* ኢትዮጵያውያን ማን ይታደጋቸው ?
* ከቀሩት የውጭ ዜጎች ምን እንማር ይሆን ?
* ለነፍስ አድኑ ጥሪ የእኛ አማረጭ ምን ይሆን ?
በአረቡ ሀገር ስደት ማጥ ውስጥ የገባውን ወገን ስጋት እያደር ከስጋት አልወጣም ። ሳውዲን መዳረሻ ያደረጉ የመንን በአሳር በመከራ አልፈው በወደብ ከተማዋ ጅዳ እግራቸው ሲረግጥ በጨካኝ ደካሎችና አሸጋጋሪዎች ታግተው የድረሱልኝ ጥሪ ሲያሰሙ ደራሽ አጥተዋል። በህጋዊ የኮንትራት ስራ የመጡትም ሆኑ ህጋዊ መኖርያ ፈቃድ ይዘው ኑሮን በመግፋት ላይ ያሉ ሳይቀሩ በዙሪያቸው ባለው በሚደርስባቸው ፣ በሚያዩ በሚሰሙት እንደኔ ታመዋል ። አረቦች በደሉን ከሚባለው በላይ የራሳችን ወገኖች ደመ ነብሱን ከሚንቀሳቀሰው ያልሞላለት ግፉዕ እስከሞተው በድን ሳይራሩ ፈጣሪ ያየናል ብለው ሳይፈሩ በንዋይ ፍቅር ታውረው ግፍ እየሰሩ ነው ። ሰብዕናቸውን አሽንቀንጥረው ርቀው ሄደው የሚፈጽሙት አስነዋሪ ተግባር የጊዜውን መክፋት ያሳይ እንደሁ እንጃ … እኔም እኛም ሁላችንም ግን ችግሩን እናወራዋለን እንጅ መፍትሔ የለንም ! የየመኑን የጦርነት ግብአት ከመከታተል ጎን ለጎን ሰሞነኛ ውሎየ ያሳየኝ እውነታ ይህንኑ እውነት ነው …
እንዲህና እንዲያ እያልን ኑሮን በምንገፋበት ሰማይ ስር ከላይ ስለጠቀስኳቸው የወገን የስደት አበሳ መከራዎች መረጃ ከማቅረብ ቀዳሚው በጦርነት ማጥ ውስጥ ስለወደቁት ወገኖች አበሳ አደርገው ዘነድ ግድ ብሎኛል ። ይህንኑ የማለዳ ወግ ዳሰሳየን አጠናቅሬ ለማቅረብ ተፍ ተፍ ስል ለተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን እና ለሃያሏ አሜሪካ መሪ ለፕሬዚደንት ሁሴን ኦባማ ወገኖቻችን ይታደጉ ዘንድ ፊርማ ማሰባሰቢያ ላይ ፊርማየን አስቀምጨ መረጃ ሳገለባብጥ ለኢሮሞ ስደተኞች ድረሱላቸው የሚል የኢቦ ጁሃር መሃመድን የፊርማ ማሰባሰቢያ ጥሪ ተመልክቻለሁ ።
አንድ ሆነን በጦርነት አፋፍ ላይ ያሉ ወገኖችን እንደ መታደግ ዛሬም በልዩነት ተበታትነን የምናደርገው ጉዞ አልመችህ ቢለኝ አትፍረዱብኝ … ወደ እሰጣ ገባው ሳልገባ ከእኛ ስለሚጠበቀው አማራጭ የራሴን እይታ ላስቀምጥ ቀለም ከነጩ ወረቀት አገናኝቸ እንደጨረስኩ በቀጣዩ የማለዳ ወግ ቅኝት እስክመለስ ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የተላለፈውን ቀጣይ ዘገባ ያደምጡ ዘንድ ልጋብዝዎ ወደድኩ … ! እስኪ በሁለተኛዋ የየመን ከተማ ኤደን ውጊያው ዘገርሽቶ ፣ የአየር ጥቃቱ በርትቶ በሚገኝባት ከተማ እየሆነ ያለውን ስሙት …
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
መጋቢት 30 ቀን 2007 ዓም
The post በየመን ጦርነት ማጥ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን አበሳ ! – ነቢዩ ሲራክ appeared first on Zehabesha Amharic.