እስላሚክ ስቴት የሱኒ ካሊፌት ግዛት ለመፍጠርና ለማስፋፋት በሚል ብዥታ በክርሲቲያኖችና ሱኒ ባልሆኑ የእስልምና ተከታዮች ላይ በፈጸመው አስቃቂ ግድያና ከኑሮአቸው የማፈናቀልና እንዲሰደዱ የማድረግ አረመናዊ ተግባሩ በጣም ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቶናል። ኮፕቲክ ክርስቲያኖችን እያሳደደ በሚገድልበት ሰሞን፤ 30 የሚሆኑ ወገኖቻችን ወደ አውሮፓ ሥራ ፍለጋ ለመሸጋገር ሊቢያ እንዳሉ “የጠላታችን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አባሎች” በማለት ገሚሱን አንገታችውን በጎራዴ በማረድ ሌሎቹን በጥይት በመምታት በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎአቸዋል። ለሥራ ፍለጋ ሲሉ ከአደገኛ የባህርና የምድረ-በዳ ጉዞ ተርፈው በየመን ባህር ዳርና፤ በረሃ፤በተባበሩት መንግሥታት ጣቢያዎች የተጠለሉ ወገኖቻችን በሀገሪቱ ወሮበሎችና ዘራፊዎች፤በሕገ ወጥ መንገድ ስዎችን ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር በከፍተኛ ገንዝብ በማስተላሰፍ የሚነግዱ እንደዚሁም በሳውዲ አውሮፕላኖች ቦምብ እየተደበደቡ የሚያልቁት ኢትዮጵያኖች ሕይወት በከንቱ ማለፉ የማይጠፋ እሳት በልባችን ጭሮብናል።
በደቡብ አፍሪካ ዘርፎ-በሎች አማካኝነት በወገኖቻችን ላይ ስለሚደርስው ግፍ በተከታታይ በዜና ማስራጫዎች እንደምንሰማው ፤ በእሳት አቃጥሎ የመግደልና አይን ያወጣ ዘረፋ አስቆጥቶናል፤ አሳዝኖናል። የሀገራቸውን አምባገነን መንግሥት ሲሸሹ የተሳፈሩበት ጀልባ በመስመጡ በየጊዜው ህይወታቸው የሚያልፈው ኢትዮጵያውያኖች፤ ሌሎች አፍሪካውያንና በየመን በረሃ የስውነታቸውን አካል ለሕክምና ጥቅም ለማዋል ሲባል በየጊዜው የሚገደሉት ወገኖች ሰቆቃ እጅግ በጣም አስቆጥቶናል። በእነኝህ አረመኔአዊ ወንጀሎች እኚስ በወጣት ወገኖቻችን ላይ ከሚደርሱት በይፋ ከሚታወቁት ወንጀሎች በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ በሳውዲ አረቢያ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የተባረሩበት፤ሴቶች በጉልበት የተደፈሩበት፤ ንብረታቸው የተዘረፈበት፤ በቤይሩትና በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገሮች በሚደርስባቸው አሰቃቂ ግፍ የተነሳ ወገኖቻችን ሀይወታቸውን ለማጥፋት የተገደዱበት ይገኙበታል።
የዚህ ሁሉ ችግር መንሣኤና ምንጩ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ መታወቅ አለበት። የቀይ ሽብር ከተካሄደበት እ ኤ አቆጣጠር እስከ 1970ው አጋማሽ ድረስ ኢትዮጵያ በስደተኞች ቁጥር አንጻር ዝቅተኛ ደረጃውን የያዘችና ወደ ሀገራቸው በሚመለሱት ከፍተኛ ደረጃውን የያዘች ነበረች። ከ 1970 ዓ ም ጀምሮ በሀገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች አለመከበርና የግፍ አገዛዝ እንደዚሁም በከፍተኛ የሥራ እጦት ምክንያት ወጣቱ ህይወቱን ለአደጋ እያጋለጠ በገፍ ሀገር ለቆ ለመኮብለል ተገዶአል። የቤተስብ ችግር ያስጨነቃቸው ወጣቶችና በስደተኞች በሚላክ የሚተዳደሩት ሁለቱ ፓራሳይት፤ ግዴለሽና አምባገነን መንግሥታት ምክንያት የኢትዮጵያና የኤርትራ ወጣቶች የሚገጥማቸውን አደጋ ቢያውቁም እንኽዋን አደገኛውን የቀይ ባህር አቋርጠው መሰደዱን እንደሚመርጡ በግብር አሳይተዋል።
ይበልጥ የሚያሳዝነው የኢሐደግ መንግሥትና ኢምባሲዎቹ ከዜጎቹ ጋር ከመወገን ይልቅ የተፈጸመውን ግፍ አጣጥሎ “ስደተኞቹ ሕገ ወጦች ናቸው” በማለት ከአንድ መንግሥት የማይጠበቅ ተግባር መፈጸሙ ነው። በሊቢያ የተስውቱን ወገኖች አስመልክቶ የዓለም ህዝብ በተለያዩ የሜድያ አውታሮች ኢትዮጵያዊነታቸውን እየገለጹና የሞዋች ቤተስቦች እያሉ የኢሐደግ መንግሥት “ሞአቾቹ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን እያጣራሁ ነው” በማለት በሕዝባችን ላይ ሲያላግጥ መክረሙ ነበር።
ማናቸውም በራሱ የሚተማመን መንግሥት ዜጎቹ በአሰቃቂና በግፍ ሲገደሉ በይፋ የሚታየውን ሁኔታ እያጣራሁ ነው በማለት በሕዝብ መራራ ሀዘን ላይ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻና ማላገጥ አያደርግም ነበር፤በሀገሪቱ በይፋ ተስፋፍቶ የሚገኘውን ሥራ አጥነት ችግር ፈጽሞ እንደሌለ ለማስመል አይሞክርም ነበር። ከስሞኑ የወገኖቻንን የግፍ ግድያ አስመልክቶ በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች የሚደረጉ ስላማዊ ስልፎችን ተክትሎ የተሳተፉትን ወገኖች በአገዛዙ ላይ ተቃውሞ ተናገራችሁ በማለት ክፉኛ በመደብደብና በማቁሰል ሕዝባችንን በማስቃየት ላይ ይገኛል። ረብሻ ያስነሳሉ በሚል ክስም በአሁኑ ወቅት ከ 500 በላይ የሆኑ ወጣቶች በሰማያዊ ፓርቲ ስም ታፍሰው ገሚሱም ከየቤታቸው ተለቅመው ታሥረዎል።
ስለሆነም “ኢትዮጵያዊነት፤ የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጉባኤ” ጥሪውን ለወገኖቹና ለዓለም ሕብረተሰብ እንደሚከተለው ያቀርባል:-
- የኢትዮጵያ መንግሥት በአልባሌ ምክንያት ከሀላፊነቱ ለመሽሽ መሞከሩ እንደማይጠቅመው ተገንዝቦ፤ ወገን ሳይለይ የዜጎችን መብት በማክበር የሚጠብቅበትን ግዴታና ሀላፊነት እንዲወጣ፤ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሁንም ለሚደርስባቸው ግፍና በደል አስፈላጊውን የመከላከያ እርምጃ እንዲወስድ እናሳስባለን። ለአደጋ ተጋልጠው ለሚገኙ ወገኖችም ተፈላጊውንና ተገቢውን አስቸክዋያ እርዳታ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።
- ድምጻቸውን በአደባባይ በማሰማታቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ አለአግባብ ያሰራቸውን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የፓለቲካና የሕሊና እሥረኞች በአስቸኽዋይ እንዲፈታ እንጠይቃለን። በሕገ መንግሥቱ የተፈቀዱ የሰብዓዊ መብቶችን ማፈኑንና መርገጡን በአስቸክዋይ እንዲያቆም እንጠይቃለን።
- የሳውዲ አረብያ፤የሊቢያ፤የየመንና የደቡብ አፍሪካ መንግሥታት ዓለም አቀፍ ስደቶኞች መብትና ሕግጋት ዉሎች መሰረት ሀላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ስለሆነም በሀገራቸው ውስጥ በወገኖቻችን ላይ ለተፈጸመው ወንጀል በሙሉ ለጠፋው ሕይወትና ንብረት ለቤተስቦቻቸው ካሣ ለመክፈል ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን።
- የአውሮፓ ህብረትና የአሜሪካ መንግሥት በእነዚህ ሀገሮች (አፍጋንስታን፤ሊቢያ፤ ሶማሊያ፤ሲሪያና የመን) ላይ በሚከተሉት የሞናጋት ፖሊሲና በሚወስዱት እርምጃ ሳቢይ የስደተኞች ቁጥር እየናረ መሄዱን የሚያውቁት ሲሆን ለተፈጠረው ችግር መፍትሄውን መጋራት ይኖርባቸዋለን እንላለን። የጥቅም-መር ፓሊሲያቸውን ለማራመድ ሲሉም በተለይም ሕዝብ ካልመረጣቸውና ካልተቀበላችው አምባገነን መንግሥታት ጋር በማበር የሚፈጽሙት ተግባር ችግሩን የበለጠ አስከፊ እንዳደረገው ተገንዝበው ኅላፊነቱን መጋራት ይኖርባቸዋል። ኅያላን መንግሥታት የውች ጉዳይ ፓሊሲዎቻቸው ስለባ የሆኑትን በስብዓዊ ርኅራሄ እንዲታደጉና ችግሩን ከማፈን እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን። እንዲሁም፣
- የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን የስደተኞች መብት በማስከበርና ከአደጋ በመከላከል የጦርነት ቀጠና ከሆኑት ከሊቢያና ከየመን ወደ ሰላማዊ ቦታ በአስቸክዋይ በማዛወር ዓለም አቀፋዊ ግዴታውን በብቃት እንዲወጣ አጥብቀን እንጠይቃለን።
በመጨረሻም ሀላፊነቱ በመላው ዓለም በምንኖር ኢትዮጵያኖችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ላይ የተጣለ ስልሆነ፡ ይኅውም የስብዓዊ መብት ረገጣውን በመቅዋቃም የተጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክረን በመቀጥል፤ እንደዚሁም አስፈላጊ ድጋፍና እርዳታ ለተጎጅዎቹ በአስቸክዋይ በማድረስ፤ በዚህ አክዋያ በየጊዜው ለሚፈጠሩ ሁኔታውችን ተከታትሎ ለዓለም ህብረተሰቡ በማሳወቅና በማጋለጥ የወገኖቻችንና የውድ ሀገራችንን ችግር መታደግ ግዴታችንና ሀላፊነታችን እንደሆነ ለማስገንዘብ እንወዳለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም በልጽጋና ተከብራ ትኖራለች!
ኢትዮጵያዊነት፤ የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጉባኤ
www.ethiopiawin.com
The post በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው የግፍ ግድያ ተናደናል፣ አዝነናል፣ተቆጥተናልም! appeared first on Zehabesha Amharic.