የመረጃ ግብአት …
ዘመቻ “ወሳኙ ማዕበል ” በ8ኛው ቀን ክንውኖች …
እና በየመን ሁከትና የኢትዮጵያውያን ይዞታ !
=
> ” ኤደን በሁቲዎች እጅ አልወደቀችም! ” የሳውዲ መራሹ ዘመቻ ቃል አቀባይ
> ” በየመን ሰንአ የኢትዮጵያ ኢንባሲ ተደብድቧል፣ 2000 ተመዝግበው 30 ጅቡቲ ገብተዋል ” ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖም
> በስደተኞች መጠለያ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር የመግባት ፍላጎት አላሳዩም፣ የድረሱልኝ ጥሪ እያሰሙ ነው፣ በፖለቲካ የሸሹት የምህረት ጥሪ ይደረግላቸውም እየተባለ ነው
8ኛው ቀን የዘመቻ ክንውን መግለጫ …
========================
ኤደን በሁቲ አማጽያን ስር መሆኗን አልጀዚራና የተለያዩ የአረብ መገናኛ ብዙሀን የጠቆሙ ቢሆንም ትናንት ማምሻውን በሪያድ የአየር ኃይል የጦር ሰፈር ሆነው ለጋዜጠኞች ስለ 8ኛው ቀን የዘመቻ ክንውን መግለጫ የሰጡት የዘመቻው ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀኔራል አህመድ አሲሪ ኤደንን ለመያዝ ውጊያው እንደቀጠለ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን ኤደን ሙሉ በመሉ በሁቲዎች ቁጥጥር ስር አለመውደቋን አስታውቀዋል።።
በ8ኛው ቀን የአየር ጥቃት ዘመቻ መግለጫ የሰጡት ብርጋዴር ጀኔራል አህመድ አሲሪ በኤደን አካባቢ እግረኛ ጦር ጀምሯል ወይ ? ተብለው ተጠይቀው ፣ እግረኛ ጦር አለጀመሩን አስረግጠው ተናግረዋል ። በዚሁ መግለጫቸውም በኤደን ዙሪያ ስለተደረገውና እየተደረገ ስላለው የዘመቻው ክንውን ሲያስረዱ በዋናነት በምድርና በባህር የሁቲ አማጽያን ስንቅና ትጥቅ አቅርቦት እንዳያገኙ መንገዶችን የመዘጋጋት ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል። ከዚህ ባከፈ የእግረኛ ጦር ዘመቻ አለመጀመሩን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል ።
“ከወሳኙ ማዕበል” የአየር ጥቃቱን አፋፍሞ በቀጠለበት ሁኔታ በየመን የድንበር ከተማ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው አሲር ክልል በሚያዋስን ድንበር ግጭት መቀስቀሱ ተጠቁሟል። ባልታወቁ ታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስም ሰልማን አልመልኪ የተባሉ አንድ የበታች ሹም የድንበር ጠባቂ ወታደር መገደላቸውንና 10 ያህል መቁሰላቸውን የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ሜጀር ጀኔራል መንሱር አልቱርኪ አስታውቀዋል ። የአየር ጥቃት ከተጀመረ ወዲህ በድንበር ይህን አይነት ክስተት ሲታይ የመጀመሪያው ሲሆን በተባለው ግጭት የሞቱት የድንበር ጠባቂ የቀብር ስነስርአትም ትናንት ሀሙስ በአብሃ ከተማ ተከናውኗል !
*የኢትዮጵያ ኢንባሲ መደብደብና
አሳሳቢው የኢትዮጵያውያን ይዞታ…
======================
በየመን ሰንአ የኢትዮጵየ ኢንባሲ ባሳለፍናቸው ቀናት በጦርነቱ የድብደባ ጥቃት የተፈጸመበት መሆኑን የኢፊድሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖም ባሰራጩት መረጃ አስታውቀዋል። በተፈጸመው ድብደባ የተጎዳ ሰው የለም ከማለት ውጭ በጦር መሳሪያ ተደበደበ ስላሉት ኢንባሲ የጉዳት መጠን የሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ ግን የለም ።
በየመንን ሁከት ተከትሎ በኢትዮጵያ ኢንባሲ በኩል ወደ ሀገር ለመመለስ የተመዘገቡት 2000 ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ከተመዘገቡት መካከል 30 ያህል በጦርነት ከምትናጠው ከኤደን ተነስተው ጅቡቲ መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መረጃ ያስረዳል። በየመን እያደር የጦርነቱ መባባስ ስደተኞችን የመመለስ ስራውን እንዳወሳሰበው የጠቆሙት ዶር ቴዎድሮስ በሚቀጥሉት ቀናት የተመዘገቡትን ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር የመመለሱ ስራ በተቻለው መጠን እንደሚደረግ አስረድተዋል። በመጨረሻም ባስተላለፉት መረጃ የብዙ ሀገር ዲፕለማቶች የመን ሰንአን ለቀው ሲወጡ ” ከዜጎቻችን በፊት አንወጣም !” ብለው እስካሁን የመን አሉ ላሏቸው የኢትዮጵያ ኢንባሲ ዲፕሎማቶች ምስጋና አቅርበዋል ።
በሌላ በኩል በስደተኞች መጠለያ የሚገኙት ከ5000 ስደተኞች ጨምሮ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በየመን በኩል ወደ ሳወዲ ለመግባት አስበው በተለያዩ የየመን ክልሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ አዳዳቢ እንደሆነ ቀጥሏል። ወደ ሶስተኛ ሀገር እንጅ በኑሮው ውድነትና በፖለቲካው አለመረጋጋት ተማረው በ UNHCR የስደተኛ ማረጋገጫ የተሰጣቸው ግን ወደ መጡባት ሀገራቸው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው እየተናገሩ ነው። እኒሁ በጭንቅ ላይ ሆነው ወደ ሀገር የመግባቱ ነገር እንደ ተሻለ አማራጭ የማያዩት ወገኖች አማራጩ ጥሏቸው ከየመን የወጣው በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን UNHCR ወደ ሶስተኛ ሀገር ያሸጋግራቸው ዘንድ የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶችን እንዲማጸኑላቸው በተለያዩ አለማት ላሉ ኢትዮጵያውያን የድረሱልኝ ጥሪ እያሰሙ ነው!
በየመን ሁከቱ እያየለ ከሄደና የሳውዲ መራሹ የ10 አረብ ሀገራት የምድር ጦር እግረኛ ማዝመት ከጀመረ ያለውን አማራጭ መጠቀም ባልፈለጉ ኢትዮጵያውያን ላይ የከፋ አደጋ እንዳያጋጥማቸው ስጋት ተደቅኖባቸዋል ። በተለያየ ምክንያት ፖለቲካውን ሸሽት ሀገር ለቀው አሁን አደጋ ላይ ሲወድቁ ወደ ሃገራቸው እንዳይመለሱ የእስራት ፍርዱን የፈሩ ዜጎች ቁጥር ከፍ ያለ መሆኑ ይነገራል። ይህን መሰሉን ችግር ማቅለል ይቻል ዘንድ የኢትዮጵያ መንግስት ከችግሩ ቀጠና ወደ ሃገር ለሚመለሱ ማናቸውም ስደተኞች የምህረት ጥሪ ያቀርብ ዘንድ በዚሁ ዙሪያ ያነጋገርኳቸው ወገኖች ያስረዳሉ !
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
መጋቢት 25 ቀን 2007 ዓም
The post (የየመን ጉዳይ) ዘመቻ “ወሳኙ ማዕበል ” በ8ኛው ቀን ክንውኖች … እና በየመን ሁከትና የኢትዮጵያውያን ይዞታ ! appeared first on Zehabesha Amharic.