ከሰማያዊና ከአንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማህበራት የተሠጠ መግለጫ
ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፤ ከውጭም፣ ከውስጥም፣ ያላችሁ፦
ሕውሃት/ኢህአዴግ ጠንካራ ተቃዋሚ የለም በማለት በብቸኝነት በሚቆጣጠራቸው የመገናኛ ሚዲያዎች በሕዝቡ እያላገጠ በስተጀርባ ግን የፖለቲካ አመራሮችንና የፖርቲዎችን ሕልውና ማሣደድ ቀጥሎበታል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት የአንድነት ፓርቲን ማፈራረሣቸው አልበቃ ብሏቸው አሁን ደግሞ በትናትናው ዕለት የሰማያዊ ፖርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ወደ ውጭ እንዳይመጣ በማንአለብኝነት በእብሪት በመወጠር ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮኘላን ማረፊያ ከልከለው መልሰውታል፡፡ በሃሰት ሚዲያዎች ሕዝቡን አፍኖ በመያዝ አገዛዙን ለመቀጠል እየተውተረተረ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት ቆራጥ የሆኑ የሠላማዊ ትግል አመራሮችንና አባላትን እያዋከበ ትግሉን ለማሰናከል ከመቼዉም ጊዜ በላይ ቀጥሎበታል፡፡ የኢንጂነር ይልቃል የውጭ በሪራ ጉዞ የመከልከል ህገ-ወጥ ድርጊትም ከነዚህ ዕኩይ ተግባራቸው አንዱ ነው፡፡
የኢህአዴግ ባለስልጣናትና የቢሮ ኃላፊዎቻቸው በመንግስታዊ መዋቅር ሥልጣናቸዉን በመጠቀም የተለመደውን የማታለልና የህገ-ወጥነት ተግባራቸውን ተግተው ቀጥለውበታል፡፡ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ህልውና ቀምቶ ለታማኝ ግለሰቦች በመስጠት የሚደረገውን የነፃነት ትግል ለማኮላሸት በሃሰት በመወንጀል በህገ-ወጥነት አባሎቻቸውን ማሣደድና ማሠር፣ ሃብታቸውን መዝረፍ፣ ግድያ፣ እስር፣ ማዋከብና፣ ከቦታ ማፈናቀል የዕለት፡ዕለት ተግባራቸው ሆኗል፡፡
ውድ ነፃነት ናፍቂ ኢትዮጵያውያን፦
የኢህአዴግ ዘረኛ መንግስት በህዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ጭቆና/ስቆቃ ለመከላከል ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት፣ በአንድ ድምፅ ፣አገዛዙን መቃወም ይገባናል፡፡ አምባገነኖች በሚያደርሱብን ጭቆና እና አስተዳደራዊ ግፍ ተሠላችተን ተስፋ መቁረጥ በየትኛውም መስፈርት መፍትሔ አይሆንም፤ መፍትሔው ጨቋኙን ኃይል ታግሎ አሸቀንጥሮ መጣል ነው፡፡ ስለሆነም የፖርቲዎችን ሕጋዊ ህልዉና በማሣጣት፣ ሠለማዊ ትግሉን በማደናቀፍና የፖለቲካ አመራሮችን ወደ ወጭ እንዳይወጡ በመከልከልና በተለያዩ የአገዛዙ የውንብድና ድርጊቶች ሠላማዊ ትግላችን ለአንድም ሰከንድ አይቋረጥም! እንዳውም የበለጠ እልህ እንድንገባና ትግላችንን አጠናክረን ድጋፋችንን ለሠላማዊ ትግል ኃይሎች የማቴሪያልና የሞራል ትብብራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በትናትናው ዕለት የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ወደ ውጭ እንዳይወጣ አገዛዙ በማንአለብኝነት ቢከለክለውም እኛ እዚህ በውጭ አገር ያለን ደጋፊዎችና አባላት በየከተሞች በወጡት የስብሰባ ቀኖች መርሐ-ግብር መሠረት በየዕለቱ በየቦታው በመገኘት መላው ደጋፊያችንና የነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ሁሉም በነቂስ በመውጣት ስብሰባዎቻችንን በደማቅ ሁኔታ ከመሪዎቹ ጋር ከአዲስ አበባ ዘመኑ ባፈራው የጥበብ ውጤት በመጠቀም እንድናከናውን በቂ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ሕዝባችንም በየስብሰባዎቹ በመገኘት ድጋፋን በበለጠ ሁኔታ እንደሚያሣይ አንጠራጠርም፡፡ በዚህ አጋጣሚም ጥሪያችንን በአክብሮት እናስተላልፋለን፡፡
የስብሰባዎች መርሐ ግብር ከዚህ ደብዳቤ ጋር ተያይዞ ቀርቧል፡፡
የአንድነትና የሠማያዊ ድጋፍ ማህበሮች በሰሜን አሜሪካ አስተባባሪ ኮሚቴ
The post የሠላማዊ ትግላችን የፓለቲካ አመራሮችን ውጭ እንዳይወጡ በማገድና በምርጫ ቦርድ ፖርቲዎችን የማፍረስ ሴራ በፍጹም አይቋረጥም፤ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል! appeared first on Zehabesha Amharic.