በየማነ ናግሽ
አሸባሪው አይኤስ ምንም ከለላ በሌላቸው ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ላይ በሊቢያ ሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ ላይ የፈጸመውን አሳፋሪ ድርጊቱን የሚያሳይ ቪዲዮ ከተለቀቀ በኋላ፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተቀባብለውታል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ይኼ አስደንጋጭ ዜና ያጥለቀለቀው ማኅበራዊ ሚዲያውን ነበር፡፡
ሰላሳ ወጣት ኢትዮጵያውያን የዚህ አስከፊ ግፍ ሰለባ በመሆናቸው በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጠው የዳግማይ ትንሳዔ በዓል ዕለት በአሸባሪው በአይኤስ የተለቀቀው ቪዲዮ፣ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈጸሙት አሰቃቂ የሽብር ድርጊቶች እጅግ የከፋው ነው እየተባለ ነው፡፡ ይኼ አረመኔያዊ ድርጊት ቀደም ብሎ በሌላ መጥፎ ዜና ከወደ ደቡብ አፍሪካ የታጀበ ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካ በዘር ጥላቻ የተለከፉ ግለሰቦች፣ ‹‹የውጭ አገር ስደተኞች ከአገራችን ይውጡልን፤›› በማለት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ አፍሪካውያን ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ምላሾች ተለሳልሰዋል በማለት ብዙዎችን ሲያበሳጭና ሲያናድድ አንድ ሳምንት አልሞላውም ነበር፡፡
ጥቃቱም በዚሁ አላበቃም፡፡ የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት በልጦባቸዋል እየተባሉ ሲተቹ የቆዩት የመንግሥት ባለሥልጣናት ምላሽም በዚህ አላበቃም፡፡ በሊቢያ የኢትዮጵያውያን ምሥል እየታየ የተለቀቀው ቪዲዮ እውነትነት ጥርጣሬ ገብቶዋቸው ይሁን ወይም በሌላ ምክንያቱ ባይታወቅም፣ ብዙዎቹ በሊቢያ የተፈጸመውን ድርጊት ፈጥነው ማውገዝ አልቻሉም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአንዱ የአይኤስ ሰለባ እህት የወንድሟን አገዳደል ቀድማ መለየት በመቻሏ፣ በተለይ በተለምዶ ጨርቆስ (ቂርቆስ) በመባል በሚታወቀው አካባቢ ሐዘንና ቁጣ ቀሰቀሰ፡፡
በፀጉሩ ምክንያት ቤተሰቡ በቀላሉ መለየት የቻሉት ኢያሱ ይኩኖአምላክ ነው፡፡ ጓደኛው አብሮ መጓዙን የሚያውቁ የወጣት ባልቻ በለጠ ቤተሰቦችም መጠርጠር ጀመሩ፡፡ እሱም የሰለባው አካል መሆኑ ታወቀ፡፡ ድንኳኑ በጋራ ተጣለ፡፡ የቂርቆስ አካባቢም ድባብ በሐዘን ተዋጠ፡፡ ይህ የሆነው ሰኞ ጠዋት ሲሆን፣ መንግሥት የሰጠው መግለጫ አልነበረም፡፡ በተለይ ‹‹የሟቾቹን ማንነት እናጣራለን፤›› የሚል መግለጫ መባሉ ብዙዎችን አስቆጣ፡፡ በሐዘን ቤት የተገኙት ለቀስተኞች በመንግሥት መግለጫ ማዘናቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው ደግሞ ማውገዙን ቀጠለ፡፡ በኢሕአዴግ ደጋፊነታቸው የሚታወቁ ፌስቡከሮች ሳይቀሩ መንግሥትን አወገዙ፡፡ አንዱ፣ ‹‹መንግሥታችን ለመሆኑ የሰብዓዊ ፍጡር ስብስብ ነው ወይ?›› አለ የኢሕአዴግ የምርጫ ቅስቀሳ ሰኞ ማታ ሲተላለፍ አይቶ፡፡ በእርግጥ ወደ ኋላ መንግሥት ስህተቱን ያረመ ይመስላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሐዘን መግለጫ አሰሙ፡፡ በነጋታውም የአገሪቱ ፓርላማ የሦስት ቀናት ሐዘን አወጀ፡፡ የአገሪቱ ባንዲራም ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተደረገ፡፡ የመንግሥትን አቋም የለወጠው የማኅበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት ተሰማ፡፡
የሟች ኢያሱ እናት ወ/ሮ አኸዛ ካሳዬ፣ ልጃቸው ወደ ሊቢያ መጓዙን የሰሙት ዘግይተው ነበር፡፡ የበለጠ ቤተሰቦችም ቢሆኑ አላወቁም ነበር፡፡ ጉዳዩ በሁለቱ አብሮ አደጐችና ጓደኞች በሚስጥር የተደረገ ነበር፡፡ አሁን የሰሙትን መቀበል አቅቷቸዋል፡፡ የሰለባዎቹ ቤተሰቦች በሥርዓቱ አልነበረም የተረዱት፡፡ በፌስቡክና በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ነበር ያወቁት፡፡
ሐዘኑ በዚህ አላበቃም፡፡ በትግራይ ክልል የእንትጮ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪ የሆነው የ25 ዓመቱ ወጣት ዳንኤል ሐዱሽ ፎቶም ተለይቶ ተለቀቀ፡፡ ዳንኤል ባለፈው ዓመት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በዲግሪ የተመረቀ ነው፡፡ በ1982 ዓ.ም. በአስመራ ከተማ የተወለደው ዳንኤል፣ የሁለት ዓመት ሕፃን ሆኖ ወደ አገሩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ከቤተሰብ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ተወልደ ተክሉ ከተባለው (አሁን ያለበት ሁኔታ አልታወቀም) ጓደኛው ጋር ነበር ወደ ሊቢያ የተጓዘው፡፡ በዚሁ አረመኔያዊ ድርጅት አራተኛ ልጃቸውን ያጡ እናት ወ/ሮ ዛፏ ገብረ ኢየሱስ እንደ ሌሎቹ እሳቸውም የልጃቸውን ወደ ሊቢያ መሄድ አያውቁም፡፡ ሑመራ የስኳር ፋብሪካ ውስጥ እንደሚሠራ ነግሯቸው ነበር የሄደው፡፡ ‹‹በአካባቢው ኔትወርክ አይሠራምና አልደወለም ብለሽ እንዳታስቢ፤›› ብሏቸው ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም. መሄዱን ይናገራሉ፡፡ ሪፖርተር ያናገራት አንዲት ዘመዱ እንደምትለው፣ ‹‹ሥራ አላገኘሁም፡፡ ሰው በዘመድ ነው ሥራ የሚገባው፡፡ እኔ ዘመድ የለኝም፤›› ብሎ ነበር፡፡ ሑመራና መቐለ ተመላልሶ ሥራ በማጣቱ ምክንያት ስደትን አማራጭ አድርጐ መወሰኑን ትናገራለች፡፡
አሁንም መርዶ
በዚሁ አላበቃም፡፡ ባለፈው ሳምንት እሑድ ጀምሮ በሐዘን በቁጣና በተቃውሞ በተጨናነቀው ቂርቆስ፣ አሁንም ሌላ መርዶ ተሰማ፡፡ ከሦስት ወራት በፊት የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀደም ብለው ወደ ሊቢያ ያመሩት ሦስት ወጣቶች ከሰለባዎች መካከል መሆናቸው ታወቀ፡፡ ኤልያስ ተጫነ፣ ብሩክ ካሳና በቀለ ታጠቁ ይባላሉ፡፡ ሁሉም ኑሮ የከበዳቸውና ምንም የሥራ አማራጭ ያጡ እንደነበሩ የሠፈር ጓደኞቻቸው ይናገራሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል የበቀለ ታጠቁ የአጐት ልጅ የሆነውን ታምራት ታረቀኝን ሪፖርተር አናግሮት ነበር፡፡ በቀለ ከወልቂጤ ነው የመጣው፡፡ ቤተሰቡ አሁንም ድረስ እዚያው ነው ያሉት፡፡ ሲሄድ አልነገረውም፡፡ መተማ ዮሐንስ እንደደረሰ ግን ደውሎ 11,000 ብር እንዲልክለት ይነግረዋል፡፡ ዱብ ዕዳ ሆኖበት አገር ቤት ልጆች በሰንበት ትምህርት ቤት ተሰብስበው ቲሸርት ያሳትሙ ነበር፡፡ ኃላፊውም በቀለ ራሱ ነበር፡፡ በቀጣይ ዓመት ተመሳሳይ ነገር ለመሥራት ያተረፉትን 3,600 ብርና የቀረውን ጨምሮ ይልክለታል፡፡ ቀጥሎም ከሁለት ቀናት በኋላ ሱዳን ካርቱም ላይ ሆኖ 34,000 ብር እንዲልክለት በደላሎቹ ያስነግራል፡፡ ካልሆነም ወንድሙ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ይነግሩታል፡፡ ሊያገናኙት ግን አልቻሉም፡፡ ወልቂጤ ድረስ በመሄድ ለወላጆቹ ነግሮ ከዚያም ከዚህም ተበድሮ አሰባስቦ አሁንም ሕይወቱን ለማትረፍ ይልክለታል፡፡ እንደምንም ደውሎ አንድ ጊዜ ድምፁን ሰምቷል፡፡ ከዚያ በኋላ አላገኘውም፡፡ አሸባሪው አይኤስ ይህንን ዘግናኝ ድርጊት የፈጸመ ዕለት እሑድ ታምራት አገር ቤት ነበር፡፡ ቀደም ብሎ ያያትን ልጅ ለማጨት ከጓደኛው ጋር ነበር የሄደው፡፡ እንደ አገሩ ባህል ሽማግሌዎች የላከ ሲሆን፣ ከመካከላቸው የሟቹ የወጣት በቀለ አባት አቶ ታጠቁ ይገኙበታል፡፡
እሑድ ከሰዓት በኋላ ‹‹ሰጠናችሁ›› ተብሎ እዚያው የደስ ደስ ፍንጥር አድርገው ነበር ያደሩት፡፡ ሰኞ እዚህ እንደመጣ ይህንን መጥፎ ዜና ታክሲ ውስጥ ይሰማል፡፡ ይደነግጣልም፡፡ ‹‹ቀልቤ ልክ አይደለም፤›› ይላል፡፡ በቀለ መሄዱን ከእሱ ውጪ እምብዛም ሰው አያውቅም ነበር፡፡ ለጓደኞቹ በቀለ እንደሄደ ነግሯቸው በፌስቡክ እንዲያዩ ይጠይቃቸዋል፡፡ ‹‹እኔ ማየት አልቻልኩም፡፡ ድፍረቱም የለኝም፤›› ይላል፡፡ ከዚያ ሐሙስ ጠዋት ሌላ አጐቱ ዘንድ በመሄድ እሱም ከሌሎቹ ጋር እንደሞተ ይናገራል፡፡ በኃላፊነት ከአገር ቤት አስመጥቶ በዕዳ የላከው ልጅ ሐዘን በርትቶበት እንባ እየተናነቀው፣ ከዚያ ውጪ መናገር አልቻለም፡፡ የሦስቱ ወጣቶች ሐዘን የተከናወነው በአንድ ድንኳን ሲሆን፣ የሌሎችም ታሪክ አሳዛኝና ተመሳሳይ ነው፡፡ አንዳች ዕርዳታና ድጋፍ ካልተደረገላቸው በቀላሉ የሚፅናኑ አይመስልም፡፡
በአካባቢው ከተቀመጡት ወጣቶች መካከል መናገር የሚፈልገው ነገር እንዳለ እያሳበቀበት ነው፡፡ ‹‹እባካችሁ ሕገወጥ ስደተኞች አትበሉ፡፡ ልጆቹ ሕገወጥ አይደሉም፡፡ እንጀራ ፈላጊ ናቸው፡፡ ሱዳን ኤምባሲ ከፌዴራል ፖሊስ ጽሕፈት ቤት መቶ ሜትር አይርቅም፡፡ በሕጋዊ መንገድ ነው የሚወጡት፡፡ በሰላምና በስካይ ባስ ነው ተሳፍረው በሱዳን የወጡት፤›› ይላል የሰለባዎቹ ጓደኛ ወጣት ያሬድ አሰፋ፡፡ ‹‹እዚህ አካባቢ ያለው ሰው በሙሉ መሥራት ይፈልጋል፡፡ መንጃ ፈቃድ ማውጣት ይፈልጋል፡፡ አልቻለም፡፡ ክፍያው ቀላል አይደለም፡፡ ለመንግሥት ንገሩልን፡፡ ይቀንስልን፤›› በማለት በተስፋ መቁረጥ መንፈስ ተናግሯል፡፡
የሠፈሩ ልጆች ብሎኬት አምርቱ ተብለው ለሥራ ተሰማርተው እንደነበር ያስረዳል፡፡ የሚሠሩበት የኮንዶሚንየም ሳይት ቃሊቲ አካባቢ በመሆኑ የባሰ ዕዳ አመጣችሁ ተብለው የመንግሥት ትራንስፖርት ተከልክለው በራሳቸው እንዲጓዙ መደረጋቸው፣ በዚህም ተስፋ ቆርጠው ሥራውን እንዳቆሙ ይናገራል፡፡
‹‹እኛም ለመሄድ ነው የምናስበው››
ሮቤል ደፋሩ የኤልያስና የብሩክ ጓደኛ ነው፡፡ ከዋሊያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ስለሺ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አብሮአቸው ተምሯል፡፡ በ2002 ዓ.ም. በኮብልስቶን ሠልጥነዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ቁጭ ብለናል፤›› ይላል፡፡ ‹‹እኛም ለመሄድ ነው የምናስበው፡፡ ልንከተላቸው ነበር፤›› በማለቱ ‹‹አሁንስ ምን ታስባላችሁ?›› የሚል ጥያቄ ቀረበለት፡፡ ሮቤል ብቻ ሳይሆን አጠገቡ የነበሩት ሌሎችም የሠፈሩ ልጆች አንድ ላይ፣ ‹‹አሁንም እንሄዳለን፡፡ ምንም ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለም፡፡ ዕድላችንን እንሞክራለን፤›› አሉ፡፡
በአሸባሪዎች ሊቢያ ውስጥ የተጨፈጨፉ ጓደኞቻቸውን እየተመለከቱ አሁንም ለመሄድ ያስባሉ፡፡ እዚህ አገር ባለው ነገር ተስፋ መቁረጣቸውን ይናገራሉ፡፡ ሄደው ጣሊያንና ጀርመን ገብተው ያለፈላቸው እንዳሉም ያስረዳሉ፡፡
አሸናፊ ቦጋለ የተባለው ወጣት ከመካከላቸው በጣም ተስፋ የቆረጠ ይመስላል፡፡ ‹‹እኛ ምርጫ በመጣ ቁጥር ነው መንግሥት የሚፈልገን፤› በማለት እሱም በኮብልስቶንም፣ በኤሌክትሪክም ሠልጥኖ ምንም መሥራት አለመቻሉን ይናገራል፡፡ ‹‹አንዳንድ ጊዜ የምናገኛትን ብር አጠራቅመን እንሄዳለን፡፡ ሕጋዊ መንገድ ተዘጋ፡፡ እዚህ ያለው ወጣት በሙሉ በዚሁ መንገድ ለመሄድ የተዘጋጀ ነው፤›› ይላል፡፡
ሪፖርተር በአካባቢው ተዟዙሮ ያነጋገርናቸው ወጣቶች ጥያቄያቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ምንም የሥራ አማራጭ እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ወሮአቸዋል፡፡ አንድ ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ ወጣት፣ ‹‹ሌላስ ይቅር እባካችሁ መንግሥት ሊቢያ በአደጋ ላይ ያሉትን ሕይወት ለመታደግ ምን እየሠራ እንደሆነ ጠይቁልን፤›› ይላል፡፡ ‹‹አገር ውስጥ ስላለው ችግር ብናገር ምንም አዲስ ነገር ስለሌለው ባልናገር ይሻላል፤›› በማለት ተንሰቀሰቀ፡፡
ዓምደ ዲኖ የተባለው ሌላው ጓደኛው ግን ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ስብሰባ ጠርተው ሃምሳ ሃምሳ ብር ሰጥተው ወጣቱ እየሠራ ነው የሚል ፕሮፓጋንዳ ከሚሠሩብን ምን አለ ሥራ ቢፈጥሩልን?›› በማለት ይጠይቃል፡፡
ዳዊት ላቀው የተባለው ሌላው ወጣት ግን ችግሩ ከመንግሥትም አቅም በላይ እንደደረሰ ይናገራል፡፡ ‹‹ምንም ዓይነት የሥራ ዕድል የለም፡፡ የሚወራውና መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ነገር ለየቅል ነው፡፡ ያልፍልናል ብለው ነበር የሄዱት፡፡ አሁን ግን ከቤተሰብም አልፈው አገር አሳዝነዋል፡፡ ከዚህ በፊት ብዙ ሰው ተሳክቶለታል፡፡ ያንን ስኬት አይተው ነው የተሳሳቱት፤›› ይላል፡፡ እሱም ከመንግሥት የሚጠብቀው አንዳች ነገር የለም፡፡
‹‹ምን ማድረግ እንደሚቻል አይታወቅም፡፡ መንግሥትም የሚቻለው ነገር አይመስለኝም፡፡ ስደት ይብቃ ብለህ የምታስቆመው አይደለም፡፡ ይህንን ያህል ሥራ አጥ ወጣት ማብቃት ከባድ ነው፡፡ መንግሥት እንዴት እንደሚቋቋመው አላውቅም፡፡ ከባድ የቤት ሥራ ነው ያለበት፤›› ብሏል፡፡
ሌላ ‹‹ሕገወጥ›› የሚለው አገላለጽ እጅግ ያስከፋው ወጣት፣ ‹‹ደልቶት ወይም ከመንግሥት ጋር ተጣልቶ አይደለም የሄደው፡፡ ይኼ ነገር ቢታረም ደስ ይለኛል፤›› ብሏል፡፡ የአንድ የመንግሥት ባለሥልጣን አነጋገርንም በመተቸት ‹‹እባክህ ምን አለበት አንድ የሚያሳርፍ ቃል ቢጠቀም፤›› ብሏል፡፡
‹‹ያመለጠው››
በአካባቢው ከተገኙት የሟቾች ጓደኞች መካከል ወጣት ልዑል ሰገድ ንጉሥ አንዱ ነው፡፡ ጉዳት ከደረሰባቸው ጓደኞቹ በፊት ከሌሎች ሦስት የሠፈር ልጆች ጋር ነበር ወደ ሊቢያ የተጓዘው፡፡ ታሪኩን ይናገራል፡፡ ከአዲስ አበባ ትኬት ቆርጠው ባህር ዳር ይደርሳሉ፡፡ ከዚያም መተማ ከደላሎች ጋር ተገናኝተው ወደ ገለባት ሄዱ፡፡ ገለባት ላይ የኢትዮጵያና የሱዳን ሲም ካርድ ተሰጣቸው፡፡ ሁለቱም ይሠራሉ፡፡ ከመተማ ወደ ካርቱም 12,000 ብር ተጠይቀዋል፡፡ ብሩ የሚከፈለው ካርቱም ሲገባ ነው፡፡ እዚህ ያለ ቤተሰብ ነው የላከለት፡፡ የሚቀበሉዋቸው ደላሎች ሱዳናውያን ሲሆኑ፣ አልፎ አልፎ ሐበሾችም አሉ፡፡ ጉዞ በመኪና በመሆኑ በሌሊት ነው፡፡ ገዳራት የሚባል ቦታ ላይ 15 ቀናት ያህል ቆይተዋል፡፡ ‹‹ምንም ምግብ አይሰጡንም፡፡ በረሃብ አልቀን ነበር፤›› ይላል፡፡
ከዚያ ካርቱም ላይ ከሚጠብቃቸው ልጅ ጋር ተገናኝተው፣ ከሌሎች በጐንደር አቋርጠው ከመጡ ሦስት ልጆችም ጋር ተቀላቅለው ሰባት ሆኑ፡፡ በልጁ ቤት አራት ቀናት ቆዩ፡፡ ከዚያ ወደ ሊቢያ ተነሱ፡፡ 28,000 ብርም ተጠየቁ፡፡ ‹‹የተጓዝነው በፒካፕ ሲሆን፣ ደህና ብር የከፈሉት ጋቢና ሌሎቻችን ከ30 በላይ የምንሆን ከኋላ ተጫንን፤›› ይላል፡፡
ለሁለት ቀናት ከተጓዙ በኋላ ሊቢያ ድንበር ላይ የሱዳን ፖሊሶች ይይዟቸዋል፡፡ ፖሊሶቹ ከደላሎች ጋር እያወሩ እንዲከፈላቸው ቢጠይቋቸው አልተስማሙም፡፡ ከዚያ ሦስት ጊዜ አስቁመው ጠየቁአቸውና አልተስማሙም፡፡ ቀጥሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አስገቡዋቸው፡፡ እስር ቤቱ ውስጥ ብዙ ኤርትራውያንንና ኢትዮጵያውያንን ተመልክተዋል፡፡ አድራሻቸው አዲስ አበባ መሆኑን ተናግረው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ አምስት አምስት ጅራፍ ተገርፈው ወጡ፡፡
ከዚያ ለ15 ቀናት ‹‹ጉዳ›› የሚባለው ማረሚያ ቤት ላይ ታሰሩ፡፡ በቀን ሁለት ሁለት ቂጣና የተቀቀለ ምስር ይሰጡዋቸዋል፡፡ ‹‹እዚያ ውስጥ ብዙ ነገር ብዙ ፈተና ይገጥምሃል፤›› በማለት ለመናገር ያዳገተው ነገር እንዳለ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ከዚያ ወደ ካርቱም መለሱዋቸው፡፡ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ገቡና ወደ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ወሰዱዋቸው፡፡ እነሱም መክረውና የይለፍ ወረቀት ሰጥተው ወደ መተማ መለሱዋቸው፡፡
ልዑል ሰገድ እንደሚለው በዚሁ ጉዞ ላይ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መታወቂያም ሆነ ፓስፖርት መያዝ አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው መንገድ ላይ አደጋ ሲገጥም ሰው ማንነቱ የማይታወቀው፡፡ ሁለቱ ጓደኞቹ ከመተማ ተመልሰው ወደ ሊቢያ የሄዱ ሲሆን፣ እሱና ጓደኛው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ አንዱ ጓደኛው ጣሊያን ሲገባ፣ አንዱ ወደ ጣሊያን ለመሻገር መርከብ የሚጠበቅበት ሥፍራ ላይ መሆኑን ነግሮታል፡፡ አሁን የደረሰውን አደጋ እያሰበ ‹‹ለበጐ ይሆናል›› በማለት ታሪኩን ቋጨ፡፡ ዋይታው ግን ቀጥሏል፡፡
Source: Ethiopian Reporter Newspaper
The post (የሊቢያው ጉዳይ) ‹‹አሁንም የመሄድ ሐሳባችንን አልቀየርንም›› በግፍ የተገደሉት የሠፈር ጓደኞች appeared first on Zehabesha Amharic.