁ። ከጠቀስኩት ኤምባሲ ድጋፍ የሚያገኙት ድረ-ገጾች ታዲያ ከዚያች አገር ጋር በቅርብ የሚሠራ እና ስሙን መጥቀስ የማልፈልገውን የፖለቲካ ድርጅት በግልጽ መደገፍ አለባቸው። ኢትዮጵያ እያለሁ የ‹‹እከሌ ተላላኪዎች›› እየተባለ በቴሌቭዥን ሲለፈፍ እውነት አይመስለኝም ነበር። ኢቴቪ አብዛኛውን ጊዜ ውሸት ስለሚያወራ በእነዚያ ውሸቶች መሀከል ጥቂት እውነት ይወራል ብለህ አትጠብቅም። አሜሪካ በመጣሁ በሣምንቴ ከአንድ የፖለቲካ ተንታኝ ጋር ስናወራ የተጠቀሰው ኤምባሲ እንዴት ድረ-ገጾችን እንደሚረዳ በቁጭት ሲያጫውተኝ በጣም ነበር የተገረምኩት። በኋላ እኔም ዌብሳይት ስጀምር ተመሳሳይ የ‹‹እንደግፍህ›› ጥያቄ በሰዎች አማካኝነት ሲቀርብልኝ በጣም አዘንኩ። ‹‹ለሻዕቢያ ድጋፍ እጄን ከምዘረጋ ልማታዊ ዘገባዎችን ብቻ እያቀረብኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ሳይነካኝ አልኖርም ነበር እንዴ?›› የሚል ምላሽ ሰጠሁ። አጋጣሚው ግን በዳያስፖራ ያለው የተቃውሞ ፖለቲካ በማን እየተጠለፈ እንደሆነ ለመረዳት አስችሎኛል። ለማንኛውም አውራምባ ታይምስ ድረ-ገጽ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር የድጋፍ ውል የለውም። በርካታ ትራፊክ (ጎብኚ) ካላቸው ዌብሳይቶች አንዱ እንደመሆኑ ከጉግል መጠነኝ ገቢ ያገኛል። በተጨማሪ ደግሞ ለፕሬስ ነጻነት መከበር ድጋፍ የሚያደርጉ (ምንም ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳ የሌላቸው) ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም አልፎ አልፎ ይደግፉኛል። ከእነዚህ የምናገኘው ድጋፍ ድረ-ገጹን ለማንቀሳቀስ የምናወጣውን ወጪ ይደጉምልናል።
በስደት ላይ የምትገኙ ጋዜጠኞች ‹‹የስም እንጂ የተግባር ጋዜጠኞች›› ናችሁ ማለት ይቻላል?
አሁንም ደግሜ ልንገርህና ስለ ሌሎች የድረ-ገጽ አዘጋጆች አቋም መናገር አልፈልግም። እኔ ግን ነኝ ማለት እችላለሁ።
በአገር ውስጥ አብዛኞቹ የኅትመት ሚዲያ ተቋማዊ መሠረት እንዳይኖራቸው ምን ያገዳቸው ይመስልሃል? በምሳሌነት የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ መቀጠል አለመቀጠል በአንተ መኖር እና አለመኖር ተወስኖ ነበር። ‹‹የጋዜጣ ባለቤቶችስ የሚዲያ ተቋም መገንባት ይሻሉን?›› የሚል ጥያቄም ይነሳል።
ይህ እኮ የመንግሥት እንጂ የአሳታሚ ግለሰቦች ችግር አይደለም። የአውራምባ ታይምስ አሳታሚ በሆነው ብሉ ኧርዝ ኃላ.የተ.የግል ማኅበር ውስጥ እኔ የነበረኝ ድርሻ 90 ከመቶ ነበር። በዚያ ላይ ሥራ አስኪያጁም እኔ ነበርኩ። ስለዚህ እኔ ከአገር ስወጣ ድርጅቱ ተቋማዊ መሠረት ይዞ እንዲቀጥል እኔ መስጠት የምችለው ውክልና ብቻ ነው። ተቋም እንዲመሠረት በኛ በኩል የፈለገውን ያህል ሕልምና ፍላጎት ቢኖር፤ በኢትዮጵያ መንግሥት ባህሪ እና በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ሊሆን የሚችል አይደለም። እንኳን አውራምባ ታይምስ የሚለውን ስም በውክልና ይዛችሁ ልትቀጥሉ ቀርቶ፤ የአውራምባ ታይምስ ባልደረቦች ስለነበራችሁ ብቻ አዲስ ጋዜጣ ለማውጣት ፍቃድ ተከልክላችሁ የለም እንዴ?
ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት ሲዘጉ እና አሳታሚዎች ወይም ጋዜጠኞች ከአገር ሲሰደዱ የአንድ ሰሞን ርዕስ ይሆንና ዝምታ ይውጠዋል። የዝምታው አንድምታ ምን ይመስልሀል?
የዝምታው አንድምታ፣ ያው ፍርሃት እንጂ ሌላ ምን ትለዋለህ። መቼም በመንግሥት እርምጃ ‹‹መስማማት ነው›› ልንል አንችልም።
ኑሮ ሲወደድ፣ መብቱ ሲገፈፍ፣ ሕልውናው ፈተና ላይ ሲወድቅ ሕዝብ በተመሳሳይ ዝምታን ይመርጣል። ምንጩ ‹‹ፍርሃት ነው›› ብለን መደምደም እንችላለን?
ታዲያ ከዚህ ሌላ ምን ይባላል። ስደትን አማራጭ ያደረገ እንደኔ ዓይነት ሰው ከዚህ ያለፈ ምን መረጃ ሊኖረው ይችላል?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የታሠረ ጋዜጠኛ ይሸለማል!›› የሚሉ ንግግሮች በቁም ነገር እና በቀልድ መልክ ሲነገሩ ይደመጣል። ሳይታሰር በላቀ ሥራው የሚሸለም ጋዜጠኛ በኢትዮጵያ ሊፈጠር አይገባም? በኢትዮጵያችን በጋዜጠኝነት የሙያ ዘርፍ ‹‹ጀግና›› የምንላቸውስ እነማንን ነው ብለህ ታምናለህ?
‹‹በላቀ የጋዜጠኝነት ተግባር ላይ መሳተፍ›› የሚለው አባባል በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ እንዴት ነው የሚገለጸው? እንደኔ እንደኔ ሙስናን ማጋለጥ፣ ፍትሕ ሲዛባ መጮህ፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሙያዊ ኃላፊነትን መወጣት ነው። አሜሪካዊያን እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች በአገራቸው እንዲከበሩ ስላደረጉ ‹‹ፐልቲዘር››ን የመሳሰሉ ሽልማቶችን ለጋዜጠኞቻቸው ይሰጣሉ። እኛ አገር መሠረታዊ የሰው ልጅ ነጻነት በበቂ ሁኔታ ሳይከበር፤ ‹‹የሰው ልጅ መሠረታዊ መብት ይከበር!›› ብለው የሚጠይቁ ጋዜጠኞች እንደጥጃ በሚታሰሩበት ሁኔታ ‹‹በሥነ-ጽሑፍ ክህሎት፣ ውበትና ፍሰት›› ጋዜጠኛን መሸለም ቅንጦት ይሆናል። ገና ለገና ‹‹የታሠረ ይሸለማል›› በሚል ጉጉት ‹‹ካላሠራችሁን›› ብለው የሚማጸኑ ሰዎችም ሊኖሩ ይችላሉ።
ሰማያዊ መጽሔት ላይ በዚህ ዓመት … የሰጠኸውን ቃለ-ምልልስ ተንተርሰው ሁለት የአገር ውስጥ መጽሔቶች ጽሑፍ በማዘጋጀት ለንባብ አብቅተው ነበር። አንደኛው፣ ‹‹ዳዊት፣ የዳያስፖራውን ፖለቲካ ተቋቁሞ በሙያው እየሠራ ይቀጥል ይሆን?›› ዓይነት ጠያቂ ይዘት የነበረው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ‹‹ይቅርታዬ ተነሥቶ እንደምታሰር ከፍትሕ ሚኒስቴር አስተማማኝ መረጃ ደረሰኝ›› ብለህ የተናገርከውን ከመጠራጠር ባለፈ፣ በጋዜጠኝነት ሙያ እስር እንደሚኖር መጀመሪያ እየታወቀ፣ ከመጀመሪያውም ወደ እዚህ ሙያ መግባት እንደማይገባ ስምህን ሳይጠቀስ ተቺ ጽሑፍ ቀርቦብህ ነበር። ምን ምላሽ አለህ?
አስቀድመህ የጠቀስከውን ጽሑፍ ወዳጆቼ መጽሔቱን ልከውልኝ አንብቤዋለሁ። ‹‹የዳያስፖራውን ፖለቲካ ተቋቁሞ ይቀጥል ይሆን ወይ?›› የሚለው ተገቢ ስጋት ነው። ስጋታቸው ምን ያህል ተገቢ እንደሆነ ለማረጋገጥ ከዚያ በኋላ በተከታታይ በእኔ ላይ የደረሱ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን መመልከቱ ብቻ በቂ ነው። እዚህ በዳያስፖራ አንድ ሰው ‹‹የሌላውን የፖለቲካ ስትራቴጂ አልተቀበለም›› ማለት ጦርነት እንደሚታወጅበት ግልጽ ነው። እንደ አለመታደል ሆነና የፖለቲካ አካሄዳችን ‹‹የአጥፍቶ መጥፋት›› ነው። ሁለተኛውን ጽሑፍ ግን በዝርዝር አላነበብኩትም። ሰዎች ናቸው አንብበው ‹‹ኧረ! ጓደኞችህ እንዲህ እያሉህ ነው..›› ያሉኝ። እንደተነገረኝ ከሆነ ጽሑፉ የተስተናገደው ከአንድ አመት በፊት እኔ ስሰደድ ‹‹ጓደኞቻችንን መልሱልኝ›› ብለው የተማጸኑ ወዳጆቼ በሚያሳትሙት መጽሔት ላይ ነው። እነዚህ ሰዎች ያኔ በምን ምክንያት እንደተሰደድኩ፣ እነማን እንዳባረሩኝና ያባረሩኝ ሰዎችም በነካ እጃቸው ወደ አገሬ እንዲመልሱኝ ለሚመለከተው አካል በጽሑፋቸው ጥያቄ ያቀረቡ የማከብራቸው ጓደኞቼ እንደመሆናቸው ከአንድ ዓመት በኋላ መልሰው ‹‹የለም ማንም አላባረረውም!›› ብለው ጣታቸውን ወደኔ ይቀስራሉ የሚል እምነት የለኝም። እንደው አንባቢ የላከላቸውን ጽሑፍ ሳያዩት ወጥቶ ይሆናል እንጂ ‹‹በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ መስዋዕትነት ሊኖር እንደሚችል ዳዊት ፈጽሞ አያውቅም›› የሚለው ዐረፍተ ነገር ዐይናቸው እያየ ያሳልፉታል አልልም።
በአሜሪካ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተደረገብህ ገልጸሃል። [ኢትዮ ሚዲያ ድረ-ገጽ ዳዊት የሕወሃት/ኢሕአዴግ ደጋፊ መሆኑን ያሳያሉ ያላቸውን 11 ዝርዝሮችን አቅርቦ ተችቶት ነበር] አንተም የኢትዮ ሚዲያ ድረ-ገጽ ኤዲተር አብርሃ በላይን ስም በመጥራት መጻፍህ ተገቢ ነው?
ነገሩ እንደዚያ አይደለም። ድረ-ገጹ 11 ያህል ገጽ ያለውና በብዕር ስም የተጻፈ በጣም የወረደ ጽሑፍ ይዞ ወጣ። እንዳየሁት ወዲያውኑ ኤዲተሩን አነጋገርኩት። ‹‹ይህ ጽሁፍ እኔን እንደማይወክል ባለን የግል ወዳጅነት ጠንቅቀህ ታውቃለህ። አዲስ ዘመን በገጽ 3 ላይ የሚፈጽመውን ስህተት አንተ የ’ዴሞክራሲ ጠበቃ ነኝ’ የምትል ሰው ልትደግመው አይገባም›› አልኩት። እሱም ‹‹እዚህ ስንኖር የሚኖረን አማራጭ ሁለት ብቻ ነው፤ ወይ ዳያስፖራ ያለውን የፀረ-ወያኔ ትግል መደገፍ፤ ወይም ደግሞ ወያኔን መቀላቀል›› አለኝ። ጽሑፉ የእሱም እምነት እንደሆነ ነገረኝ። እዚህ ላይ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በ2001ዱ የሽብር ጥቃት ማግስት የተናገሩትን አስታወሰኝ። ‹‹You are either with us or with the terrorists›› (እናንተ ወይ ከእኛ ወይም ከሰሸባሪዎች ጋር ናችሁ) ነበር ያሉት። ጉዳዩ የሽብርተኝነት ጉዳይ እስከሆነ ድረስ ቡሽ እንዲህ ዓይነት አማራጭ ቢያቀርቡ ብዙም ላያስተቻቸው ይችላል። ‹‹በኤርትራ አማካኝነት የሚደረግን ትግል ካልደገፍክ›› ተብሎ እንደዚህ ዓይነት ጭፍን አማራጭ መስጠት ነውረኝነት ነው። ግለሰቡ በደርግ ጊዜ የሳንሱር ክፍል ኃላፊ ሆኖ እንደማገልገሉ እና በኢሕአዴግ ዘመንም የኢትዮጵያን ሄራልድ አዘጋጅ ሆኖ እንደ መሥራቱ የተለያዩ ሐሳቦችን ማስተናገድ እንደ ‹‹አላማጣ ዳገት›› ቢከብደው አይገርመኝም። ‹‹ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ብዙ የጋራ ጉዳይ እያለን እርስ በርሳችን ጭቃ መቀባባት የለብንም›› በማለት በዚህ አቋሙ የሚቀጥል ከሆነ ግን ራሴን ለመከላከል እንደምገደድ ነገርኩት። በዚያ ላይ ደግሞ የኔንም ሐሳብ መስማት የሚፈልጉ በርካታ ኢ-ሜይሎች ደርሰውኛል። ስለዚህ ምላሼን ሰጠሁ። መጀመሪያ ላይ ‹‹የእኔም ጭምር እምነት ነው›› ያለ ሰውዬ እኔ ምላሽ በሰጠሁ በሦስት ሰዓታት ውስጥ ይቅርታ የሚመስል ‹‹ኤዲተርስ ኖት›› አስቀምጦ ጽሑፉን ሰረዘው። እኔም እነ ኦባንግ ሜቶ፣ አበበ ገላው፣ የአትላንታው ዳዊት ከበደ፣ ዶ/ር ሼክስፒርና ሌሎችም ሰዎች ባቀረቡት ተማጽኖ ለእሱ የሰጠሁትን ምላሽ ከድረ-ገጼ አነሣሁት። እውነታው ይኼ ነው።
ይህ ታዲያ ሚዲያህን ለራስ ፍላጎት መሙያ ማዋልህን አይገልጽም?
የእኔ ምላሽ በቀጥታ አውራምባ ታይምስ ላይ ከመውጣቱ በፊት የሙያው ሥነ-ምግባር በሚጠይቀው መሠረት በራሱ ድረ- ገጽ ላይ እንዲስተናገድልኝ ልኬለታለሁ። መላኬንም በሞባይል የጽሑፍ መልዕክት አሳውቄዋለሁ። ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀርና መድረክ ሳጣ ታዲያ ምን ማድረግ ነበረብኝ? የኔ ምላሽ እኮ የወጣው ከ24 ሰዓታት በኋላ ነው። ይህም በምንም መመዘኛ ሚዲያውን ለራስ ፍላጎት ማዋል ሊሆን አይችልም።
የዳያስፖራ ጋዜጠኝነት በኢሕአዴግ ደጋፊነት እና በፀረ-ኢሕአዴግ ካምፕ (ለሁለት) የተከፈለ ነው። አንተ የቱ ጋር ነህ?
ሁለቱንም አይደለሁም።
የጋዜጠኝነትን ‹‹ABC›› እየተገበሩ (አንድ ጽንፍ ሳይዙ) የዳያስፖራ ሚዲያ ላይ እየሠራህ እስከመቼ ትዘልቃለህ? በፊት በኢትዮጵያ በሽብርተኝነት የተፈረጁ ሰዎችን ሐሳብ አታስተናግድም ነበር። በኋላ ላይ ግን ማስተናገድ ጀመርክ። ግፊት የበረታብህ አያስመስለውም?
አንድ ጽንፍ ሳይዙ መሥራት ፈታኝ እንጂ አስቸጋሪ አይደለም። ወደ ማብራሪያው ከመሄዴ በፊት ግን ጥያቄህን ላስተካክለው። ‹‹በሽብርተኝነት የተፈረጁ ሰዎችን ሳታስተናግድ ቆይተህ በኋላ ላይ ማስተናገድ ጀመርክ›› የሚለው ስህተት ነው። ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ቃለ-ምልልስ ያደረግኩት ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ የተነገረ ዕለት ነበር። የእኔ ችግር በሽብርተኝነት መፈረጃቸው እና አለመፈረጃቸው አይደለም። የኢትዮጵያ የፀረ- ሽብር አዋጅ የሚሠራው በኢትዮጵያ ግዛት ስር ነው። አውራምባ ታይምስ ድረ-ገጽ በአሪዞና ስቴት የንግድ ሕግ የተመዘገበ የሚዲያ ተቋም ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታይ ደግሞ መንግሥት አግዶታል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አዋጆች በሥራዬ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩት ለምንድን ነው? ወደ ዋናው ነጥብ ስመለስ፣ እዚህ ዳያስፖራ ያሉ ሚዲያዎች በአብዛኛው በሁለት ፅንፍ የተሰለፉ ናቸው። በየፅንፋቸው ‹‹አክራሪ›› እና ‹‹ለዘብተኛ›› የሚባሉም አሉ። ሁለት ድረ-ገጾችን ምሳሌ አድርጌ ላቅርብልህ፤ ‹‹ትግራይ ኦንላይን›› እና ‹‹ኢካድፎረም››ን፤ ‹‹ትግራይ ኦንላይን›› በኢሕአዴግ ስር ያለችው ኢትዮጵያ የፕላኔታችን መንግሥተ-ሰማያት እንደሆነችና መሪዎቿም መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው መላዕክት እንደሆኑ አድርጎ ያቀርባል። ‹‹ኢካድፎረም›› በበኩሉ አዲስ አበባን ሲገልጻት ማንም በነጻነት የማይንቀሳቀስባት፤ ከትግራይ ተወላጆች ውጪ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆች በጠራራ ፀሐይ የሚረሸኑባት የሲኦል ከተማ ያደርጋታል። መሪዎቿን ከተለያዩ አደገኛ የእንስሳት ዝርያ ጋር እያመሳሰለ የሚያቀርብ እና ለዴሞክራሲ እታገላለሁ የሚል ድረ-ገጽ ነው። ‹‹ትግራይ ኦንላይን›› እና ‹‹ኢካድፎረም›› የሚስሏትን ኢትዮጵያ እኔ አላውቃትም። ሌሎቹ ሚዲያዎችም በእነዚህ ግራ እና ቀኝ ባስቀመጥኳቸው ሞዴል ድረ-ገጾች ስር ለዘብ ባለ አኳኋን የተሰለፉ ናቸው። በአውራምባ ታይምስ እና በኢትዮ-ሚዲያ መካከል ግጭት ሲፈጠር ‹‹ኢካድፎረም››፣ ‹‹የሁለት ወያኔዎች ጠብ›› ሲል፤ ‹‹ትግራይ ኦንላይን›› ደግሞ ‹‹የብርሃኑ ነጋ ግራ እጅ እና ቀኝ እጅ ጠብ›› ብሎ ነበር የዘገበው። አውራምባ ታይምስ ድረ-ገጽን ከእነዚህ ‹‹ሚዲያዎች›› ጎን እንድትሰለፍ ማድረግ ሞራላዊ አይደለም። ስለዚህ እነዚህን ሁኔታዎች በመመርመር አውራምባ ታይምስ ባለፈው ጥቅምት ወር አንድ የፎርማት ለውጥ አደረገች። ይህም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በተለይ ደግሞ አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎችን በሚያበረታታ ሁኔታ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት፣ የፕሬስ ነጻነት እንዲያብብ፣ ከአንድ የሚዲያ ተቋም የሚጠበቅ አስተዋጽኦ በጨዋነት ማበርከት›› የሚል ነው።
ዞሮ ዞሮ ያው ሆነ… ተቃዋሚዎችን ማበረታታት የአንድ ሚዲያ ተቋም ተግባር ሊሆን ይገባል?
ተቃዋሚዎችን ማበረታታት ስንል የተቃዋሚዎችን ፖሊሲ ከመደገፍና ከመቃወም አንጻር ሳይሆን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲኖር ከመፈለግ ነው። ተቃዋሚው አንድ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሚዲያው ማበረታታት አለበት። በአንድ አገር ዴሞክራሲ የመኖሩ አንዱ መገለጫ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መኖር እና ሕዝብ ደግሞ በምርጫ ወቅት የሚበጀውን እንዲመርጥ ምቹ የሆነ ሁኔታ መፍጠር ነው። ስለዚህ ‹‹ተቃዋሚዎች መጠናከር አለባችሁ›› ሲባል ‹‹ለመራጩ ሕዝብ ጥሩ አማራጭ መሆን የሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ሚዲያው ሊያበረታታቸው ይገባል፤ ፖሊሲዎቻቸውንና አማራጮቻቸውን ሕዝቡ ጋ እንዲያደርሱ ተገቢውን ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል›› ለማለት ነው። እዚያ ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ የመምረጥ እና ያለመምረጥ ኃላፊነት የሕዝቡ ስለሚሆን እንደሚዲያ ባለሙያዎች ላያገባን ይችላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረጉ ያሉ ምርጫዎችን ተመልከት። ‹‹ዴሞክራሲ ሂደት ነው›› እየተባለ 22 ዓመት ያስቆጠረው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጨረሻው እንዲህ ሲሆን መመልከት ነበረብን? አሁን ባለፈው ወር (ሚያዚያ 2005 ዓ.ም.) የተደረገው ምርጫ ምርጫ ነው? እውነት የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በዚህ ውጤት መኩራት አለባቸው? በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዚህ መንገድ ምርጫን ‹‹ማሸነፍ›› ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥ ማሳመኛ በቅንነት ሊያቀርቡልን ይችላሉ? ዴሞክራሲ እንዲያብብ የሚፈልግ የሚዲያ ተቋም ይህን ቢያደርግ ምንድነው ችግሩ?
‹‹የእኔ ችግር በሽብርተኝነት መፈረጃቸው እና አለመፈረጃቸው አይደለም›› ብለሃል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በኢትዮጵያ በሽብር በተፈረጁ በአንዳንድ ቡድኖች ላይ የሰላ ትችት ትሰነዝራለህ። ምክንያትህ ምንድነው?
ለምሳሌ ‹‹ግንቦት 7››ን በተመለከተ፣ አገር ቤት ያለ ሰው ትልቅ ድርጅት አድርጎ ይመለከተው ይሆናል። በእኔ እምነት የ‹‹ግንቦት 7›› ታላቅነት ኢሕአዴግ የሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች ደጋግመው ስለሚያወሩለት ብቻ ነው። በተረፈ በዓምስት አመት ውስጥ ‹‹ግንቦት 7›› ያበረከተው አስተዋጽኦ ምንድን ነው? ካልከኝ ኢሳት የተባለ ‹‹የሳይበር ቴሌቭዥን›› ማቋቋሙ ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ የራሱ የሆነ ስትራቴጂ የለውም። ጥቂት የመከላከያ ጄኔራሎች እና ኮሎኔሎች በራሳቸው መንገድ ሲደራጁ ‹‹አለሁበት›› ይላል። የሰሜን አፍሪካ አመጽ ሲነሣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አመጹ እንዲደገም ጠንክረን እየሠራን ነው፤ ግንቦት 21/2003 ነጻ ትወጣላችሁ›› ይላል። ‹‹የኔሰው ገብሬ ራሱን አቃጠለ›› ሲባል ‹‹ኢትዮጵያዊው ቡአዚዝ የለኮሰውን እሳት በሳምንታት ውስጥ አራት ኪሎ እናደርሰዋለን›› ሲል ይደመጣል። ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን የ‹‹ሃይማኖት ነጻነት ይከበር!›› ሲሉ ‹‹ጥያቄው የእኛም ነው›› በማለት ክርስቲያን የፓርቲው አመራሮች በአደባባይ ‹‹አላሁ አክበር!›› ማለት ጀመሩ። የአማራ ተወላጆች ከጉራፈርዳ እና ከቤንሻንጉል ክልል ሲባረሩ ‹‹የአማራ ጠላቶችን ድል እንንሣ፤ ተነሡ!› ይላል። እንዲህ እያለ ይቀጥላል። በነገራችን ላይ ሙስሊሞች ላነሱት የሃይማኖት ነጻነት ጥያቄና ለአማራ ወገኖቻችን መፈናቀል አጋርነት ማሳየት ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ። ነገር ግን፣ የፓርቲው አመራሮች ከእያንዳንዱ ክስተት ፖሊቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የሚያደርጉት አስቂኝ ጥረት ደግሞ በጣም ይገርመኛል። ስትራቴጂያቸው ኢሕአዴግ የሚፈጥራቸውን ስሕተቶችና በየአጋጣሚው የሚፈጠሩ ክስተቶችን ለራሱ ዓላማ ማዋል ብቻ ነው።
እንደምታስታወሰው፣ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣን ስንሠራ አየለ ጫሚሶን ለመሳሰሉ ተቃዋሚዎች ‹‹ሽፋን አንሰጥም›› እንል ነበር። ለምን ከተባለ የራሳቸው የሆነ አጀንዳ ስለሌላቸው ነው። በአየለ እና በብርሃኑ መካከል ያለው አንድነት የኢሕአዴግን አጀንዳ ከማራገብ ውጪ እውነተኛ ለውጥ እንዲመጣ አለመፈለግ ሲሆን ልዩነታቸው ደግሞ አ… በኢሕአዴግ እየታዘዘ ብርሃኑ ግን በሻዕቢያ እየተጠመዘዘ መሆኑ ነው።
ትውልደ ሩሲያዊው ባለቅኔ፣ የኖቤል ሽልማት ባለድል፣ ሟች ጆሴፍ ብሮድስኪ ‹‹አንድ ነጻ ሰው ሲወድቅ ማንንም አይወቅስም›› በማለት ጽፏል። ይህ አባባል ራሳቸው ሊኖሩበት ለመረጡት ኅብረተሰብ ዕጣ ፈንታ የመጨረሻውን ኃላፊነት መቀበል ባለባቸው የዴሞክራሲ ዜጎችም ላይ የሚፀና ሀቅ ነው ተብሎ ይገለጻል። በአንጻሩ በአገራችን በመንግሥት፣ በተቋማትና በግለሰቦች ደረጃ አንዱ አንዱን አጥብቆ ሲወቅስ ይታያል።
ይህ ዓይነቱ የመወቃቀስ ባህል ገንቢ በሆነ መልኩ ቢሆን እንደ አገር እና እንደ ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አንሆንም ነበር። መወቃቀሱ በፖለቲካ ልዩነት ደረጃ ሲሆን ከመተራረም ያልፍ እና ወደ መጠፋፋት ይቀየራል። በአገራችን፣ በ1960ዎቹ መጨረሻ የነበረው የፖለቲካ አሰላለፍ እና ልዩነት ቤተሰባዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነትን ሁሉ በጣጥሶ ያልፍ ነበር። እህት እና ወንድም በሁለት የአስተሳሰብ (የርዕዮተ ዓለም) ልዩነት ምክንያት ለመገዳደል ሲፈላለጉ አይተናል ወይም አንብበናል። ‹‹ማኅበራዊ ግንኙነት ሁሌም ፖለቲካን ማለፍ አለበት›› የሚባለውን የሰለጠነው ዓለም አካሄድ ከመከተል ይልቅ በአገራችን ያለው የፖለቲካ ልዩነት ወደ መጠፋፋት ሲያመራ ታያለህ። ያ ልዩነትን በ‹‹አጥፍቶ መጥፋት›› ለመፍታት ይደረግ የነበረው ጥረት ዛሬም ድረስ ዘልቆ በዚህኛው ትውልድ ላይም እየተንፀባረቀ ነው። የ‹‹አጥፍቶ መጥፋት›› ፖለቲካ የግድ ከፖለቲካ ልዩነት ጋር ተያይዞም ላይመጣ ይችላል። ልዩነትም ሳይኖር ሰውን ለመፈረጅ (ብላክ ሜይል ለማድረግ) የተካኑ የፈጠራ ባለሙያዎች ካሉ እንደተፈጸመ ተደርጎ ሊወራ ይችላል። ካንተ የሚጠበቀው፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለአሻሚ ትርጉም ተጋላጭ የሆነች ዓረፍተ-ነገርን ብቻ መተንፈስ ነው። በጋዜጠኝነት ውስጥም የምትመለከተው ተመሳሳይ መፈራረጅን ነው። በደጉ ጊዜ አብሮህ የበላ እና አብሮህ የጠጣ ባልደረባህ ያንተን አቋም በተሳሳተ ሁኔታ ተርጉሞ ለገበያ በማቅረብ መጠነኛ የስደት ፖለቲከኛነት ትርፍ ለማግኘት ሲጥር ታያለህ። እንደ አለመታደል ሆነና ከዚህ ያለፈ ገንቢ መወቃቀስ ብዙም አትመለከትም። ምናልባት ይህ እንዲለወጥ ማድረግ የሚችሉት የዳያስፖራ ፅንፈኞች ያልበከሏቸው የአገራችን ፖለቲከኞች ብቻ ናቸው።
በፅንፈኝነት አልተበከሉም የምትላቸውን የአገራችንን ፖለቲከኞች በምሳሌነት ልትነግረኝ ተችላለህ?
በጣም በርካታ ፖሊቲከኞችን ልጠራልህ እችላለሁ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ስዬ አብርሃ፣ አቶ ያሬድ ጥበቡ፣ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፣ አቶ ግርማ ሰይፉ… በጣም በርካታ ሰዎችን መጥራት ይቻላል።
በእነዚህ የጠቀስካቸው ስሞች አማካኝት የአገራችን የፖለቲካ ሂደት አንድ ደረጃ ፈቀቅ የሚል ይመስልሀል?
ተስፋ አለኝ።
‹‹ዴሞክራሲ ለነጻነት ተቋማዊ ይዘት መስጠት ነው›› ይባላል። ከዚህ አኳያ ዴሞክራሲያዊ ነጻነትን በአሜሪካ፤ እንዲሁም በኢሕአዴግ ዴሞክራሲ እየተገነባባት መሆኑ በሚነገርባት አገራችን ‹‹አለ›› የሚባለውን የነጻነት ገጽታ እንደ ጋዜጠኛ ትዝብትህን ንገረኝ?
በዚህ ረገድ እኮ ያለው አንዱ መሠረታዊ ችግር፣ ኢሕአዴግ ነጻነትን የሚሰጥ እና የሚከለክል ሆኖ መገኘቱ፣ ‹‹ሰጪ›› እና ‹‹ከልካይ›› መሆኑንም ጭምር አምነን መቀበላችን ነው። አንድ አሜሪካዊ ነጻነቱን ተግባራዊ ሲያደርግ ፖሊስ በቁጥጥር ስር የሚያውለው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ከሚፈቅድለት ውጪ ከተንቀሳቀሰ ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ ኋይት ሀውስ ፊት ለፊት መፈክር ይዘህ ባራክ ኦባማን ስትራገም ብትውል ማንም አይነካህም። ዛሬ አራት ኪሎ በሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ፊት ለፊት ቆመህ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን ልትቃወም ቀርቶ ‹‹ጣሊያን አገር ለግራዚያኒ የመታሰቢያ ሐውልት ሊሠራ አይገባም!›› ብለህ በሰላማዊ ሰልፍ ወደ ጣሊያን ኤምባሲ መሄድ ያሳስራል። ይህ እርምጃ የተወሰደው፣ ‹‹ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት›› በሕገ መንግሥቱ ስላልተካተተ አይደለም። አሊያም ዋቢ ሸበሌ ሆቴል እራት ለመመገብ ከማዘጋጃ ቤት ፍቃድ ማግኘት አስፈላጊ ስለሆነም አይደለም። ‹‹አባይን እየገደብን ስለሆነ፣ በቃ! ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን አትጠይቁ!›› እያሉን ነው።
እዚህ የምታገኘው ነጻነት ምን ያደርግልሀል? ምንስ ትለውጥበታለህ? እዚህ ያሉ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ እዚህ ያገኙትን የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ነጻነት የፖለቲካ ባላንጣቸውን ሲሰድቡበት እና ሲያዋርዱበት እንጂ ቁም ነገር ሲሠሩበት አይታይም። ያ ደግሞ ከየትም የመጣ ችግር አይደለም። ሌሎችን የምንተቸውን ያህል በውስጣችን ነጻነት አለመኖሩ ነው። ‹‹ነጻነት የማያውቅ ነጻ አውጪ›› ብለን መጽሐፍ ከመጻፍ ውጪ ወደ ስልጣን እየተጓዝን ያለነው ሌሎች በነጻነት እንዲተቹን መፍቀድ ሳንችል ነው። የፕሬስ ነጻነትን ማፈን የምንጀምረው ገና መንግሥታዊ ሥልጣን ሳንይዝ ነው። የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም አምባገነንነትን ስለመቃወም የተናገሩትን ነገር ሁሌም አልረሳውም። ‹‹እኛ እኮ በሥልጣን ላይ ያሉትን የምንቃወመው አምባገነንነታቸውን እንጂ በግለሰብ ደረጃ ጥላቻ ኖሮን አይደለም፤ ስለዚህ በተቃዋሚውም ጎራ አምባገነኖች ሲኖሩ ‘ትግሉ ይጎዳል’ በሚል ሽፋን ካበረታታናቸው ነገም የስም ለውጥ ባደረጉ አምባገነኖች ነው የምንገዛው›› ብለው ነበር። ኢሕአዴግ የራሱን ሕግ እንዲያከብር ከመታገል ጎን ለጎን የፕሮፌሰርንም ምክር መስማት ተገቢ ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሚዲያ አራተኛው የመንግሥት አካል ተደርጎ አልተቆጠረም። ሚዲያ 4ኛ የመንግሥት አካል መሆን እንዲችል ወሳኙ እውነት ምንድን ነው? ከሚዲያ ባለሙያዎች ምን ይጠበቃል ትላለህ?
ኢሕአዴግ ሚዲያውን እንደ አራተኛው የመንግሥት አካል ሊቆጥር ቀርቶ [ድሮ እንደሚያደርገው] በጠላትነት ፈርጆ እንኳን ሊያሠራው አልቻለም። የፕሬስ አዋጁ በ1985 ዓ.ም. ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ያሉትን 20 ዓመታት ስትመለከት በነጻ ሚዲያው እና በመንግሥት ሹማምንት መሀከል የነበረው ግንኙነት የአይጥ እና ድመት ዓይነት ነው። ጋዜጠኞች ሲታሰሩ እና ሲፈቱ፣ ጋዜጦቹም ‹‹ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ›› እርምጃ ሲወሰድባቸው አስተውለናል። ስለዚህ ጋዜጠኛው ‹‹እንደ አራተኛ የመንግሥት አካል ልቆጠር!›› የሚል የቅንጦት ጥያቄ ሊጠይቅ ቀርቶ ‹‹ሳልታሰር፣ ሳልሰደድ፣ ድርጅቴ ሳይዘጋ በነጻነት ልሥራ›› ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ እንኳን አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም። ዛሬም የምናወራው ስለ እስክንድር የይግባኝ ውሳኔ፣ ስለ ውብሸት ወደ ዝዋይ እስር ቤት መዘዋወር፣ ስለ ርዕዮት ሕክምና ማጣት ነው። ‹‹ከሚዲያ ባለሙያዎች ምን ይጠበቃል?›› ላልከው ግን ምንም እንኳን ችግሮች ቢኖሩም ሚዲያው ሚዛናዊ ሆኖ መቀጠል አለበት እንጂ የአጸፋዊ ምላሽ መስጫ መድረክ መሆን የለበትም የሚል እምነት አለኝ።
ሚዲያውስ ‹‹አራተኛው የመንግሥት አካል›› ለመሆን ‹‹ማድረግ ያለበትን አድርጓል›› ብለህ ታስባለህ?
ያ ደግሞ የ20 ዓመት ዕድሜ ብቻ ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሬስ ይቅርና ከ200 ዓመት በላይ ታሪክ ባለው የአሜሪካ ፕሬስም ችግሮች ይታያሉ። ሁሌም በክልከላ የሚታረም ነገር አይኖርም። መብቱ ሲሰጥህ ኃላፊነት እየተሰማህ ይመጣል። ሕዝቡ ይበልጥ እየሰለጠነ በመጣ ቁጥር ስልጡን ፕሬስ ወደ መምረጥ ይሄዳል። በሰለጠነው ዓለም ያሉት ፕሬሶች የመጡበት ታሪክ በክልከላ ሳይሆን ኃላፊነት እየተሸከሙ መሆኑን ያሳያል።
አቦይ ስብሃት በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ-ምልልስ ‹‹…እጅግ የሚገርመው ለኋላቀርነታችን መሠረት የሆነው ይኼ ነጻ ፕሬስ ነው። አብዛኛው ነጻ ፕሬስ ኢትዮጵያዊ አይደለም። የሚነሳው አገርን ማዕከል አድርጎ አይደለም። ጥላቻን ነው የሚሰብከው። የኢትዮጵያን የጥላቻ ፖለቲካ ለማጥናት የተትረፈረፈው መረጃ የሚገኘው ከኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ነው። በአንድ ጋዜጣ አራት እና አምስት ዕትም ለማስተርስ ድግሪ የሚሆን የመመረቂያ ጽሑፍ መጻፍ ይቻላል። …ከሥነ-ምግባር አኳያ ተለክተው የመንግሥትም ሆነ ነጻ ፕሬስ ፍርድ ቤት ቢሄዱ ቅር አይለኝም።›› ብለው ነበር። ለዚህ ምን ምላሽ ትሰጣለህ?
በአቦይ ስብሃት አባባል ውስጥ መጠነኛ እውነት የለም ማለት አይደለም። ‹‹አብዛኛው የነጻ ፕሬስ›› የሚለው ድምዳሜ ግን ትክክል አይመስለኝም። በተለይ በ1980ዎቹ ብዙ የሥነ-ምግባር ችግር እንደነበር አይካድም። ‹‹ፕሬሱስ በምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ [ፖሊቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች] ውስጥ ሆኖ ነበር የሚሠራው?›› የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። እንደ አንድ ጀማሪ የዴሞክራሲ ተቋም፣ በወቅቱ ነጻው ፕሬስ እንዲጠናከር የአቦይ ስብሃት መንግሥት ምን ዓይነት አስተዋጽኦ አደረገ? እንደ ሌሎች አገሮች የገንዘብ ድጎማ ማድረግ ባይቻል እንኳን ቢያንስ ጋዜጠኛውን ባለማሰር ነጻ ፕሬስ እንዲያብብ ማድረግ ይቻል ነበር። አቦይ ስብሃት በሚገልጹት ደረጃ ፕሬሱ ፕሮፌሽናል አለመሆኑ ‹‹የሚያስወቅሰው ሙያተኛውን ብቻ ነው›› ካልን ተሳስተናል። ሌሎች የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተለይ ከውጪ አገር ዲፕሎማቶች ጋር ሲያወሩ ስለ ነጻው ፕሬስ ያላቸው ዕይታ እና ድምዳሜ እንደ አቦይ ስብሃት የተንሸዋረረ ነው። እሺ! እውነታው አቦይ እንዳሉት ይሁን እንበልና ማነው ተጠያቂው? ‹‹የአገሬ ፕሬስ ኋላቀር ነው›› ብሎ ለውጭ ሰዎች አፍን ሞልቶ መናገርስ መንግሥትን ያስከብራል?
ኢትዮጵያን እና አውራምባ ታይምስ ጋዜጣን ስታስብ ምን የሚቆጭህ ነገር አለ?
አውራምባ ታይምስ እንደ አንድ ነጻ ሚዲያ በሦስት ዓመት ከስምንት ወር ዕድሜዋ ብዙ የዳሰሰቻቸው ርዕሠ ጉዳዮች ነበሩ። ከመጀመሪያ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ድረስ አብረውን የዘለቁት አንባቢዎቻችን የብርታታችን ምንጭ ነበሩ። የበለጠ ሥራ እንድንሠራ አበረታተውናል፣ ገስጸውናል፣ መክረውናል። እንደምታስታውሰው፣ በመጀመሪያው እትም ላይ የነበረ የጋዜጣዋ ባልደረቦች ቁጥር ቁጥራችን አምስት ነበር፡፡ ከዚያ ቀስ በቀስ ወደ 20 ገደማ አደገ። መጀመሪያ ስንጀምር በ16 ገጽ ነበር፤ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ 24 ገጽ አሳደግናት፤ ከሁለት ዓመት በኋላም ባለቀለም ጋዜጣ እንድትሆን ተደረገ… እንዲህ እንዲህ እያልን ብዙ ነገር እያሻሻልን ነበር። እስከ ዛሬ ብንቆይ ኖሮ ምናልባትም በሣምንት ሁለት ጊዜ እንድትወጣ ማድረግ ችለን ሊሆን ይችል ነበር። በምንወዳት አገራችን በአስር ሺህዎች ከሚቆጠሩ ሳምንታዊ አንባቢዎቻችን የምንወደውን ሥራ እየሠራን፣ የጎደለውን እየሞላን መሥራትን የመሰለ የሚያረካ ነገር የለም፤ ግን አልሆነም። የምንሠራው በኃላፊነት መንፈስ ሕገ- መንግሥቱን እና በየደረጃው ያሉ ሕጎችን አክብረን ነበር። ግን እኛ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት የምናበረክታት ሚጢጢ ድርሻ በአዎንታዊ መንገድ አልታየችም። ‹‹አውራምባ ታይምስ የተዘጋችው ከስራ ነው፤ እኛ አልተጫንናችሁም›› ያሉ ሰዎች ዌብሳይታችንን ወዲያውኑ በማፈን ‹‹ጫና ወይስ ኪሳራ?›› የሚለውን እንቆቅልሽ ራሳቸው ፈትተውታል። እኔ ከመላው የአውራምባ ታይምስ ባልደረቦች [በፕ/ር አለማየሁ ገብረማሪያም አገላለጽ ‹‹ቲም አውራምባ››] ጋር የነበረኝ የሦስት ዓመት ከስምንት ወር አስደሳች ቆይታ መቼም ቢሆን በሕይወት ዘመኔ ተመልሶ የሚመጣ አይመስለኝም። እስኪ አስበው፣ የፍጼን የ‹‹መርሕ›› ጥያቄዎች፣ የግዛውን ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ የማየት ችሎታ፤ የውብሸትን የሥራ መንፈስ አነቃቂ ጨዋታዎች፣ የአቤልን እልህ አስጨራሽ ክርክር፣ የነብዩን የግራፊክስ ክህሎት፣ ያንተን ጤና ነክ ትንታኔዎች፣ የወሰንን የደስታ እና የመከራ ዘመን ወዳጅነት፤ (እንዲሁም የሌሎች ባልደረቦቻችን ትዝታዎች ተጨማምረው) ሁሉም ለአውራምቢት [በፍጼ አጠራር] የነበረው ፍቅር መቼም ከኅሊናችን አይጠፋም!!!
ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ ከአገሩ ከወጣ ወይም ከተሰደደ ‹‹ከባህር የወጣ አሳ ማለት ነው›› ከአገር የተሰደዳችሁ ጋዜጠኛች ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማችሁ ‹‹ኢምንት ነው›› ይባላል። ድረ- ገጾች ስለሚታፈኑ፣ ኅብረተሰቡም ድረ-ገፆች የመከታተል ልምዱ ዝቅተኛ ስለሆነ በሥራችሁ የምትደርሱት የኅብረተሰቡ ክፍል ዝቅተኛ አይሆንም? ከ97 ምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ ከአገር የተሰደዱ ጋዜጠኞች ከተለያየ የዓለም ክፍል የቻሉትን ያህል ቢተጉ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ብለህ ታስባለህ?
ይሄ ምንም አያጠያይቅም። ፖለቲከኛም ይሁን ጋዜጠኛ ከአገሩ ከወጣ ምንም የሚፈጥረው ተጽዕኖ የለም። ውጪ ሆነህ የምትሠራውን ሥራ በብዛት የሚያነበው ስደተኛ ነው፤ እሱ ደግሞ ተለወጠ/ አልተለወጠ ምንም የሚያመጣው ተጽዕኖ የለም። ላለመመለስ አገር ለቀህ ስትወጣ ሁሉም ነገርህ የሚቀረው እዚያችው ኤርፖርት ኬላ ላይ ነው።
የአንተም ሆነ የሌሎች በኢትዮጵያ ላይ የሚያጠነጥኑ የድረ-ገጽ ዜና እና ሀተታዎች ብዙዎቹ በራስ የተሰሩ ዘገባዎች (ኤክስክሉሲቭ) አይደሉምና የዳያስፖራ ሚዲያዎች በሌላ ድረ-ገጽ ጉዳይ የመጠቀም (Copy–Paste) ሥራን የምትከተሉ አይመስልህም?
በእርግጠኝነት የምነግርህ ነገር ይህን ጥያቄ አውራምባ ታይምስ ድረ-ገጽን ተመልክተህ የሰነዘርከው አይመስልም። ምክንያቱም የኛ ድረ-ገጽ በይዘት እና በሚሳተፉ ጸሐፊዎች ማንነት ረገድ ካየኸው ከሌሎቹ ፍጹም የተለየ ነው። ከሌሎቹ የተሻለ ወይም የበለጠ ነው ግን እያልኩህ አይደለም። ‹‹የተለየ ነው›› ስልህ በሌሎች ድረ-ገጾች ላይ አዘውትረው የሚጽፉ ጸሐፊዎችን እኛ አናስተናግድም። ያንን የምናደርግበት ዋናው ምክንያት ከሌሎቹ የተለየ ነገር ይዘን ለመቅረብ እንጂ ጸሐፊዎቹን ሳንፈልጋቸው ቀርተን አይደለም። አንዳንዶቹ አድርጉ እንደሚሉን የ‹‹ሥርዓቱ ሰለባ ነን›› ብለን ከጋዜጠኝነት መርህ አንወጣም። በተቻለ መጠን ሚዛናዊ ለማድረግ እንጥራለን። ያ ደግሞ ልዩ ያደርገናል ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ጭፍኖች ዘንድም እያስተቸን ነው።
‹‹በራስ የተሰሩ ዘገባዎች (ኤክስክሉሲቭ) አይደሉም›› ያልከው ነገር ትንሽ ፈገግ ያሰኛል። እስኪ ሌሎች ትልልቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ተከታተል። በራሳቸው ዘጋቢ የሚሠራ ነገር የሚያቀርቡት ምን ያህሎቹ ናቸው? በተረፈ እንደ ምንጭ እየጠቀሱ የሚያወጡት ሬውተርስ፣ አሶሺየትድ ፕሬስና አጃንስ ፍራንስ ፕሬስን ከመሳሰሉ ሚዲያዎች የሚያገኙትን መረጃ አይደለምን? ሌሎቹን ተዋቸው፣ እዚያው አጠገብህ ያለውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ያሉት ኢቴቪ እንኳን አብዛኛዎቹ ዜናዎቹ ከዋልታ እና ከኢዜአ የሚወሰዱ አይደሉም? ይህ ማለት ግን ‹‹ኤክስክሉሲቭ›› ነገር አውራምባ ታይምስ ላይ አይሠራም ማለት አይደለም። የምንሠራው ሥራ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ እንደመሆኑ ኤክስክሉሲቭ ሥራ ለመሥራት በቋሚነት የሚሠሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዘጋቢዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖሩህ ይገባል። ያ ደግሞ በእኛ ውስን አቅም አስቸጋሪነቱ ምን ድረስ እንደሆነ አንተም ታውቀዋለህ።
ከዲሲ ወደ ፊኒክስ አሪዞና ሄደህ መኖር ጀምረሃል። በዲሲ ያለው የዳያስፖራው ተጽዕኖ ከብዶሀል ይባላል። በአንድ ወቅት በማኅበራዊ ድረ-ገጽ ላይ ራስን መሆን ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ገልፀህ ነበር። እስኪ አስቸጋሪነቱን በደንብ ግለጸው?
በዋናነት ወደ አሪዞና የመጣሁት በ‹‹ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አሪዞና›› ያገኘሁትን የትምህርት ዕድል ለመጠቀም ቢሆንም ዲሲ አካባቢ ካለው የፖለቲካ ሙቀት ለመራቅም አጋጣሚውን ተጠቅሜበታለሁ። አገር ቤት እያለን መንግሥት ልማታዊ ዘገባዎችን አቅርቡ እያለ እንደሚወተውተን ሁሉ እዚህም ያሉ ፖሊቲከኞች እኛ ስለምናውቃት ኢትዮጵያ ሳይሆን እነሱ በምናባቸው ስለሚስሏት ኢትዮጵያ እንድንጽፍ ይፈልጋሉ። ‹‹ዳያስፖራ ያለ ጋዜጠኛ ወይ ወያኔን አሊያም እከሌ የተባለን ድርጅት መደገፍ አለበት›› ብለው በአደባባይ የሚናገሩትን ጨምሮ ማለቴ ነው። በቅርቡ ከወዳጄ መስፍን ነጋሽ ጋር ስናወራ፤ በንግግሩ መሀል አንድ እጅግ የሚማርክ አገላለጽ ሲጠቀም ሰማሁት። ‹‹እኛ ጋዜጠኞች ገና ለገና ኢሕአዴግ ስላባረረን እና ስለከሰሰን አንዳንድ ተቃዋሚዎች የእነሱ የግል ንብረት የሆንን ይመስላቸዋል፤ ከኢሕአዴግ ጋር ተጣላን ማለት እኮ ተቃዋሚዎች የሚሉት ሁሉ ይስማማናል ማለት አይደለም›› ብሎ ነበር። የሚሰደዱ ጋዜጠኞችን በተመለከተ፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አንድ የተሳሳተ ግንዛቤ አለ። መከራን ሸሽቶ የመጣ ጋዜጠኛ ‹‹ዳያስፖራ ያሉ ጽንፈኛ ፖሊቲከኞችን በባርነት ሊያገለግል ይገባል›› የሚል ያልተጻፈ ሕግ አለ። አንዳንዶቹ የተሰደዱ ጋዜጠኞች ኢሕአዴግን ማገልገል እንጂ ተቃዋሚን ማገልገል እንደ መጥፎ ነገር አድርገው አይመለከቱትም። የእነዚህን ጥቂት ጋዜጠኞች ደካማ ጎን የተመለከቱ ተቃዋሚዎችም ሁሉም የተሰደደ ጋዜጠኛ የእነሱ የግል ንብረት እንደሆነ አድርገው ማመን ጀመሩ። ይህንን እምነታቸውን የሚፈታተን ጋዜጠኛ ካለ በተለመደው የፍረጃ ስትራቴጂያቸው በወያኔነት ይፈርጁታል። በየቦታው ያሉ ፓልቶኮቻቸው፣ ብሎጎቻቸውና ዌብሳይቶቻቸውም ያንን ፈጠራ ያስተጋቡታል። በዚህ መልኩ ሁሉም አንገቱን መድፋት ይመርጣል። ከ1997 ዓ.ም. በፊት በነጻው ፕሬስ ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ እጅግ የምናደንቃቸው እና በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲያጋልጡ የኖሩ ጋዜጠኞች ከእስር ቤት እንደወጡ በቀጥታ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጥላ ሥር ሲሰባሰቡ መመልከት ያሳዝናል። ‹‹ከቅንጅት መሪዎች ጋር ተባብራችሁ መንግሥትን ልትገለብጡ ነበር›› የሚለውን ክስ ሐሰትነት በተደጋጋሚ የተናገርን ሰዎች፤ ‹‹ክሱ እውነት ነበር እንዴ?›› በሚያስብል መልኩ በ1997 ዓ.ም. ከቅንጅት መሪዎች መካከል አንዱ የነበሩ ግለሰብ ባቋቋሙት የስደት የፖሊቲካ ድርጅት እና በእሱ ስር ባለ የሚዲያ ተቋም መሰባሰብ ሙያውን ማዋረድ ነው።
እውን ‹‹ሚዛናዊ ጋዜጠኛ ነኝ›› ብለህ ታምናለህ?
አቅሜ በፈቀደ መጠን ሚዛናዊ ለመሆን እጥራለሁ። በአገራችን ተጨባጭ የፖሊቲካ ሁኔታ በተለይ በዳያስፖራ ሚዛናዊ መሆን የራሱ የሆነ የሚያስከፍለው ዋጋ እንዳለ እሙን ነው። ለምሳሌ፣ በአገር ቤት ያለ አንባቢ ገለልተኛ ሆነህ መረጃውን እስካቀረብክለት ድረስ ይቀበልሀል። ምሳሌ፣ እንደምታስታውሰው በጋዜጣችን ላይ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት [ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም፣ አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው፣ አቶ ሽመልስ ከማል፣ ኮሚሽነር ዓሊ ሱሌይማን፣ ዶ/ር ደብረፅዮን ...ና ሌሎች] እንግዳ ሆነው ቀርበዋል። የአቦይ ስብሐት መጣጥፎችም በፍትሕ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ይስተናገዱ ነበር። አንባቢ ግን ወቀሳ ሲያቀርብ አላስታውስም። እዚህ ዲያስፖራ ያለው ሁኔታ ደግሞ ፍጹም የተለየ ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማቅረብ ቀርቶ አቶ ስዬ አብርሃን ቃለ-ምልልስ በማድረጌ የደረሰብኝን ውግዘት እኔ ነኝ የማውቀው። በቃ ፖሊቲካችን እንደዚህ ሆኗል።
ለኢትዮጵያ የሚበጃት ማን ነው? ምንድን ነው? አሁን ላለችበት ችግር፣ ፈተና፣ ድህነት…ማን ይታደጋት?
በእርግጠኝነት የምነግርህ፣ ለነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ እና ቤዛ ሊሆኑ የሚችሉት በአገር ቤት ያሉ ጋዜጠኞች፣ ተቃዋሚዎችና የለውጥ አራማጆች ብቻ ናቸው። ዋጋ የሚከፍሉት፣ መከራ የሚቀበሉት ጫናው የሚበረታባቸውም እነሱ ላይ ነው። አንድ ችግር ቢፈጠር ቀድመው ክፍተቱን የሚሞሉትም እነሱ ናቸው። እዚህ ያሉ ፖለቲከኞች የቤት ሥራው ከተሠራ በኋላ መምጣት የሚፈልጉ ናቸው። አስታውሳለሁ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መሞታቸው ሲነገር የአውሮፕላን ትኬት ለመቁረጥ የዳዳቸው የተቃዋሚ አመራሮች ነበሩ። እንደኔ እንደኔ በኢሕአዴግ ላይ አንዳች አስገዳጅ ነገር ቢመጣ እና ፈተና ቢጋረጥበት፣ ሕዝቡን አንቀሳቅሰው አንድ ለውጥ ለማምጣት ቅርብ የሆኑት በአገር ቤት ያሉት ፖሊቲከኞች ናቸው። ከኢሕአዴግ ሴራ ጎን ለጎን በ1997ቱ ምርጫ የተገኘው የዴሞክራሲ ጭላንጭል በድጋሚ እንዲጨልም ያደረገው የስደት ፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት ነው። ፓርላማ አለመግባት፣ አዲስ አበባን አለመረከብ የማንም ሳይሆን የዳያስፖራው ፍላጎት ነበር። እዚህ ሆነው የአገር ቤት ታጋዮችን እጅ ለመጠምዘዝ የሚዳዳቸው ፖለቲከኞች ለትግሉ ቁርጠኛ ሊሆኑ ቀርቶ የኢትዮጵያን ዜግነት ይዘው ለመቆየት እንኳን ወኔ የላቸውም። ከ‹‹ግንቦት 7›› የሥራ አስፈጻሚ አባላት መካከል 80 ከመቶ የሚሆኑት ዜግነታቸውን ቀይረዋል። እዚህ ሆነው ግን እርስ በርሳችን እንድንተላለቅ የሚያደርግ የእልቂት ነጋሪት ሌት ተቀን ይጎስማሉ። በሆነ አጋጣሚ አገር ቤት ቢገቡ እና አንድ ችግር ቢከሰት እንኳን የሚሸሹበት አገር ስላላቸው ያለ ምንም ችግር በቻርተር አይሮፕላን ይወጣሉ። ገና ለገና ‹‹ድጋፍ የሚሰጠን በውጭ ያለው ማኅበረሰብ ነው›› በሚል ጊዜያዊ ፈተና በአገር ቤት የሚደረገው ትግል የስደት ፖለቲካ መጠቀሚያ መሆን የለበትም። ‹‹ኢሕአዴግም ቢሆን በሩን ለድርድር ክፍት አድርጎ የፖሊሲ ማሻሻያ ሊያደርግ የሚችለው ከስደተኛቹ ፖለቲከኞች በሚመጣበት ጫና ነው›› የሚሉ የዋሆች ካሉ ተሳስተዋል። የአገር ቤት ፖለቲከኞች በሚያራርቃቸው ሳይሆን በሚያቀራርባቸው ጉዳይ ላይ ጊዜ ማጥፋት አለባቸው። ከፖለቲካዊ ፅንፍ እና ከመጠፋፋት ወጥተን የሰለጠነ ፖለቲካዊ ንግግር ወይም ውይይት ለማድረግ ዝግጁነቱ ሊኖር ይገባል። በዚህ መንገድ አገር በቀል የፖለቲካ ለውጥ/መሻሻል ቢመጣ ችግራችን እና ድህነታችንም አብሮ መፍትሄ ያገኛል።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከፖለቲካው ሜዳ ጠፍታለች በማለት ተስፋ በመቁረጥ የሚተቿት አሉ። በቅርብም ያስተዋልከው ነገር ስለሚኖር በዚህ ላይ ምን ትላለህ?
እንዳልከው የብርቱካንን ወቅታዊ አቋም በተገቢው ሁኔታ ያልተረዱ ሰዎች እዚህም ሲተቿት ይደመጣል። ምን ማድረግ ነበረባት? እዚህ እንደመጣች እዚህ ያሉ ተቃዋሚዎችን መቀላቀል ነበረባት? ይኼ ብርቱካንን እስከ ወዲያኛው ያጠፋታል እንጂ ወሳኝ ስፍራ ኖሯት እንድትወጣ አያደርጋትም። እሷም ያንን እንደማታደርግ ከመነሻው አዲስ አበባ ሆና ተናግራለች። የአንዳንዶቹ ምክንያት ‹‹ድምፅዋን አጠፋች›› የሚል ነው። ይህም ቢሆን ከፖለቲካ መውጣቷን የሚያረጋግጥ አይደለም። እዚህ እንደመጣች ‹‹የዴሞክራሲ ፌሎው›› ሆና የተቀላቀለችው ‹‹National Endowment for Democracy›› የተባለ ትልቅ ዓለም አቀፍ ተቋምን ነው። በዚህ ተቋም ለአንድ ዓመት ያህል ቆይታለች። ከአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ፖሊሲ አስፈጻሚዎች፣ የተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የምርምር ተቋማት ኃላፊዎች፣ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ እውቅ የለውጥ አራማጆች፣ አንግ ሳን ሱቺን ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ታጋዮች፤ ከታወቁ የፖለቲካ አቀንቃኞች ጋር የልምድ ልውውጥ ስታደርግ እና ዕውቀት ስትቀስም ነበር።
ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዴት እንደሚገነቡ፣ በበለጸጉ አገራት ስላሉ የሲቪክ ድርጅቶች ሚናና ስለ ሰላማዊ ትግል መሠረታዊ አካሄድ በተለያዩ የ‹‹ቲንክ ታንክ›› መድረኮች እየተገኘች ልምዷን ስታካፍልና ልምድ ስትቀስም ነው የቆየችው፡፡ ይሄ በብርቱካን ደረጃ ላለ ወጣት ፖለቲከኛና በአገራችን ላለው ያልተቀናጀ የሰላማዊ ትግል አካሄድ ወሳኝ ይመስለኛል። እንዲህ ዓይነቱ ልምድ ለወደፊቱ የፖለቲካ ሕይወቷ ቀላል ልምድ አይደለም። ማንም በእሷ የእውቅና ደረጃ ላይ ያለ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅት መሪ ይህ ዓይነቱን ልምድ የመቅሰም አጋጣሚ አግኝቷል ብዬ አላስብም። በቅርቡ የሚጠናቀቀው የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የአንድ ዓመት ቆይታዋም የዚህ አንድ አካል ነው። በቀጣይ ደግሞ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሜሪላንድ ትምህርቷ ይቀጥላል።
እንግዲህ ‹‹ከፖለቲካ አልወጣም፤ ብርቱካን ከፖለቲካ ትወጣለች የሚባለው አባባል ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፤ ለሦስት ወይም ለአራት ዓመታት ያህል ግን አቅሜን በእውቀት መገንባት እፈልጋለሁ›› ብላ የመጨረሻውን ጋዜጣዊ መግለጫ ለሚዲያዎች ሰጥታ ከአገር የወጣችው ብርቱካን ጊዜዋን በዚህ መልኩ እየተጠቀመችበት ነው። ታዲያ በአንድ ዓመት ውስጥ የትኛውን ቃሏን አጥፋ ነው ተወቃሽ የምትሆነው?
ብርቱካን የ‹‹ከሰረች ፖለቲከኛ›› ማለት አይቻልም?
አይቻልም፤ ቃሉም አይገልጻትም። እንዲህ የሚሏትን ሰዎች አስተያየት አከብራለሁ። በእኔ እምነት ብርቱካን ማድረግ የሚገባትን እያደረገች ነው ብዬ አምናለሁ። በእርግጠኝነት ይህን ፕሮግራሟን አጠናቃ በዚህ ልምዷ ወደ ፖለቲካ ስትመለስ የተቃውሞ ፖለቲካውን ትግል አንድ ደረጃ ከፍ ታደርገዋለች የሚል ተስፋ አለኝ።
አውራምባ ታይምስ ስትጀመር ‹‹ዝክረ- ቃሊቲ›› በሚል አምድ ስር የ21 ወራት የእስር ቤት ቆይታህን በተከታታይ ትጽፍ ነበር። በኋላም ተቋረጠ። ጽሑፉ ቢቀጥል ኖሮ ‹‹እጽፈው ነበር›› የምትለውን የ‹‹ቃሊቲ›› አጋጣሚ ልትነግረኝ ትችላለህ?
አብረውን የታሰሩ አራት ያህል የአዕምሮ በሽተኞች ነበሩ። የእነዚህ ምስኪኖች ታሪክ አንባቢ ጋር ባለመድረሱ ሁሌም ይከነክነኛል። እነዚህ የአዕምሮ በሽተኞች ሁሉም የየራሳቸው የሆነ ባህሪ ነበራቸው። አንዱ ደስታ ይባላል። ደስታ መንገድ ላይ ህጻን ልጅ በመግደል ወንጀል ተፈርዶበት የመጣ ነው። ነገር ግን የአዕምሮ በሽተኛ መሆኑ ከአማኑኤል ሆስፒታል ቢረጋገጥም የሚረከበው ቤተሰብ በመጥፋቱ ነው እኛ ጋር እንዲቆይ የተደረገው። ደስታ ማለት ቡና እና ሲጋራ ከገዛህለት የማያጫውትህ ታሪክ የለም። በእሱ እምነት ለእስር የበቃው ሰው በመግደሉ ሳይሆን የተባበሩት መንግሥታት ከሱዳን መንግሥት ጋር ተመሳጥሮ እዚህ እንዲቆይ ስላደረገው እና የኢትዮጵያ መንግሥትም ‹‹ከሱዳን ጋር ምን አጨቃጨቀኝ›› ብሎ ዝም እንዳለው ደጋግሞ ይናገራል። ሌላው እስረኛ ደግሞ አባስ ይባላል። አባስ ሁሌም አድመኛ ነው። በስጦታ መልክ የሚሰጡትን ሱሪዎች እየቆረጠ ወደ ቁምጣነት ካልቀየራቸው በስተቀር የሚሰጠውን የሰው ልብስ አይለብስም። አንድ ጊዜ የእስረኛ አስተዳደሩ በእርዳታ ከተገኙ አልባሳት መካከል አንዱን ሱሪ አንስቶ ለአባስ ይሰጠዋል። እንዳይቆርጠው ጥብቅ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው አድመኛው አባስ አማራጭ ሲያጣ የተሰጠውን ሱሪ ገልብጦ ለበሰው። አባስ ‹‹ለምን እንዲህ ያደርጋል›› ብዬ ሰዎችን ስጠይቅ የፖለቲካ እስረኛ በመሆኑ ምክንያት ያዳበረው እልህና ‹‹አልሸነፍ ባይነት›› በዚህ መልኩ እንደሚገልጸው አጫወቱኝ።
አባስ የታሰረው በ1993 ዓ.ም የፒያሳው አንበሳ ጫማ ሲዘረፍ ነው። ከጓደኞቹ እንደሰማሁት፤ ፒያሳ አካባቢ በሊስትሮነት ሲተዳደር የነበረው አባስ አንድ ደንበኛው ጫማውን አስጠርጎ ሲያበቃ እዛው እንደተቀመጠ የግራ እግር ጫማውን አውልቆ ‹‹ስፋልኝ›› በማለት ለአባስ ይሰጠዋል። አባስ ተቀብሎ ጫማውን እየሰፋ እያለ አካባቢው ቀውጢ ይሆናል። ደንበኛ ሆዬ የግራ እግር ጫማውን አባስ ጋር ትቶ እግሬ አውጪኝ ይላል። በአካባቢው የደረሱ ፖሊሶች ግን በአባስ እጅ ላይ ያለው አንድ እግር ጫማ በቸልታ አልተመለከቱትም። ‹‹ከአንበሳ ጫማ የተዘረፈ ነው›› በማለት አባስን በአመጽ እና ሁከት ማነሳሳት ወህኒ ቤት ይጨምሩታል… እንዲህ እንዲህ አይነት ብዙ አሳዛኝ ታሪኮች ነበሩ።
ጋዜጠኛ ዘጋቢ፣ ፀሐፊ እና ታዛቢ ብቻ ሳይሆን አንባቢ መሆንም የግድ ይገባዋል። የሚያነብ ጋዜጠኛ ደግሞ ዕይታው ሰፍቶ ነገሮችን በጥልቀት የመጻፍ አቅምን ያዳብራል። ዳዊት አንባቢ ነህ? የንባብ ልምድህ ምን ይመስላል?
የማንበብ ልምድ የሌለው ጋዜጠኛ መጀመሪያውኑ ጋዜጠኛም መሆን አይችልም። የሚጻፍም ነገር አይኖረውም። እኛ አገር እንደምታወቀው የውጭ መጽሐፎችን ለማግኘት ያለው ችግር ራሱ በጣም ከባድ ነው። ቡክ ወርልድ እና የኤድናሞሉ ስቶር ብቻ ነው ወቅታዊ መጽሐፎችን የሚያቀርበው። እነሱም በበቂ ሁኔታ አያቀርቡም። ለምሳሌ፣ አዲስ አበባ በነበርኩበት ጊዜ የኖአም ቾምስኪይ፣ የጆን ግሪሻምና የታሪቅ ዓሊ መጽሐፎችን በነዚህ ስቶሮች ውስጥ ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም ነበር። ወደ ጥያቄህ ስመለስ፣ እንኳንና እኛን ቀርቶ ዘመናቸውን በሙሉ በንባብ ያሳለፉ ሰዎች ብዙ ባነበቡ ቁጥር ብዙ ያላነበቡት ነገር እንዳለ ነው እየተገነዘቡ የሚሄዱት። በተለይ ለማንበብ ደግሞ ጊዜ በጣም ወሳኝ ነው። እስር ቤት በነበርኩበት ጊዜ የነበረኝ ጊዜ እና አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ እየሰራሁ እያለ የነበረኝ ጊዜ እኩል ሊሆን አይችልም። የጋዜጠኝነትን ስራ እየሰራህ መጽሐፎችን በበቂ ሁኔታ ለማንበብ ጊዜ ባይኖርህ እንኳን ሳታስበው ከንባብ ጋር ያለህ ቁርኝት እንዳለ ይሆናል። ለምሳሌ፣ በሣምንት ውስጥ አንድ የሀተታ (ፊቸር) ጽሑፍ ለመስራት የሚያስፈልጉህን ግብአቶች ለመሰብሰብ ብቻ ብዙ ነገሮችን ታነባለህ፤ ታገላብጣለህ። የትርጉም ሥራዎችን ለመሥራት የምታነባቸው ጽሑፎች ዞሮ ዞሮ ውስጥሀ እየቀሩ ይሄዳሉ። አውራምባ ታይምስ ውስጥ የሳምንቱ ሥራችንን ጨርሰን ቅዳሜ እና እሁድ የሚኖረን የእረፍት ጊዜ በራሳችን እና በሌሎች ጋዜጦች ላይ የተዘገቡ ጽሑፎችን ከማንበብ ባሻገር የሚተርፈንን ጊዜ መጽሐፍ በማንበብ እናውለዋለን። የጋዜጣ ሥራ በበቂ ሁኔታ ለማንበብ አዳጋች መሆኑ ጥርጥር የለውም። ከተሰደድኩ በኋላ ያለኝን ጊዜ ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው እጅግ በተሻለ ሁኔታ (የመጽሐፍ አማራጭ እዚህ ያለገደብ ስለሚገኝ) ለንባብ እየሰጠሁ ነው። እንደዛም ሆኖ ግን ‹‹አንባቢ ነኝ›› ብዬ በድፍረት ለመናገር ይከብደኛል።
ቃሊቲ እያለህ የነበረው የንባብ ል ምድ ምን ይመስል ነበር?
አሳሪዎችህ እስርቤት ሲያስገቡህ ዋናው አላማ እንድትጎዳ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ አሳሪዎችህ የማያስተውሉት አንድ እድል ግን አለህ። እሱም ከሌላው ጊዜ (ባትታሰር ኖሮ ከሚኖርህ ሁኔታ) የበለጠና የተትረፈረፈ ጊዜ ታገኛለህ። አንተ ብልጥ ከሆንክ ግን ሁኔታውን ለራስህ በሚጠቅም መልኩ ተጠቅመህበት የተሻልክ ሰው ሆነህ መወጣት ትችላለህ። ከተለያየ ቤተሰብ ወዳጅና ዘመድ ለእስረኛ የቅንጅት አመራሮችና ጋዜጠኞች የተለያዩ መጽሐፍቶች ይገቡ ነበር። በተለይ ከሌላው እጅግ በተሻለ ሁኔታ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ጋር ብዙ መጽሐፎች ተከማችተው ነበር። ከማዕከላዊ ወደ ቃሊቲ ስንዘዋወር ዶ/ር ብርሀኑ አንድ ሀሳብ አቀረበ። ‹‹ሁላችንም ጋር ያሉ መጽሐፎች ተሰብስበው በኃላፊነት አንድ ሰው ጋር ይቀመጡ፤ ከዚያ ማንበብ የሚፈልግ ሰው ስሙንና የመጽሐፉን ርዕስ እያስመዘገበ ወስዶ ያንብብ›› የሚል ነበር። በዚህ መልኩ በመቶዎች የሚቆጠሩ በርካታ መጽሐፎች ተሰባሰቡ። በዚህ ፋይል የተከሰስን ሰዎች በየቀኑ የላይብረሪ ሰዓት መድበን ማንበብ ጀመርን። ከመጽሐፎቹ በተጨማሪ ወቅታዊ የሚዲያ ውጤቶችን (ኒውስ ዊክ፣ ዘ-ኢኮኖሚስትና ታይምን የመሳሰሉ) በስፋት የማግኘት እድል ነበረን። ይህ እንግዲህ የእስር ቤቱ ላይብረሪ ከሚያቀርበው የመጽሐፍ አቅርቦት በተጨማሪ ነበር። ይህ ሁኔታ በአንድ ዞን ውስጥ ለነበርነው አምስት ጋዜጠኞች እና 14 የቅንጅት አመራሮች ቀላል አማራጭ አልነበረም።
ስለታሰርክ ትጎዳለህ ብቻ ማለት አይደለም። እስር ከራስህ ጋር ይበልጥ እንድትቀራረብ ያደርግሃል። ውጪ ብትሆን ግን ጊዜህን በመዝናናት ልታጠፋው ትችላለህ። እስር ቤት ለንባብ ይጠቅማል። ቃሊቲ ውብሸትን ለመጠየቅ የሄድን ጊዜ የምንልክለትን መጽሐፍ በሚፈልገው መጠን እንዳይገባለት ማረሚያ ቤቱ የተለያየ ሰበብ እየፈጠረ ሲከለክለው እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህ ትልቅ ችግር ነው። ከስቪል መብቶች መታገድ ሲባል አንዳንድ ኃላፊዎች ይህንንም የሚጨምር ይመስላቸዋል መሰለኝ። በተለይ በዚያን ጊዜ ስለ እስክንድር የማስታውሰው ነገር ልንገርህ። ሰዎች ‹‹ምን እናምጣልህ›› ሲሉት ሁሌም ምርጫው የነበረው ‹‹ዘ-ኒውዮርከር›› የተሰኘው ታዋቂው የኒውዮርክ ጋዜጣ ነበር። ሁል ጊዜም የእስክንድር ምርጫ እሱ ነበር። በነገራችን ላይ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ እኔና የሲፒጄው መሐመድ ኬይታ ለ‹‹ዘ-ኒውዮርከር›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሁኔታውን ከገለጽንለት በኋላ በጣም ተደስቶ በቋሚነት ጋዜጦቹ እንዲላኩለት ሁኔታውን አመቻችቷል።
አስገራሚ የማስታወስ ችሎታ እንዳለህ አውቃለሁ። ከረዥም ዓመታት በፊት የተጻፈ ጽሑፍ ረዥም ዐረፍተ ነገርና እና የሥርዓተ ነጥብ ግድፈትን ሁሉ አስታውሰህ በፍጥነት ትገልጻለህ። ይኼ በተፈጥሮ ያገኘኽው ወይስ በልምድ ያዳበርከው? በሌላ በኩል ደግሞ ትችት ሲሰነዘርብህ ስሜታዊነት የታከለበት ፈጣን ምላሽ እንደምትሰጥ ይነገራል። ስሜታዊ ነህ ማለት ይቻላል።
እንግዲህ እንዳንተ ዓይነት አብሮኝ ብዙ ዓመት የሠራ ሰው ስለ እኔ ባህሪ (ስሜታዊ መሆንና አለመሆን) መናገር ይችላል። እንደ ማንኛውም ሰው ጥቃትን አሜን ብዬ አልቀበልም። እንደምታስታውሰው፣ እዚያ እያለ ሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የሚጻፉ ጽሑፎች በጣም ስ ሜታዊ እንድንሆን ያደርጉን ነበር። በአዲስ ዘመን፣ ገጽ 3 ላይ እንደዚያ የዘለፉን ሰዎች ነገ በሆነ አጋጣሚ ወደ አሜሪካ ሲመጡም ሁለት አማራጭ ብቻ የሚያቀርቡልን አምባገነኖች እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። እንዲህ ዓይነቶቹ የራሳቸው መርሕ የሌላቸው፣ ይሉኝታ ቢሶች ለፖለቲካ ትርፍ ሲሉ የሚደፈጥጡት መሠረታዊ የሰው ልጅ ነጻነት ስሜታዊ እንደሚያደርግ አያጠራጥርም። የማስታወስ ችሎታ ላልከው ተፈጥሯዊ ነው፡፡
ስለ ነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
እኔም ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>