ከቁምነገር መጽሔት
ጓደኛዎ ቢሮ እንደ ገቡ ስልክ ደውሎ ትምህርት ቤት ለመግባት በጠዋት የወጣው ልጅዎ የመኪና አደጋ ደርሶበት ወደ ሆስፒታል መወሰዱን ይነግርዎታል፡፡ ተደናግጠው ጉዳዩን ለአለቃዎ አሳውቀው ወደ ሆስፒታል ሊያመሩ ሲሉ ሌላ ስልክ ይፈልግዎታል ይባላሉ፡፡ የልጅዎ ሳያንስ ሌላ አስደንጋጭ መልዕክት ይደርስዎታል፡፡
ንዝህላሏ የቤት ሰራተኛዎ በለኮሰችው እሳት ‹‹ቤትዎ እየነደደ ነው›› ይባላሉ፡፡ መኪና ተመድብዎሎት ወደ ቤትዎ ለማምራት ሲዘጋጁ ይኸው ጓደኛዎ ሞባይል ላይ ደውሎ ዕድሜ የጠገቡት ወላጅ እናትዎ ማረፋቸውን ያረዳዎታል፡፡ በድንጋጤ በንዴትና በብስጭት ውስጥ ሆነው ወደ ልጅዎ ት/ቤት ሲሄዱ ልጅዎ በሰላም እየተማረ ነው፡፡ እቤትዎ ሲደርሱ ቤትዎ ሰላም ነው፡፡ እናትዎ ቤት ሲያመሩም እናትዎ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለው ፀሐይ ሲሞቁ ያገኘዋቸዋል፡፡
‹‹እንዴት እንዲህ አይነት የጅል ቀልድ ይቀልድብኛል?›› በማለት ወደ ጓደኛዎ መ/ቤት በፍጥነት ይገሰግሳሉ፡፡ ጓደኛዎን ገና ሲመለከቱት በሳቅ ይፈርሳል፡፡ ሁኔታው ግራ አጋብቶዎት ‹‹ምንድነው የምትሰራው?›› ብለው ሲጠይቁት ሳቁን እንደምንም ችሎ ‹‹ዛሬ እኮ ኤፕሪል ዘ ፉል ነው›› ይሎታል በዚህ ጊዜ የሚያዝኑት በማነው? በእርስዎ ጭንቅ በተሳለቀ ጓደኛዎ ወይስ…. የማሞኛ ቀን / April the fool/ በየዓቱ በፈረንጆች ሚዚያ 1 ቀን የሚውል የአውሮፓውያን የቀልድ ልማድ ቀን ነው፡፡ በዚህ ዕለት አውሮፓውያን ወዳጅ ዘመድ ጓደኛን በማሞኘት ነው የሚያሳልፉት፡፡ ለመሆኑ የዚህን ዕለት ታሪካዊ አመጣጥ ያውቃሉ?
እ.ኤ.አ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የኖርዌይ ወላጅ የሆነው ሉፍ ሊርፓ /Loof Lirpa/ የተባለ ሳይንቲስት የበረራ ምስጥርን ለማወቅ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ አንድ ቀን ሙከራው ስለተሳካለት በወቅቱ የሀገሪቱ ንጉሥ ለነበረው ለንጉሥ ሄነሪ ስምንተኛ ደብዳቤ ይፅፍለታል፡፡ የደብዳቤ ፍሬ ሃሳብ የበረራ ምስጢርን ተመራምሮ ማግኘቱንና አውሮፕላን ሰርቶ መጨረሱን የሚገልፅ ነበር፡፡ የሙከራውን ድንቅ ውጤት ለህዝብ በትርኢት መልክ ለማሳየት ስለፈለገም በዚሁ ዕትም ንጉሱ የክብር እንግዳ በመሆን የልፋቱን ውጤት እንዲመለከትለት ይጋብዘዋል፡፡ ትርኢቱም የሚቀርብበት ዕለት እ.ኤ.አ ሚያዚያ 1 ቀን 1545 ነበር፡፡
ንጉሱ የሊርፓን ደብዳቤ ካነበበ በኋላ በሳይንቲስቱ የምርምር ችሎታ በመደሰት ታላላቅ ሹማምንቱን አስከትሎ ወደ ትርኢቱ ሥፍራ ይሄዳል፡፡ ለክብሩ በተዘጋጀው ሰገነት ላይ በአካባቢው ከተሰበሰበው ህዝብ ጋር ሆኖ ሳይንቲስቱን መጠባበቅ ጀመረ፡፡ ይሁን እንጂ ሊርፓ በወቅቱ ሳይመጣ ቀረ፡፡ የንጉሱ ባለሟሎች ተጨነቁ ተጠበቡ፡፡ በመጨረሻም ንጉሱም ተናዶ ወደ ቤተመንግሥቱ ተመለሰ፡፡ ለጊዜው የሊርፓ ጉዳይ ምስጢር ሆኖ ቆየ፡፡
ድርጊቱ ሊርፓ ንጉሱን ለማሞኘት ሆን ብሎ ያደረገው አልነበረም፡፡ ሙከራው ሳይሳካለት ቀርቶም አይደለም፡፡ ከጊዜ በኋላ እንደተረጋገጠው ሉፍ ሊርፓ የበረራውን ትርኢት ሳያሳይ የቀረው እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ነበር፡፡ ሊርፓ የክብር እንግዳውና ህዝቡ ወደተሰበሰቡበት ቦታ አውሮፐላኑን እያበረረ ለመድረስ ገና ጉዞ እንደጀመረ ከአንድ ትልቅ ዛፍ ጋር ተላትሞ ህይወቱ ያልፏል፡፡ በዚህ የተነሳም ከሚያዚያ 1 ቀን 1545 እ.ኤ.አ ጀምሮ የሀገሩ ህዝብና አውሮፓውያን አሜሪካውያንም ጭምር የደረሰውን አጋጣሚ መሠረት በማድረግ ልክ እንደ አንድ ልማድ በመውሰድ ዘመድ ወዳጅና ጓደኞቻቸውን በማሞኘት በተሞኙት ላይም በመሳቅ ቀኑን ማክበር ጀመሩ፡፡ በሊርፓ ስምም ከአሣ ከሙዝ ከማርማላታና ከቼኮላት ልዩ ልዩ ኬኮችን በመስራት በመመገብ ያከብሩታል፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ቀኑን የሚያከብሩት ሰዎችን በሚያስቅና በሚያዝናና ሁኔታ በማሞኘት ነው፡፡
ይህ ልማድ ከግለሰቦች የእርስ በእርስ ማሞኘት ሌላ በዜና ማሰራጫዎችም አልፎ አልፎ ይደረጋል፡፡ ግን በማይጎዳ መልኩ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የቢቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ በዚያን ዕለት ያቀረበው ዜና ከመሞኘትም አልፎ የሚያጃጅል ነበር፡፡ ጣቢያው እንዳለው ከሜዲትራንያን የባህር ዳርቻ የነፈሰው ነፋስ በዛፍ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱና የፖስታ ምርት ስለቀነሰ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እንዳስከተለ የሚገልፅ ዜና አስተላለፈ፡፡
ይህንን አሰከፊ ዜና የሰማው ህዝብም ከየመደብሮቹ የቀሩትን ፖስታ ለመግዛት ሰልፍ ያዘ፡፡ ህዝቡ በወቅቱ ፖስታ ከዱቄት እንጂ ከዛፍ እንደማይመረት ለማገናዘብ አልቻለም ነበር፡፡ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ጣቢያው ዕለቱ ኤፕሪል ዘፉል መሆኑነ ሲገልፅ ህዝቡ በራሱ ላይ ስቋል፡፡ይህ ልማድ በሰፊው በሀገራችን አይሰፋፋ እንጂ በከተሞች አካባቢ አለ፡፡ ያተደረጉ ያልተከሰቱና አስደንጋጭ ወሬዎችን በስልክም ሆነ በሌላ መንገድ በመንገር ማሞኘት እየተለመደ ነው፡፡ ለማንኛውም በሞኞች ቀን ሞኝ ከመሆን ይሰውረን፡፡ ለመሆኑ የሉፍ ሊርፓ /Loof Lirpa/ ስም ከቀኝ ወደ ግራ ሲነበብ / April fool/ መሆኑን ልብ ብለዋል?
The post ‹የማሞኛ ቀን› ወይስ ‹የሞኞች ቀን› / April the fool/ appeared first on Zehabesha Amharic.