Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሚካዔል በላይነህ “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን” ትንሳዔ ሰንደቅ ነውን?

$
0
0

(ዳኝነት መኮንን እና ማስረሻ ማሞ)

በኢትዮጵያ የሙዚቃ አድናቂዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ካተረፉት የልብ አድርሶች አንዱ ድምጻዊ ሚካዔል በላይነህ ነው። “ሕይወትን ከምንጯ ጠጣሁ ተመልሼ” እያለ ሲዘፍን በእርሱ ሙዚቃ ሌሎች ሕይወትን ከምንጯ ደግመው እንዲጠጡ ያደርጋል ቢባልም የተሳሳተ ሚዛን አይመስለንም።
michael belayneh

የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊዎች በሚካዔል ዘፈን ጉዳይ ከበርካታ የሙዚቃ ባለሞያዎች ጋራ ሲወያዩ የሚነሳው አንድ ዋነኛ ነጥብ አቀንቃኙ የ60ዎቹ ወርቃማ የሙዚቃ ዘመን ትንሳዔ ዐይተኛ ትዕምርት (exceptional symbol) መኾኑ ነው። ከዚህ ተነስተን በ7 ኪሎ መጽሔት የመጀመርያ ዕትም ላይ ይህ ርእሰ ጉዳይ ቢዳሰስ ተገቢ ይኾናል ብለን ሁለት ኹነኛ ጭብጦችን አንስተናል።

1ኛ) ሚካዔል የፈረንጅ ዘፈን የግጥም ሐሳቦችን ወደ አማርኛ በመተርጎም ወደ ሙዚቃው ዓለም ጎራ ብሎ፤ ጥልቅ የኾነውን የኢትዮጵያውያንን ኑሮና ሕይወት ወደሚበረብረው ሙዚቃ እንዴት ሊሻገር ቻለ? የሚለው ቀዳሚው ጭብጥ ሲኾን የዚህ ፊቸር ጸሐፊዎች በሚካኤል የሙዚቃ ዕድገት ላይ ሐሳብ የሚሰጡ ደርዘን የሙዚቃ ባለሞያዎች አነጋግረዋል።

2ኛ) የሚካዔል የቅርብ ጊዜ የሙዚቃ ሥራዎች የብዙሃን ብልሃት (collective wisdom) ውጤት ናቸው። አንዳንድ ባለሞያዎች የሙዚቃውን ሙጡቅነትም ከዚህ የመነጨ እንደኾነ ይገምታሉ። ታዲያ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን የባተው የብዙሃን ብልሃት በግለኛ መክሊቶች (individual talents) ላይ የበላይነት በመቀዳጀቱ ይኾን?” ከ1950ዎቹ መጀመርያ እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ ባለው ጊዜ የኪነ ጥበብ ዛር ከጠርሙሱ የወጣበት ዘመን ነበር ብለው ለመናገር የሚደፍሩ ብዙ የሙዚቃ ባለሞያዎች እና የኢትዮጵያ ሙዚቃ አጥኚዎች አሉ። እነዚህ ባለሞያዎች በዚህ “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን” እየጎመራ የመጣው የብዙሃን ብልሃት የአንድን ድምጻዊ ሥራ ውብ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖ ሳያበረክት አይቀርም ብለው ያትታሉ። ሐሳቡ እንዲህ ነው፤ በዚያ ዘመን ገጣሚው አምጦ የወለደውን፣ ዜመኛው በምናቡ ያረገዘውን፣ ሙዚቀኛው በመሣርያው ምናብን ከግጥም ጋራ እየፈተለ . . . እያባዘተ . . . የሙዚቃ ልቃቂት ሰርቶ፤ ሁሉም በጋራ የሸመኑትን ለአድማጩ የነፍስ ፍሰሐ ያቀብላሉ። እነዚህ ባለሞያዎች ይህን አቋማቸውን ለማስደገፍ በሶሻል ሳይንስ እና ኔትዎርክ ቲዮሪ የሕዝብ ብልሃት (wisdom of crowds) ላይ የተደረጉ ምርምሮችን ማጣቀሻ ያደርጋሉ።

ይኹንና እነዚህ ባለሞያዎች ወርቃማ በሚሉት ዘመን የተነሱ እንደ እነ ምንሊክ ወስናቸው፣ ጌታቸው ካሳ፣ ግርማ በየነ፣ ሰይፉ ዮሐንስ እና ወዘተ . . . የግለኛ መክሊት ባለቤቶች ነበሩ። እነዚህ ምሳሌዎች የብዙሃን ብልሃትን መላ ምት ፉርሽ የሚያደርጉ ናቸውን? በፊቸራችን በጊዜው የነበሩ የበርካታ ታዋቂ አቀንቃኞችን ሥራዎች በመመርመር ብዙሃኑ የትኛውን እንደሚከተሉ ለማየት ሞክረናል። ያገኘነው ውጤት የባለሟያዎቹን ሐሳብ የሚያረጋግጥ ነው።

ከዚያ በሁዋላ የቡድን የፈጠራ ሥራ ውጤት የኾኑት ሙዚቃዎች ብዙ አቀበት እና ቁልቁለት እያስተናገዱ እስከ 1990ዎቹ ዘልቀዋል። በዚህ ላይ-ታች ውስጥ ጥቂት የማይባሉ የግለኛ መክሊት ባለቤቶች ታይተዋል፥ ንዋይ ደበበ ለ1970ዎቹ አጋማሽ እና ለ1980ዎቹ ዐይነተኛ ትዕምርት ተደርጎ ቢወሰድ የተገባ ነው። ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ አንድ ሰው ራሱ ገጣሚ፣ ራሱ ዜመኛ፣ ራሱ አቀናባሪ መኾን ሥጦታ ብቻ ሳይኾን ፋሽን ኾነ። በዚህ ወቅት ላይ ይሠሩ የነበሩት አብዛኛዎቹ ሥራዎች የፋሽኑ ተከታዮች ኾኑ። ከእነዚህ በግል መክሊተኞች መካከል አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ላይ አሻራቸውን ጥለው ያለፉ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) እና ቴዲ አፍሮ (ቴዎድሮስ ካሳሁን) ይገኙበታል። እጅጋየኹ ሽባባው ነፍሷ የሚወደውን ሥራ ሠራች። አብዛኛዎቹ ዘፈኖቿ በሰው ልጅ ሕይወት ላይ የሚያጠነጥኑ፣ ታሪክን መሠረት ያደረጉ፣ ብሔርተኝነትን የሚያጸኑ እና ሰው መኾንን የሚያስታውሱ ናቸው። የቴዎድሮስ ካሳሁን ሥራዎች ደግሞ ማንነትን የሚያጠይቁ፣ ፍቅርን የሚሰብኩ፣ ፖለቲካን የሚጓጉጡ እና ብሔርተኝነትን የሚያንጹ ናቸው።

የሙዚቃ ባለሞያዎቹ እነዚህ ጥቂት ዘፋኞች የሂደቱ አዎንታዊነት መገለጫዎች ሳይኾኑ ከተራው ጎራ የማይመደቡ (outliers) እንደኾኑ ይናገራሉ። በግለኛ መክሊቶች ዘመን የተፈጠሩ አብዛኞቹ ሙዚቃዎች በጥራት ቀድሞ ከነበረው በጋራ ሲታዩ ያነሱ ናቸው። የሚካዔል ሙዚቃዎች ይህን የግለኛ መክሊት መጋረጃ ሸነቆረ፤ ይሸረክተው ይኾን?

ማሳረጊያ

እውን ሚካዔል በላይነህ “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን” ትንሳዔ ትዕምርት ነውን? ሚካዔል ወደ ሙዚቃው ዓለም ሲመጣ “አንተ ጎዳና – አንተ መንገድ”ን ይዞ ተከሰተ። መንገድ እያናገረ መጣ። መንገድን እንደ አንድ ገጸ ባሕርይ ጥያቄ እየጠየቀው አዜመ። ይህ ዐይነቱ አመጣጥ ብዙም የተለመደ አይደለም። የመጀመርያው አልበሙ አብዛኞቹ ዘፈኖች ሐሳባቸው ከእንግሊዝኛ የተወሰዱና ወደ አማርኛ የተተረጎሙ ናቸው። “ይህ ተጽዕኖ ምናልባት በየክለቡ በሚዘፍንበት ጊዜ ድምጹን የፈታው በእንግሊዝኛ ዘፈኖች ስለኾነ ይኾናል” ብለው የሚሄሱ ባለሙያዎች አሉ። “ሙዚቃው እንደ ወንዝ የሚፈስ፣ የተረጋጋና ስክነት የተሞላበት ነው” የሚሉ ማሞካሻዎች የሚቀርቡለት ሚካዔል፥ በወቅቱ አስቀድሞ ለቆት በነበረው ነጠላ ዜማ ራሱን አስተዋውቆ ስለነበር ወደ አድማጮች ለመድረስ ብዙም አልተቸገረም ቢባል ስህተት አይኾንም።
michael

የሚካዔል ሁለተኛ ሥራ “መለያ ቀለሜ” የሚል አልበም ነው። ይህ ሥራው “ሙዚቃ ማለት ቺክቺካ ነው” ወይም “ለክለብ አስረሽ ምቺው ድለቃ የሚኾን ነው” ብለው ከሚያስቡና ከሚያምኑ አድማጮች ጋራ የማይሰናሰል ነው የሚሉት ሃያሲዎች፤ “የሚካዔል “መለያ ቀለሜ” ጸጥታ የረበበበት፣ ተመስጦ የሚያሻው፣ ጊዜ፥ ቦታ፥ እና ተመክሮ ተውበው የተቀመሩበት ምጡቅ ነገር ግን ዩኒቨርሳል ሥራዎች አካትቷል” በማለት “መለያ ቀለሜ”ን ውዳሴ ያዘምኑለታል። በዚህ መወድስ የማይስማማ አንድ ሃያሲም “ለአንዳንድ አድማጮች ነፍስ የሚያሳርፍ የሚባል ዐይነት ነው እንጂ፥ “መለያ ቀለሜ” ዩኒቨርሳል አይደለም” ሲል ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል። በ“መለያ ቀለሜ” አልበሙ ሚካዔል “ጥልቅ የኾኑ ሐሳቦችን ያዘሉ፣ ማንነትን የሚበረብሩ፣ ግጥም ብቻ ሳይኾን የተዋጣለት ሰዓሊ የቀመራቸው ሥዕሎችም እንድሚቀባ ተሰድረዋል” የሚሉ ማሞካሻዎችም በበዙ ሃያሲዎች ተችሮታል። የግርማ ይፍራሸዋ ፒያኖ ከሚካዔል ድምጽ ጋራ ተሰናስሎ በጸጥታ ሲደመጥ (እጅግ ተጋነነ ካልተባለ) የደከሙ የደም ስሮችን ያነቃቃል . . . በእያንዳንዱ የሰውነት ክፍል ውስጥ እንደ ወንዝ ይፈሳል። የዚህ ሙዚቃ ምሥጢር ሌላ አይደለም። እውን የሚካዔልን “መለያ ቀለሜ” የብዙሃን ብልሃት ዳግም መወለድ ነው ልንል እንችል ይኾን? ሚካዔል ድምጹን ይዞ መጣ፤ እነ ጌትነት እንየው አምጠው የወለዱትን ምጡቅ ድርሰት ሰጡት፣ ግርማ ይፍራሸዋ ከፒያኖው ውስጥ አዕዋፍን የሚያስንቅ የሙዚቃ ሕብር ፈጠረ።

ከዚያስ? ሚካዔል ወደየት እየተጓዘ ነው? ከ“መለያ ቀለሜ” በኋላ ይዞት የመጣው ሣልሳዊ አልበሙ “ናፍቆት እና ፍቅር” የብዙኃን ብልሐት (collective wisdom) ልቆ ታይቶበት ይኾን? ይህ ቅምሻ ነው፤ ለዚህ እና ለሌሎች ጥያቄዎች መልስ ሙሉውን ጽሑፍ በ7 ኪሎ መጽሔት ላይ ይጠብቁ!

Source: 7 ኪሎ መጽሔት

The post ሚካዔል በላይነህ “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን” ትንሳዔ ሰንደቅ ነውን? appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles