ዳንኤል ስተሪጅ ራሱን እየገለፀ ነው፡፡ ስለ ሰብዕናው ለማብራራት ሞከረ፡፡ ባህሪው በምን አይነት መንገድ እንደተቀረፀ ለመተንተን ጣረ፡፡ ገለፃውን የጀመረው በርሚንግሃም ውስጥ በሆክሌይ ጎዳናዎች አቆራርጦ ወደ ትምህርት ቤት ስለሚጓዘው የ10 ዓመት ታዳጊ በማውሳት ነው፡፡ የወሮበሎች ጥቃት እንግዳ ባልሆነበት አካባቢ ታዳጊው እራሱን ከአደጋ ለመጠበቅ ያደርግ የነበረውን ሁሉ ያስታውሳል፡፡ ታዳጊው እንዴት ራሱን ደፍቶ መንቀሳቀስ እንደለመደ አይዘነጋም፡፡ ሰዎች ጋር አይን ለአይን ላለመተያየት ያደርግ የነበረው ጥንቃቄ አይረሳውም፡፡ የሆነ ሰው ቢጠራው ዞሮ አይመለከትም አልያም ሰላምታ አያቀርብም፡፡ ዝም ብሎ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ አዲስ ወይም እንግዳ የሆነ ሰው ሁሉ በጥርጣሬ ይታያል፡፡ ለወዳጅነትም አይታጭም፡፡
የታዳጊው የተለመደ ተግባር ያ ነበር፡፡ ጠዋት መኖሪያ ቤቱ ከሚገኝበት ሆክሊይ ትምህርት ቤቱ ወዳለበት ኒውታውን ወደተባለ የከተማው ክፍል ይሄዳል፡፡ ከሰዓት በዚያው መንገድ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ ቤተሰቦቹ አብረውት ነበር፡፡ ጥብቅ ግንኙነት የነበራቸው ጓደኞችም ነበሩት፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከእግርኳስ ተለይቶ አያውቅም፡፡ በዚያ ምክንያት ከብዙ ነገሮች ተገልሎ በግሉ ዓለም ውስጥ መኖርን ተካነበት፡፡
ስተሪጅ አሁን 25 ዓመት ሆኖታል፡፡ የሊቨርፑል እና እንግሊዝ ኮከብ ተጨዋች ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ድረስ ያ ታዳጊ በውስጡ ይኖራል፡፡ ወደ እውቅና የመጣ ሰሞን ‹‹ቁጡ›› ተብሎ ሲገለፅ የነበረው ለዚያ ሊሆን እንደሚችል ያምናል፡፡ ቁጡ አይደለም፡፡ በብዙ መንገድ የዚያ ተቃራኒ ነው፡፡ አስደሳች እና ሰው አክባሪ ነው፡፡ ነገር ግን የተወሰነ ቁጥብነት ይታይበታል፡፡ በአብዛኛው ኮስታራ መስሎ ይታያል፡፡ ግንባሩ አይፈታም፡፡ በፌዝ እ በቀልድ በሚታወቀው የእግርኳሱ ዓለም ባልተለመደ መልኩ ገለልተኝነት ይታይበታል፡፡
‹‹ጥበብ ያለ ዓለም ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ የጓደኞቼ ቁጥር ከአንድ እጅ ጣቶች አይበልጥም፡፡ ሁሉም ሰው በሥራ አጋጣሚ የሚተዋወቃቸው ሰዎች፣ የቡድን ጓደኞች እና የመሳሰሉት ይኖሩታል፡፡ ነገር ግን ከዚያ ውጪ ባለው ህይወቱ ከቤተሰቦቼ ሌላ በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው›› ይላል ስተሪጅ፡፡
‹‹እንደሚመስለኝ ያ የሆነው በአስተዳደጌ ምክንያት ነው፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች ስታድግ ድምፅህ በጉልህ እንዲሰማ ወይም ለቀቅ ያለ የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖርህ አትፈልግም፡፡ ምክንያቱም ያንን ማድረግህ ለማትፈልገው ነገር ሊያጋልጥህ ይችላል፡፡ እኔ ባደግኩበት አካባቢ ወንጀል እና ሌሎች ተዛማጅ ነገሮች ተንሰራፍቶ ነበር፡፡ በርሚንግሃም ጥሩ ከተማ ነው፡፡ ሆኖም ባደረግኩበት አካባቢ ከአዲስ ሰዎች ጋር መተዋወቅ እና ወዳጅነት ለመመስረት አይደለም፡፡ የሆነ ጥቃት ሊሰነዝሩብህ እንጂ፡፡
‹‹በበሚንግሃም ታዳጊ ሳለሁ የወሮበሎች ባህል በከተማው ተንሰራፍቶ ነበር፡፡ ከዚያ ርቆ መቆየት ቀላል ነበር፡፡ ምክንያቱም እግርኳስ አለና፡፡ ነገር ግን ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከሰዎች ጋር ብዙም የማልቀላቀል ሰው ሆንኩ፡፡ እንደዚያ ማድረግ ሁለተኛ ተፈጥሮዬ ሆነ፡፡ ሁልጊዜ ተጠራጣሪ መሆን ነበረብኝ፡፡ ውንብድናው የቆዳ ቀለምን መሰረት ያደረገ አልነበረም፡፡ ይበልጥ በአካባ የተከፋፈለ ነው፡፡ በሆነ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፍ ሰው የቤተሰብህ ወዳጅ ሊሆን ሁሉ ይችላል፡፡ እኔ በዚያ መሰሉ እንቅስቃሴ ውስጥ ፈፅሞ ተሳትፎ አልነበረኝም፡፡ በዚያ አካባቢ በማደግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ለማደግ የሚረዳ ጥሩ ስፍራ ነው፡፡ መቼም ቢሆን አቃልዬ ልገልፀው አልችልም፡፡ ቤቴ ነው፡፡ አካባቢውን እወደዋለሁ፡፡ በዚያ ከፍተኛ የሆነ የካሪቢያን ባህል አለ፡፡ ምግቡ እና ሁሉም ነገር አስደሳች ነው›› የሊቨርፑሉ አጥቂ ንግግሩን ይቀጥላል፡፡
ስተሪጅ በቀላሉ ሊገለፅ የሚችል ሰው አይደለም፡፡ ስለ እርሱ ማውራትን አስደሳች የሚያደርገው አንደኛውነገር ያ ነው፡፡ በሊቨርፑል ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው ተጨዋቾች አንዱ ነው፡፡ ከቡድኑ መሪዎች እንደ አንዱ ይታያል፡፡ ወጣት ተጨዋቾ እርዳታ እና ምክር ፍለጋ ወደ እርሱ ይመጣሉ፡፡ እርሱም ቢሆን ምክር የሚግለሳቸው በደስታ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ብቸኛ እንደሆነ ያስባል፡፡
በከተማዋ እምብርት በሚገኝ ህንፃ ብቻውን ይኖራል፡፡ አንዳንዶች ጎል ካገባ በኋላ ደስታውን የሚገልፅበትን መንገድ ተመልክተው ማህበራዊ ኑሮ የሚወድድ እና ወጣ እያለ የሚዝናና አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ነገር ግን እንደዚያ አይነት ሰው እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ ከፊሎቹ ከልዊስ ቶምሊንሰን አልያም ቲኒ ቴምፓህ ጋር የተነሳውን ፎቶ ተመልክተው እዩኝ እዩኝ ማለት እንደሚወድድ ይገምታሉ፡፡ ነገር ግን እርሱ ያን አይነት ፍላጎት እንደሌለው ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ ሌሎች ግልፅ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ በዚህም ቢሆን አይስማማም፡፡
ከአብዛኞቹ ተጨዋቾች በተሻለ አስተዋይ እና ዝምተኛ ነው፡፡ የተወሰኑ ሰዎችን ምቾት የሚነሳቸው ያ ይመስላል፡፡ ‹‹ከአዳዲስ ሰዎች ጋር ስገናኝ በራሴው ዛቢያ ላይ የምሽከረከር ይመስለኛል›› በማለት ይናገራል፡፡ በሌሎ መንገዶችም የተለየ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ከሊቨርፑል የልምምድ ሜዳ ወደ ቤቱ የሚመለሰው በቅንጡ መኪኖች ሳይሆን በታክሲ ነው፡፡ ከጉዳቱ ለማገገም በዩናይትድ ስቴትስ ቆይታ ባደረገበት ወቅትም ቢሆን ከእያንዳንዱ ዕለት ህክምና በኋላ የሚያመራው ወደ ቅንጡ ሬስቶራንቶች አልያም ዘመናዊ ባር አልነበረም፡፡
‹‹ጠዋት አንድ ሰዓት አካባቢ እነሳለሁ፡፡ አስር ወይም አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ የዕለቱን መርሃ ግብር አጠናቅቃለሁ፡፡ ያን ጊዜ መጨላለም ይጀምራል፡፡ ፀሐይ መጥለቅ ትጀምራለች፡፡ ያን ጊዜ ወደ ክፍሌ እመለሳለሁ፡፡ እመገባለሁ፡፡ የተወሰነ ጊዜ ዶሚኖ እጫወት እና ወደ መኝታዬ አመራለሁ››
ጉዳት የስትሪጅን የውድድር ዘመን ጉዞ አስተጓጉሎበታል፡፡ በ2013/14 የውድድር ዘመን በስምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ጎል በማስቆጠር ክብረወሰን ተጋርቷል፡፡ ከልዊስ ሱአሬዝ ጋር አስፈሪ የአጥቂ መስመር ጥምረት ፈጥሯል፡፡ ከዚያ በኋላ ባጋጠመው ተደራራቢ ጉዳት ምክንያት ለአምስት ወራት ከሜዳ ለመራቅ ተገደደ፡፡
የሱአሬዝ ለባርሴሎና መሸጥ ከእርሱ አለመኖር ጋር ተደማምሮ ሊርፑል የውድድር ዘመኑን በመጥፎ ሁኔታ እንዲጀመር አስገድዶታል፡፡ ስተሪጅ በጃንዋሪ መጨረሻ ወደ ቡድኑ የተመለሰ ሲሆን የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ብልጠት በሚታይበት መልኩ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ የሜርሲ ሳይዱ ክለብ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ በሚያደርገው ጥረት የእንግሊዛዊው መመለስ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም ይታሰባል፡፡ ሮይ ሆጅሰን ወደ እንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ይመልሱት እንደሆነም የሚታወቀው ዛሬ (ማክሰኞ) ነው፡፡ ከሎቲንያ እና ጣልያን ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚጫወተውን ቡድናቸውን አባላት ይፋ ሲያደርጉ ከስተሪጅ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ዳግም ትኩረት ያገኛል፡፡ አጥቂው የውድድር ዘመኑን ያደበዘዘበትን የመጀመሪያ ጉዳት ያስተናግደው በሴንት ጆርጅ ፓርክ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ልምምድ በሚሰራበት ወቅት ነበር፡፡
በሊቨርፑል ሮጀርስ ከጨዋታ በኋላ ሁለት የማገገሚያ ቀናትን ይፈቅዳሉ፡፡ ነገር ግን ሆጅሰን ተጫዋቾቻቸው በሁለተኛው ቀን ልምምድ እንዲሰሩ ይጠይቃሉ፡፡ በሴፕቴምበር 3 ረቡእ እንግሊዝ ኖርዌን ባሸነፈችበት የዌምብሌይ ጨዋታ ስተሪጅ ለ83 ደቂቃዎች በሜዳ ውስጥ ቆይቷል፡፡ አርብ ዕለት ሴፕቴምበር 5 ከብሔራዊ ቡድን ጋር አፈትልኮ የመሮጥ ልምምድ ሲሰራ በታፋው ጡንቻ ላይ ጉዳት ደረሰበት፡፡
የተለመደው የክለብ እና ብሔራዊ ቡድን ንትርክም ተጀመረ፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ስተሪጅ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኞች ስታፍ አባላት ለልምምድ ዝግጁ አለመሆኑን እንደነገራቸው ነገር ግን የሚሰማው እንዳላገኘ ይናገራሉ፡፡ ሆጅሰን ግን ስተሪጅ ልምምዱን ለመስራት አለመፈለጉን እንዳላሳወቃቸው ይናገራሉ፡፡ ንትርኩ ግን ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ስተሪጅም በዝምታው ገፍቶበታል፡፡ አጋጣሚውን በግልፅ ለመናገር ዝግጁ አይደሉም፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ነው፡፡በሆዱ ምንም አይነት መጥፎ ስሜት አለመኖሩንም ይገልፃሉ፡፡ ሆጅሰንንም ለጉዳቱ ተጠያቂ አያደርግም፡፡
‹‹ከዚህ በፊት ምንም አይነት ነገር ቢከሰት ለእንግሊዝ መጫወት ያስደስተኛል፡፡ አጋጣሚው ተከስቷል፡፡ ነገር ግን ያለፈ ታሪክ ነው፡፡ ሳስታውሰው ልኖር አልፈልግም፡፡ የእግርኳስ ህይወት እንደዚያ ነው፡፡
‹‹ከብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ጋር መልካም ግንኙነት አለን፡፡ ምንም የሚያስጨንቅ ነገር የለም፡፡ የፅሑፍ መልዕክቶችን እንለዋወጣለን፡፡ በአካል ተገናኝተንም እንነጋገራለን፡፡ ግንኙነታችን አልተቋረጠም፡፡ በጉዳት ላይ በነበርኩባቸው ጊዜያት ሁሉ ከጎኔ አልተለየም፡፡ ላጋጠመኝ ጉዳት እርሱን ተወቃሽ አላደርግም፡፡ ሌሎቹ አሰልጣኝ ቡድኑ አባላትም ተጠያቂ ሊደረጉ አይችሉም፡፡ ጉዳቱ ከመጥፎ ዕድል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለእርሱም ሆነ በዙሪያው ላሉት ሰዎች ከፍተኛ ክብር እና አድናቆት አለኝ፡፡ ግንኙነታችን በጣም ሰላማዊ ነው፡፡
‹‹ለእኔ ከጨዋታ በኋላ የሚደረግ የሁለት ቀን እረፍት ይስማማኛል፡፡ ነገር ግን እኔ ሁሉንም ተጨዋቾች ልወክል አልችልም፡፡ እያንዳንዱ ተጨዋች የተለየ ልማድ አለው፡፡ በሁለተኛው ቀን መለማመድ የሚወድድ አለ፡፡ አንዳንዶች ያ አይመቻቸውም፡፡ በአሁኑ ወቅት የሁለት ቀን የማገገሚያ እረፍትን ለምጄያለሁ፡፡ አንድን ነገር ስትለማመደው ይዋሃድሃል፡፡ ሁለት ከድካም የማገገሚያ የእረፍት ቀናት በማይሰጥባቸው ክለቦች ውጤታማ ለመሆን ተቸግሬያለሁ፡፡ በመሆኑ የአሰልጣኝ እርምጃ ያልተለመደ አይደሉም›› ስተሪጅ አስተያየቱን ይቀጥላል፡፡
‹‹በየትኛውም አካባቢ ብትሆን ሁኔታውን በፀጋ መቀበል አለብህ፡፡ በማንም ላይ ጣቴን አልቀስርም፡፡ ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር የትኛውንም ነገር እንድፈፅ ቢያዘኝ አደርገዋለሁ፡፡ ምክንያቱም አለቃው እርሱ ነው፡፡ እግሯስ የቡድን ሥራ ነው፡፡ ልጆቹ የሚሰሩትን ሁሉ መፈጸም ይጠበቅብሃል፡፡ ያንን መቀበል ይኖርብሃል፡፡ በዚህ ምክንያት ማንንም አልወቅስም››
እናንተ እንደፈለጋችሁ ተርጉሙት፡፡ ስተሪጅ ለወቀሳ የሚጣደፍ ሰው አይደለም፡፡ ቆራጥ እና እልኸኛ መሆኑ አይካድም፡፡ ነገር ግን ቂመኛ አይደለም፡፡ በእምነቱ የፀና ክርስቲያን ነው፡፡ ከሜዳ ርቆ በነበረበት ወቅት ከተጋፈጣቸው ችግሮች የቀሰመውን ትምህርት ሲያስረዳ ድምፁ የወንጌላዊ ቃና ይላበሳል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት ስላደረገልኝ እና ወደፊት በህይወቴ ስለሚሰራው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ›› ይላል የሊቨርፑሉ አጥቂ፡፡ ‹‹የምትወድቅባቸው እንደዚሁም የምትነሳባቸው ጊዜያት አሉ፡፡ ሁሉም ነገር ሁልጊዜ አልጋ በአልጋ አይሆንም፡፡ በህይወትህ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ሰብዕናህን፣ ፅናትህን፣ እምነትህን በራስህ ላይ ያለህን እምነት እና የመሳሰሉትን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንድታልፍ የምትገደድባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡
‹‹በአዕምሮዬ ጥርጣሬ የሚባል የለም፡፡ በራስ እምነት አለኝ፡፡ በእግዚአብሔር አምናለሁ፡፡ እምነት አለኝ፡፡ በችሎታዬም እተማመናለሁ፡፡ በምንም ነገር አልጨነቅም፡፡ ጎሎችን በቋሚነት ማስቆጠሬን እንደምቀጥል አምናለሁ፡፡ በሁሉም ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ እንደምችልም እተማመናለሁ››
ስተሪጅ ባልነበረባቸው ጊዜያት እግርኳስ ባለበት አልቆመም፡፡ ሆጅሰን በሚመርጡት የአጥቂ መስመር የመግባት ዕድል ያላቸው ተጨዋቾች ተበራክተዋል፡፡ ዳኒ ኢንግስ እና ቻርሊ ኦስቲን በዚህ ተርታ ይሰለፋሉ፡፡ አሰልጣኙ የስኳዳቸውን አባላት ይፋ ሲያደርጉ ተመረጠም አልተመረጠም ከፍተኛውን ትኩረት የሚወስደው ሃሪ ኬን መሆኑ ግን አይካድም፡፡ ስትሪጅ አዲስ ተፎካካሪ ተፈጥሮበታል፡፡ የተጫዋቹ አድናቂ እንደሆነ ሲጠየቅ ‹‹የሌሎች ሰዎችን ድልና ስኬት የምከታተልበት ምክንያት ምንድን ነው? ተጨዋቾች የሚሰሩት ነገር እና በቡድኑ ውስጥ የሚኖራቸው ቦታ አያስጨንቀኝም፡፡ ለእኔ ትርጉም የለውም፡፡ ሌሎችን በመመልከት በህይወትህ የትም አትደርስም፡፡ ምክንያቱም ከራስህ ጋር ግብግብ ትፈጥራለህ፡፡ ሃሪ ኬን ለፈፀመው ገድል እና ላሳካው ስኬት እንኳን ደስ ያለህ ልለው እችላለሁ፡፡ ነገር ግን እየሰራ ያለውን ነገር እየተከታተልኩ አይደለም፡፡ በራሴ እምነት አለኝ›
ስተሪጅ በስሱ ፈገግ አለ፡፡ ነገር ግን ልቡ በፍጥነት የምትመታ ይመስላል፡፡ ለጊዜው መጋረጃውን መልሷል፡፡ በሃሳቡ ራሱን የሚመለከተው በሆክሌይ ጎዳና ተግዳሮቶችን ለማሸነፍ አንገቱን ደፍቶ ብቻውን እንደሚጓዝ ታዳጊ ነው፡፡
The post Sport: ቁጥቡ እንግሊዛዊ የሊቨርፑል አጥቂ ስተሪጅ ማነው? appeared first on Zehabesha Amharic.