በአፋችን ውስጥ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች አሉ። እነዚህ ባክቴሪያዎች ንፅህናው በተጠበቀ አፍ ውስጥ ከሆነ የሚገኙት ምንም አይነት ጉዳት ሳያደርሱ ተስማምተው የሚኖሩ ሲሆን፤ ንፅህናው ካልተጠበቀ ግን አፋችን ውስጥ በሚገኙ አካሎቻችን ላይ ችግር ከመፍጠርም አልፈው ለመጥፎ የአፍ ጠረን ያጋልጡናል። መጥፎ የአፍ ጠረን ደግሞ በማኅበራዊ እና ስነልቦናዊ መንገድ ህይወታችንን ከማስተጓጐልም አልፎ ህይወትን ለሚነጥቅ ችግር ሊዳርገን ይችላል። በዚህ መጥፎ የአፍ ጠረን እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ትምህርት ቤት መምህር ከሆኑት ዶክተር ሔኖክ ገዛኸኝ ጋር ቆይታ ሰንደቅ አድርገል።
ሰንደቅ፡- ለመጥፎ የአፍ ጠረን የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። በሕክምናው ረገድ በትክክል እነዚሁ ናቸው ተብለው የሚቀመጡት መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
ዶ/ር ሔኖክ፡- ለዚህ መጥፎ የአፍ ጠረን ወይም በህክምናው ሀሊቶሲስ (Halitosis) ለሚባለው ችግር በርካታ ምክንያቶች አሉ። እነዚህን ምክንያቶች በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን። አንደኛው በአፍ ውስጥ የሚፈጠር ምክንያት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የውስጥ ህመሞች ሊሆን ይችላል። በአብዛኛው ግን ለዚህ ችግር ምክንያት የሚሆነው በአፍ ውስጥ ያለው ችግር ነው። ጥርሳችን ላይ ወይም ምላሳችን ላይ የሚኖር ቆሻሻ ወይም ፈንገስ፣ የጥርስ መቦርቦር እና ቆሻሻ መያዝ በአፍ ውስጥ የሚፈጠሩ የመጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤዎች ናቸው። በተጨማሪም በጥርሳችን እና በድዳችን መካከል የሚኖረው ክፍተት የሰፋ ከሆነ በርካታ ባክቴሪያዎች በዚያ ቦታ ላይ በመፈጠር ለዚህ ለመጥፎ የአፍ ጠረን ያጋልጡናል።
የውስጥ ህመም ወይም ሲስተሚክ ዲዝስ የምንላቸው ደግሞ አንዱ ከጭንቀት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ሊሆን ይችላል። እንዲሁም የመድማት ችግር ያለባቸው (Hemophilic) የሆኑ ሰዎች መጥፎ የአፍ ጠረን ይኖራቸዋል። በተጨማሪም የስኳር ህመም፣ የጨጓራ ህመም ወይም የአንጀት ችግር እና የማስመለስ ችግር ያለባቸው ሰዎች ለዚህ ችግር የተጋለጡ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በምራቅ አመንጪ ዕጢዎች ላይ የሚከሰት በሽታ ለዚሁ ችግር መንስኤ ሊሆን ይችላል። እነዚህ በምራቅ አመንጪ ዕጢ ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች በአፍ ውስጥ የምራቅ መመንጨት አቅምን በመቀነስ አፍ እንዲደርቅ ያደርጉታል። በዚህም ሳቢያ መጥፎ የአፍ ጠረን ሊከሰት ይችላል።
ሰንደቅ፡-በአብዛኛው መጥፎ የአፍ ጠረን በሰዎች ላይ የሚስተዋለው ጠዋት ላይ ነው። ምናልባት መጥፎ የአፍ ጠረን የተለያዩ አይነቶች ይኖሩት ይሆን?
ዶ/ር ሔኖክ፡- የአፍ ጠረን በሁለት የሚከፈል ነው። አንደኛው ጠዋት ላይ የሚሸት የአፍ ጠረን (Morning Bad Breath) እንዲሁም ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች የሚፈጠር መጥፎ የአፍ ጠረን ናቸው። ጠዋት ላይ የሚፈጠር መጥፎ የአፍ ጠረን በማንኛውም ሰው ላይ የሚከሰት ነው። በአፋችን ውስጥ የሚገኙት ምራቅ አመንጪ ዕጢዎች በሽታ እንኳን ባይኖርባቸው ምሽት ላይ እንደ ቀኑ ብዙ ምራቅ ማመንጨት አይችሉም። በዚሁም ሳቢያ የአፍ መድረቅ ስለሚከሰት ጠዋት ላይ መጥፎ የአፍ ጠረን ይፈጠራል። ሁለተኛው ግን ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የሚከሰት ነው።
ሰንደቅ፡- የምንመገባቸው የተለያዩ የምግብ አይነቶች ለምሳሌ ነጭ ሽንኩርትን የመሳሰሉት ለመጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤ ይሆናሉ የሚል አመለካከት አለ። ይኔ ነገር ምን ያህል የተረጋገጠ ነው?
ዶ/ር ሔኖክ፡- ልክ ነው። ነጭ ሽንኩርት ብቻም ሳይሆን የተለያዩ ከፍተኛ የቅመም መጠን ያለባቸው ምግቦችን የምናዘወትር ከሆነ መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያመጡ ይችላሉ። እነዚህን ምግቦች በከፍተኛ መጠን የምንመገብ ከሆነ ወደ ደም ዝውውር ስርዓት ውስጥ ስለሚገባ የአፋችንን ጠረን ወደ መጥፎነት የመቀየር አቅም አለው። እነዚህ ነገሮች ከተዘወተሩ ከጊዜያዊ ሽታ አልፈው ቋሚ መጥፎ የአፍ ጠረን ያመጣሉ። በዚህ በኩል በእስያ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ከፍተኛ ቅመም ያለባቸው ምግቦችን ስለሚጠቀሙ ተጠቃሾች ናቸው።
ሰንደቅ፡- ብዙዎች ዘመናዊ የጥርስ ሳሙናዎች ተጠቅመን ስናቋርጥ ለመጥፎ የአፍ ጠረን ተጋለጥን ሲሉ ይሰማሉና ምን ያህል እውነት ነው?
ዶ/ር ሔኖክ፡- እንደዚህ አይነት ነገሮች ብዙ ጊዜ ይነገራሉ። ተጠቅሜ የማቋርጥ ከሆነ የአፍ ጠረኔን ሊለውጥብኝ ስለሚችል አልጠቀምም የሚሉ አሉ። በመሠረቱ እነዚህን የጥርስ ሳሙናዎች መጠቀም ግዴታ ነው። ጀምሮ ማቋረጥም አያስፈልግም። እነዚህ የጥርስ ሳሙናዎች አገልግሎታቸው ማፅዳት ብቻ አይደለም። የጥርስ ሳሙናም ሆነ የእንጨት መፋቂያ ጥርስን ያፀዳሉ። በእንጨት ሲፋቅ የጥርስን የውጪውን ክፍል ሊጐዳው ይችላል። የጥርስ ሳሙና ግን ከማፅዳትም በላይ በርካታ ንጥረ ነገሮች አሉት። እነዚህ ንጥረ ነገሮች የጥርስን ጥንካሬ የሚጠብቁ እና ቀለሙን እንደጠበቀ እንዲቆይ የሚያደርጉ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ፍሎራይድ የሚባል ንጥረ ነገር ስላለው ጥርሳችን የፍሎራይድ እጥረት ተፈጥሮበት እንዳይበልዝ ያደርገዋል። ስለዚህ ጥርስን በተከታታይ ማፅዳት ግዴታ ነው።
ባይቋረጥ የሚባለው ነገር መታሰብ የለበትም። ልብሳችንን የምናጥብ ከሆነ ማጠቡን ስናቋርጥ ልብሱ ይቆሽሻል። ልክ እንደዚያው ጥርስን ማፅዳት ማቆሙ ችግሩን ሊያመጣው ይችላል እንጂ ችግሩ የሳሙናው አይደለም። ከጥቅሙም አንፃር በሳሙናው የማፅዳት ተግባሩ መቋረጥ የለበትም።
ሰንደቅ፡- ብዙ ጊዜ መጥፎ የአፍ ጠረንን በአዋቂነት እድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ነው የምናያይዘው። በህፃናት ላይስ የመታየት እድሉ ምን ያህል ነው?
ዶ/ር ሔኖክ፡- ህፃናት ከእድሜ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ የአፍ ችግሮች ገና ናቸው። ህፃናት አፋቸውን ለረጅም ጊዜ ስላልተጠቀሙበት ከጥርስ መቦርቦር ጋር ተያይዞ ለሚመጣው የአፍ ጠረን አይጋለጡም። እነዚህ ነገሮች ሊረዷቸው ይችላሉ። ነገር ግን ከውስጥ ህመም ጋር የተያያዘ እና ከምራቅ አመንጪ ዕጢዎች ህመም ምክንያት የሚመጣው ችግር በእነርሱ ላይም ይከሰታል። ለምሳሌ የስኳር ህመም ከህፃንነት እድሜ ጀምሮ ስለሚከሰት ህፃናትም የችግሩ ተጠቂዎች ናቸው። ህፃናት በንፅህና ካልተያዙ ዞሮ ዞሮ ለችግሩ የመጋለጥ እድል አላቸው።
ሰንደቅ፡- መጥፎ የሆነ የአፍ ጠረን ከሰዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ላይ በተለያዩ መንገዶች አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ይሄ ችግር በወቅቱ መፍትሄ ካልተገኘለት የሚያመጣው የመጨረሻ ውጤት ምንድን ነው?
ዶ/ር ሔኖክ፡- መጥፎ የአፍ ጠረን በዋናነት በሰዎች ላይ ስነ-ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ተፅእኖዎችን ያስከትላል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች መጥፎ የአፍ ጠረን ይኑራቸው አይኑራቸው ላይገነዘቡት ይችላሉ። አፍ-ለአፍንጫ ቅርብ በመሆኑ ይሄ ነገር ሁልጊዜ ካለ የመለመድ ነገር ሊመጣ ይችላል። ነገር ግን ሌላ ሰው ሲያሳውቃቸው ከሰው ጋር ለማውራት መፍራት እና መራቅ ይመጣል። ይሄ ነገር ግንኙነትን ይጐዳዋል። ፍቅረኛሞች ወይም ባልና ሚስት ይሄንን ችግር መነጋገር በመተፋፈር እስከመለያየት የደረሱበት ጊዜ እንዳለ አውቃለሁ። ስለዚህ ግንኙነት ላይም ሆነ ስራ ላይ ከፍተኛ ችግር ያመጣል።
በአፍ ውስጥ በሚከሰት ችግር ምክንያት የሚመጣው መጥፎ የአፍ ጠረን ካንዲዲያሲስ የሚባለው ፈንገስ ነው። ይሄ ፈንገስ በአብዛኛው ምላስን እና የአፍን ወለል የሚያጠቃ ነው። በመሆኑም በወቅቱ ካልታከመ በምላስ እና በአፍ ላይ ጉዳት ያመጣል። በጥርስ ላይ የሚከማች ቆሻሻ በጊዜ የማይፀዳ ከሆነ ድድን የመብላት እና የጥርስን ስር የማጋለጥ ችግር ይፈጥራሉ። ከድድ ስር ከገባም ጥርስ እንዲበላ እና ኢንፌክሽን እንዲፈጠር ያደርገዋል። ይሄ ኢንፌክሽን ወደ አጥንት ከዘለቀ ደግሞ የላይኛውን እና የታችኛውን የጥርስ ደጋፊ አጥንት ያጠቃል። የላይኛው ጥርስ ቆሻሻ ተጠራቅሞበት የማይታከም ከሆነ የሳይነስ ህመም፣ የአጥንት ኢንፌክሽን እና የመሳሰሉትን ሊያመጣብን ይችላል። በዚህ መልኩ የሚመጡት ችግሮች ደግሞ ህይወትን እስከማጣት የሚያደርሱ ሊሆኑ ይችላሉ።
ሰንደቅ፡- ሰዎች መጥፎ የአፍ ጠረንን ለመከላከል የሚጠቀሙባቸው እንደማስቲካ ያሉ ዘዴዎች ይኖራሉ። በህክምናው ዘርፍ ያሉት መከላከያዎች ምንድን ናቸው?
ዶ/ር ሔኖክ፡- በቅድሚያ ይሄ መጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤው በአፍ ውስጥ በተፈጠረ ችግር ወይም በውስጥ ህመም ምክንያት መሆኑ መለየት አለበት። ጥሩ ነገሩ መጥፎ የአፍ ጠረን ወይም የአፍ ውስጥ ችግሮች ሲያጋጥሙ የአፍ ውስጥ ችግርን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተያያዥ ችግሮችንም ለመታየት ያግዛል። ችግሩ የኤች አይ ቪ ወይም የኩላሊት አሊያም ደግሞ የልብ ችግር መሆኑን በአፍ ውስጥ ምልክቶቻቸውን ማየት ይቻላል። በዚህ ህክምና ከአፍ ችግር አልፎ ሌሎች ችግሮችንም ለመለየት ጠቃሚ ነው። ዋናው ነገር ችግሩ እንደተከሰተ ወደ ህክምና መሄዱ አስፈላጊ ነው።
በአብዛኛው ይሄ መጥፎ የአፍ ጠረን የሚከሰተው በአፍ ውስጥ በሚከሰት ችግር ነው። ይሄ ችግር ደግሞ መንስኤው ብዙ ጊዜ የንፅህና ጉድለት ነው። ስለዚህ ጥርሳችንን እና ምላሳችንን ምግብ ከተመገብን በኋላ በመቦረሽ ማፅዳት ያስፈልጋል። ይሄ መሆን ካልቻለም ቢያንስ ጠዋትና ማታ ድድን እና ምላስን በማይጐዳ መልኩ መቦረሽ ያስፈልጋል። አፋችን ከፍተኛ የሆኑ ባክቴሪያዎች የሚገኙበት የሰውነት ክፍል ነው። ጥርስ ከተቦረሸ ከሁለት ደቂቃ በኋላ በአፋችን ውስጥ የሚኖረው ባክቴሪያ ቢጠና በአንዱ ጥርስ ላይ ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች ይገኛሉ።
በአፋችን ውስጥ ቢያንስ ከ500 ዓይነት በላይ ባክቴሪያዎች እያንዳንዳቸው ደግሞ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች አሉ። እነዚህ ባክቴያዎች አፋችንን በንፅህና ካልያዝን ወይም ለሌላ በሽታ ተጋልጠን የመከላከል አቅም የሚያንሰን ከሆነ ጉዳት ያደርሳሉ። ነገር ግን ጤናማ ከሆንን ተቻችለው ይኖራሉ እንጂ ወደ ማጥቃት አይገቡም። እነዚህ ባክቴሪያዎች አፋችንን በንፅህና ካልያዝን በአፋችን ውስጥ ያለውን ቆሻሻ እንደ ድንጋይ እንዲጋገር ያደርጉትና የድድ መቁሰልን ጭምር ሊያመጡብን ይችላሉ። የውስጥ ደዌ ችግር ከሌለ የአፍ ንፅህናን በመጠበቅ እነዚህን ችግሮች መከላከል ይቻላል።
ጊዜያዊ መከላከያዎችን በተመለከተ ማስቲካ በህክምናውም የሚበረታታ ነው። እንደ ማስቲካ ያሉ ነገሮችን በአፋችን ውስጥ የምናመላልስ ወይም የምናኝክ ከሆነ በአፋችን ውስጥ ምራቅ እንዲመነጭ ስለሚያደርግ ከአፍ መድረቅ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን መጥፎ የአፍ ጠረን መከላከል ይቻላል።
ህክምናውን ስንመለከት ችግሩ ከአፍ ውስጥ በሚፈጠር ምክንያት ከሆነ የሚከሰተው አፍን የማፅዳት እና ለፈንገሱም መድሐኒት የመስጠት ስራ ይሰራል። አፍ ከተፀዳ በኋላም ድድ እንዲጠነክር የማድረግ ስራ ይሰራል። በድድ እና በጥርስ መካከል ያለውን ክፍተት መሙላት በክፍተቱ ውስጥ የሚከማቹትን ባከቴሪያዎች መከላከል ይቻላል።
The post Health: መጥፎ የአፍ ጠረን ሕይወትን እስከማሳጣት ሊደርስ ይችላል appeared first on Zehabesha Amharic.