በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቶክ ሾው አዘጋጅና አቅራቢ የነበረው የኮሜዲያን አለባቸው ተካ የግል የመድረክ አልባሳትና የግል ቁሳቁሶች ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም ተበረከተ፡፡
ለሙዚየሙ የተሰጡት የአለባቸው ተካ የግል ቁሳቁሶች መሃከል የመድረክ ልብሶቹ፤ፎቶግራፎች፤ዋንጫዎች፤መፅሔቶችና የአለባቸውን ተካን ስራና የግል ሕይወት የተካተተበት ዶክመንተሪ ፊልም እንደሚገኝበት የአለባቸው ባለቤት ወ/ሮ ሳባ ሀይሌ ለቁም ነገር መፅሔት ተናግራለች፡፡
አለባቸውን ከዚህ ዓለም የተለየበትን 10 ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የግል መጠቀሚያ ንብረቶቹን ጠብቃ በማቆየት ለሙዚየሙ ያስረከበችው በተለያየ ጊዜ ስለ አለባቸው ጥናትና ምርምር ለማድረግ የሚፈልጉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስለ ስራውና ማንነቱ በተደራጀ መልኩ መረጃዎች በአንድ ቦታ እንዲያገኙ በማሰብ እንደሆነ አስድታለች፡፡
አለባቸው በህይወት በነበረበት ጊዜ የሰራቸውን ስራዎች ከግምት በማስገባት ከታላላቅ ኢትዮጵያውያን ባለታሪኮ ጎን ሆኖ ሥራው ለትውልድ እንዲተላለፍ ዪኒቨርቲው በመፍቀዱ ከፍ ያለ ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡
የዛሬ አስር ዓመት ለስራ ወደ ጅማ ከተማ ሲያመራ በደረሰበት የመኪና አደጋ ሕይወቱን ያጣው አለባቸው ተካ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይቀርብ በነበረው ፕሮግራሙ አማካይነት የተረሱ ቀደምት የጥበብ ሰዎችን ከማስታወሱም በላይ የተቸገሩ ወገኖቹን እንዲረዱ በማድረግ ‹የድሃ አባት› የሚል የክብር ስም ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ የአለባቸውን ተካን ስራና ህይወት ከሚያሳየው ዶክመንተሪ ፊልም በተጨማሪ የአለቤ ማስታወሻ የተሰኘ ልዩ ፕሮግራም በቅርቡ ለማቅረብ እየተሰራእንደሆነ ወ/ሮ ሳባ አስታውቃለች፡፡
Source: ቁም ነገር መፅሔት 14ኛ ዓመት ቅፅ 14 ቁጥር 200 ልዩ ዕትም\
The post የኮሜዲያን አለባቸው ተካ አልባሳትና የግል ቁሳቁስ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙዚየም ተሰጠ appeared first on Zehabesha Amharic.